11 Jun, 2016
በኦሮሚያ ክልል ብጥብጥ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ኃይል ተጠቅመዋል ተባለ
ከፍተኛ ኃይል የተጠቀሙ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላት በሕግ እንዲጠየቁ ተወሰነ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ በርካታ ቦታዎች ተፈጥሮ የነበረውን ግጭትና ሁከት በራሱ አነሳሽነት እንዲሁም በአማራ ክልል በሰሜን ጐንደር ከቅማንት የምንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የቀረበለትን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ያካሄደው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ባለፈው ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡
የሪፖርቱ ጭብጥ የተመሠረተበትን ይዘትና የተደረገውን ውይይት በተመለከተ ዮሐንስ አንበርብር ያጠናከረው ዘገባ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ቅማንት
የቅማንት ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን የማንነት ጥያቄ ማስተናገድ ሕገ መንግሥቱ ችግር ኖሮበት ሳይሆን ጥያቄውን በሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሠረት ባለመፈታቱ ነው፡፡ በመሆኑም ገና ከጅምሩ በዚሁ መሠረት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ሊፈታ ይገባ ነበር፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የመጀመሪያ ውሳኔ በአንድ በኩል ጥቂት ቢሆኑም ቋንቋውን የሚናገሩ መኖራቸውን ተቀብሎ ነገር ግን ለብዙ ዘመናት ቋንቋው እንዳይበለጽግ ተደርጐ መቆየቱ ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ በሌላ በኩል የቋንቋ መሥፈርት አልተሟላም ከሚል መነሻ የቅማንት የማንነት ጥያቄን ውድቅ ማድረጉ ተገቢ አልነበረም፡፡
የክልሉ ምክር ቤት በሁለተኛው ስብሰባ ይህንን ጉዳይ አስተካክሎ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ይዋል ይደር ሳይባል ምላሽ ማግኘት ነበረበት፡፡ ከ2001 እስከ 2007 ዓ.ም. ማለትም ለስድስት ዓመታት መዘግየት ያልነበረበት መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡ የቅማንት የማንነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ሕገ መንግሥታዊውን ድንጋጌ ተከትሎ ምላሽ ሊሰጥ ይገባ ነበር፡፡ በኋላም የቅማንት ማኅበረሰብ ተወካዮች የክልሉን ምክር ቤት ውሳኔ በመቃወም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ ሒደቱ በዚያው ቀጥሎ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ማግኘት ነበረበት፡፡ የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን በአጭር እንፈታዋለን በማለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሒደት እንዲቋረጥ ከተደረገ በኋላ የቅማንት ብሔረሰብ ተወካዮችን ባሳተፈ መልኩ መፍታት ነበረበት፡፡
እስከ 42 ቀበሌዎች በሚደርሱ ቦታዎች የሚለው የክልሉ ምክር ቤት የሰኔ 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ውሳኔም ከጥብቅ የሕግ አተረጓጐምና አንፃር ሌሎች ቀበሌዎችን በሕዝቦች ፈቃድና አንፃር ለማካተት ክፍተት እንደነበረበት ያመለክታል፡፡
በተለያዩ ወቅቶች በተካሄዱ የሕዝብ ቆጠራዎች ለምሳሌ በ1987 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ የቅማንት ብሔረሰብ የራሱ መለያ ኮድ ተሰጥቶት ይቆጠር የነበረ ሲሆን፣ በ1999 ዓ.ም. በተካሄደው ቆጠራ ግን ቅማንት የሚለው መለያ ተሰርዞ ሌሎች በሚል መተካቱን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የሰብዓዊና የማንነት መብቶች የመከበር ሁኔታን በተመለከተም የቅማንት ብሔረሰብ የማንነትና ራስን ማስተዳደር ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌውን መሠረት በማድረግ አፋጣኝና ሁሉን አሳታፊ የሆነ መፍትሔ ባለማግኘቱ ወደ ግጭት ማምራቱ፣ ግጭቱም ወደ ሕይወት ማጥፋት፣ አካል ማጉደልና ንብረት ማውደም ተሸጋግሯል፡፡
