May 30, 2016
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የነገሩ መነሻ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ጉዳይ ነው። ለትምህርት ሚንስትሩ “ኦሮሚያ ውስጥ በተካሄደው ረብሻ ምክንያት፤ ተማሪዎች አልተዘጋጁም። ስለሆነም ተጨማሪ ግዜ ይሰጠን” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ በኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በኩል ይቀርባል። የትምህርት ሚንስትር ግን ሃሳቡን የማይቀበለውና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ በተያዘለት ቀን፤ ማለትም ዛሬ ግንቦት 22 እንደሚካሄድ ገለጸ።
በዚህ ግትር የሆነ አቋም ምክንያት (የኦሮሚያ መምህራን ወይም ትምህርት ቢሮው እጁ እንዳለበት ይነገራል) ፈተናውን አስቀድሞ በማውጣት ለተማሪዎች እንዲሰራጭ አድርገዋል።
ይህ የሆነው ፈተናው ከመጀመሩ በፊት ሲሆን፤ የዛሬውም ሆነ በሚቀጥሉት ቀናት ፈተና ላይ የሚቀርቡት ጥያቄዎች ተወስደው ወይም ተሰርቀው በማህበራዊ ድረ ገጾች ተሰራጭተዋል። ይህም ሆኖ የትምህርት ሚንስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው፤ “ውሸት ነው ምንም አልተሰረቀም” የሚል ማስተባበያ ሰጡ። ውሸት የተናገሩት ግን ራሳቸው አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው። ፈተናው ከተያዘለት ቀን ቀደም ብሎ ተሰራጭቷል።
በፎቶዎቹ ላይ ከፈተናው በፊት የወጡትን የማትሪክ ወረቀቶች ነው።
ሌላው ቀርቶ ገና ፈተና ላይ ያልቀረበው የሳይንስ ፈተና መልስ ጭምር በማህበራዊ ድረ ገጾች ጭምር ተሰራጭቷል። የሁሉንም መልስ ማቅረቡ ምንም ጥቅም የሌለው ከመሆኑ በተጨማሪ ለሰነፍ ተማሪዎች መንግድ ክከፋ ስለሆነ ትተነዋል። ይህንን ለህትመት ያበቃነው፤ የኢህአዴግ ባለስልጣናት “ፈተናው አልተሰረቀም” የሚል የቅጥፈት ዜና በማሰራጨታቸው፤ ትክክል አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ያህል ነው።
ጎበዝ ተማሪዎች በጥረታቸው ለማለፍ በሚታትሩበት ወቅት፤ ያለአግባብ ፈተናው እንዲወጣና እንዲሰራጭ መደረጉ የሚያሳየው አንድ ነገር ቢኖር፤ የስርአቱን ብልሹነት ነው። ይህም የስርአት ብልሹነት ግንቦት ሃያ ካስገኛቸው ፍሬዎች አንዱ ሆኗል። መልካም ፈተና።