18 May, 2016
ከተፈጥሮ የተቀዳ ሙዚቃ
ጥንታዊቷ አክሱም ካፈራቻቸው ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ የዛሬ 1,500 ዓመት ገደማ የተወለደው ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ የዘር ሐረጉ የሚመዘዘው ከክርስቲያኖች በመሆኑ፣ ከልጅነቱ ጀምሮ የቤተክርስቲያን ትምህርት እንዲከታተል ተደረገ፡፡ ስኬማታ ሊሆን ግን አልቻለም፡፡ በተደጋጋሚ ማምጣት ከሚጠበቅበት ነጥብ በታች ያመጣ ጀመር፡፡ ይህም የዕድሜ እኩዮቹ መቀለጃ አደረገው፡፡ መምህራኑም እሱን እስከማባረር ደረሱ፡፡
አባቱ በድንገት ያርፉና በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ታዋቂ ከነበሩ አጎቱ ጋር መኖር ይጀምራል፡፡ በትምህርቱ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ቢሞክርም ከቀደመው ጊዜ የተለየ ነገር ሊፈጠር አልቻለም፡፡ በዚህ ተስፋ የቆረጠው ቅዱስ ያሬድ ታዲያ ወደ ሌላ አጎቱ ዘንድ ለመሄድና ለመኖር መንገድ ይጀመራል፡፡
በመንገዱ ላይ ዝናብ ይይዘውና ከአንድ ዛፍ ሥር ይጠለላል፡፡ በትምህርቱ ደካማ ስለመሆኑ እያሰለሰለ ሳለ አነስተኛ ትል ትልቅ ፍሬ አንግቦ ዛፉን ለመውጣት ሲጣጣር አስተዋለ፡፡ ትሉ ዛፉን ለመውጣት ያደረጋቸው ስድስት ሙከራዎች እየወደቀ ባይሳኩም በሰባተኛው ሙከራ ከተመኘው ቦታ ደረሰ፡፡
ቅጽበቱ የቅዱስ ያሬድን ሕይወት እስከወዲያኛው ለወጠው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ሳለ የዕውቁ አጎቱን ቦታ ተካ፡፡ ወደር የማይገኝለት ሙዚቃ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ ደራሲና ኬሮግራፈር ሆነ፡፡ የሦስት አዕዋፋት ዝማሬ መነሻ የሆናቸው ግዕዝ፣ እዝልና አራራይ ለኢትዮጵያ እንዲሁም ለዓለም ያበረከታቸው ስጦታዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም እስከዛሬ ግልጋሎት ላይ ይውላሉ፡፡
ቅዱስ ያሬድ በሙዚቃ ጽንሰ ሐሳብ ረገድ ከዓለም የቀዳሚነቱን ድርሻ እንደሚወስድ ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አምስቱ ቅኝቶች ምንጭም ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ድምፃዊት መክሊት ሐደሮ ‹‹ዘ አንኤክስፔክትድ ቢውቲ ኦፍ ኤቭሪደይ ሳውንድ›› (የዘወትር ድምጾች አስደናቂ ውበት) በሚል ርዕስ ንግግር ባደረገችበት ወቅት ትኩረቷን ያደረገችው በእነዚህ አምስት ቅኝቶች ዙሪያ ነበር፡፡
‹‹የቅዱስ ያሬድ ስኬሎች ቅኝቶችን ፈጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ የሆነው ፔንታቶኒክ ኖታ ዛሬም እያደገ ነው፤›› በማለት ነበር መክሊት የገለጸችው፡፡ መክሊት የተወለደችው ኢትዮጵያ ሲሆን፣ ኑሮዋ በሳንፍራንሲስኮ ካሊፎርኒያ ነው፡፡ ጃዝ፣ ሮክና የምሥራቅ አፍሪካን ሙዚቃ በማዋሃድ በምትሠራቸው ጥዑመ ዜማዎች ትታወቃለች፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት ቴድ ቶክስ በተሰኘው የቴክኖሎጂ፣ መዝናኛና ዲዛይን ርዕሰ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት መድረክ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ተናግራ ነበር፡፡ ቴድ ቶክስ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ቢዝነስ፣ ባህል፣ ጥበብና ዲዛይን ባለሙያዎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ መክሊት በመርሐ ግብሩ ተጋብዛ በባህል፣ ቋንቋና ጽሞና ላይ ያተኮረ ንግግር አድርጋለች፡፡ ተፈጥሮ ለሙዚቃ ሥራዎች መነሻ እንደሚሆን የሚያመላክት ነጥብም አንስታለች፡፡
