ሄኖክ የሺጥላ
May 28, 2016
የኤርትራ ህዝብ 25 ኛ አመት የናፅነት በኣሉን አከበረ የሚል ነገር ሰማሁ ልበል ?
የዜናው መንፈስ መጥፎ አይደለም ። እንኳን በባርነት ስር ነበርን ብሎ የሚያምን አካል ፥ እዳሪውን የሚከውንበት አጥቶ ፥ ግምኛው ያፋጠጠው ሰው ፥ ሰዋራ ስፍራ ሲያገኝ እና ቆሻሻውን ሲገላገል የሚሰማው እፎይታ ይኽ ነው የሚባል አይደለም ።
ግን ደሞ ነፃ ከወጡ 25 አመት የሆናቸው ኤርትራዊያን ወንድሞቻችን እንዴት እንዴት እየሆኑ ሃገራቸውን እየለቀቁ እንደሚወጡ ስናስብ ፥ ቀኑን የሚያከብሩት እንደ ናፅነት እለት ወይስ እንደ ሙት አመት ብለን ልንጠይቅ እንገደዳለን ።
የኤርትራ ህዝብ ፥ በሻዕቢያ አባባል « በኢትዮጵያ ቀኝ በተገዙበት » ዘመን ሁሉ እንዲህ ተዋርደው እና አንሰው ያውቃሉ ለማለት ይከብደኛል ። ወዳጅ እና ጓደኞቼ የነበሩ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ሲባረሩ ይሰማቸው የነበረውን ፍፁም የሆነ ኢትዮጵያዊነት ስሜት እና ሌሎች በሪፈረንደሙ ጊዜ እነ ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራን ህዝብ « ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋ የአብሮነ መኖር ምርጫውን » የምርጫ ኮሮጆውን እየቀደዱ ፥ በኤርትራ መገንጠል ላይ እንደተስማሙ አስመስለው ያቀረቡትን ሻቢያ ሰራሽ ፥ ወያኔ መራሽ የሁለቱን ሃገር ህዝቦች የመለየት ሴራ ትተነው ማለት ነው ።
ይሄ የናፅነት 25 አመት ምናልባች በሁለት ሊከፈል ይችል ይሆናል ( እነሱ የምለው ሻዕቢያን እንጂ የኤርትራን ህዝብ እንዳልሆነ አንባቢ ይረዳልኝ ዘንድ አሳውቃለሁ )
የመጀመሪያዎቹ 7 አመታት ፥ ደርግን በመደምሰሳቸው ብሎም ያ ጀግንነት ባመጣው እብሪት ፥ ካንድነት ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን ጉልበት በመናቅ ብሎም ኢትዮጵያን ላሜ ቦራ አድርጎ በመሳል የተሳሳተ ሂሳብም በመስራት በፍጥነት የልዩ ሃገርና የልዩ ህዝብነት ስሜት በኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ላይ በመንዛት ፥ የማያምኑበትን ብቻ ሳይሆን ያልመረጡትን መርጠው ፥ ድንበር እና ማንነት ፈጥረው ለመኖር ተግባራዊ እንቅስቃሴ የጀመሩበት ሲሆን ቀጣዩ 18 አመት ደሞ በወያኔ የሴራ ብትር ተመትተው ፥ በነፃነት ለድህናት እና ለችግር ባሪያ የሆኑበት ዘመን አድርጌ ነው የማያው።
በይበልጥም በሁለቱ ህዝቦች መኻከል ቀረ የሚባለውን የአንድነት ክር ለመበጠስም ሲባል ፥ በመለሰ ዜናዊና በኢሳያስ አፈወርቂ ተደርሶ ፥ በብዙ ብዙሃን ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ደም ተዋናይነት የተከወነው ደም አፋሳሽ ጦርነት ፥ ውጊያው በኢትዮጵያ አሸናፊ ተጠናቀቀ ሲባል ፥ ሻዕቢያ ደሞ (ስለመሸነፉ ሲባል የተሸለመው እንደሆነ አልገባኝም) ብቻ የጦርነቱ መንስኤ የሆኑትን መሬቶች በአልጀርሱ ስምምነት እንዲወስድ ተደርጓል ( ከሞላ ጎደል )።
