Wednesday, 01 June 2016 11:54
በ 
 በኢትዮጵያ 18 ሚሊዮን ህዝብ በተረጂነት ይኖራል

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በየሁለት ወሩ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እያዘጋጀ በምሁራን በሚቀርቡ ጥናቶች ተመርኩዞ ሀሳብ እንዲሰጥባቸው ያደርጋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከሰሞኑ “የገጠር ተጋላጭነት ሁኔታ በኢትዮጵያ ልማት” በሚል ርዕስ ዙሪያ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ በቀረቡት ጥናቶች ዙሪያ ሰፋ ያሉ ውይይቶች ተካሂደዋል።

 በዕለቱ ሁለት ምሁራን በዚሁ ዙሪያ የጥናት ወረቀቶቻቸውን አቅርበዋል። በመጀመሪያ ጥናታቸውን ያቀረቡት በገጠር ልማትና በመሬት ይዞታ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ልምድን ያካበቱት አቶ ደሳለኝ ራህማቶ ናቸው። ከሳቸው በመቀጠል ሌላ ጥናት ያቀረቡት በልማት ጉዳዮች ላይ ተመራማሪና የግል አማካሪ የሆኑት ዶክተር አምዲሳ ተሾመ ናቸው። በድርቅ ተጋለጭነትና በሚኖረው አሉታዊ ተፅዕኖ ዙሪያ ሳፋ ያለ ጥናት ያቀረቡት አቶ ደሳለኝ ራህማቶ፤ በጥናታቸው መግቢያ ዳሰሳ በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ድርቅ ዙሪያ ሰፋ ያለና በአሃዝ የተደገፈ ማብራሪያን ሰጥተዋል። የተጠቀሟቸው አሃዞች መንገስት ይፋ ካደረጋቸው ሰነዶችና ድረገፆች የተወሰዱ መሆኑን ያመለከቱት         አቶ ደሳለኝ፤ በአሁኑ ሰዓት በመላ አገሪቱ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ ለድርቅ ተጋላጭ መሆኑን የመንግስትን ሰነድ ዋቢ በማድረግ ገለፀዋል። በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ በተረጂነት ደረጃ ያለውን ህዝብ በሁለት ከፍሎ ማየት የሚቻል መሆኑን በመግለፅ፤ እነዚህም ተረጂዎች አስቸኳይ ጊዜ እርዳታን የሚሹና  በሴፍቲኔት የታቀፉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

 በዚሁ መረጃ መሰረት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ህዝብ በቀጥታ ለድርቅ ተጋልጦ ፈጥኖ ደራሽ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን 8 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ደግሞ በሴፍቲኔት ታቀፎ በተረጂነት የሚኖር ነው። “በአገሪቱ በአሁኑ ሰዓት ሁለት አይነት ተረጂዎች እንዳሉ መታወቅ አለበት”ያሉት ባለሙያው፤ የሁለቱ ድምር በአንድ ላይ ሲታይም 18 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ ገደማ በተረጂነት የሚኖር መሆኑን አቶ ደሳለኝ በዚህ ጥናታቸው ጨምረው አመልክተዋል።

ለድርቁ ተጎጂዎች የእርዳታ እህልን ለማቅረብ መንግስት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እገዛን ከውጪ መጠየቁንና እስከአሁንም ድረስ 300 ሚሊዮን ዶላር ከራሱ ካዝና ማውጣቱን በዚሁ ጥናት ተጠቁሟል። ይህም የወጪ መጠን በቀጣይ ሊጨምር ይችላል የሚል ግንዛቤ ያለ መሆኑም ተመልክቷል። ትምህርት ሚኒስቴር የለቀቀውን መረጃ መሰረት በማድረግ በጥናቱ ላይ እንደተጠቆመው በአሁኑ ሰአት በተከሰተው ድርቅ በመላ አገሪቱ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ተፅዕኖ  ደርሶባቸዋል። ከእነዚህም ህፃናት ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ተማሪዎች ከድርቁ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶቻቸው ስለተዘጉ የትምህርት ገበታ ላይ አይደሉም።