ግጭቱን አስታከው በብጥብጥና ደም መፍሰስ የሚጠቀሙ ፀረ ሰላምና የውጭ ኃይሎች አፍራሽ ሚና እንደነበራቸው ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ ሁኔታ በመነሳት የሰሜን ጐንደር ሕዝብ በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ በዞኑ የሚኖሩ ውህዳን (የሌሎች ብሔረሰብ አባላት በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች) ተገቢው የመንግሥት ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚገባ ቢሆንም ይህ ባለመደረጉ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት በተፈጸመው ሕገወጥ ግድያና አካል ማጉደል በማውራና በአይከል ወረዳዎች የተሰማራው የክልሉ ልዩ ፖሊስ ኃይል አዛዦችና አባላት እጅ እንዳለበት አረጋግጧል፡፡
በዚህ የግድያ፣ የአካል ማጉደልና የንብረት ማውደም በግጭቱ ተሳትፎ በነበራቸው ሌሎች ግለሰቦች የተፈጸመ መሆኑን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
በማውራ ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩባቸው የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች መካከል ውጊያ በመክፈት ግድያ እንዲፈጸም ያዘዙትም ሆነ ትዕዛዙን የፈጸሙ በስፍራው የተሰማራው ልዩ የፖሊስ ኃይል አዛዦችና አባላት በሕግ ያልተጠየቁ መሆናቸው በምርመራ ታውቋል፡፡
በሽንፋ የተካሄደው ሠልፍ የቅማንት የማንነት ጥያቄን ለመድፈቅ አልሞ የተካሄደና ግጭትን ለማቀጣጠል የተደረገ ስለመሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡
ሕገወጥ ሠልፍ እንደሚካሄድ መረጃ ደርሷቸው ዕርምጃ ያልወሰዱ የተባበሩ በየደረጃው ያሉ አመራሮች መኖራቸው ግንዛቤ ተይዟል፡፡
በድርጅት ብአዴንና በክልል መንግሥቱ የተለያዩ መዋቅሮች በቁጥር የበዙ የሁለቱም ማኅበረሰብ አባላት ለየብሔረሰባቸው የመሠለፍ ተገቢ ያልሆነ አዝማሚያ ግጭቱን በማባበስና ደም በማፋሰስ ረገድ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
የቅማንት ሕዝብ ሰላማዊ ሠልፉ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ሆኖ ሳለ ከክልሉ መንግሥት አመራሮች ሰላማዊ ሠልፍ እንዳይካሄድ ዘግይተው የላኩት ደብዳቤና መከልከሉ ለሁሉም ግልጽ ሳይደረግ ለሰኔ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሚካሄድ ሠልፍ ሰኔ 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በአይከል ከተማ ሕዝቡን ለሰላማዊ ሠልፍ እንዲወጣ በማድረግ የቅስቀሳ ሒደት ላይ በተሳተፉ ያልተጠበቁ ዜጐች ላይ የተፈጸመው ግድያና እስራት ሕገወጥ ነው፡፡
ሰላማዊ ሠልፍ ያለ ጦር መሣሪያ መካሄድ ሲኖርበትና ይህም ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ሆኖ ሳለ ህዳር 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በጭልጋ ወረዳ በአይካል ከተማ ከ500 በላይ ታጣቂዎች የተሳተፉበት ሠልፍ እንዲሁም ህዳር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የጦር መሣሪያ ይዘው በመተማ ወረዳ በሽንፋ ወረዳ ሠልፍ ሲያካሂዱ ቁጥጥር አለመደረጉና የእርምት ዕርምጃ አስቀድሞ አለመወሰዱ፣ ከሰላማዊ ሠልፍ መርህ ጋር የተቃረነና ውጤቱም የዜጐችን ሞትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት ውድመት ያስከተለ መሆኑ ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
ይህ በመሆኑም የቅማንት ተወላጆች ግልጽ የሆነ መድሎ እንደሚደረግባቸው እንዲረዱ አድርጓል፡፡
