Saturday, 04 June 2016 12:08
Written by አዲስ አድማስ
ሪፕራይቭ የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም በበኩሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የኢትዮጵያን መንግስት አልጠየቁም በሚል ትችት ሰንዝሮባቸዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ኢትዮጵያን የጎበኙት ፊሊፕ ሃሞንድ፤ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በጉብኝታቸው ዋና አጀንዳ እንዳደረጉት የጠቆመው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ዙሪያ መምከራቸውንና አቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ማቆም እንደሚችሉ ማረጋገጫ እንደተሰጣቸውም ገልጧል፡፡
ፊሊፕ ሃሞንድ ምንም እንኳን አቶ አንዳርጋቸውን የእንግሊዝ ቆንስላ እንዲጎበኛቸው መፈቀዱና ወደ ፌደራል እስር ቤት እንዲዛወሩ መደረጋቸው አንድ እርምጃ ቢሆንም፣ ሌሎች ቀጣይ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም መግለጻቸውንና፣ የህግ አማካሪ እንዲኖራቸው መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡
እንግሊዝ በሌሎች አገራት የፍትህ ስርዓት ጣልቃ እንደማትገባ የገለጹት ፍሊፕ ሃሞንድ፤ የአገሪቱ ቆንስላ የአቶ አንዳርጋቸውን ደህንነትና የህግ ምክር አገልግሎት ማግኘት የማረጋገጥ ሚናውን እንደሚጫወት ጠቁመው መንግስታቸው ግለሰቡንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳቱን እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለስልጣን ባለፈው ረቡዕ አቶ አንዳርጋቸውን እስር ቤት ሄደው መጎብኘታቸውንም መግለጫው አክሎ ገልጧል፡፡
ሪፕራይቭ የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ “ፊሊፕ ሃሞንድ ጉብኝታቸው የፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ አልተጠቀሙበትም፤ አቶ አንዳርጋቸው የህግ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ፈጥሪያለሁ ማለቱም ትርጉም የለውም” በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን መግለጫ አጣጥሎታል፡፡