ሄኖክ የሺጥላ
May 28, 2016
እውቀት ምንድን ነው ? መማር ማለት ከድንቁርና በመውጣቱ ፥ ተፈጥሮንና በአካባቢዋ ያሉትን ነገር በመረዳቱ ፥ ነፍሱ ከጨለማ የወጣ ሰው ፥ ወይም ብርሃንን ያይ ዘንድ የተማረ ማለት ይሆናል ። የትምህርት ጥቅምስ ምንድን ነው ? ተቀጣሪ አገልጋይ እና ቀጣሪ ደሞዝ ባልነበረበት ፥ እውቀት እንደ ቅዳሴ እና አዛን ከመንፈስ ጅረት ውስጥ ሿ ብሎ በሚፈስበት ዘመን ማስተማር ማለት ምን ማለት ነበር ? መማርስ ?
እነ ሶቅራጥስ ሲምፖዚየም በተሰኘው ድንቅ ስራቸው ውስጥ « ፍቅር ምንድን ነው?» ብለው ሲጠያየቁ ፥ እነ አጋቶን ሲመሰጥሩ ፥ ያስተማሩን እና ያስተጋበሩት እብይ ነገር ፥ የነሱን ስራ አንብቦ የጥቅስ ጎተራ መሆንን ይሆን ወይስ ሁሉም ሰው የራሱን ሲምፖዚየም ይዞ የሚዞር የሃሳብ ሙዚየም ነው ፥ ልዩነቱ እራሱን ሳያውቅ ሌሎቹን ካላወቅሁ ብሎ በቁንፅልነት እና በመምሰል አባዜ ተጋግጦ እና ተላልጦ መድከሙ እና መውደቁ እንጂ እያሉን ይሆን ?
አንዳንዴ በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ ።
ወድቆ መነሳት ላቃተው ህዝብ፥ ማህሌት ደርሶ ፥ ድጓ ፥ እዝል እና አራራይ በነፍሱ አፎት ሰብዞ ፥ የህይወታችን ብቻ ሳይሆን የእምነታችን አካል እንዲሆን ያደረገው ቅዱስ ያሬድ ፥ እውቀቱን እና የመጀመሪያ መረዳቱን ያገኘው ሰባት ጊዜ ወድቆ ከተነሳ ባለ ብርቱ መንፈስ ትል መሆኑን ስታስቡ እንደ ሰው ምን ይሰማችኋል ?
ታዲያ ትናንት ከትል ህይወት ሳይቀር ምሳሌ መቅሰም የሚችል ህዝብ ዛሬ የት ሄደ? ወይስ እኛ በመንፈስም በአካልም ትናንት ያሬድን ካስተማረው ትል እጅግ ያነስን ስለሆነ ይሆን ?
ቁልቁል የሚንዶሎዶል ጎርፍ ጠራርጎ የሚወስደው ቆሻሻን ብቻ አይደለም ፥ ጎርፉ በሚያልፍበት መንገድ የቆመ እና ከጎርፉ ሃይል ያነሰ ሃይል ያለውን ማናቸውም ነገር እንጂ ። ለኔ የኛ ዘመናዊነት ፥ የኛ እውቀት ፥ የኛ ሃገር መውደድ እና ለሃገር መቆጨት በጎርፍ መሃል ከቆመ ከብት ወይም ከባለጌ ፉጨት አልለይ ያለኝም ለዚህ ነው ።
በምንም አይነት ሃሳብ ተጠራርገን የምንወሰድ ፥ የትም ተንጠባጥበን የምንቀር የወንዝ ዳር ግባሶዎች መሆናችንን መካድ ይከብደኛል ። ያሬድ ከአንድ ደካማ ከሚመስል ግን ተስፋ መቁረጥ ከማያቅ ትል ተምሮ የደረሴውን ዜማ ተጠቅመን ጠሎት አድረሰን ስራችንን የምንጀምር ሰዎች እንዴት ከጠሎቱ ጀርባ ፥ ከዜማው ባሻገር የዜማው ህብለ ሰረሰር እና መንስኤ የሆነውን የተስፋ አለመቁረጥ ምክንያት ፥ ትንሹ « ትል » መሆኑን እንዴት መረዳት አቃታን?
የማይገቡኝ ብዙ ነገሮች አሉ !
በአክሱም እና ላሊበላ የምንመካ ፥ እኛ ግን የምንኖርበትን ጎጆ የሳር ክዳኑን ንፋስ ገልቦ ጨርሶት የዝናብ ማጥለያ በሚመስል ወንፊት ቤት ውስጥ የምንኖር መሆናችንን ሳስብ ፥ አይደለም ከትሉ ከትልቁ ፋሲል መማር ያልቻልን መሆናችንን ሳስብ እንደ አንድ የ ህዝብ አካል ያመኛል። እዎ ግር ይገባኛል ! እኛ አይደለም ዛፍ ላይ ወድቆ ከተነሳ ትል ፥ አናታችን ላይ ከፈላው ተባይ እንዴት ማገገም እንደምንችል መፍትሄ ለመሻት ምንም ግድ የሚለን አይደለንም ?!
ሃሳብ ምንድን ነው ? እውነት ምንድን ነው ? ለውጥ መመኘት ማለት ምን ማለት ነው ? እሻላለሁ ስትል « በምን » የሚል ጥያቄ እኮ ቀጥሎ ይመጣል።
ብርታትን ከትል ሳይቀር ተምረው ፥ ዜማ የደረሱ አባቶች ልጆች እንዴት ከትል ባነሱ ልጆች ይተካሉ ? አይገባኝም!