Wednesday, 08 June 2016 12:31
በ1983 ዓ.ም አገሪቱን ኢህአዴግ ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በየአቅጣጫው ከሚስተዋሉ አበይት ክስተቶች መካከል ብሔር ተኮር እና ህብረ ብሔር የፖለቲካ ፓረቲዎች መቋቋም ነው። አንዳንዶቹ የምስረታ በዓላቸውን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ዓመት የልደት ሻማቸውን ሳይለኩሶ የሞታቸው መርዶ የሚሰማ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ መኖራቸውን የሚያሳውቁት በአምስት ዓመት አንዴ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ላይ ብቅ ብለው በመታየት ብቻ ሲሆን ይታያሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ “በገዥው ፓርቲ በኩል ጫና ቢበረታብንም ከተነሳንበት የትግል ዓላማ አንጻር ትግላችንን ከዳር ሳናደርስ መደናቀፍ ብሎ ነገር አይነካንም” ሲሉ ደግመው ደጋግመው ሲናገሩ ይሰማል። ብዙዎቹ ከመተባበርና ከመዋሃድ ይልቅ በየፊናቸው መታገልን የሚመርጡ በመሆናቸውና በተለይ በምርጫ ወቅት የደጋፊዎችን ድምጽ እንዲበታተን የሚያደርግ በመሆኑ ህዝቡ “ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” እያለ በይፋ እስከመተቸት የደረሰበት ወቅት ሩቅ አይደለም።
ሰሞኑን በአገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የድርጅታቸውን ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደዋል። በጠቅላላ ጉባኤያቸውም የፓርቲዎቻቸውን አመራሮች በሌሎች አዳዲስ አመራሮች የተኩ ሲሆን በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ ላይም መግለጫ አውጥተዋል። የፓርቲዎቹን መግለጫ እና ጠቅላላ ጉባኤ ሪፖርት ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
የሊቀመናብርት ምርጫ እና የስራ አስፈጻሚ ሹም ሽር
ላለፉት ሁለት ዓመታት እና ከዚያ በላይ መኢአድን በሊቀመንበርነት የመሩት አቶ አበባው መሃሪ ከመንበረ ስልጣናቸው ተነስተው የ72 ዓመቱ አዛውንት ዶክተር በዛብህ ደምሴ መንበሩን ተረክበውታል። ከአቶ አበባው ከስልጣን መውረድ ጋር በተያየዘም መኢአድ በዶክተር በዛብህ ደምሴ የሚመራ አዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ አካሂዷል። በዚህም መሰረት ዶክተር በዛብህ የፓርቲው ሊቀመንበር ሲሆኑ አቶ አሰፋ ሀብተወልድ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፣ አቶ ሙሉጌታ አበበ ምክትል ሊቀመንበር እና አቶ አዳነ ጥላሁን ደግሞ ዋና ጸሀፊ ሆነው የተመረጡ ሲሆን የቀድሞውን ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪን ጨምሮ ሌሎች አባላት ደግሞ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ተመርጠዋል። የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ እንድሪያስ ኤሮ ደግሞ ከፓርቲው ተወግደዋል።
የፓርቲውን አዲሱን ካቢኔ በማዋቀር በኩል ምን እየሰሩ ነው? ተብለው ከሰንደቅ ጋዜጣ የተጠየቁት ዶክተር በዛብህ “የፖለቲካ ፓርቲ መመራት ያለበት በእውቀት ላይ ሊሆን ይገባል የሚል እምነት አለኝ ምክንያቱም ሰዎቹ የሚሰሩትን የሚያውቁ መሆን አለባቸው። በዚህም መሰረት የትምህርት ደረጃንና እውቀትን መሰረት ባደረገ መልኩ የትኞቹ ብቁ ናቸው የሚለውን መመዘኛ ካየን በኋላ በቅርቡ መዋቅር እንሰራለን። የስራችንን ውጤት በቅርቡ ይፋ የምናደርግላችሁ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
መድረክ በበኩሉ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን ለአንድ ዓመት በሊቀመንበርነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን በድጋሚ ለመጭው አንድ ዓመት በሊቀመንበርነት እንዲመሩ መርጧል። (በመድረክ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት አንድ ሊቀመንበር ፓርቲውን ማገልገል የሚቸለው ለሁለት ዙር ምርጫዎች ብቻ ሲሆን በአጠቃላይ ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው) ከፕሮፌሰር በተጨማሪ ደግሞ ፓርቲው አራት ምክትል ሊቃነ መናብርትን የመረጠ ሲሆን ዶክተር መረራ ጉዲናን ምክትል ሊቀመንበርና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ ገብሩ ገብረማሪያምን ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ዶክተር ሚሊዮን ቱማቶን ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ እና አቶ ካሳዬ ዘገየን ምክትል ሊቀመንበርና የፋይናነስ ጉዳይ ኃላፊ አድርጎ መርጧል። አቶ ዓለሙ ኩይራን ደግሞ ጸሀፊ ሆነው እንዲሰሩ መርጧቸዋል።
