Wednesday, 25 May 2016 12:58
በ ፋኑኤል ክንፉ
ቅሬታ አቅራቢ ሰራተኞች
“ይህ አመለካከት የጥቂት ኪራይ ሰብሳቢ ሠራተኞች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል”
አቶ ዘነበ ይማም
“መልካም አስተዳደር እንኳን በመተሐራ በሀገራችንም ውስጥ መቶ በመቶ የሆነ መልካም አስተዳደር የለም”
አቶ ተመስገን ወ/መስቀል
ባሳለፍነው ሳምንት በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ በዕለት ረቡዕ በጠዋት እና በከሰዓት ፈረቃ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር በተገኙበት የመተሐራ ሰራተኞች ውይይት አድርገው ነበር። በዚህ ውይይት ላይ በማኔጅመንቱ፣ በሠራተኛ ማሕበሩ እና በሠራተኞች መካከል ያልተጠበቀ ውዝግብ ተፈጥሯል።
የውይይቱ አጀንዳ ታሳቢ የተደረገው በ2006/በ2007 ዓ.ም. የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞች ለፈጸሙት የላቀ ምርታማነት ተገቢውን የማትጊያ ክፍያ አለመከፈሉ ቅሬታ መፍጠሩ ተከትሎ ለመወያየት ነበር። ሆኖም የውይይቱ አጀንዳ ከማትጊያ ክፍያ ወደ መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መሸጋገሩን ዋና ዳሬክተሩን ጨምሮ ሌሎች ተሰብሳቢዎችን ያደናገጠ ክስተት ነበር።
ባለፈው አስራ አምስት ቀናት የስኳር ኮርፖሬሽን 77 ቢሊዮን ብር ለስኳር ልማት አውጥቶ አንድም ፋብሪካ ወደስራ አለመግባቱን ይፋ አድርጎ ነበር። እንዲሁም በቀጣይ ዓመት 13 ቢሊዮን ብር እዳ መክፈል እንደሚጀምር ማስታወቁ አይዘነጋም።
የስኳር ኮርፖሬሽኑ አፈፃጸም መገምገም ያለበት፣ በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ፣ በአስሩ ስኳር ፋብሪካዎች እና በነባር ፋብሪካዎች ዙሪያ መሆኑን ባለፈው ሳምንት ባቀረብነው ጽሁፍ ላይ ማስፈራችን ይታወሳል። ለዛሬም በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ላይ የኮርፖሬሽኑ አመራር አሰጣጥ ምን ይመስል እንደነበረ እንዲሁም የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ማኔጅመንት እና ሠራተኞቹ ያላቸውን ግንኙነቶች እንመለከታለን።
ኮርፖሬሽኑ በ2007 ዓ.ም. በጀት ዓመት ያቀረበው ሪፖርት ላይ ያሰፈረው እቅድ ከአሠራር ሥርዓትና አፈፃፀም ምዘና ረገድይህን ይላል፤ በዋናው መ/ቤት፣ በፋብሪካዎችና ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ያሉ የአሠሪር ሥርዓቶች ላይ ጥናት በማካሄድ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ፣ በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት፣ በፋብሪካዎችና ስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ያሉ የአደረጃጀት ክፍተቶች ላይ ጥናት ማካሄድ፣ በጥናቱ መሠረት አዲስ የሥራ ቀረፃ፣ ትንተናና የሥራ መዘርዝር ማዘጋጀቱን ይጠቅሳል፡፡
እንዲሁም የሠራተኛና የኢንዱስትሪ ግንኙነትን በተመለከተ ይህንን አስፍሯል፣ በኮርፖሬት ደረጃ በሚዋቀረው መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር እና በኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት መካከል የሁለትዮሽ የምክክር ሥርዓት እንዲዘረጋና ለችግሮች የቅድመ-የመከላከልና የመፍትሔ እርምጃ የመስጠት አቅምን ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር በጋራ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ፣ በፋብሪካዎች እና በፕሮጀክቶች ለሚገኙ የሠራተኛና ኢንዱስትሪ ግንኙነት የሥራ ክፍል አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማከናወን እና ከሠራተኛ ማኅበር የሚነሱ ቅሬታዎችን በመመርመር አስፈላጊውን ምላሽ መስጠት፤ በኮርፖሬት ደረጃ ከሚቋቋመው የሠራተኛ ማኅበር ጋር በኢንዱስትሪ ግንኙነት ዙሪያ በሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት መደበኛ ውይይት ማካሄድ ናቸው።
በተጨማሪም የሠራተኛ ግንኙነትን በተመለከተ ከሚለቁ ሠራተኞች (exit interview) የሚገኙ አስተያየቶችን መሰብሰብ፣ መረጃ ማጠናቀርና መተንተን፤ በፕሮጄክቶች የሠራተኞችን አስተያየት በመቀበልና አስፈላጊውን ዳሰሳ በማድረግ ችግሮችን መለየትና የመፍትሄ ሀሳብ በመቅረጽ ተግባራዊ ማስደረግ፤ ከሠራተኞች የሚነሱ ቅሬታዎች መንስዔያቸውን በመለየት መረጃዎቹን በማጠናቀር ዳታ ቤዝ መያዝ ነው ይላል።
ከላይ ከሰፈረው የእቅድ አፈፃጸም አንፃር የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ማኔጅመንት እና ሠራተኞችን በተመለከተ ኮርፖሬሽኑ ምን ተግባራት መስራት ይጠበቅበት ነበር ለሚለው ምላሽ የሚሰጡ ሁኔታዎችን እንመልከታቸው። ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዲሁም በስብሰባው ዙሪያ ከሠራተኞች፣ ከከፍተኛ ማኔጅመነት የተሰነዘሩ ቅሬታዎችን አቅርበናል። እንዲሁም የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ዘነበ ይማም እና የማሕበሩ ሊቀመንበር አቶ ተመስገን ወ/መስቀልን ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡም አድርገናል።
በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ማኔጅመንት ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት ሠራተኞች እንደሚሉት፣ “ሠራተኞችን አለምክንያት ያባርራል። ሠራተኞችን በመሳዳብ በማሸማቀቅ አምባገነን አሰራሮችን ዘርግቷል። ከሕብረት ስምምነቶች ውጪ ያባርራል። የማሕበሩ ሊቀመንበር ይነሳ ብለን ጥያቄ ስናቀርብ ጥያቄዎቻችን ወደጎን ተደርገው ማኔጅመንቱ ካለምንም ተወዳዳሪ ከመደብ 10 አንስቶ መደብ 14 ሊቀመንበሩን አሳድጓል። ማን አለብኝነቱም አሳይቶናል። ተገቢ ፊርማዎችን ሰብስበን ስብሰባ ለመጥራት ስንቀሳቀስ ማሕበሩን በመቃወም መፈራረም ከስራ ያሰናብታል የሚል የቃል መመሪያ ያስተላልፋል። ማሕበሩ ደግሞ ሠራተኞች ሲባረሩ ጥያቄ አያቀርብም። ስለዚሀም መንግስት ችግራችን ሰምቶ መፍትሔ እንዲሰጠን” እንጠይቃለን ብለዋል።
ከከፍተኛ ማኔጅመንት ስሜ አይጠቀስ ያሉ የዘርፍ ሥራአስኪያጅ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳሉት፣ “የሠራተኛው እንባ መቆም አለበት። አንባገነን የሆነ አስተዳደር ጊዜው አይደለም። የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተገቢው ሁኔታ መተግበር አለባቸው። የጋራ ተጠቃሚነት ሊኖር ይገባል፡፤ በግል ተደራጅተው ለግል ጥቅማቸው የሚሰሩ ሰዎችን በቃችሁ መባል አለበት። የሚሰራና የማይሰራ መለየት አለበት። የማይሰራ የሚሾምበት፣ የሚዋሽ የሚሾምበት፣ ይህን መሰል አሰራር አምባገነን የሆነ መንገድ በመሆኑ መቆም አለበት። ፋብሪካው እየሞተ ነው። አመራሩ ባለው የአቅምና የአስተሳሰብ ችግር የመልካም አስተዳደር እጦት እያስከተለ በመሆኑ መተሐራ ስኳር ፋብሪካን መታደጊያ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል
አያይዘውም፣ “በእርሻው ዘርፍ ከፍተኛ የባለሙያ ፍልሰት አለ። የሚሰራው አቅም ያለው ሰራተኛ የለም። ጥራት ያለው አገዳ እየተመረተ እና እየቀረበ አይደለም። በፋብሪካ ውስጥ ሙያ ያላቸው ተፈናቅለው ውሸት የሚያመላልሱ ቦታ እንዲይዙ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው፡፤ የተለያዩ መለዋወጫዎች ብንገዛም የተለያዩ የአመለካከቶች ስልጠና ብንወስድም ሠራተኛው በመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ተስፋ በመቁረጡ እንደሚፈለገው ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም።”
በተለይ “በሁለት ዓመታት በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤት በመመዝገቡ ሁሉም ተጠቃሚ ነበር። ደስተኛም ነበር። ከቅርብ ጊዜ በኋላ ግን አመራሩ በተለይ ከከፍተኛ ማነጅመንቱ ከፍተኛ ችግር ያለበት ሆኗል። በአመለካከት በአስተሳሰብ ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማባረር የሚሰሩ ስራዎችን ለተመለከተ በእውነት ደርግም በሠራተኞች ላይ ይህንን ተግባር አልፈጸመም። ደርግ ከሰራተኛው ውጪ የሚቀጣው አልነበረም። አሁን ላይ አንድ ሠራተኛ ከነቤተሰቡ የሚቀጣበት አሰራር ነው ያለው። ባለው አሰራር ደስተኛ ሳይሆን የለቀቀ ሠራተኛ ቤተሰቡ በፋብሪካ ውስጥ የሚሰራ ከሆነ እንዲለቅ ይደረጋል። ተደርጓልም። ከአመራሩ ጋር ልዩነትት የፈጠረ የከፍተኛ ማኔጅመንት ቤተሰቡ ከሕክምና ውጪ ተደርገዋል። በግዳጅ ከስራ ውጪ እረፍት እንዲወስድ ተደርጓል። ይህን መሰል አደረጃጀት እና የኔትወርክ አስተዳደር መፍትሔ ካልተሰጠው የድርጅቱ ሕልውና አደጋ ላይ ነው። በፖለቲካ እምነት እንዲሁም ዘርን መሰረት በማድረግ የሚደረጉ ጥቃቶችም ካልታረሙ ተጨማሪ አደጋዎች ናቸው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ዘነበ ይማም
