Wednesday, 01 June 2016 11:54
 በይርጋ አበበ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ግንቦት 20 እና 21 ቀን 2008 ዓ.ም አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል። በጠቅላላ ጉባኤውም የአመራር ለውጥ ያደረገ ሲሆን በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረትም ሰባት አባላቱን ከፓርቲው ሙሉ በሙሉ ማሰናበቱንም ፓርቲው ያደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት በአራተኛ ጠቅላላ ጉባኤው ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱ የሆነው ፓርቲውን ላለፉት ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩትን አቶ አበባው መሃሪን አንስቶ በምትካቸው ዶክተር በዛብህ ደምሴን መርጧል። ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ እንዳመለከተው አቶ አበባው መሃሪ በድጋሚ ለሊቀመንበርነት እንዲያገለግሉ ቢጠቆሙም እሳቸው ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ተብሏል። በስራ አስፈጻሚ አባልነት ግን እንደሚቀጥሉ ታውቋል።

ፓርቲው የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ እንድሪያስ ኤሮን በዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት ከፓርቲው እንዳሰናበተ የገለጸው የፓርቲው መግለጫ በአቶ እንድሪያስ ኤሮ ምትክም አቶ አሰፋ ሀብተወልድ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን አስታውቋል። መኢአድን ላለፉት ሁለት ዓመታት በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሙሉጌታ አበበ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውን ፓርቲው አስታውቋል።

320 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት እንደተገኙበት በተገለጸው የመኢአድ አራተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የምርጫ ቦርድ ተወካዮች በስፍራው ተገኝተው ሂደቱን መከታተላቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሰባት የፓርቲው አባሎች የማዕከላዊ ኮሚቴ ባቀረበው የስነ ስርዓት ሪፖርት መሰረት ከፓርቲው መሰናበታቸውን የገለጸው መኢአድ የቀድሞው ሊቀመንበሩ አቶ ማሙሸት አማረ እና ካቢኔያቸውም ከፓርቲው መታገዳቸውን ገልጿል። ሆኖም የእነ አቶ ማሙሸትም ሆነ ከእነ አቶ እንድሪያስ ጋር በመሆን በዲሲፕሊን ግድፈት ከፓርቲው የተሰናበቱት አባላት በይቅርታ መመለስ ከፈለጉ ፓርቲው በሩ ክፍት መሆኑንም ገልጿል።

ስንደቅ

Leave a Reply