Wednesday, 08 June 2016 12:23

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ በትላንትናው ዕለት አጽድቋል። በአዋጁ ትርጓሜ መሠረት ኮምፒውተር ወይም የኮምፒውተር ሥርዓት ማለት በሶፍትዌር አማካይነት እና ማይክሮቺን ቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ የዳታ ፕሮሰሲንግ፣ ክምችት፣ ትንተና፣ ሥርጭት ግንኙነት ወይንም ሌሎች ሂሳባዊ ወይም አመክንዮአዊ ተግባራትን የሚያከናውን መሳሪያ ሲሆን ተገጣሚ አካላትንም ይጨምራል። የአዋጁ ዝርዝር ቁምነገር እንደሚከተለው ቀርቧል።

አዋጁ ለምን አስፈለገ?

በኢንፎርሜሽን ኮምኒዩኬሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋትና የሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጥገኛ እየሆነ መምጣቱ ለአዳዲስ ወንጀሎች መፈጠር ብቻ ሳይሆን መደበኛ ወይም ነባር ወንጀሎችም ውስብስብና ሊገመቱ በማይችሉ መንገዶች እንዲፈፀሙ መንስኤ ሆኗል። እነዚህ ወንጀሎች የቴክኖሎጂው ተደራሽነት ተከትሎ በሀገራችንም ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ግለሰባዊ ስጋት እየሆኑ መጥተዋል። ለዚህም በርካታ መንስኤዎች ያሉት ቢሆንም፤ ጠንካራና ከቴክኖሎጂው ውስብስብነት ጋር አብሮ መጓዝ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር አንዱ በመሆኑ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ ማዘጋጀት አስፈልጓል።

የአዋጁ ዝግጅት እሳቤዎች

የረቂቅ ሕጉ ዝግጅት በዋናነት በሚከተሉት መሰረታዊ እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ ነው፤

  •   የኮምፒውተር ወንጀል ዓለም አቀፍ ባህሪ ያለው መሆኑና ወንጀሉን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መሰረት ያደረገ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ማስፈለጉ፤
  •      በሳይበር ምህዳር መስፋፋት ምክንያት አዳዲስ ወንጀሎችና አዳዲስ የወንጀል አፈፃፀም ስልቶች መፈጠራቸው፤
  •      በሃገሪቱ የኮምፒውተር ወንጀልን የሚገዙ መሰረታዊም ሆነ የሥነ-ሥርዓት ሕጎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፤
  •     በሃገሪቱ የኢንፎርሜሽን መሰረተ ልማቶች መስፋፋትና ከዲጂታላይዜሽን ሥራዎች ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ሰፊ የደህንነት ተጋላጭነት፤
  •     የኮምፒውተር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተወሰዱ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ የጋራ ግንዛቤዎችና ስምምነቶች መፈጠራቸው ይጠቀሳሉ።

የረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ይዘት

–    የቋንቋ አጠቃቀም፡- የኮምፒውተር ወንጀል ከኢንፎርሜሽን ኮምኒዩኬሽን ቴክኖሎጂ ፈጣን እድገትና ውስብስብነት ጋር አብሮ የሚለዋወጥና እየተወሳሰበ የሚሄድ እንዲሁም የሳይበር ምህዳር በየቀኑ አዳዲስ የወንጀል አይነቶች የሚፈጠሩበት በመሆኑ እያንዳንዱን ወንጀል መዘርዘርና የሕግ ሽፋን እንዲኖረው ማድረግ አዳጋች ብቻ ሳይሆን ወንጀሎቹ በተለዋወጡ ቁጥር የሕግ ስርዓቱም በዚያው ፍጥነት መለወጥ አለበት ማለት ነው። ይህም ፈፅሞ የማይቻልና የፍትህ ስርዓቱንም የሚያመሰቃቅል በመሆኑ የሚቀረፀው የሐግ ማዕቀፍ በተቻለ መጠን በሳይበር ምህዳሩ በሚከሰቱ ሁሉም የወንጀል ድርጊቶች ተፈፃሚ እንዲሆንና አሁን የተፈጠሩትን የወንጀል አይነቶች ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊፈጠሩ በሚችሉት ላይም ተፈፃሚ እንዲሆን ተደርጎ ሊቀረፅ ይገባል። ይህንንም ለማሳካት በበርካታ መስፈርቶች የሚመሳሰሉ የኮምፒውተር ወንጀል አይነቶችን በአንድ ምድብ ማስቀመጥና የሕጉ ተፈፃሚነት ቀጣይነት ይኖረው ዘንድ ቴክኖሎጂያዊ ያልሆነ (technology neutral) ቋንቋ ወይም አገላለፅ መጠቀም ያስፈልጋል። ይህም ማለት የወንጀሉ የአፈፃፀም ስልት ወይም ጥቅም ላይ የሚውሉ የቴክኖሎጂ አይነቶች ግምት ውስጥ አይገቡም ማለት ነው። ይህ አካሄድ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሞዴል ሕጎችና ስምምነቶች የሚመከር ሲሆን፤ የአፍሪካ ኅብረት የሳይበር ሕግ ረቂቅ ስምምነትም እንደ ግዴታ አስቀምጦታል። በዚህ መሰረትም ረቂቅ አዋጁ በዋናነት ቴክኖሎጂያዊ ባልሆነ (technology neutral) ቋንቋ ወይም አገላለፅ ተዘጋጅቷል።