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ /በስልክ የተደረገ ቃለ ምልልስ
ሰንደቅ፡- የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር በተገኙበት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖራቸውን ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኞች ነበሩ። በቅሬታዎቹ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ዘነበ፡-ከሠራተኞች፣ ከማህበር፣ ከተማሪዎችና መምህራን እንዲሁም ከወረዳ መስተዳድሮች ጋር በጋራ በመሆን ውይይቶች ከተደረጉ በኋላ ችግሮችን ለይተን የመፍትሄ አቅጣጫዎች አስቀምጠን ነው ወደስራ የገባነው። ይህም በመሆኑ በካይዘን ትግበራ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሁለት ጊዜ አሸናፊዎች ነበርን። ይህን አተገባበራችን ለማስቀጠል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም በስራ ሒደት ውስጥ አንዳንድ የኪራይ ሰብሳቢነት ድርጊቶች ይታያሉ። በቁጥር አራት ሶስት የሚሆኑ ሠራተኞች ከዚህ ችግራቸው እንዲወጡ እንዲታረሙ በተደጋጋሚ ሲነገራቸው ሊታረሙ ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ የዲሲፕሊን እርምጃዎች የተወሰደባቸው ናቸው፣ በማኔጅመንቱና በሠራተኛው መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት ከፍተኛ የሆነ የስም ማጥፋት ውስጥ የገቡት። እነዚህን መሰል ኪራይ ሰብሳቢዎችን ስታታገል እነሱም ላለመሸነፍ አሁን ካሉት የበለጠ ስም ማጥፋት ውስጥ መግባታቸው የማይቀር ነው። ሆኖም ከተራ ስም ማጥፋት በዘለለ ትርጉም አለው ብዬ አልወስደውም።
ሰንደቅ፡- የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር አቶ እንዳወቅ አብቴ በተገኙበት በተካሄደ ስብሰባ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች በሶስት ወይም በአራት ሰራተኞች ፍላጎት የተንጸባረቁ አድርጎ መውሰድ ይቻላል?
አቶ ዘነበ፡- የስብሳበው መንፈስ የነበረው መተሐራ ስኳር ፋብሪካ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ ውይይት ለማድረግ ነበር። ይህም ሲባል የተገኘውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ምን እናድርግ የሚል ነበር። ፋብሪካውን ማስፋፋት ምርታማነት ማሳደግ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሠራተኛውንም ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ለመወያየት ነበር። ሆኖም ጥቂት ሠራተኞች በማኔጅመንቱ፣ በማሕበሩ እና በሠራተኛው መካከል ያለውን ግንኙነት ለማበላሸት የዕለቱን መድረክ ለመጠቀም አጀንዳ ለመቀየር የተደራጁ ናቸው።
እነዚህ ሠራተኞች ራሳቸው በኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ የተዘፈቁ በስም ሊጠቀሱ የሚችሉ፣ ድርጅቱም ሠራተኛውም የሚያውቃቸው፣ በአንደም በሌላ መልኩ ጥቅማቸው የተነካባቸውን ሰዎችን አደራጅተው ነው የገቡት። እንዲሁም ችግር ውስጥ ያሉ ችግራቸውን አርመው ይቅርታ ጠይቀው ወደሥራ ገበታቸው የተመለሱ ሠራተኞች ናቸው፣ የመድረኩን አጀንዳ ለመቀየር የፈለጉት። በግልፅ ነው የምንናገረው፣ ኪራይ ሰብሳቢዎቹ ከዚህም በላይ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። እውነቱ ግን በእኛ ዘንድ ስላለ የትኛውም አካል ሊፈትሸው ሊያጣራው ይችላል።
ሰንደቅ፡- በግልፅ ነገሮችን ለማስቀመጥ ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኞች “መንግስቱ ኃ/ማሪያም ዚምባቡዌ ነው ያለው ቢባልም መንግስቱ ግን መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ነው ያለው” ሲሉ በማኔጅመንቱ ላይ ተቃውሞቸውን እያሰሙ ነው። የቅሬታ አቅራቢዎቹ ሠራተኞች አገላለጽ ለእርሶ ምን አይነት ትርጉም ይሰጥዎታል?
አቶ ዘነበ፡- እኔም ነገሮችን በግልፅ ማስቀመጥ ይኖርብኛል። ይህ አመለካከት የጥቂት ኪራይ ሰብሳቢ ሠራተኞች መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። አስፈላጊ ከሆነ እገሌ..እገሌ..ተብሎ ማስቀመጥ ይቻላል። የተለያየ ሕገወጥ ጥቅም የጠየቁ አሉ። አደጋ ያልደረሰበትን ደርሶብኛል ሲል 44ሺ ብር ጥያቄ ያቀረበ ሠራተኛ አደጋ ያልደረሰበት መሆኑ ተነግሮት ጥያቄው ውድቅ ተደርጓል። ሌሎቹ ከደሃው ወዝአደር የሰራበትን እየቀነሱ ክፍያውን ወደሌላው ወዝአደር በማዞር ገንዘብን ከድርጅቱ ካዝና የሚያወጡ ናቸው። ይህ ተግባራቸው ሠራተኞች ባሉበት ተጋልጦ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ከስራ አሰናበትናቸው። ሆኖም ሠራተኛ ማሕበሩ ከስህተታቸው ይማራሉ በማለት ኃላፊነት ወስዶ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመሉ ተደርገዋል። እነዚሁ ሠራተኛች ናቸው ወደ ስም ማጥፋት ውስጥ የተሰማሩት።
ኮርፖሬሽኑ የሚያውቀው እውነት ነው። አሁን ማንኛውም አካል መጥቶ ሊያጣራው የሚችል እውነታ ነው። እነሱ እንደሚሉት አይነት አስተዳደር በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ቢኖር መተሐራ ስኳር ፋብሪካን ከወደቀበት እንዴት ማንሳት ይቻል ነበር? በአካባቢው ሠራተኛ ማሕበር፣ የወረዳ መስተዳደርና መንግስት አሉ፣ እነዚህ ሶስተኛ ወገን ታዛቢዎች ባሉበት የመንግስቱን ኃ/ማርያም አይነት አስተዳደር በስኳር ፋብሪካ ውስጥ እንዴት መዘርጋት ይቻላል?
ኪራይ ሰብሳቢዎች ግን ችግሮቻቸውን ስትንካካባቸው ሕልውናቸውን ለማስቀጠል መፈራገጣቸው አይቀርም። ችግሮቻቸውን ለመደበቅ ከዚህ በላይ ሥም ማጥፋት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። እኛም እንታገላቸዋለን። ዴሞክራሲያዊ መንግስት እየገነባን በመሆኑ ሁሉም አካል በተፈጠረለት መድረክ መታገል መብቱ ነው። እነሱም ቢሆኑ መብታቸው ነው፣ እኛም ብንሆን መብታችን ነው። እውነቱ ግን በመጨረሻ ሰዓት ላይ ይወጣል።
ሰንደቅ፡- ፋብሪካው ከተቀመጠለት ዓመታዊ የምርት ኮታ አንጻር በአሁን ሰዓት 650ሺ አካባቢ ነው ያመረተው። ዓመቱ እየተገባደደ በመሆኑ የተቀመጠለትን ኮታ የማምረት እድሉ በጣም አናሳ ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያያት ምንድን ነው? ከምርታማነት መቀነስ አንጻር በመሰረታዊነት የሚጠቀሱ ችግሮችስ ምንድን ናቸው? የተቀመጠላችሁን ኮታስ ታሳኩታላችሁ?
