ከዋናው የክብረ በዓሉ ቀን ቀደም ባሉት ሳምንታት ጀምሮ በማግስቱ ቀኖች ጭምር ለበዓሉ ማድመቂያነት ከቀረቡና ከተስተዋሉት ነገሮች መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ የያዘው ‹‹ብዝኃነት›› የሚለው ቃል በጥቅሶች፣ በሸራ ላይ በተወጠሩ መፈክሮች አልፎ አልፎ ከተሽከርካሪ እስከ የንግድና የመኖሪያ ቤት ግድግዳዎች ላይ በወረቀት ተከትቦ ይታይ ነበር፡፡ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት በድምፅና በምስል ይሰማና ይታይ ነበር፡፡ ‹‹ብዝኃነት›› የሚለው ቃል በገላጭነት ያልተያያዘበት ዘርፍም አልነበረም፡፡ ከአገር ልማት፣ ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከፖለቲካው ልማት፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት፣ ከሃይማኖት እኩልነት፣ ከሴቶች ተጠቃሚነት፣ ከወጣቶች ሥራ ፈጣሪነትና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር ለማያያዝ በመሞከር የግንቦት 20 ፍሬ መሆኑን በስፋት ለማሳየት ተሞክሯል፡፡

 

ምንም እንኳ ‹‹ብዝኃነት›› ውልደቱ ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ቢያያዝም የአገዛዙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቁልፍ መሳሪያ ከሆነው ፌዴራላዊ ሥርዓት ጋር ይበልጥ የተቆራኘ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ‹‹ብዝኃነት›› የሥርዓቱ መገለጫ መሆኑን የገዢው ፓርቲም ሆነ የመንግሥት አመራሮች ደጋግመው ሲገልጹት የሚስተዋለው፡፡ ‹‹ግንቦት 20 የብዝኃነታችን ማኅተም ያረፈባት ቀን ናት!››፣ ‹‹ግንቦት 20 በብዝኃነት ላይ ተመሥርታ ራሷን እያደሰች ያለች አገር የተመሠረተችበት ቀን!›› እና የመሳሰሉት መፈክሮች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በአካል ተገኝተው በታደሙበትና ሕዝባዊ መልዕክት ባስተላለፉበት የብሔራዊ ስታዲየም ውስጥ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ተስተጋብቷል፡፡

‹‹ብዝኃነታችንን አጎናፅፋ ለህዳሴያችን የመሠረት ድንጋይ የጣልንበት ቀን ናት፤›› በማለት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለበዓሉ ታዳሚዎች መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡ ‹‹ብዝኃነት›› ከግለሰብ ነፃነት ወይም ከአንድነት ይልቅ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው አይገባም በማለት ከሚሞግቱ አካላት ጋር ገዢው ፓርቲ ያለው እንካሰላንቲያም ያለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሌላ መገለጫ ነው፡፡

የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ወይም ተቺዎች ለአገሪቱ ደኅንነትም ሆነ ቀጣይነት ሊያረጋግጥ ከሚችለው በላይ ሕዝቦቿን እርስ በርስ በማናከስ አገሪቱን ሊያፈራርስ የሚችል አደጋ አድርገው በማንሳት ይሞግታሉ፡፡ ከ25 ዓመታት በኋላ የአገሪቱ አንድነት ተጠብቆ መቀጠል የአቋማቸውን ስህተት በግልጽ እንደሚያሳይ ለመከራከር ለገዥው ፓርቲ ከግንቦት 20 የተሻለ ቀን ማግኘት ይከብዳል፡፡

ሥርዓቱ የአገሪቱ ህልውና ከመቼውም በተሻለ በማረጋገጥ ሕዝቦቿን ተጠቃሚ በማድረግ ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ እንድትሸጋገር ማስቻሉን በማንሳት መንግሥት ይገልጻል፡፡ በአንፃሩ ተቺዎችና ተቃዋሚዎች አገሪቱን በመከፋፈል አንዱ ብሔር ሌላኛውን በጥርጣሬና ሥጋት እንዲያዩ በማድረግ ብሔራዊ አንድነትን እያጠፋ መሆኑን በሌላ ጎኑ ሲገልጹት ይሰማል፡፡

ሥርዓቱ ዛሬ ላይ የፀጥታ ሥጋት ወይስ ትጥቅ?

የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ሒደት ባለፉት 21 ዓመታት አገሪቷ ያለፈችበትንና ያጋጠሟትን ፈተናዎችና ድሎች በማየት ሁለቱም ወገኖች በየራሳቸው ሚዛን የክብደት መጠኑን ሲለኩት ቆይተዋል፡፡

ነገር ግን የዚህ የክርክር የሐሳብ ፍጭት አግዝፈው ካሳዩት አጋጣሚዎች ውስጥ አገሪቱ ሁለት ጊዜ ያስተናገደቻቸውን ክስተቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህም የገዢው ፓርቲን ሥርዓት አደጋ ውስጥ ሊከቱት የነበሩ አልያም ያንቀጠቀጡት በ1997 የነበረው የምርጫ ሒደትና በዚህ ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ለወራት የዘለቀው የሕዝብ ተቃውሞ ናቸው፡፡

ከቅድመ ምርጫውም አንስቶ እስከ ድኅረ ምርጫ ወቅት ድረስ ብዙ የተወራለት የ97ቱ ምርጫ ገዢውን ፓርቲም ሆነ ሥርዓቱን ነዝሮት የነበረ ክስተት ሆኖ ቢያልፍም፣ ሥርዓቱ አገሪቱን ለአደጋ የሚጥል መሆኑን አሳይቷል በማለት ተቃዋሚዎቹ አሁንም ይገልጻሉ፡፡ ይህን የማይቀበለው ገዢው ፓርቲ ግን በወቅቱ ከነበው አደጋ ሥርዓቱ እንደታደገው ሲመልስ ይደመጣል፡፡

በዚሁ ሁኔታ በሥርዓቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችም ሆኑ ክርክሮች የቀጠሉ ሲሆን፣ ይኸው ጉዳይ በዚህ ዓመትም ጎልቶ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ ታይቷል፡፡

ዓመቱ ገዢው ፓርቲ ካለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ ሙሉ በሙሉ የፓርላማውንም ሆነ የክልል ምክር ቤቶችን ያለ አንድም ተቃዋሚና የግል ተወካይ በመቆጣጠር ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መተግበር የጀመረበት መሆኑ ጋር ተያይዞ የመድብለ ፓርቲን ሥርዓቱ አጥፍቶታል የሚል ትችት ተነስቶበታል፡፡ ከዚህ በባሰ ሁኔታም የአገሪቱ ደኅንነት ፀጥታ በተፈጥሯዊና በሰብዓዊ (ፖለቲካዊ) ምክንያቶች ከባድ ፈተናዎች የተጋረጠበት ዓመት እያሳለፈች እንደሆነም ይነገራል፡፡

በተለይም ኤሊኒኖ የተባለው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ድርቅና በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተነሱ ተቃውሞዎች በዋነኝነት ይነሳሉ፡፡ ከእነዚህን ዋና ዋና ችግሮች በተጨማሪም የአገሪቷን የፀጥታ ሁኔታ አስጊ አደጋ ላይ መሆኑን ያሳዩ እውነታዎች መከሰታቸው ሌላው የዓመቱ ክስተት ነው፡፡ ለአብነትም ያህል ባለፈው የካቲት ወር ላይ በአገሪቱ ሰሜናዊ አቅጣጫ በትግራይ ክልል በሥራ ላይ ያሉ 85 ያህል ዜጎች በኤርትራ ታጣቂዎች ታፍነው መወሰዳቸው፣ በጋምቤላ በአኙዋክና በኑዌር ጎሳዎች የተነሳው ደም አፋሳሽ ግጭት፣ በዚሁ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በመግባት ከ200 በላይ የኑዌር ማኅበረሰብ ዜጎችን ከመጨፍጨፍ ባሻገር ከ160 በላይ ሕፃናትን አፍነው መውሰዳቸው እንዲሁም በቤንሻንጉል ከ40 በላይ የሚሆኑ ዜጎች በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች መታገታቸው ባለፉት አሥር ወራቶች ብቻ ከታዩ ክስተቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህንና ሌሎች አበይት ጉዳዮችንና በተለያዩ አጎራባች ክልሎችና ወረዳዎች ለብዙ ጊዜያት ከድንበር ወሰንና ከግጦሽ መሬት እንዲሁም ከውኃ ሀብት ይዞታ ጋር ዕልባት ያላገኙ የግጭት መንስዔዎችን አስመልክተው የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ግንቦት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባቀረቡበት የአሥር ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ሪፖርታቸው በወቅቱ አገሪቷ የገጠማትን የፀጥታ ችግር አስመልክተው ሲያብራሩ ‹‹አፋጣኝ ሥራ ካልተሠራ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የግጭትና ብጥብጥ መሠረታዊ መንስዔዎች ከሆኑት መካከል አንዱ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ሌሎች ኃይሎች አጋጣሚውን በመጠቀም ችግሩን ለማባባስ እየሞከሩ መሆናቸውን ጨምረው ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹በሌላ በኩል ከውስጥም ከውጭም የተጠራሩ አንዳንድ ኃይሎች የመንግሥትን በግልጽነት ድክመት ማየትና መፍታት እንደ ሽንፈት በመቁጠርና የሕዝብን ትክክለኛ ጥያቄዎች ሽፋን በማድረግ ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ ሥርዓቱን ለመቀየር የያዙትን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት ሁከትና ብጥብጥን በስልትነት በመጠቀም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ፣ በአማራና በጋምቤላ በዚህ ዓመት የተከሰተውን በማንሳት ‹‹በተናበበና በተደጋገፈ ሁኔታ ሊተገበሩ የሚገባቸው ሲሆን፣ የፀጥታ ሁኔታዎችን በተመለከተ የተደረገው ክትትልና ግምገማ መልካም ውጤቶችንና አሳሳቢ ጉዳዮችን አመላክቷል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

‹‹አንዱ ጥያቄያቸው ምላሽ ሲያገኝ በፍጥነት ሌላ ጥያቄና አጀንዳ በመፍጠር ሕዝቡን ያዋክቡታል፡፡ በራሳችን በኩል ለጥያቄዎች የተሟላ ፈጣን ምላሽ የማንሰጥ መሆናችን ለነውጠኞች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

የፀጥታ መዋቅሩ ልምዱን በማዳበር ሁከት ያለባቸው አካባቢ እየተደራጀ ቢሆንም ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ቀደም ብሎ ለመከላከል የነበረው ዝግጅት ግን ከሚጠበቅበት በታች ውሱንነት እንደነበረበትም አቶ ካሳ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ክልሎች ያለው ሰላማዊ ግንኙነት ቢቀጥልም፣ የአስተዳደራዊ ወሰን እልባት የመስጠት ጉዳዮች አልተጠናቀቁባቸውም ባሏቸው ቦታዎች ግጭቶች መከሰታቸውንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት እልባት አግኝተዋል ካሏቸው ውስጥ በ21 ዓመታት ሳይፈታ የቆየው የቢሮና የዲማ ድንበር ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ጉዳዩ በፌዴራል መንግሥት፣ በደቡብ ክልልና በጋምቤላ ክልሎች መንግሥታት መፍትሔ እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡

‹‹ከወሰን ጋር በተገናኘ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም የሚቀጥሉ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በአብዛኛው ለግጭት ምክንያቱ የወሰን ጉዳይ ሳይሆን በአመዛኙ የውኃ እጥረት ነው፤›› በማለት አቶ ካሳ ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአጎራባች ክልሎች መካከል ቀጥተኛ የግጭት መነሻ የሚሆነው አንዳንድ አመራሮች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የወሰን ግጭት ማስነሳታቸው እንደሆነ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳ ስለእነዚህ አመራሮች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ባይሰጡም ‹‹እነዚህን ልክ ማስገባት ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ አባላት ተመሳሳይ የድንበርና የወሰን ግጭት በተነሳባቸው አካባቢዎችን መንግሥት ለ21 ዓመት ሙሉ ለምን መፍታት እንዳልቻለ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በተለይ ከአዋሽ-ወልዲያ የሚገነባው የባቡር መንገድ የሚያቋርጠው የሰሙ ሮቢ ወረዳ፣ በምንጃር-መተሐራ-ፈንታሌ አካባቢ ተደጋጋሚ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንዲሁም በርከት ያሉና በሁሉም ክልሎች በሚባል መልኩ ግጭቶች አሉባቸው የተባሉ ቦታዎች ተጠቅሰዋል፡፡ ምንም እንኳ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ ከምክር ቤቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ሁሉ አንድ በአንድ ባይመልሱም ጠቅለል ያሉ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት ረዥም ዓመታት እንዲወሰዱ ካደረጉት ዋና ዋናዎቹ በክልልና ወረዳ አመራሮች አፋጣኝ መልስ ለመስጠት የፖለቲካ ተነሳሽነት ችግር፣ የአመራር ብቃት ችግር እንዲሁም ወሰን ተጋሪ ክልሎች አመራሮች ተቀራርበው በጋራ ያለመሥራት ችግሮች መሆናቸው የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ተጠቅሷል፡፡

ከምክር ቤት አባል ከተነሱት አፋርና አማራ በሚዋሰኑበት በአንድ ወረዳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ግጭቶችን በዋቢነት አንስተዋል፡፡

በተለይ የአማራ ክልል ነዋሪዎች የአፋሮች ይዞታ በሆነ መሬት ላይ የመለስ ፋውንዴሽን የተገነባበት ስፍራ አሁን በሁለቱ ክልል ነዋሪዎች የግጭት መነሻ ሆኗል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ‹‹የእኛ ሥራ በሁሉም ችግሮች ጣልቃ እየገባን መፍታት አይደለም፡፡ ትልቁ ሥራችን ክልሎች በየአካባቢያቸው የተፈጠሩ ችግሮች እንዲፈቱ ማበረታታትና አቅም መገንባት ነው፡፡ እኛ በቀጥት ልንገባ የምንችለው ክልሎች ሲጠይቁን ብቻ ነው፤›› ብለው አብራርተዋል፡፡

‹‹ለአብነት በምንጃር፣ መተሐራ እንዲሁም ፈንታሌ አካባቢ ለተከሰቱት ግጭቶች ጣልቃ የገባነው ክልሎች ስለጠየቁን ነው፤›› ሲሉ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ በአገሪቱ ባለፉት አሥር ወራት የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክተው ሚኒስትር ዴኤታው ሲገልጹት፣ ‹‹ዘንድሮ የተነሳው ማዕበል አገር ጠራርጎ የሚሄድ ነበር የሚመስለው፡፡ በሁለት ነገር ነው ያረጋጋነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ መሆኑን በማረጋገጥና በፀጥታ ኃይላችን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአፋርና የሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የድንበር ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል፣ መለስተኛ ጉዳዮች ያልተጠናቀቁ ከመኖራቸው በስተቀር በአካባቢው ሰላም ሰፍኗል፡፡ የአፋርና የኢሣ ማኅበረሰቦች ወንድማማችነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በመቀናጀት ሕዝቦቹን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፤›› በማለትም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ይገልጻል፡፡

የኦሮሚያና ሶማሌ፣ የሶማሌና አፋር፣ የአማራና ትግራይ፣ የአማራና ኦሮሚያ፣ የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ (ውስን ቦታዎች) የአስተዳደራዊ ወሰን የማካለል ሥራዎች ሊጠናቀቁ ከሚገባቸው ጊዜ በላይ እየወሰዱ አንዳንዶቹም የግጭት መንስዔ እየሆኑ መምጣታቸውን የአቶ ካሳ ሪፖርት ይገልጻል፡፡