–    የወንጀል ፈፃሚዎች የሃሳብ ክፍል፡- በዚህ ረቂቅ አዋጅ የተካተቱት አብዛኞቹ ድርጊቶች በወንጀል ሊያስቀጡ የሚችሉት “ሆን ተብለው” የተፈፀሙ እንደሆነ ብቻ ሲሆን፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በሃገራችን ያለው የኮምፒዩተር አጠቃቀምና ደህንነት ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ በቸልተኝነት የሚፈፀሙ ጥፋቶችን ወንጀል ማድረግ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል በሚል እሳቤ ነው። ይህ ማለት ግን ቸልተኝነት በኮምፒውተር ወንጀል ፈፅሞ አያስቀጣም ማለት አይደለም። (ለምሳሌ አንቀፅ 7(5) ይመልከቱ)

–    የወንጀል ሕግ አጠቃላይ መርሆዎች ተፈፃኒት፡- ይህ ረቂቅ አዋጅ ምንም እንኳን አዲስ የወንጀል ሕግ ቢሆንም፤ በ1997 ተሻሽሎ በመጣው የወንጀል ሕግ አንቀፅ 3 ላይ እንደተመለከተው አጠቃላይ የወንጀል ሕጉ መርሆናዋችን በዚህ አዋጅ ላይም ተፈፃሚ እንደሚሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል።

የኮምፒውተር ወንጀሎች የትኞቹ ናቸው?

በኮምፒውተርና ሥርዓትና በኮምፒውተር ዳታ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በተለያዩ ጥናቶችና ዓለም አቀፍ መድረኮች እንደተመለከተው የዲጂታል ዘመን የወለዳቸው ቀዳሚ ሥጋቶች ወይም ወንጀሎች በኢንፎርሜሽንና በኢንፎርሜሽን መሠረተ ልማት ሚስጢራዊነት ፣ተአማኒነትና ተደራሽነት ላይ የሚፈጸሙ ናቸው። እነዚህ ሕገወጥ ድርጊቶች በዋናነት የኮምፒውተር ሥርዓትን ወይም የኮምፒውተር ዳታን ኢላማ የሚያደርጉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የቴክኖሎጂው ዕድገት የወለዳቸው አዳዲስ ወንጀሎች በመሆናቸው በሥራ ላይ ባሉት ሕጎች ሽፋን ያላገኙ ናቸው። በዚህ አዋጅ መሠረት ሊያስቀጡ የሚችሉት ድርጊቶች ያለፈቃድ ወይንም ፈቃድን ያለአግባብ በመጠቀም ወንጀል ሲፈጸም ብቻ እንደሆነ ደንግጓል።

ወንጀሎቹ የግለሰቦችን የኮምፒውተር ሥርዓትና ዳታ ከማጥቃት ጀምሮ ከፍተኛ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት (የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ) የኮምፒውተር ሥርዓቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ናቸው። በተጨማሪም በዚህ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት የኮምፒውትር ሥርዓት ስርሰራ (Hacking)፣ ሰርጎገብነት (Intrusion)፣ ሚስጢራዊ ይለፍ ቃልን ሰብሮ መግባት (Cracking)፣ ኢስፖኔጅ፣ ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ጼፍ ወይንም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ደርጊቶች፣ በሰዎች ክብር ነጻነት ላይ የሚፈጸሙ ድርጊቶች፣ በኮምፒውትር አማካይነት የሚፈጸሙ የማታለል ድርጊቶችና የመሳሰሉት የሚያስቀጡ የወንጀል ድርጊቶች ሆነዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply