May 31, 2016
የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፍራው ሽጉጤ ትናንት የተቋረጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በአዲስ መልክ የሚሰጥበትን ቀን ይፋ አደረጉ:: ሚኒስትሩ ፈተናው ከሰኔ 27 እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ይሰጣል ያሉ ሲሆን ከነዚህ እለት አንዱ የረመዷን ጾም መፍቻና የኢድ አልፈጥር በዓል የሚውልበት ዕለት ነው::
ምን ያህል መንግስት ተብሎ የተቀመጠው ስርዓት ነገሮችን በግምት እንደሚመራ ያሳያል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች ሚኒስትርን የሚያህል አንድ ስልጣን የያዘ ሰው የፈተና ቀናትን ሲናገር እንዴት ዓመት በዓሉች እና የመንግስት በዓላት የሚዘጉበትን ቀናት ካላንደሩን ከፍቶ አይመለከትም? ሲሉ ይጠይቃሉ::
ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 33.9%, የሚሆነው የ እስልምና እምነት ተከታይ ሆኖ እያለ እንዲሁም የዘንድሮውን የሚኒስትሪ ፈተና ይወስዳሉ ከተባሉት በመቶሺዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች መካከል በርካቶቹ የ እስልምና እምነት ተከታዮች መሆናቸው እየታወቀ በረመዷን ጾም ፍቺ እለት ፈተና ይወስዳሉ ብሎ ማወጅ ምን የሚሉት እብደት ነው? የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ::
አቶ ሽፈራው ለመንግስት ቅርብ ለሆኑ ሚድያዎች እንደተናገሩት ሀገር አቀፍ ፈተናው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ማዕከል አማካኝነት በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚዘጋጅና ባለሙያዎቹ ተፈታኝ የስጋ ዘመድ እንደሌላቸው ተረጋግጦ በፈተና ዝግጅት ይሳተፋሉ ብለዋል:: አሁንም ፈተናው እንዳይሰረቅ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ከሕትመቱ እስከ ስርጭቱ ድረስ እንደሚደረግ አስታውቀዋል::