በምክር ቤት አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በመንግሥት በኩል አፋጣኝ ምላሽ አለመሰጠቱን ሚኒስትሩ ተቀብለውታል፡፡ ለምሳሌ ያህል በኬንያ ጠረፍ በኩል የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ በሆነችው የሞያሌ ከተማ እንደምሳሌ የተነሳች ሲሆን፣ ከተማዋ እስካሁን የራሷ ባለቤት ስለሌላት የልማት ተጠቃሚ መሆን አለመቻሏ ተነስቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልልና በሶማሊ ክልሎች ሥር ትገኛለች፡፡

‹‹የድንበር ጉዳዮቹ እልባት አለማግኘታቸው የየክልሎቹ አመራሮች ድክመትና ተጠያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የፌዴራል መንግሥት አካላትም ጉዳዩን በጥብቅ ዲሲፕሊን ይዘው በተጠያቂነት አለመከታተል በፍጥነት ሊታረም እንዳይችል አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን እነዚህ ችግሮች የፌደራል ሥርዓቱ የፈጠራቸው ችግሮች ናቸው ተብለው የሚነሱ ክርክሮችን ሚኒስትሩ አጣጥለውታል፡፡

‹‹በዚህ ዓመት የተፈጠሩ ግጭቶችን አንዳንድ ወገኖች የፌዴራል ሥርዓቱ የፈጠራቸው ችግሮች አድርገው ለማቅረብ ጥረት አድርገዋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓታችን ለእኛ የተሻለ አማራጭ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛው መፍትሔ መሆኑን ባለፉት 25 ዓመታት ሕዝባችን ከተግባራዊ ልምዱ የተገነዘበው ጉዳይ ሆኗል፡፡ የመንግሥት ግንኙነት የፖሊሲ (ሕግ) ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በጋራ እየሠሩ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ካሳ ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮው ዓመት በአንዳንድ ክልሎች የተነሱ ብጥብጦችን ከመከላከልም ሆነ ከተከሰቱም በኋላ በመፍታቱ ሒደት ውስጥ ችግሩ በውል መታየቱን መንግሥት አልካደም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለም የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ ላይ ፈተና የሆኑ ሌሎች ችግሮችንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም ሕገወጥ የጦር መሳሪያ እንደሚገኝበት አቶ ካሳ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አገር እየገባ የፀጥታ ሥጋት ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ሁሉም ክልሎች ሕገወጥ የጦር መሳሪያን ለመቆጣጠር ያከናወኑት በተለያዩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጅምር ሥራ የሚያበረታታ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት እየተከናወኑ ያሉ ጅምር ሥራዎች ቢኖሩም፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመሄድ አዝማሚያ በማሳየቱ ሌላኛው የፀጥታ ሥጋት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሚመለከታቸው አካላት መካከል ቅንጅታዊ ሥራው ያልተጠናከረ መሆኑ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ደላሎችን ለማስታገስ በአንዳንድ ክልሎች ይዞ የማስቀጣት ጅምር ሥራዎች የተመዘገቡ ሆኖ ሕገወጦቹ ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የሚያደርግ ጠንካራ ዕርምጃ ከመውሰድ አኳያ ሰፊ ሥራ መንግሥትን እንደሚጠብቀውም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ወቅት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የፀረ ሰላም ኃይሎች የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በግብዓትነት እየዋለ የሚገኝ መሆኑን ወስደን ስንመለከት የችግሩ ደረጃ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እንገነዘባለን፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

ሌላኛው የፀጥታ ሥጋት ተብሎ በሚኒስትሩ የተጠቀሰው ዓብይ የፀጥታ ሥጋት ደግሞ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ‹‹ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድን የመቆጣጠር አቅማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ቢሆንም፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመሆኑ መንግሥትና ሕዝብን ከፍተኛ ሀብት እያሳጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በየደረጃው የሚገኙ አመራር አካላት ለሥራው ተገቢውን ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥተው አለመምራት፣ በየደረጃው ያለው የአመራር አካል ቁርጠኝነት መጓደል፣ ኅብረተሰቡን በኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ መቆጣጠር ሥራ ላይ በባለቤትነት እንዲሳተፍ አለማድረግ ትልቅ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