አቶ ዘነበ፡- በሀገር ደረጃ የኤሊኖ ችግር ነበር። በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ላይ ከፍተኛ ችግር ነው ያስከተለው። ምክንያቱም መተሐራ የቆቃ ግድብ የመጨረሻው ተጠቃሚ አካል ነው። ከቆቃ ግድብ የሚለቀቀው ውሃ በኮታ የተበጀተ ነበር። በተቀመጠው ኮታ መሰረት ሁሉም አካል ባለመጠቀማቸው በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ላይ የውሃ እጥረቱ ከፍተኛ ነበር። አዋሽ ወንዝ ደርቆ ሰዎች በእግራቸው ነበር የሚሻገሩት። በሸንኮራ አገዳው ምርታማነት ላይ ችግር ደርሷል። ስኳር ለማምረትም ከፍተኛ ውሃ ስለሚያስፈልግ በማምረት ሒደቱም ላይ ችግር ገጥሞንም ነበር።
ሌላው በተደጋጋሚ የመብራት መቆራረጥ ችግሮች ገጥመውናል። በዚህም የተነሳ ረጅም ሰዓት ፋብሪካው ይቆም ነበር። የፋብሪካውም ረጅም እድሜ ማገልገል ሌላው ለምርታማነት መቀነስ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ነበረው። ከዚህ አንጻር አንድ ቁጥር ወፍጮ ለተወሰነ ጊዜ ከስራ ውጪ ሆኖ ነበር። ይህን ወፍጮ በአዲስ ለመተካት ግዢ ሒደት ላይ እንገኛለን።
የተቀመጠልንን ግብ ይመታል፣ አይመታም ለማለት አሁን በምርት ሒደት ላይ ነው የምንገኘው። ስለዚህም ይህ ነው ለማለት አይቻልም። የምርት ዘመኑ ሲያልቅ ነው ይህንን መመለስ የሚቻለው። ሆኖም ማኔጅመንቱም ሠራተኛውም ማሕበሩም ኮርፖሬሽኑም እጅ ለእጅ ተያይዘን እየሰራን በመሆኑ ግቡን የማይመታበት ሁኔታ ሊኖር አይችለም።
ሰንደቅ፡- የመብራት መቆራረጥ በችግርነት አንስተዋል። ሆኖም ከዚህ በፊት ፋብሪካው ራሱ በሚያመርተው ከተፈጨ አገዳ ገለባ ወይም ባጋስ ነበር ኃይል የሚያገኘው። በምን መነሻ ነው ፋብሪካው ቀጥታ ከመብራት ኃይል እንዲወስድ የተደረገው? በማምረቻ ወጪያችሁ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምን ይመስላል?
አቶ ዘነበ፡- መተሐራ ኃይል አመንጭቶ ለራሱ የሚጠቀምበት አሰራር አለ። እያንዳንዳቸው ሦስት ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ተርባይኖችን ይጠቀማል። እነዚህ ተርባይኖች ለድርጅቱ እድሜ ጋር የቆዩ ናቸው። በየአራት ዓመቱ ጥገና ይደረግላቸዋል። ሆኖም ይህ አዲስ ማኔጅመነት ከመምጣቱ በፊት ሶስት ቁጥር ፓዎር ተርባይን እሳት አደጋ ደርሶበት የተቃጠለ ነው። ስለዚህም ሁለቱ ፖዎር ተርባይኖች ናቸው ስራ ላይ ያሉት። ከእነዚህ ከሁለቱ ፓዎር ተርባይኖች ስድስት ሜጋዎት እናገኛለን፣ ቀሪውን ሶስት ሜጋ ዋት ግን በቀጥታ ከመብራት ኃይል በመውሰድ እንጠቀማለን።
ሰንደቅ፡- ኤሊኖ ባስከተለው የውሃ ድርቅ በመጪው የምርት ዘመን በቂ ምርት የሚሰጥ አገዳ ለማግኘት አትቸገሩም? ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖስ እንዴት ይገለጻል? በአማራጭነት ያስቀመጣችሁት አቅጣጫስ ምን ይመስላል?
አቶ ዘነበ፡-የሚያስከትለው ተፅዕኖ ይኖራል። ሆኖም ግን ሰፊ ስራዎችን ሰርተናል። በአጭር ጊዜ ማለትም በአስራ ሶስት ወራት የሚደርሱ ከኩባ የተገኙ የአገዳ ዝርያዎችን ተክለናል። እነዚህ ዝርያዎች በአጭር ጊዜ መድረሳቸው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎች ናቸው። በአሁን ሰዓት ደግሞ በቂ ዝናብ በመዝነቡ የውሃ ፍላጎታችን ተሟልቷል። ስለዚህም ተረባርበን በቂ ዝግጅት እያደረግን በመሆኑ የሚፈራውን ያህል ጉዳት ሊከሰት የሚችልበት እድል አይኖርም።
ሰንደቅ፡- መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ራሱን ችሎ ይተዳደር እንደነበረ የሚታወቅ ነው። በአዲስ አደረጃጀት ደግሞ በስኳር ኮርፖሬሽን ስር ተጠቃሏል። ከሠራተኞቹ የሚደመጠው ለሥራ የሚሆኑ መገልገያዎችን ለመግዛት ከፍተኛ የገንዘብ አቅርቦት እጥረት መጥፋቱን ነው። ከሁለቱ አደረጃጀት አንፃር የሠራተኞቹን ቅሬታ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ዘነበ፡- ለፋብሪካ የሚቀርብ ግብአቶች የሚገዛው ስኳር ተሸጦ ነው። ዘንድሮ በኤሊኖ ምክንያት ቀደም ብለን ካቀድነው 1.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር እቅዱን ከልሰን ወደ 1.1 ሚሊዮን ወረድ አድርገነዋል። ይህም ሆኖ ከፍተኛ ፈተናዎች ናቸው የገጠሙን። ፈተናዎቹን ለማለፍ ጠንክረን እየሰራን ነው። ስለዚህም ስኳር ካልተመረተ ካልተሸጠ የምትፈልጋቸውን ግብዓቶች ልታገኝ አትችልም። ኮርፖሬሽኑም እኛ ስኳር አምርተን ካልሰጠነው ግብዓቶችን ገዝቶ ሊያቀርብልን አይችልም። ይህም ሆኖ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ ባመረተው ልክ ግብዓት አግኝቷል።
