June 13, 2016
(ኢ.ኤም.ኤፍ) ቀደም ሲል ባቀረብነው ዜና ላይ በሰሜን ግንባር ስለተቀሰቀሰው አዲስ የጾረና ግንባር ጦርነትን በተመለከተ አጭር ሪፖርታዥ ማቅረባችን ይታወሳል። ዜናውን የሚያጠናክር መግለጫ በኤርትራ በኩል ሲሰጥ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምንም ምላሽ አልሰጠም። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር እንዳለው ከሆነ፤ “ጦርነቱን በጾረና ግንባር የጀመረው ህወሃት ነው” ብሏል።
የ’ኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስቴር መግለጫ በጥንቃቄ የወጣ ይመስላል። በመሆኑም “ጦርነቱን የኢትዮጵያ መንግስት ወይም ሰራዊት ከፈተብኝ” ሳይሆን፤ “ህወሃት” ጦርነቱን እንደተነኮሰው በግልጽ አስቀምጦታል። በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ምላሽ አልሰጠም። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሆንም አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ግን በዚህ ጉዳይ ምንም የሰጡት መግለጫ የለም።
በ’ርግጥም የኢትዮጵያን መንግስት ከላይ ሆኖ የሚያንቀሳቅሱት የህወሃት ሰዎች ለመሆናቸው አሁን የተፈጠረው ሁኔታ በቂ ምስክር ነው። የጠቅላይ ሚንስትሩም ዝምታም የመነጨውም በህወሃት በኩል ምንም እንዳይነገሩ መመሪያ ስለተሰጣቸው ወይም ምንም መረጃ ስላላቀበሏቸው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በህወሃት (በወያኔ ትግራይ) የበላይነት የተገነባው የጦር ሰራዊት በከፍተኛ ሙስና ውስጥ መዘፈቁ በምክር ቤቱ ጭምር ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል። ዋናው የጦሩ መሪ ተብለው የተሾሙት ጄነራል ሳሞራ የኑስ በቅርቡ ወደ ትግራይ ሄደው ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር፤ “የላይኛው አመራር ስራ ፕሮጀክት መምራት እና በቴሌቪዥን መታየት ነው” ሲሉ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በካቢኔያቸው ላይ መሳለቃቸው የሚታወስ ነው። ጄነራሉ በዚህ አላበቁም የሲቪል አስተዳደሩ ደካማ መሆኑን እና በአንጻራዊነት ወታደራዊ አስተዳደሩ የተጠናከረ መሆኑን በግልጽ ተናግረዋል።
ሌላ ዝርዝር ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ፤ ይህንኑ የጄነራል ሳሞራን ንግግር በጥሬው ስንመረምረው በሲቪል እና በወታደራዊው አስተዳደር መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ይጠቁማል። የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አስተዳደር መግለጫ ያልሰጠበት፤ ቢሰጥም ከወታደራዊው ክንፍ የተነገረውን ብቻ የሚደግም ሊሆን እንደሚችል የጄነራል ሳሞራ የኑስ ንግግር አመላካች ሆኗል።
በጾረና የተጀመረው ጦርንነት ወደ ዛላ’ምበሳም እየተሸጋገረ መሆኑ በሚነገርበት በአሁኑ ወቅት በኤርትራ በኩል ከተሰጠው አጭር መግለጫ በቀር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትርም ሆኑ ቃል አቀባይ ምንም ከማለት ተቆጥበዋል።