Wednesday, 25 May 2016 12:24
ከግማሽ በላይ የሚሆነው የህፃናት ሞት የሚከሰተው ከግል እና ከአካባቢ ንፅህና ጉድለት የተነሳ እንደሆነ ተገለፀ።
ትናንት ድፍርስ ውሃን የሚያጣራ ኬሚካል ይፋ በተደረገበት ዝግጅት ላይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካይ የቀረበ ጥናት እንዳመለከተው በሀገሪቱ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ ከሚከሰተው ሞት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው በግል እና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት የተነሳ ነው። ባለፈው ዓመት እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ቀዳሚ የሞት መንስኤዎች መካከል በንጽህና ጉድለት የሚከሰተው የተቅማጥ በሽታ እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል። በኢትዮጵያ ከሚገኙ አባወራዎች መካከል 46 በመቶዎቹ ንጽኅናውን ያልጠበቀ ውሃን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ያልታከመ ውሃን ይጠቀማሉ ሲል ጥናቱ አመልክቷል። በከተማ ከሚኖረው ህዝብም 86 በመቶ ያልታከመ ውሃን ይጠቀማል። የግል እና የአካባቢ ንጽህና ጉድለት እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሃ ማጣት በህፃናት ላይ የተቅማጥ በሽታ እንዲከሰት በማድረግ በርካታ ህጻናትን ለሞት እየዳረገ ይገኛል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚወለዱ አንድ ሺህ ህጻናት መካከል 68ቱ ከዚሁ ከንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት የተነሳ አምስት ዓመታቸውን ሳያከብሩ ህይወታቸው ያልፋል ተብሏል።
ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንደልብ ማግኘት አለመቻል ጥራቱን ያልጠበቀ ውሃ እንዲጠቀሙ ስለሚያስገድድ በተለያዩ ጊዜያት ውሃን ሊያጣሩ የሚችሉ ኬሚካሎች አገልግሎት ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። በአለም ጤና ድርጅት ፈቃድ አግኝተው አገልግሎት ላይ እየዋሉ ካሉት ኬሚካሎች በተጨማሪ ድፍርስ ውሃን ሊያጣራ የሚችል ኬሚካል ትናንት በሀርመኒ ሆቴል ይፋ ተደርጓል። በፒኤስ አይ ኢትዮጵያ አማካይነት የሚሰራጨው ፒ ኤንድ ጂ የተባለው ውሃ ማጣሪያ ኬሚካል በተለይ ድፍርስ ውሃን ለማጣራት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ይህ ኬሚካል በዱቄት አራት ግራም መጠን ኖሮት ታሽጎ የቀረበ ሲሆን አንዱ እሽግ አስር ሊትር ውሃ የማጣራት አቅም አለው። የውሃ ማጣሪያውን አጠቃቀም አስመልክቶ በፒኤስአይ ኢትዮጵያ የውሃ ጥራት እና ጤና አጠባበቅ (WASH) ፕሮግራም ማናጀር አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ይህን ኬሚካል በድፍረስ ውሃ ውስጥ በመጨመር ለአምስት ደቂቃዎች በማማሰል፣ ከዚያም ቆሻሻው እስከሚዘቅጥ ለአምስት ደቂቃዎች መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ዳንኤል፣ በመቀጠልም ውሃውን በንፁህ ጨርቅ አጥልሎ ለሃያ ደቂቃዎች በማስቀመጥ ለመጠጥነት ማዋል እንደሚቻል ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የነበሩት የውሃ ማጣሪያ ኬሚካሎች በአይን ሲታይ ንጹህ የሚመስልን ውሃ ባክሬቲያ እና የተለያዩ ተዋስያንን ለመግደል የሚያግዙ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ይሄንኛው ኬሚካል ግን ድፍረስ ውሃንም የማጣራት ተጨማሪ አገልግሎት አለው ብለዋል። አዲሱ የውሃ ማጣሪያ ውሃን በማጣራት ሂደቱ ውስጥ ባክቴሪያዎችን እና ቫይረሶችን (የፖሊዮ እና ሮታ ቫይረስን ጨምሮ) የመግደል አቅሙ ከፍተኛ ሲሆን፣ በውሃ ውስጥ የሚገኙ ከባድ ብረቶችን እና አላስፈላጊ ነገሮችን እንደሚያስወግድ በአሜሪካ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የተረጋገጠ መሆኑንም ተገልጿል። ይህ አዲስ የውሃ ማጣሪያ በዋናነት እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት እናቶች፣ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ላሉ ሰዎች እንዲሁም ድንገተኛ እና ውስብስብ የጤና ችግር ላለባቸው ሰዎች በስፋት እንደሚሰራጭም ተገልጿል። ይህ የውሃ ማጣሪያ ኬሚካል ከውሃ አጋር እና ከእንክብል የውሃ ማጣሪያ ጎን ለጎን የሚሰራጭ ሲሆን፣ በተለይ በቆላማ አካባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በስፋት እንዲዳረስ ደረጋል ተብሏል።
ስንደቅ