እንዲሁም ፋብሪካው ወደ ለአርባ ስድስት አመታት አገልግሎት የሰጠ ነው። ለምሳሌ ወፍጮ አንድን ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ግዢው ተከናውኖ እቃው ገብቷል። አገዳ መቁረጫ እንዲሁም የተለያዩ ፓምፖች ተገዝው ገብተዋል። ሌሎች አስፈላጊ እቃዎችም ደረጃ በደረጃ ለማሟላት እየተሰራ ነው የሚገኘው። ምርታማነቱንም ለመጨመር በኮርፖሬሽኑ እና በመንግስት በመታመኑ ከፍተኛ ድጋፍ ነው እየተደረገልን ያለው። አስተማማኝ ደረጃም ላይ ተደርሷል።
አቶ ተመስገን ወ/መስቀል
የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ መሰረታዊ ሠራተኞች ማሕበር ሊቀመንበር ጋር በስልክ የተደረገ ቃለ ምልልስ
ሰንደቅ፡- ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው አለምክንያት ሲፈናቀሉ ማሕበሩ የሚያደርገው ነገር የለም የሚሉ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ተመስገን፡- ሠራተኛ ማሕበሩ የሚተዳደረው በ377/96 አዋጅ ነው። የሚከራከረውም በዚህ አዋጅ ውስጥ ለሚታቀፉ ሠራተኞችን ነው። ከዚህ አንጻር ከሥራ ገበታው አለምክንያት ተባሮ እንዲሁም በጥፋት ተባሮ ማሕበሩ ጋር ቅሬታውን አቅርቦ ቅሬታውን ያላየነው ወይም ያልሰማነው ሠራተኛ የለም። በሚቀርቡ የቅሬታ መነሻዎች ከማኔጅመንቱ ጋር በጋራ በመወያየት ወደሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ ያደረግናቸው ሠራተኞች አሉ። ሆኖም ግን የሥራ መሪዎች ሱፐርቫይዘሮች ከሥራ ገበታቸው በአንድም በሌላ መልኩም ሲባረሩ በአዋጅ 377/96 የታቀፉ ባለመሆናቸው ሠራተኛ ማሕበሩን አይመለከትም። ሠራተኛ ማሕበሩ ጋር ቀርበው ግን ወደ ስራ ገበታቸው ያልተመለሱ ሠራተኞች የሉም።
ሰንደቅ፡- የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ የማሕበሩ ሊቀመንበር እንደማንፈልገው አስታውቀናል። ሆኖም ግን መብታችን ማስፈጸም አልቻልንም ሲሉ ቅሬታ ያቀረቡ ሰራተኞች አሉ። የሠራተኞቹ ቅሬታን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ተመስገን፡- ኮርፖሬሽኑ የጠራው ስብሰባ አጠቃላይ ሠራተኛውን ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ስለሠራተኛ ማሕበሩ መነሳቱ በራሱ ቦታው አይደለም። ጥያቄውን ያነሱትም በቡድን የተደራጁ ናቸው። ማሕበሩም ሆነ ሊቀመንበሩ ይውረዱ ሲባል ምክንያቶች መዘርዘር አለባቸው። ቢያንስ በዚህ በዚህ ምክንያቶች ጥቅማችን አላስከበረም የሚል መከራከሪያ ቢነሳ ለመወያየትም ጠቃሚ ይሆናል። ከዚህ ውጪ በቡድን ተደራጅቶ ብቻ ይውረድ ማለት ምን ማለት ነው? ማሕበሩ ጠቅላላ ጉባኤ፣ ምክር ቤት እና ሥራአስፈጻሚ ያለው ተቋም ነው። ሥልጣን እርከኖች እንዴት እንደሚወጣባቸው እንደሚወረድባቸው የራሱ አሰራር አለው።
በቡድን የተደራጁት ሰዎች ጥያቄ ብቻ አቅርበው ስብሰባውን ለቀው ነው የወጡት። ለምን በአደባባይ መወያየት ስለማይችሉ ነው። እነዚህ ሰዎች በሙስና የተጨማለቁ፣ በተደጋጋሚ ማኔጅመንቱን እየለመንን ወደሥራ ገበታቸው የመለስናቸው፣ ማሕበሩን ለግል ጥቅማቸው ማዋል የሚፈልጉ፣ የሞተ ሠራተኛን ጉዳይ አስጨርሳለሁ ብለው 3ሺ ብር ጉቦ የተቀበሉ፣ የድርጅት ጥበቃ ተመድበው የአገዳ ገለባ እየሸጡ ገንዘብ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ፣ ከሠራተኞች ደሞዝ ላይ የሚያጭበረብሩ፣ የሕክምና ወረቀት አለኝ የስራ ዝውውር ይደረግልኝ እያሉ የሚያስገድዱ፣ ለግል ጥቅማቸው ብቻ ያደሩ ናቸው።