የቀድሞው ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ከፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ውጭ ሆነዋል። አቶ ጥላሁን ለምን ከኃላፊነት ውጭ ሊሆኑ እንደቻሉ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አቶ ጥላሁን “አሁን በዝርዝር መግለጽ በማልፈልገው መልኩ በስራ አስፈጻሚነት መስራት አለመፈለጌን በቃል ባቀረብኩት አቤቱታ መሰረት ነው ከስራ አስፈጻሚ ውጭ የሆንኩት” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን ከትግል ውጭ አለመሆናቸውን ጨምረው ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹ ስለ ወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ
መድረክ በጠቅላላ ጉባኤው ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ በአሁኑ ወቅት አትዮጵያ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን አስታውቆ በተለይ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ አገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይጎለብትና ሰብአዊ መብት ሳይሸራረፍ እንዲከበር እየሰራ አለመሆኑን አስታውቋል። ይህን በተመለከተ ባወጣው መግለጫም “መድረክ ሰላማዊ የትግል ስልትን መርጦ የሕዝባችንን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የምርጫ ሥርዓት በሀገራችን ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በ2002 ዓ.ም እና በ2007 ዓ.ም በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጓል። ይሁን እንጂ በሕዝብ ፈቃድ ሳይሆን በጉልበቱ በስልጣን ላይ ለመቆየት ቆርጦ የተነሳው የኢህአዴግ አገዛዝ ምርጫዎቹን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚውል የይስሙላ ምርጫ ብቻ እንዲሆኑና የሕዝባችን ነፃ የመምረጥ መብትና የሥልጣን ባለቤትነት ተግባራዊ እንዳይሆን በምርጫው በሚሳተፉ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ላይ ዘግናኝ የሆኑ የአፈና እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። በተለይም በ2007 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ በንቃት ከተሳተፉ አባሎቻችን ውስጥ በአምስት አባሎቻችን ላይ የግዲያ ወንጀል የተፈጸመ ሲሆን ገዳዮቻቸውም ለሕግ ቀርበው ፍትሐዊ ውሳኔ ያገኙበት ሁኔታ የለም። ብዙ አባሎቻችንም ለእስራትና ለተለያዩ እንግልቶች ተዳርገዋል። ስለዚህም ገዥው ፓርቲ በአገዛዝ ዘመኑ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ ፍትሐዊ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ታአማኒነት ያለው ምርጫ በሀገራችን እንዳይካሄድ አድርጎ ሀገራችንን በማን አለብኝነት በጉልበት ለመግዛት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በጥብቅ እናወግዛለን” ሲል አስታውቋል።
መድረክ ከዚህ በተጨማሪም እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን ግጭት አስመልክቶ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ያወገዘ ሲሆን በግጭቱ ሳቢያም ከ300 በላይ ዜጎች መሞታቸውንና የፓርቲውን አባላትና አመራሮች ጨምሮ በርካታ ዜጎች ለእስር መዳረጋቸውንም ገልጿል። ይህን ድርጊትም እንደሚያወግዘው ፓርቲው ባወጣው የአቋም መግለጫ አስታውቋል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት አዲሱ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብህ በበኩላቸው የወቅቱ የአገራችን የዴሞክራሲ ምህዳር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መውደቁን ተናግረው በተለይ የዜጎች ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት እየተጣሰ መሆኑን ተናግረው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመወዳደር እድላቸውም እየተዳፈነ መምጣቱን አሳውቀዋል።
የፓርቲዎቹ ቀጣይ ጉዞ እና
የተቃውሞው ጎራ እድል ፈንታ
መድረክ ባወጣው መግለጫ “በአሁኑ ወቅት የኢህአዴግ አገዛዝ በማን አለብኝነት ዜጎችን በየሰበብ አስባቡ ማሰሩን ቀጥሏል። ዛሬም በሀገራችን በአጠቃላይና በተለይም በኦሮሚያ ክልል እስሩ ተባብሷል። ስለሆነም በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት በየቦታው ታስረው የሚገኙት እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጉባኤው አጥብቆ ይጠይቃል” ያለ ሲሆን ፓርቲው አክሎም በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ የተቃውሞ ሀሳቦችን ኢህአዴግ ተቀብሎ ማስተናገድ እየቸገረው መምጣቱን ገልጿል። ለዚህም መድረክ በተለያዩ ጊዜያት የጠራቸውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን መንግስት መከልከሉን አስታውሷል።
