መድረክ በ2002 ዓ.ም. ከተመሠረተ በኋላ በግንባር አደረጃጀት ተደራጅቶ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት አቅፎ በፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ጉልህ ሚና ለመፍጠር ቢሞክርም፣ እስካሁን ማሳካት የቻለው አንድ የፓርላማ መቀመጫን ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ የመድረክ የአቋም መግለጫ ይህ ገደብ የመጣው ለሕዝብ ፈቃድ የማይገዛ ገዥ ፓርቲ ስላለ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

መድረክ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ መብቶችን በመጠቀም ወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳዮችን በሚመለከት ሰላማዊ ሠልፎች ለማዘጋጀት ያደረጋቸው ሙከራዎች በገዥው ፓርቲ ክልከላ ሊካሄዱ እንዳልቻሉም ጠቅሷል፡፡ የአባል ፖለቲካ ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤቶችም በገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በመዘጋታቸው ሥራዎችን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻለ አመልክቷል፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በተነሳው የተቃውሞ እንቅስቃሴ መንግሥት አግባብ ያልሆነ የኃይል ዕርምጃ ወስዷል ሲል የከሰሰው መድረክ፣ በድርጊቱ ከ300 በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ጠቅሷል፡፡ ‹‹በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች በገፍ ታስረው በመንገላታት ላይ ይገኛሉ፡፡ በርካታ የመድረክ አባላትም በግፍ ታስረው በመሰቃየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ገዥው ፓርቲ ራሱ ባመነበት ብልሹ አስተዳደር ምክንያት የተነሳውን ሰላማዊ የሕዝብ ተቃውሞ በኃይል ለመጨፍለቅ የወሰደው የግፍ ዕርምጃ በመሆኑ አጥብቀን እንኮንነዋለን፤›› በማለት መግለጫው ያትታል፡፡

መድረክ ገዥው ፓርቲ ነፃ የግል ፕሬሶችን በማዳከምና የመንግሥት ሚዲያዎችን የፕሮፖጋንዳ መሣሪያው አድርጎ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ አፈና ፈጽሟል ብሏል፡፡ በተጨማሪም መድረክ ከገዥው ፓርቲ ጋር ለመወያየት በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጥያቄዎች ውድቅ እንደተደረጉበት አመልክቷል፡፡ በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በየቦታው ታስረው የሚገኙት እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡

የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ውይይትን በመግፋት ጥሎ የወጣው ራሱ መድረክ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ሥነ ምግባርና ሕግ ላይ ስንወያይ ከኢሕአዴግ ጋር ብቻዬን ነው መወያየት የምፈልገው በሚል ውይይቱን ጥሎ ወጥቷል፡፡ በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል አይደለም፡፡ የምርጫ ቦርድ በሚያደርጋቸው የውይይት መድረኮች ግን ከመሳተፍ የከለከለው የለም፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲወያዩ መድረክ የመሳተፍ ዕድል አለው፡፡ ከዚያ ውጭ ግን በአገሪቱ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት አንፃር ኢሕአዴግ በተናጠል እያንዳንዱ ፓርቲ ጋር መወያየት አስቸጋሪ ነው የሚሆንበት፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

መድረክ ብቻ ለብቻ መወያየት የሚፈልገው ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ከመሆኑ አኳያ ነውና ኢሕአዴግ በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም ለመውሰድ ያደረገው ውይይት ካለ የተጠየቁት አቶ ደስታ፣ ‹‹ኢሕአዴግ በጉዳዩ ላይ የተለየ አቋም ለመውሰድ ያደረገው ውይይት የለም፡፡ ዋነኛ ተቃዋሚ የሚለውን ስምም መድረክ ለራሱ የሰጠው ነው፡፡ ሕጉ ያስቀመጠውን መሥፈርት አሟልቶ ሕጋዊ ዕውቅና የተሰጠው ፓርቲ ሁሉ ለኢሕአዴግ እኩል ነው፡፡ ትልቅነትና ዋነኛ ተቃዋሚነት የሚለካው በሰላማዊ ውድድር ሕዝብ በሚሰጠው ድጋፍ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች በመድረክ ላይ እያደረሱ ነው በሚል ስለቀረበው ወከባና የመብት ጥሰት አስመልክተው ሲናገሩም፣ ‹‹የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ይህን የማድረግ ሥልጣን የላቸውም፡፡ የሥነ ምግባር ደንቡም አይፈቅድላቸውም፡፡ ይኼ አስተማማኝና ተጨባጭ ማስረጃ የማይቀርብበት ተራ ስም የማጥፋት ድርጊት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢሕአዴግ አባላትን ጨምሮ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ወንጀል ከፈጸሙ በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ያስታወሱት አቶ ደስታ፣ የፍትሕ አካላት ከዚህ አንፃር ዕርምጃ ወስደው ከሆነ ኢሕአዴግ የሚወቀስበት ምክንያት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ ካድሬዎች የመብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚል ፓርቲ እነማን? መቼ? የት? የሚሉትን ጥያቄዎች ሊመልስ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ቢሆን ኖሮ እነዚህ ነገሮች በተጨባጭ ለማጣራት ይቻል እንደነበር የጠቆሙት አቶ ደስታ፣ ‹‹ኢሕአዴግም የተባሉት ጥሰቶች ስለመከሰታቸው ካረጋገጠ ዕርምጃ ለመውሰድ ይቀለው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

መድረክ አራት ፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት አቅፏል፡፡ እነዚህም ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ አረና፣ የሲዳማ ነፃ አውጪ ንቅናቄና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኅብረት ናቸው፡፡