ሰንደቅ፡- ሌላው የቅሬታ አቅራቢዎቹ አቤቱታ የሠራተኛ ማሕበሩ ሊቀመንበር ያለምንም ተወዳዳሪ ከመደብ 10 ወደ መደብ 14 ማኔጅመንቱ እንዲያድግ በማድረጉ ለሠራተኛው ጥቅም አይቆምም ሲሉ ይከሳሉ? እድገቱም ከሕብረት ስምምነት ውጪ ነው ይላሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ተመስገን፡- በሕብረት ስምምነቱ መሰረት በተለያየ ሁኔታ እድገት ይሰጣል። በውድድር የሚያድጉ ሠራተኞች አሉ። በስራ ብቃታቸው ታምኖ በማኔጅመንት ውሳኔ የሚያድጉ አሉ። በቂ የትምህርት ወረቀት የሌላቸው በስራቸው ግን የተሻለ አፈፃጸም ያላቸው በሥራ መሪዎች ውሳኔ ያድጋሉ። በማኔጅመንት ውሳኔ የማሕበሩ ሊቀመንበር እድገት አግኝቷል ተብሎ ለሚቀርበው ጥያቄ፣ ከዚህ በፊት በማኔጅመንቱ ውሳኔ ያደገ ሠራተኛ የለም ለማለት ነው? ቢያንስ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው አቶ ሐብታሙ ዮሃንስ ያደገው በማኔጅመንት ውሳኔ አይደለምን? የሚገርመው ከስብሰባው በፊት ለሠራተኛው በዚህ በተደራጀ ቡድን የተሰራጨው ሕብረት ስምምነቱን ሸጠው መጡ የሚል ነበር። ስብሰባው ሲጀመር ደግሞ ወደሌላ ጥያቄ ውስጥ ነው የገቡት።
ሰንደቅ፡- በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሠራተኞች ፍልሰት አለ። ከሚለቁ ሠራተኞች (exit interview) የሰበሰባችሁት አስተያየቶች አሉ። ካሉ፣ ለሰራተኞች ፍልሰት ያላችሁ ትንተና ምን ይመስላል?
አቶ ተመስገን፡- የባለሙያ ፍልሰት መኖሩን እስከጠቅላይ ሚኒስትር መስሪያቤት ድረስ ማሳወቃችንን ሄዳችሁ ማጣራት ትችላላችሁ። የሠራተኞች ፍልሰት ለድርጅቱ ሕልውና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸን አስረድተናል። አሁን ላለው ኮርፖሬሽንም አስታውቀናል። አሁን ላይ ደግሞ ጊዜያዊ ሠራተኞች በከፍተኛ ፍጥነት እየለቀቁ ነው። ወደ ኩራዝ ወደተንዳሆ ወደተለያዩ ፕሮጀክቶች እየሄዱ ነው።
ከዚህ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የሚመራ ቡድን መተሐራ ድረስ መጥተው አነጋግረውናል። ወድቆ የነበረው ፋብሪካ በ2006/2007 ዓ.ም. ወደ ውጤታማነት በሠራተኛው ከፍተኛ ትግል መመለሱን ነግረናቸዋል። ሆኖም ግን ሠራተኛው ተገቢውን የማትጊያ ክፍያ አልተፈጸመለትም። ሁለተኛ፣ ለጊዚያዊ ሠራተኞች የሚከፈለው አከፋፋል በጣም ዝቅተኛ ነው። ባለሙያ ሠራተኞችም በከፍተኛ ሁኔታ እየለቀቁ መሆናቸውን ለቡድኑ አስታውቀናል። ደጋግመን ተናግረናል፣ የሚሰማን ግን አጥተናል።
ተከታትለን ባጣራነው መሰረት ቡድኑ ለላከው አካል ሙሉ ሪፖርት አቅርቧል። የሠራተኛው የማትጊያ ክፍያ ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አስታውቋል። ባቀረቡት የውሳኔ ሃሳብ መነሻነትም የ2006/2007 የሁለት ወር ደሞዝ ለማትጊያ ክፍያ መፈቀዱን አወቀን። በደብዳቤም ለድርጅቱም ለእኛም ደረሰን። ሆኖም ግን ኮርፖሬሽኑ ካለብኝ የአቅም ማነስ ክፍያውን አልፈጽምም አለ። ሠራተኛው ማኔጅመንቱንና ማሕበሩን መግቢያ መውጫ አሳጡት። በርግጥም በዚህ የኑሮ ውድነት የሠራተኛው ጥያቄ አግባብ ነው። ክፍያም ሊፈጸም ይገባል።
በዚህም ሳናበቃ ለኮርፖሬሽኑ ስጋታችን አስቀምጠናል። አሁን ፋብሪካ ሊዘጋ ተቃርቧል። በእርሻ ክፍል የተሰማሩ በአገዳ ተከላና ቆረጣ ላይ የሚሰሩ ሠራተኞች ወደሀገራቸው ተመልሰው መግቢያቸው ነው። ይህን ክፍያ ሳንፈጽምላቸው ቢቀር በሚቀጥለው አመት ለቅጥር ስንሄድ የሚቀጠር ሠራተኛ አይገኝም። ስለዚህም ስላለው ጉዳይ ሠራተኛውን ቀርባችሁ አስረዱት ብለን ለኮርፖሬሽኑ አስታውቀናል። ኮርፖሬሽኑ ለውይይት ሲቀርብ ግን የእኛ ጥያቄ የማትጊያ ጥያቄ አይደለም። ችግራችን የመልካም አስተዳደር እጦት ነው አሉ። የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ብቻ አቅርበው ጥለው ወጡ።
ሰንደቅ፡- የሠራተኞች ፍልሰት በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ የጨመረው ከደሞዝ ክፍያ ማነስ ጋር በተያያዘ ብቻ ነው የሚል ትንተና ነው ሠራተኛ ማሕበሩ ያለው?
