Saturday, 11 June 2016 12:06
Written by አለማየሁ አንበሴ
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ተከስቶ በነበረው ተቃውሞና ግጭት 173 ሰዎች መሞታቸውንna 14 የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ገልፆ የመንግስት ፀጥታ አካላት የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝ ነበር ብሏል፡፡
ሪፖርቱን ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሔር፤ በተለይ ግጭቱ ጠንካራ በነበረባቸው ምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያና ምዕራብ አርሲ ዞኖች ሠፊ ምርመራ መካሄዱን ጠቅሰዋል፡፡ ተቃውሞና ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ከህዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የደረሱ ጉዳቶችን መመርመሩን የገለፀው ኮሚሽኑ፤ ወደ ክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች 23 ባለሙያዎችን የያዘ 9 የምርመራ ቡድን ተንቀሳቅሶ በአካል ምልከታ፣ በቃለ መጠይቅ፣ በቡድን ውይይት፣ የተለያዩ ሰነዶችን በመፈተሽ ማስረጃ ተሰባስቧል ተብሏል፡፡
የግጭቱና ተቃውሞው መነሻም የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ስራ አጥነት፣ የፍትህ እጦት መሆናቸው የተጠቀሱ ሲሆን የመንግስት ፖሊሲዎችና አፈፃፀሞች ላይ ክፍተት መኖሩም ለተቃውሞው ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ፖሊሶችና የህግ አካላት አላግባብ ድብደባን የሚፈፅሙ ሲሆን ፍትህን በሙስናና በጥቅማጥቅም እንደሚለውጡም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
በደጀንነት የተፈረጀው ኦነግና ህጋዊ እውቅና ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግጭቱን በማባባስ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው ያለው ሪፖርቱ፤ በተለይ በኦነግ የተሠራው “ማስተር ፕላን” የተሰኘ የኦሮሚኛ ሙዚቃ ግጭቱን በማባባስ ከፍተኛ ሚና ነበረው ብሏል፡፡ የኦነግ ባንዲራንም ለማውለብለብ ጥረት ሲደረግ እንደነበር በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
አንዳንድ የመንግስት የወረዳ ሹማምንትም የግኝቱ አንቀሳቃሾች እንደነበሩ የጠቀሰው ሪፖርቱ በአንዳንድ ወረዳዎችም ሹማምንቱና የፀጥታ አካላት ግጭቱ ሲባባስ መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በመተው ከወረዳዎቹ መሸሻቸው ተጠቁሟል፡፡
ከሟቾቹ መካከል 14 የፀጥታ አካላት እንደሚገኙበት የጠቀሱት ዶ/ር አዲሱ፤ አብሃኞቹ የፀጥታ አካላት ሰውነታቸው በገጀራ ተቆራርጦ በእሳት በመቃጠል በዘግናኝ ሁኔታ የተገደሉ ናቸው ብለዋል፡፡ከ173ቱ ሟቾች 14 ያህሉ የመንግስት አመራር አካላት መሆናቸው የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ 261 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቁሞ ከነዚህም ውስጥ 110 ያህሉ የፀጥታ አካላት ሲሆኑ፣ 13ቱ የመንግስት አመራሮች ናቸው ተብሉል፡፡
በግጭቱ ከሰው ህይወት መጥፋት ባሻገር በህዝብና በመንግስት ንብረት ላይ ውድመት ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፤ የፖሊስ ጣቢያዎች፣ ፍ/ቤቶችን፣ የወረዳ ጽ/ቤቶች፣ የሹማምንት መኖሪያ ቤቶችና ንብረትን ጨምሮ በርካታ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በእሣት ተቃጥለው እንዲወድሙ ከመድረጋቸውም በላይ ዘረፋ ተካሂዶባቸዋል ብለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትና የኢንቨስተሮች ንብረት የጥቃቱ ሰለባ እንደነበር የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህም ውስጥ 120 የዳንጐቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ተሽከርካሪዎች ከጥቅም ውጪ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡ በአመፁ ተሣታፊ የነበሩ አካላት የእጅ ቦንብን ጨምሮ ገጀራ፣ መጥረቢያ፣ ማቀጣጠያ ነዳጅ በመያዝና የጦር መሣሪያ ከሚሊሻዎች በመንጠቅ፣ ህዝብን ለአመጽና ለብጥብጥ አነሳስተዋል፣ በያዙት መሣሪያም በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
ቀደም ሲል ሂውማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፤ ባወጡት ሪፖርት በግጭቱ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሞ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰው የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ በ33 ወረዳዎች ላይ ባደረገው የምርመራ 103 ሰዎች በፀጥታ ሃይሎች በቀጥታ መገደላቸውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
አዲስ አድማስ