እንደምሳሌ የጠቀሰችው በኮንጎ የሚኖሩት ጎሳ የሆኑት የፒግሚ ጎሳዎች የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ቅኝት የሚመርጡት በአካባቢያቸው ያሉ አዕዋፋትን ዝማሬ ቃና በመከተል እንደሆነ ነው፡፡ ‹‹ሙዚቀኛና የሙዚቃ ኤክስፐርት በርኒ ክራውስ እንደሚለው፣ ጤናማ የሆነ አካባቢ የሚኖሩ እንስሳትና ነፍሳት የሚያወጡት ድምፅ እንደ ሲምፎኒ ነው፡፡ በርካታ የሙዚቃ ሥራዎች መነሻቸው በጫካ ውስጥ ያሉ አዕዋፋት ድምፅ ነው፤›› በማለት የተናገረችው መክሊት፣ ተፈጥሮ የብዙዎች መማሪያ እንደሆነ አስረድታለች፡፡
ለንግግሯ መነሻ የሆናት በርኒ በአንድ ወቅት በቴድ ቶክስ ላይ ያደረገው ንግግር የመክሊትን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ተፈጥሮን የተመረኮዘ ሙዚቃ ለመሥራት ምርምር ባደረገው ወቅት ነፍሳትና ጥቃቅን ቫይረሶች ሳይቀር የራሳቸው ድምፅ እንደሚያወጡ መገንዘቡን ተናግሯል፡፡ ‹‹እንደ ትሮፒካል ሌክ ፎረስት ባሉ ቦታዎች ልዩ የእንስሳት ኦርኬስትራ ይደመጣል፤›› ሲል ነበር የገለጸው፡፡
መክሊትና በርኒ የንግግራቸው መነሻ ያደረጉት በተፈጥሮና ሙዚቃ መካከል ያለውን ትስስር በጥልቅ የሚያወሳው ሳውንድስኬፕ፣ በአንድ አካባቢ ከሚገኙ ማንኛውም ነገሮች በሚወጡ ድምጾች ውህደት ስለሚፈጠረው ሙዚቃ ያወሳል፡፡ በበርኒ አገላለጽ ሳውንድስኬፕ ሦስት ምንጮች አሉት፡፡ አንዱ ጂኦፎኒ ሲሆን፣ እንደ ውኃ፣ ንፋስና ዛፍ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚያወጡትን ድምፅ ያመላክታል፡፡ ሌላው ባይፎኒ ደግሞ በአንድ ጊዜና ቦታ የሚኖሩ ነፍሳት የሚያወጡት ድምፅ ነው፡፡ አርትሮፎኒ ከሰው ልጆች የሚወጣውን ማንኛውንም ዓይነት ድምፅ ይወክላል፡፡ በጥናቱ ከ15,000 በላይ ተፈጥሯዊ ሳውንድስኬፖችን ያገኘ ሲሆን፣ ሙዚቀኞችም እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡
መክሊት ከተፈጥሮ በተጨማሪ ቋንቋ የሙዚቃ መነሻ እንደሆነና የእሷ መነሻ አማርኛ እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ‹‹እንደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊት ያደኩት በአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች አካባቢ ነው፡፡ አማርኛ የቤተሰቦቼ ቋንቋ ሲሆን፣ የእኔም አፍ መፍቻዬ ነው፡፡ የቋንቋው ጥልቀት፣ አባባሎቹ፣ የወርቅና ሰም ይዘቱና ሌሎችም እውነታዎች ቋንቋውን እንድወደው አድርገውኛል፤›› ትላለች፡፡ በቋንቋው ውስጥ ካሉ ቃላት መካከል እንደ አገባባቸው በየአካባቢያቸው የተለያየ ትርጓሜ የሚሰጡ ቃላት መኖራቸው ለሙዚቃው ያለውን አስተዋጽኦ ተናግራለች፡፡ ‹‹እንዴ›› የሚለው ቃል መገረምን፣ ተቃውሞንና መጠየቅን ማንፀባረቁ ከልጅነቷ ጀምሮ ያስገርማት እንደነበርና ለሙዚቃዎቿ መነሻ ከሆኑ ቃላት አንዱ እንደሆነ አስረድታለች፡፡
መክሊት ለሙዚቃ መነሻ ብላ ያነሳችው ሌላው ነገር ጥሞና ነው፡፡ እንደ ምሳሌ የጆን ኬጅ ቅንብር የሆነውን 4፡33 አንስታለች፡፡ ቅንብሩ ለማንኛውም የሙዚቃ መሣሪያ ወይም የመሣሪያዎች ውህድ ይሆናል፡፡ በ4፡33 ላይ የተጻፈ አንዳችም ኖታ ስለሌለ በመድረክ ሲቀርብ ለ4 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ ያህል ፀጥታ ይሰፍናል፡፡ ‹‹ማንኛውም የሙዚቃ መሣሪያ ባይደመጥም ሙዚቃ ግን ምንጊዜም መኖሩን ያመላክታል፤›› ትላለች ሙዚቀኛዋ፡፡
ሙዚቃ ከዘወትር እንቅስቃሴም እንደሚመነጭ ታስረዳለች፡፡ ‹‹ከሰዎች ትንፋሽ፣ ሹክሹክታ፣ ሳል፣ ጉሮሮ ሲፍታታና ሲኮማተር ከሚያወጣው ድምፅም ሊሆን ይችላል፤›› ትላለች፡፡ በንግግሯ መደምደሚያ ሁሉም ሰው ለሙዚቃ ሥራ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ተናግራለች፡፡ ‹‹ታዳሚዎቹ የሙዚቃ አቀናባሪዎቹም እኛ ነን፤›› በማለት ተፈጥሮ፣ ቋንቋና ጥሞና በሙዚቃ ያላቸውን ቦታ በአጽንኦት አስረድታለች፡፡
- አንባቢ’s blog
- 152 reads