አቶ ተመስገን፡- አይደለም።
ሰንደቅ፡- ሌሎቹ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ተመስገን፡- ለሠራተኛው አመቺ የስራ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው ነው። እንደተባለውም የመልካም አስተዳደርም አንዱ ችግር ነው። መልካም አስተዳደር በአንድ ጊዜ ሊመጣ የሚችል አይደለም። ደረጃ በደረጃ የሚመጣ ለውጥ ነው። ሆኖም ግን ከዚህ በፊት ከነበረው አስተዳደር የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። እንደሚታወቀው መልካም አስተዳደር እንኳን በመተሐራ በሀገራችንም ውስጥ መቶ በመቶ የሆነ መልካም አስተዳደር የለም። ለውጦች አሉ። የተሻሉ እይታዎች አሉ። ከዚህ በፊት ብዙ የሥራ ክርክሮች በፍርድ ቤት ይያዙ ነበር። አሁን በመመካከር በፍርድ ቤት የተያዘ የሠራተኛ መዝገብ የለንም። የሥራ መሪዎች በራሳቸው ጊዜ ሰራተኞችን ያቆሙ ነበር። አሁን ግን ከሰው ኃይል ውጪ ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ላይ ማንም እንዳያስቆማቸው አድርገናል። እነዚህ የተገኙ መልካም ጅምሮችን አጠናክረን የተሻለ ነገር ለመስራት ዝግጁ ነን።
ሰንደቅ፡- ለሰንደቅ ዝግጅት የደወሉ ሠራተኞች እንዲሁም በስብሳበው ላይ ቅሬታ ያቀረቡ ሠራተኞች ያቀረቡት ቅሬታ፣ እንሰደባለን፣ ያንጓጥጡናል፣ አለምክንያት እንባረራለን እና ከመንግስቱ ኃ/ማሪያም አገዛዝ ያልተናነሰ አስተዳደር ነው ያለው ብለዋል። ይህንን የሠራተኞቹን ቅሬታ ይጋሩታል?
አቶ ተመስገን፡- እነዚህን መሰል ቅሬታዎች መታየት ያለባቸው በ2004 እና በ2005 ከነበረው የድርጅቱ ውደቀት አንፃር ነው። አንድ ቤተሰብ ውስጥ ልጆች ጥፋት ሊያጠፍ ይችላሉ። ልጆችህን ስትቆጣ የተለያዩ ምልክቶች አሳይተህ ነው። የምታሳያቸውን ምልክቶች ልጆችህ የተለያዩ ትርጉሞች ሊሰጧቸው ይችላሉ። በተመሳሳይ መልኩ ሥራ መሪዎች ሠራተኞችን ሲቆጡ የሚጠቀሙበት አግባብ የተለያየ ነው። እንዲሁም የሚሰጠው ትርጉም። አንዳንድ ሰራተኞች በሚያጠፉት ጥፋት ከሥራ መሪዎች የሚደርሳቸው ተግሳፅ ወይም ስድብ ከጥፋታቸው ጋር በማነጻጸር ተገቢ ነው ወይም ስለተናደደ ነው ብለው በራሳቸው ጊዜ በይቅርታ ይተውታል። በአንጻሩ ደግሞ ምን ሲባል እሰደባለሁ የሚል ሠራተኛም አለ። በርግጥም ማንም መሰደብ የለበትም። አለቆች ደግሞ ያልጠበቁት እቃዎች ሲጠፉ ሲመለከቱ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆኑበት አጋጣሚ አሉ። ሆን ተብሎ ግን ሠራተኞችን ለማዋረድ ሥራ መሪዎች ይሳደባሉ ብሎ ለመደምደም ግን እንደማሕበርም እንደግለሰብም ከባድ ነው።n