ፓርቲው አያይዞም “በአሁኑ ወቅት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ታቃውሞን ለማፈን የሚወሰዱ አምባገነናዊ የኃይል እርምጃዎች፣ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦትና የዜጎች በገፍ ሥራ ማጣትና መሰደድ የሀገራችን ተጨባጭ መገለጫዎች በሆኑበት ሁኔታ የኢህአደግ አገዛዝ በልማታዊ መንግሥትነት እየተመጻደቀ ከመሆኑም በላይ ባሉት ተጨባጭ ችግሮች ላይ ለመወያየትና በሀገራችን የሕግ የበላይነት የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንዲቻል መድረክ በተደጋጋሚ ያቀረበቸውን የሰላማዊ ውይይት ጥያቄዎችን ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በማን አለብኝነት ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ተግባሩ የሀገራችን ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ የሚያገኙበትን እድል ዘግቶ ይገኛል። ጉባኤው ይህ የኢህአዴግ አምባገነናዊ ባሕሪይ በሀገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ በጥሞና የገመገመው ሲሆን ኢህአዴግ ከዚህ አደገኛ ባሕሪው በአስቸኳይ ታርሞ በአሁኑ ወቅት ዘግቶ የሚገኘውን የሰላማዊ መፍትሔ በር በአስቸኳይ እንዲከፍትና ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ እንዲሆን አጥብቆ ይጠይቃል” በማለት አስታውቋል።
መኢአድ በበኩሉ ዛሬ (እሁድ ሰኔ 5 ቀን 2008 ዓ.ም) በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተፈጠረ ብጥብጥ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎችን የሚዘክር የሻማ ማብራት ፕሮግራም በጽ/ቤቱ ያዘጋጀ ሲሆን ይህን በተመለከተ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ “ያለፈው መጥፎ ታሪክ እንዳይደገም ሁላችንም ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። በተለይ ኢህአዴግ ከተጠናወተው አምባገነናዊ ባህሪው ሊስተካከል ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
የሁለቱ ፓርቲዎች መግለጫ እና አስተያየት የሚያመለክተው የተቃውሞው ጎራ ቀጣይ እጣ ፈንታው የሚወሰነው በገዥው ፓርቲ በኢህአዴግ አካሄድ ላይ መሆኑን ነው። ለዚህም እንደማሳያ አድርገው ያቀረቡት ገዥው ፓርቲ ስልጣኑን መሰረት አድርጎ ሁሉንም በሮች ዝግ ማድረጉን በመተው ለውይይትና ለድርድር በሩን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል ባይ ናቸው። ይህ ካልሆነ ግን የተቃውሞው ጎራ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ እጣ ፈንታም አሳሳቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሰላማዊ ትግሉ ተዋንያን ሚና
በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ መንግስት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪክ ማህበራት እና የአገሪቱ ዜጎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። እነዚህ አካላት ሚናቸው ከተወሰነ (ዝቅተኛ እንዲሆን ከተደረገ) ግን ሰላማዊ ትግልም ሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይደርስና በምትኩ የትጥቅ ትግልና አፈ ሙዝ ቦታውን ይረከቡታል። ይህ እንዳይሆን ነው ከላይ የተጠቀሱት አካላት ሚናቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው የሚባለው።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ስንመለከት ግን ዋናው መሪ ተዋናይ የፖለቲካ ስልጣኑን የሚይዘው ቡድን (መንግስት) ይሆንና ሌሎች አካላት የሚኖራቸው ሚና ግን እጅግ የተወሰነ ሆኖ ይታያል። ሁለቱ ፓርቲዎች የገለጹትም ከዚህ አይነት የፖለቲካ አካሄድ ወጥተን ሁሉም በውሳኔ ሰጭነት የሚሳተፍበት ነጻ ሚና እንዲሰጠው ይገባል ሲሉ የገለጹ ሲሆን በተለይ የአገሪቱ ዜጎች ሊኖራቸው የሚገባው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። በአገሪቱ እየታዩ ላሉ ችግርች ዜጎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ፓርቲዎቹ ህዝቡም ከጎናቸው እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል።
መደረክ በመግለጫው መጨረሻ “መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም ማሕበረሰብም ኢህአዴግ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን እየፈጠረ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ በወቅቱ ለማረም እንዲቻል መድረክ እያደረገው ያለውን ሰላማዊ የመፍትሔ ጥረቶች በአግባቡ ተረድቶ ከጎኑ በመሰለፍ የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያበረክት ጉባኤው ጥሪ ያቀርባል” ሲል አሳስቧል።
ስንደቅ