ከጦርነቱ በኋላ ለሻዕቢያ ፥ ከ 7 አመት በፊት « አሸነፍነው » ባሉት ህዝብ መሸነፋቸው የፈጠረባቸው የሞራል ኪሳራ ፥ በወጣት ኤርትራዊያኖች ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት እንደ ጨው ሲያሟሟው ፥ በኢትዮጵያ በኩል ደሞ ወያኔ ፤ ( ከፍ ሲልም የትግራይ ሰዎች ) ትናንት ሰሃን በማጠብ እና ድስት በመፋቅ ያገለግሉት የነበረውን የኤርትራን ህዝብ አሸነፍን ብሎ ማመን በፈጠረው የባሪያ ስሜት ፥ ኤርትራን በሰፊው ለማጥቃት እድልም ፥ ሁናቴም ፈጠረ። ጠቢቡ ሰለሞን ” ባሪያ ጌታዋን ስትወርስ” የሚለው ይኽንን አይነቱን አሰላለፍ ይመስለኛል ።
ባጭሩ ምን ለማለት ነው ፥ ኤርትራዊያኖች ከኢትዮጵያ ጋ በመኖራቸው በአንድ ሺ አመት ውስጥ የማያጡትን ክብር ፥ ማንነት እና ሰብአዊ መብት በዚህ በ ሃያ አምስት አመት ውስጥ አጥተዋል ። መልካም የነፃነት በአል ስንል በቀይ ባህር እና የሜዲ ትራይን ባህር ውስጥ የአሳ እራት የሆኑትን ኤርትራዊያን ነው ? ወይስ በየሃገሩ የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት እንደ ባህር አሸዋ የትም የተበተኑት ኤርትራዊያን ፥ ወይስ በሳዋ አደገኛ የውትድርና ማሰልጠኛ መከራቸውን የሚያይቱን ወጣት ኤርትራዊያን ፥ ወይስ ጥራቱን ባልጠበቀ ፥ አዋቂ በነጠፈ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንቶ ፈንቶ እውቀት እየቀሰሙ ተኮላሽተው የቀሩትን ኤርትራዊያን ፥ ወይስ አዳም ከመፈጠሩ አለም በቀን ከመቆጦሩ በፊት ይኖሩ የነብሩ ግን ደሞ ለ ዘፍጥረት ትረካ ያልበቁ ህዝቦች ነበሩ እንደሚባለው ፥ እኛ የማናውቃቸው ፥ ከአትላንቲስም ቀደም ብለው የሚኖሩ እና እየኖሩ ያሉ ፥ ነፃነትን ለ 25 አመት ያለ አንዳች ኢትዮጵያዊ ገደብ የሚያጣጥሙ ኤርትራዊያኖች ይኖሩ ይሆን ? ካሉ « እንኳን ናይ 25 ኛ ኣመቲ ብኣለ ነፃነት አበፃኽኩም » ማለት ባልቀፈፈን ።
ነገሩን ሳቴነው ግን የኤርትራ ህዝብ በሃያ አምስት አመቱ ውስጥ ከህዝብነት ወደ ቡድንነት አነሰ ማለት የደፈሩ ሰዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ይመስላል ።
የግርጌ ማስታወሻ
ከዚህ በታች የምታዩትን ፎቶ እያሰባችሁ ሳይሆን ፥ ይልቁንም እነዚህ ክንዶች ( ይህንን ባንዲራ የሰቀሉት ማለቴ ነው ) ዛሬ የት ናቸው የሚለውን እያሰባችሁ ጥሁፉን አንብቡት።
በየሜዲትራኒያኑ ውስጥ ፥ በሲና እና መሰል በርሃዎች ፈሰው ስለመቅረታቸው ብዙ አሳማኝ ነገሮች አሉ ልበል ።