በላይ አርማጮ በሮቢት ንዑስ ወረዳ ያለውን ያልተረጋጋ ሁኔታ ከመጀመሪያውኑ ሕዝብን የማሳመንና የማስረዳት ሥራ በማካሄድ መፍታት ሲቻል፣ በልዩ ፖሊስ ኃይል ለመፍታት ስምሪት መካሄዱ አግባብ አልነበረም፡፡
በማውራ ግጭት የሰው ሞትና የአካል ጉዳት እንዳይፈጠር በቦታው ደርሶ የነበረ የክልሉ የፖሊስ ኃይል አስቀድሞ ከአካባቢው ሽማግሌዎች በደረሰው ምክርና ሽምግልና መሠረት ከሰፈረበት ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ልቀቅ ሲባል ለቆ የመውጣት አማራጭ አለመውሰዱ፣ ጉዳዩም በሽምግልና እንዲያዝ በጥቅምት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዞ እያለ ጥቅምት 27 የአንድ አርሶ አደር ሕይወት መጥፋቱና አንድ ሌላ አርሶ አደር መቁሰሉ፣ በመቀጠልም ውጊያ ተቀስቅሶ የልዩ ኃይሉ መሪና ምክትል በቅማንት ታጣቂዎች ተመተው ሲሞቱ አካባቢው የሰዎች መኖሪያ አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ንፁኃን ዜጐችን ለመጠበቅና ለማደን የሚወስዱት ዕርምጃ ጥንቃቄና ብልኃት የተሞላው ባለመሆኑም ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ምንም የሚያውቁ ንፁኃን ዜጐች ለሞትና ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በውጤቱም ከሁለቱ የሞቱት የልዩ ፖሊስ አዛዦችና ሁለት የቆሰሉ የልዩ ፖሊስ አባላት ውጪ የ22 ሰዎች ሕይወት የጠፋው በልዩ ኃይሉ የአፀፋ ምላሽ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በመሆኑም ንፁኃን ዜጐችን ያልለየ ዕርምጃ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሰሜን ጐንደር አካባቢዎች በተነሳው ግጭት 97 ሰዎች ሞተዋል፣ 86 ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
ይህ መረጃ እንደሚያሳየው በቦታው ተሰማርቶ የነበረው ልዩ የፖሊስ ኃይል በዚህ ቦታ ላይ ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ መጠቀሙን የሚያመላክት ነው፡፡
የአማራ ኮሚቴ በሚል ስም በተደራጁት ውስጥ ያሉት ፅንፈኞች ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ሕገወጥ ሠልፎች እንዲካሄዱ፣ ግድያና ዝርፊያ እንዲስፋፋ፣ ጥላቻን በመስበክ የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት እንዲፈጠር እንደሚያደርጉና ይህም ለሁኔታዎች አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በቅማንት አስተባባሪ ኮሚቴ ራሱ ያሉት ፅንፈኞችም የቅማንት ጥያቄ በሕግ የበላይነት እንዲፈጸም ሳይሆን በአመፅና በሁከት እንዲፈፀም አድርገዋል፡፡
ከላይ የተገለጸው ቢኖርም በተፈፀመው የሕግ ጥሰት የክልሉ መንግሥት ትዕዛዝ አላስተላለፈም ወይም ተሳትፎ እንዳልነበረው ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡
ኮሚሽኑ ካቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል
በ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወቅት የቅማንት ብሔረሰብ መለያ ኮድ ተሰርዞ ሌሎች በሚል ለምን እንደተተካ ተጣርቶ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ኮሚሽኑ ባደረጋቸው ምርመራዎች ወንጀሎች መፈፀማቸውን አረጋግጧል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ማዕቀፍ ለመብት ጥሰት እጃቸው አለበት የተባሉ ግለሰቦች ተጠያቂ ማድረግን የግድ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ኮሚሽኑ አጥፊዎች ለፍትሕ የሚቀርቡበት ዕርምጃ እንዲወሰድ ምክረ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት በማውራና በአይከል የተሰማሩት የልዩ ፖሊስ አባላትና አንዳንድ የፖሊስ አዛዦች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ሌሎች ግለሰቦች በተፈጸመው ወንጀል እጃቸው እንዳለበት ማስረጃ አግኝቷል በመሆኑም፣ ጉዳዩ ተጣርቶ ለፍትሕ አካላት እንዲቀርብ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡
ወላጅ የሞተባቸው ሕፃናት በቋሚነት የሚደገፉበት ንብረት የወደመባቸው የሚካሱበት አስተዳደራዊ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡
በደረሰው ግጭት የደረሰውን ጉዳት የሚያመላክት አኃዝ እንዲሰጡ ተጠይቀው ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ የክልሉ አንዳንድ አመራሮችና የመተማና የጭልጋና የወረዳ አመራሮች በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 41 መሠረት ሊጠየቁ ይገባል፡፡
የክልሉ መንግሥት በሸንፉ፣ በአይከል፣ በማውራና በሌሎች ቦታዎች ለተፈጸሙት ነውጦችና ላስከተሉት ጉዳቶች እጃቸው ያለበት አስፈጻሚ ወይም ፈጻሚ ላይ ተገቢው የማጣራት ሥራ በማካሄድ ለሕግ የሚቀርቡትንም ለሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለበት፡፡
የቅማንት ጥያቄ በወቅቱና ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መልኩ የአሳታፊነት መርህን ተከትሎ ተግባራዊ ባለመደረጉ ለተፈጠረው ግጭትና ላስከተለው ጉዳት የክልሉ መንግሥት ሕዝቡን በይፋ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
ኦሮሚያ
በኦሮሚያ የተነሳው አመፅና ሁከት መነሻው የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ሕዝቡ በአንድ ድምፅ ገልጿል፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎችን ኃላፊዎች በአግባቡና በሚፈለገው ፍጥነት እንደማይፈጽሙ ኮሚሽኑ በምርመራው ለይቷል፡፡
ከሙስና፣ ከመሬት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ፣ በመንግሥት አሠራር ተሳትፎ የማድረግ ጉድለት፣ በክልሉ በየደረጃው ባሉ የፍትሕ ተቋማት የሚሠሩ ዳኞች፣ ፖሊሶችና ዓቃቤ ሕጐች የሚፈጽሙት መድሎ የመሳሰሉት ጥያቄ መንስዔ መሆኑን ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡
በገጠር የሚገኙ የጋራ መሬቶች በቀበሌ አመራሮች እየታረሱ ለግል ጥቅማቸው እንደሚያውሉ፣ በከተማ ያሉም እንዲሁ ለግል ጥቅማቸው እንደሚያጋብሱ፣ አመራሩ ገቢው እየታወቀ በሚሰበሰበው ሕገወጥ ገንዘብ በአጭር ጊዜ የሕዝብን ሀብት መክበሪያ እንደሚያደርገው ኮሚሽኑ ለመገንዘብ ችሏል፡፡
ፍትሕን በጉቦ የሚያዛቡ ዳኞችና ዓቃቤ ሕጐች መኖራቸው፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያለው ቅጥር በትውውቅ የሚፈጸምና አድሎ ያለበት መሆኑን ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
እነዚህ ቅሬታ በተስተዋለባቸው አካባቢ ያለው ሕዝብ ወደ አደባባይ መውጣቱን ይህም የሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ኮሚሽኑ ያምናል፡፡ ይህ የአርሶ አደሩና የከተማው ሕዝብ የተቃውሞ ሠልፍ በሰላማዊ መልክ ቢካሄድ ሕዝቡ ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንጂ ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው ኦነግና በሕጋዊ መልክ እንንቀሳቀሳለን የሚሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን የሕዝብን ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በመንጠቅ ወደ ሕዝብ እልቂትና ንብረት ውድመት ለማድረስ አቅደውና ከወዲሁ ወዳቀዱት የሚያደርሳቸው ስልት ነድፈው ሰላማዊ ሠልፉ በተካሄደበት ቦታ ሁሉ ተቀላቅለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ጥረት ማድረጋቸውን ለመርዳት ተችሏል፡፡
በዚህም መሠረት ሰላማዊ ሠልፍ የወጣውንም ሆነ ያልወጣውን በማስገደድ ወደ ብጥብጡ እንዲቀላቀል አድርገዋል፡፡
ሁከትና ብጥብጡ በተከሰተባቸው ቦታዎች ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ብጥብጡ እንደሚጀመር አስቀድሞ መረጃ ያላቸውና ዕርምጃ ያልወሰዱ ተሳታፊ የነበሩ ለሁከትና ብጥብጡ የአባባሽነት ሚና የተጫወቱ አንዳንድ በየደረጃው የነበሩ የአመራር አባላት እንደነበሩ ከምርመራው መረዳት ተችሏል፡፡
ሁከትና ብጥብጡ ከመጀመሩ በፊትም ሕዝቡን ለፀረ ሰላም ኃይሎች አጋፍጠው ከየነበሩበት ወረዳ የሸሹ አመራሮች መኖራቸውም ከተሰበሰበው መረጃ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ይህ የዜጐች ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ መብት እየተነጠቀ ሁከትና ብጥብጡ በግልጽ የተጀመረው ህዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን ዳንዲ ወረዳ ጊንጪ ከተማ የሚገኝ የጊንጪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ቤታችን መሬት ተቆርሶ ለግለሰቦች ተሰጥቷል በሚል አጀንዳ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን፣ የኦሮሚያ የከተሞች አዋጅ የኦሮሚያን መሬት ለመውሰድ ታልሞ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ የጭልሞ ደን ተሸጧል፣ ተጨፍጭፏል የሚሉ አጀንዳዎችን ምክንያት በማድረግ ሁከትና ብጥብጡን ወደ ሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ለማዳረስና በዜጐች ሕይወትና ንብረት ላይ ውድመት ለማድረስ የታቀደ መሆኑንም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ብጥብጡን የሚመሩት እነዚህ አካላት ያልተጠቀሙት ስልት የለም፡፡ ማንኛውም ለመብቱ የተሰለፈ ሰው ብጥብጡን እንዲያቀጣጥል፣ ወደ ሠልፉ ያልወጣ እንዲወጣ ትዕዛዝ በመስጠት አልወጣም ብሎ የሚያንገራግር ቤቱና ንብረቱ እንዲቃጠል ዛቻና ማስፈራሪያ መፈጸም፤ ገጀራ፣ እሳት፣ መጥረቢያ፣ ነዳጅ እንዲሁም ነዳጅ ሲያልቅባቸው ካገኙት ተሽከርካሪ ሁሉ አስገድደው የሚቀዱበት የነፍስ ወከፍና የቡድን መሣሪያ፣ የእጅ ቦንብና የመሳሰሉትን ይዘው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ እስረኞችን የማስለቀቅ፣ ፓሊስ ጣቢያዎችን በመክበብ የጦር መሣሪያዎችን በመዝረፍ ግድያ በመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡
ሕፃናትና ሴቶችን ከፊት ለፊት በመቀጠል አረጋውያንን በማሳለፍ የታጠቁ አባሎቻቸውን ደግሞ ከኋላ በማሳለፍ ዜጐችን እንደ ጋሻ አድርገው የፀጥታ ኃይሉ አፀፋ እንዳይሰጥና እንዳይከለከል በማድረግ ለሞትና አካል ጉዳት አድርገዋል፡፡
እነዚህ ብጥብጡን የመሩ አካላት ሌላው የተጠቀሙበት ስልት ገና ሁከትና ብጥብጡን እንዲጀመሩ በምዕራብ ሸዋ ዞን በአጉና ግንደበርት ወረዳ ፖሊሶችን በገጀራ ገድለው በመጥረቢያ ቆራርጠውና በእሳት አቃጥለው ጭካኔ በማሳየትና ሕዝቡን ፍርኃት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ነበር፡፡
የፀጥታ ኃይል እንዳይገባ መንገዶችን በመዝጋት፣ ድልድዮችን በመቁረጥና ለተሽከርካሪ ምቹ እንዳይሆን በማድረግ እንዲሁም በደፈጣ ውጊያ ከፍተኛ እልቂትና ውድመት ለመፈፀም አቅደው እየፈጸሙት እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡
ኦነግ ያወጣው ማስተር ፕላን የተባለ ዘፈን ለቅስቀሳ ጥቅም ላይ ሲውል ነበር፡፡ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾችንና ሞባይሎችን በመጠቀም ከአንድ ማዕከል በሚመራ በሚመስል ሁኔታ በየደረሰበት የሰው ሕይወት ከማጥፋት አካል ከማጉደል ባሻገር፣ የዜጐችን ቤት የማሳ ላይ ሰብል፣ የመንግሥት ተቋማት የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን አውድመዋል፡፡
በፓርላማው በአሸባሪነት የተፈረጀው ኦነግ በመንግሥት መዋቅር ጭምር በመግባት የመንግሥት አሠራሮችንና ፖሊሲዎችን ጭምር እየሸረሸሩ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡
መታሰርና በሕግ መጠየቅ ያለባቸው እንዲያመልጡ መደረጉን የክልሉ መንግሥት አሁንም መዋቅሩን ማጥራት እንደሚጠበቅበት ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሕገ መንግሥቱን የሚሸረሽሩ እያንዳንዱ የመንግሥት መስተዳደር አካላት የማደናቀፉ ሥራ እየቀጠለ ነው፡፡
ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል ሕገ መንግሥታዊ መብት ያለው የሃይማኖት ተቋማት ከነሙሉ ንብረታቸው ወድመዋል ተቃጥለዋል፡፡
ከላይ የተገለጹትና ሌሎች ምርመራዎች በሙሉ በፎቶ፣ በቪዲዮ በስፍራው ተገኝቶ በመመልከት በቃል ምስክርነት ማስረጃዎች ጭምር የተደገፈ ነው፡፡ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ በጥምረት በመንቀሳቀስ በመንገድ ላይ ተጥለው የነበሩትን እንቅፋቶች በፍጥነት በማስወገድ ችግሩን ባያስወግዱ ኖሮ ታቅዶ የነበረውን ሕዝብን ለዕልቂት፣ የአገርና የውጭ ለማስወገድም ፈንጂ እስከ መጠቀም ተገደው ኢንቨስትመንቶችን፣ የሕዝብና የአገር ሀብትን ወዘተ. ለጠቅላላ ውድመት የመዳረግ ዓላማቸውን ለማስቆም አስቸጋሪ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በጥቂት ወረዳዎች ሁከትና ብጥብጡን በማርገብና በመከላከል ፀንተው ከሕዝብ ጋር በመሆን ሕይወት እንዳይጠፋ አካል እንዳይጐድል ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ አመራሮች እንዳሉ ከምርመራው ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ አንዳንድ የመንግሥት አመራሮች በሁከት ማነሳሳት ተሳትፎ ማድረግና ኅብረተሰቡ አስቀድሞ የሁከትና ብጥብጥ ጥቆማ ለሚመለከታቸው ቢያሳውቅም፣ ትኩረት አለማግኘታቸውን የተሰበሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡
በኦሮሚያ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በድምሩ 173 ዜጐች ሕይወት ቀጥፏል፡፡ ከሞቱት ውስጥ 14 የፀጥታ ኃይል አባላት ሲሆኑ፣ 14 ደግሞ የመንግሥት አመራር አካላት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 261 ከባድ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 110 የሚሆኑት የፀጥታ አስከባሪ ኃይል አባላት ሲሆኑ፣ 13 ደግሞ የመስተዳደር አመራር አካላት ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 695 ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 416 የፀጥታ አባላት ሲሆኑ፣ 105 ደግሞ የመስተዳደር አመራር አባላት ናቸው፡፡
ዜጐች እርስ በእርሳቸው እንዲገዳደሉ በማድረግ እስከ 42 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸው ጠፍቷል፡፡ የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ ለማስቆም የፀጥታ አስከባሪው የወሰደው ዕርምጃ የዜጐች ሕይወት የአካል ደኅንነት በአጠቃላይ ሰላምም ደኅንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅና ተከስቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ በክልሉና ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በመዳረስ እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ የተወሰደ አስፈላጊና ተመጣጣኝ ዕርምጃ መሆኑን ከተካሄደው ምርመራ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በኦሮሚያ ላይ ኮሚሽኑ ያቀረበው ምክረ ሐሳብ መካከል
የመልካም አስተዳደር ችግር ካልተፈታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያስከትላል በመሆኑም መታረም አለበት፡፡ በሰው ሕይወት፣ ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ በሕግ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ቃል የተገቡ ፕሮጀክቶች መቼ እንደሚጀመሩና እንደሚጠናቀቁ በግልጽ ተወያይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡
ምርመራ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉ የመንግሥት አመራሮችና ፈጻሚዎች ከሁሉም በላይ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆናቸው በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው ሥራቸውን ማከናወን ካልቻሉ ለሰላም መደፍረስና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያስከትል አውቀው እንዲንቀሳቀሱ የአቅም ግንባታ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የሕዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በመንጠቅ ሁከትና ብጥብጡን ያባባሱና የመሩ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላት በቂ ማጣራት እየተደረገ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል፡፡ የኮሚሽኑን ሥራ ለማደናቀፍ የሞከሩ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ የመስተዳደር አባላት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
ፓርላማው
ሪፖርቱን ያዳመጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች የተዘጋጁ ጥያቄዎችን ለኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር አቅርበዋል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ኮሚሽኑ ምርመራውን ያከናወነው በገለልተኝነት ነው ወይ እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚና ስለተባለው ዝርዝር ማብራሪያ ቢሰጥ የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡
ለዚህ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነሩ ዶ/ር አዲሱ የምርመራ ሪፖርቱ በገለልተኝነትና ሁሉንም ወገኖች በእኩል አሳትፎ የተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ሚና በተመለከተ በሪፖርቱ በስፋት መብራራቱን የሕዝቡን ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በመንጠቅ ወደ ራሳቸው ፍላጐት እንደመሩት ገልጸዋል፡፡
ከስፋት አንፃርም በተለይ በኦሮሚያ ክልል በስፋት ሲንቀሳቀሱ የነበረ ቢሆንም፣ በአማራ ክልልም በሰሜን ጐንደር ዞን የተቃዋሚ ኃይሎች ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ በመቀጠልም የምክር ቤቱ የብአዴን አባላት የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ የተጠቀመው ኃይል የተጣጣመ አልነበረም በሚል የቀረበው ሌሎች አማራጮችን መወሰድ ነበረበት በሚል ቢስተካከል፣ ከፍተኛ ኃይል ተጠቅሟል ለማለት መለኪያው ምንድነው፣ የክልሉ መንግሥት ይቅርታ እንዲጠይቅ በምክረ ሐሳብ መቅረቡ ለምን አስፈለገ የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ የኦሮሚያ ብጥብጥን አስመልክቶ የቀረበ ጥያቄ ግን አልነበረም፡፡
ኮሚሽነሩ ዶ/ር አዲሱ በሰጡት ምላሽ ሕዝብን በዋናነት ማክበር ያስፈልጋል ከሚል እምነት የክልሉ መንግሥት ይቅርታ እንዲጠይቅ በምክር ሐሳብነት ኮሚሽኑ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ልዩ ፖሊስ ያልተመጣጠነ ኃይል ተጠቅሟል መባሉን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ‹‹በኦሮሚያ 14 የፖሊስ አባላት ስለሞቱ አይደለም የተመጣጠነ ዕርምጃ ነው የተባለው፡፡ ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት የሚገባቸውን አማራጮች በመጠቀማቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት የሕግ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ‹‹ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ ያቀረበው በመሆኑ ተቀብለነዋል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱ ምክረ ሐሳቦችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ›› በማለት ያቀረበውን ሐሳብ ምክር ቤቱ በ10 ድምፅ ተአቅቦ (አብዛኞቹ ብአዴኖች ናቸው) በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል፡፡
- ዮሐንስ አንበርብር’s blog
- 4382 reads