11 Jun, 2016
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በአሜሪካ ያልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ በማካሄዱ 6.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጣ ተወሰነበት፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥፋቱን በማመን የቅጣት ክፍያውን ለመፈጸም ተስማምቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህን ቅጣት እንዲከፍል የተጣለበት ሴኪዩሪቲና ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የተባለው ተቋምን የሰነድ ሽያጭ ሕጎች በመተላለፍ፣ በአሜሪካ ከሚኖሩ 3,100 ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 5.8 ሚሊዮን ዶላር በመሰብሰቡ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እነዚህን ሰነዶች ለሽያጭ ማቅረብ የነበረበት፣ ለአሜሪካ ሴኪዩሪቲና ኤክስቼንጅ ኮሚሽን አስመዝግቦ መሆን ሲገባው፣ ይህን ባለማድረጉ ቅጣቱ እንደተጣለበት ተዘግቧል፡፡ ከአሜሪካ የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ መንግሥት የቦንድ ሽያጭ ሕጐችን በመጣሱ ያሰባሰበውን ገንዘብ ከነወለዱ ቦንድ ለገዙ ወገኖች እንዲከፍል ይደረጋል፡፡
መንግሥት የተጣለውን ቅጣት በፀጋ ቢቀበልም ችግሩን እስከወዲያኛው ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው ሰኔ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተሰብስቦ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ችግሩን ለመፍታት መመርያ መስጠቱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
በዚህ ኮሚቴ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተካተዋል፡፡
ኮሚቴውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ የሚመሩት ሲሆን፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አቶ ግርማ ብሩና የኤምባሲው የውጭ ጉዳይ ሕግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ረታ ዓለሙ ይህን ጉዳይ እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ኮሚቴው ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ባላት የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አማካይነት ችግሩ እንዲፈታ መመርያ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ላለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ የቦንድ ሽያጭ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህንኑ ቦንድ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን (ዳያስፖራ ቦንድ) በማቅረብ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2014 ድረስ 5.8 ሚሊዮን ዶላር ሰብስቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህንን ገንዘብ ያሰባሰበው የተለያዩ ብዙኃን መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም፣ የጎዳና ላይ ትሩፋቶችን በማዘጋጀትና በሌሎች መንገዶች ባካሄዳቸው ቅስቀሳዎች አማካይነት ቢሆንም፣ የሕግ ሒደቶችን ባለማሟላቱ ችግር መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ይህን ችግር ዘግይቶ የተረዳው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማኔጅመንት ችግሩን ለመፍታት በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ ቢያቀናም ጉዳዩን በብቃት መወጣት አልቻለም፡፡
በዚህ ምክንያት መንግሥትም ሆነ መንግሥት ያቋቋመው ኮሚቴ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማኔጅመንት ላይ ከፍተኛ ወቀሳ መሰንዘሩ ተገልጿል፡፡
- ውድነህ ዘነበ’s blog
- 1593 reads