አቶ ደሳለኝ በዚሁ ጥናታቸው አጠቃላይ የድርቁን ሁኔታ ከዳሰሱ በኋላ በቀጣይ የሚኖረውንም የተራዘመ ተፅዕኖ በዳሰሳ ለማሳየት ሞክረዋል። ከዚሁ ድርቅ ጋር በተያያዘ እስከ 60 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ እህል ምርት ሊቀንስ ይችላል የሚል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የሚጠቁም መሆኑንም አቶ ደሳለኝ በዚሁ ጥናታቸው ጨምረው አመልክተዋል። ይህም ከድርቁ በፊት ከነበረው ምርት አንፃር ሲታይ 22 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው ተብሏል። ባለሙያው የአለም ባንክንም መረጃ በማጣቀሻነት ተጠቅመዋል። “የአለም ባንክ በ2002/2003 ከፍተኛ ድርቅ ነበር። አሁንም ያን አይነት ድርቅ ከሆነ 30 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የድህነት ቅነሳ ወደ ሃምሳ በመቶ ሊሻገር ይችላል ብሎ ይተነብያል” ያሉት ባለሙያው፤ በአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ መሰረትም በዚሁ 2002/2003 በኢሊኖ ተፅዕኖ   የአገሪቱ አመታዊ አጠቃላይ የምርት መጠን (GDP) በ3 እና በ5 በመቶ ዝቅ ያለበት  ሁኔታ ነበር። ባለሙያው ድርቁ የከብቶች እልቂትን በማስከተል እያደረሰ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖም አሳይተዋል። በዚህም መሰረት በ2015 እስከ 2 መቶ ሺህ የሚደርሱ ከብቶች መሞታቸውንና በ2016 ደግሞ 450 ሺህ ከብቶች ይሞታሉ ተብሎ እንደሚገመት ሰነዶችን አጣቅሰው አመልክተዋል። ባለሙያው በዚሁ ጥናታቸው በኢኮኖሚው በአጠቃላይ እንደዚሁም በከብቶች ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት በተጨማሪ በቀጥታ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳትም በመጠኑ ዳስሰዋል።

አቶ ደሳለኝ የድርቅ የተፈጥሮ ጉዳት አንድ ጊዜ ከደረሰ በኋላ ዝናብ ቢዘንብ እንኳን ተመልሶ የማገገሙ ጉዳይ ወዲያውኑ የማይታይ መሆኑን ገልፀዋል።  በዚህም ገለፃቸው መሰረት በድርቁ ተጠቂ የሆኑ ዜጎች ከአካባቢያቸው የመፈናቀል አደጋ ይደርስባቸዋል፣ የእርሻ ከብቶቻቸው ይሞታሉ፣ የጤንነት መቃወስ ችግርም ይገጥማቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ድርቁ የከፋ ከሆነ አንድ በድርቅ የከፋ ጉዳት የደረሰበት ቤተሰብ መልሶ ለማገገም ሶስትና አራት አመታት ሊፈጅበት የሚችል መሆኑም በጥናቱ ማብራሪያ ላይ ተጠቁሟል። አቶ ደሳለኝ ያቀረቡትን የጥናት ወረቀትንም መነሻ በማድረግ በተሳታፊዎች በኩል አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ተጨማሪ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ከተሰጡት አስተያየቶች መካከልም ምሁሩ ባቀረቡት ጥናት በአብዛሃኛው የመንግስት ዳታ ተጠቅመዋል። ከዚህ ባለፈ መረጃዎችን የማመሳከር ስራ መስራት ነበረባቸው የሚለው ይገኝበታል። ከዚህም በተጨማሪ መረጃው በፆታ እንደዚሁም በቆላና በደጋ ተከፍሎ ድርቁ ያደረሰው ተፅዕኖ በዝርዝር ቢቀመጥና ቢተነተን የተሻለ ይሆን ነበር ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ መረጃዎቹ በመስክ ስራ ቢዳብሩም እንደዚሁ የተሻሉ ይሆኑ እንደነበርም ተመልክቷል። በኢትዮጵያ ከምግብ አጦት ጋር የተያያዘው ችግር ከአገሪቱ ታሪክ ጋር ለረዥም ጊዜ ተቆራኝቶ የቆየ ችግር መሆኑንም ባለሙያው ጨምረው አመልክተዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply