Wednesday, 15 June 2016 12:31

በድንበሩ ስዩም

በዘመነ ደርግ በዋናነት ሊገደሉ ከሚፈለጉ ወጣቶች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው ክፍሉ ታደሰ አዲስ መጽሐፍ አሳተመ። ክፍሉ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ተነባቢነት የነበራቸውን ሶስት ተከታታይ መጻህፍትን “ያ ትውልድ” በሚል ርዕስ አሳትሟል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ ደግሞ “The Generation” በሚል ርዕስም አሳትሟል። የተለያዩ ዶክመንተሪ ፊልሞችንም ሰርቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲን /ኢሕአፓ/ን ከመሰረቱትና ፓርቲውን ከመሩት ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው። የኢሕአፓ መስራቾች ሁሉም ማለት በሚቻልበት ሁኔታ ዛሬ በሕይወት የሉም። ክፍሉ ግን አለ። ጉዳዩ ተአምራዊ ነው።

ክፍሉ ታደሰ ያንን እልቂት እንዴት ተረፈ ብለን ልናስብ እንችላለን። ምናልባት ክፍሉ ማን ነው የሚለውን ነገር በፎቶ ግራፍ ማንም ሰው አይቶት አያውቅም። በፎቶው አስከ ዛሬ ድረስ ክፍሉ ይህ ነው ተብሎ ወጥቶ አያውቅም። ክፍሉ ሆን ብሎ ፎቶው እንዳይታይ ስላደረገ ከብዙ ግድያዎች አምልጧል። አርባ አመታት ሙሉ ፎቶውን ይፋ ያላደረገው ክፍሉ ታደሰ ከአርባ አመታት በሁዋላ ክፍሉ ምን እንደሚመስል በአዲሱ መጽሀፉ አውጥቶታል። ክፍሉን በየትኛውም መጽሄትና ጋዜጣ ፎቶው የለም። በዚህ በአዲሱ መጽሀፉ ክፍሉ ታደሰ ይፋ ሆነ። ብዙ የኢሕአፓ አባላት መሪያቸው ማን እንደነበር አሁን ሊያዩት ነው። ይህ አዲሱ የክፍሉ መጽሀፍ “ኢትዮጵያ ሆይ…” ይሰኛል። 418 ገጾች አሉት። በአዳዲስ መረጃዎች የታጨቀ ነው። ክፍሉንና መጽሐፉን ሪቪው ለማድረግ ፈለኩኝ።

የዚህ “ኢትዮጵያ ሆይ…”  መጽሐፍ ደራሲ ክፍሉ ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲን/ኢሕአፓ/ን በዋናነት ከመሠረቱት የ1960ዎቹ ወጣቶች መካከል ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ነው። ክፍሉ እና ጓደኞቹ ኢሕአፓን መስርተው ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለማስፈን ብዙ ጣሩ። ብዙ መንገድ ተጓዙ። ሚሊዮኖችን ከጐናቸው አሰለፉ። ግን ያ ሁሉ ህልም ዕውን ሣይሆን ቀረ። ሺዎች በየጐዳናው ደማቸው ፈሠሠ። እናቶች አነቡ። አስክሬኖች የትም ተጣሉ። አንድ የተማረ ትውልድ እምሽክ ብሎ አለቀ። የቀረውም ተሠደደ። ግማሹ ቅስሙ ተሠበረ። አንዳዱ ደግሞ ከዚያ ውብ ሕልሙ ጋር ዛሬም በትዝታ ይኖራል።

ክፍሉ ታደሰ፣ በዚያ ሁሉ እልቂት ውስጥ በደርግ ደሕንነቶች በዋናነት የሚፈለግ የኢሕአፓ ቀንደኛ አመራር ነበር። በተገኘበት እንዲገደል ተፈርዶበት የሚታደን የዘመኑ አብዮተኛ ነበር። ክፍሉ፣ ተአምር ሊባል በሚቻል ሁኔታ ከዚያ ሁሉ ግድያ ተርፎ ዛሬም በሕይወት ያለ ምናልባትም ብቸኛው የኢሕአፓ መስራች ነው። ፈረንጆቹ A Living Legend  የሚሉት አይነት ሠው ነው። በሕይወት ያለ ሕያው ምስክር። በሕይወት በመኖሩ የያን ትውልድ ታሪክ ከመጀመሪያው እስከ ፍፃሜው ፅፎታል። ዛሬም የወደቁትንም ያሉትንም የትግል ጓደኞቹን እያነሣሣ “ኢትዮጵያ ሆይ—” ይላል። የዚህ ሁሉ የትውልድ አልቂት ምክንያቱ ምንድን ነው? የኢትዮጵያ መከራ ለምን አላባራ አለ?  የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን ትሆናለች? እነዚህንና ሌሎችንም ርዕሠ ጉዳዮች ክፍሉ ታደሰ “ኢትዮጵያ ሆይ–” እያለ ያወጋናል።

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኢሕአፓ ወጣቶች ውድ ሕይወታቸውን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ሠጥተዋል። ዛሬ የቆምንበት መሬት የነርሡ ደም የፈሰሰበት፣ አጽማቸው ስቃይ ያየበት ነው። ክፍሉ ታደሰ የነዚያን ጓደኞቹን ታሪክ አፈሩን እያራገፈላቸው በትውልድ ዘንድ ሕያው ናቸው ብሎ ሀውልታቸውን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አቁሞላቸዋል።

ክፍሉ ታደሰ ቀደም ሲል ባሳተማቸው ሶስት ተከታታይ መጻህፍት /trilogy/ ዋና ትኩረት ያደረገው የ1960ዎቹ ውስጥ ብቅ ብለው እንደ ብርሀን ነበልባል አብርተው ስለጠፉት የያ ትውልድ አባላት  ነው። ክፍሉ የራሱን ትውልድ ያ ትውልድ እያለው ይጠራዋል። የያ ትውልድ አባላት ታሪካቸውን በልዩ ልዩ ዘርፎች አቆይተው አልፈዋል። የአያሌዎች ታሪክና ገድል የሚያሳየው ሕይወታቸውን ሳይሳሱላት ለአሰቡትና ላለሙት ግብ ሰውተዋል። እጅና እግራቸው አንድ ላይ ተጠፍሮ፣ በሚዋጉ ብረቶች በተሰራ መግረፊያ እጅ፣ እግራቸው፣ ጀርባቸው፣ መላው ገላቸውን እየተገረፉ የነበሩ ወጣቶች በዐይነ-ሕሊናችን ይመጣሉ። ከዚያ የስቃይ ሲኦል ውስጥ ሆነው ከአፋቸው የሚወጣው ኢሕአፓ ያሸንፋል የሚል ቃል ነው። ከደማቸውና ካጥንታቸው የተዋሀደ አላማ ያነገቡ ወጣቶች እንደነበሩ ሌሎችንም ማመሳከሪያ ምሳሌዎችን መጠቃቀስ ይቻላል። ለአመኑበት ጉዳይ እንዲህ መስዋእትነት እየከፈሉ የኖሩ ወጣቶች በዚህች ሀገር ውስጥ ነበሩ።

ፈተናው ከብዶት ወዲያው አላማውን ቀይሮ መሐል ሰፋሪም የነበረ ወጣት በዚህች ሀገር ላይ ነበር። አንዱ ሌላኛውን በጭካኔ የሚገድል፣ የሚያስገድል ወጣትም ነበር፡ መሳሪያ ይዘው የጅምላ ፍጅትም ያካሄዱ አሉ። መሳሪያ ከአፍ እስከ አፍንጫው የታጠቀውም ወታደራዊ ክፍል መሳሪያውን እንደወደረ በመተኮስ መነጋገር ጀመረ። ያ ሁሉ የሀሳብ ፍጭት ቀርቶ መተላለቅ ሆነ። ኢትዮጵያ  ውድ ልጆችዋን አጣች። የወላድ መሀን ሆነች። ሀገሪቱ የተማሩ ልጆችዋን ክፉኛ ተነጠቀች።

ራውል ቫልዲስ የተባሉ ጸሀፊ “Ethiopia the Unknown Revolution” የተሰኘ መጽሀፍ አሳትመዋል። እኚህ ደራሲ ይህን መጽሀፋቸውን በሚያዘጋጁበት ወቅት የገጠማቸውን አስደናቂ ነገር በማስታወሻ ደብተራቸው ላይ አስፍረዋል። ጉዳዩ እንዲህ ነው።

ታሪኩ የተፈጸመው ኢትዮጵያ ውስጥ ዋነኛዋ የኢሕአፓ መናኸሪያ በነበረችው ጎንደር ክፍለ ሐገር በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው። አንድ ገበሬ ሰርግ ይኖርበትና ቀልቦ ያሳደጋቸውን ሁለት በሬዎች ያሳርዳል። እነዚህ በሬዎች የእርሱ ናቸው። ከጥጃነት እስከ ወይፈንነት፣ ከዚያም እስከ ደለበ በሬነት ያሳድጋቸዋል።

እንዲህ ተንከባክቦ ያሳደጋቸውን በሬዎቹን አርዶ ለሰርጉ እድምተኞች አበላ። ጣፋጭ ጥብስ ለመጥበስ እሳቱ በኩበት መቀጣጠል አለበት ተባለ። ኩበቱ የነዚህ የታረዱት በሬዎች ነው። ስጋቸው የሚጠበሰውም በራሳቸው በበሬዎቹ ኩበት ነው።  የመጽሀፉ ደራሲ ራውል የ1960ዎቹን የኢትዮጵያ ወጣቶች እልቂት በነዚህ በሬዎች ጥብስና በኩበቱ ያመሳስሉታል። ከበሬዎቹ ውስጥ የወጣው ኩበት የበሬዎቹን ስጋ መጥበሻ ሲሆን፣ በሬዎቹን ተንከባክቦ ያሳደጋቸው ገበሬም ሲያርዳቸው ደራሲው አይተዋል። እናም የኢትዮጵያን አብዮት ሲጽፉ ተምሳሌት ሆኖ አገልግሏቸዋል። ገበሬ፣ በሬ፣ እና ኩበት። ኢትዮጵያም የተላለቀችው እርስ በርስዋ ነው።

በርግጥ ደራሲ ራውል ቫልዲስ እልቂቱ ከውስጥ ነው ብለው ግምታቸውን ቢያስቀምጡም የመጨረሻ ድምዳሜያችን ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ አብዮት ከውስጥ መንጭቶ ከውስጥ የፈነዳ ብቻም አይደለም። ሌሎች ዙሪያ ከበብ ታሪኮችም አሉት። የሶሻሊስቱ እና የካፒታሊስቱ ጽንፎች ተፅዕኖም ቀላል አይደለም። በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ ያሉ የአረብ ሃገራት ሴራም የተጐነጐነበት ነው።

የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ እና ከሩሲያ የተጐነጐነ ነው። ክፍሉ ታደሰ ይህን ሁሉ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሂደታችንን ያ ትውልድ በተሠኙት ሦስቱ ተከታታይ መፃሕፍቱ አማካይነት በሰፊው ተንትኖ አሣይቷል። ይህ አራተኛው መጽሐፉ የነዚያ ሦስቱ መፃሕፍት ውስጥ ያልተብራሩትን ድፍን ሃሣቦች እየዘረዘረ የልቡን ፅሁፍ ያስነብበናል። ደራሲት ስንዱ ገብሩ የልቤ መጽሐፍ ብለው እንደፃፉት ሁሉ፣ ክፍሉ ታደሰም ኢትዮጵያ ሆይ…  የልቡ መጽሐፍ ነው።

በዚህ ኢትዮጵያ ሆይ በተሠኘው መጽሐፍ ውስጥ የበርካታ ወጣቶችን ለሀገራቸው የነበራቸውን ርዕይ (Vision) እናገኛለን። ወጣትነት ከሀገርና ከሕዝብ ፍቅር ጋር እንዴት እንደተቆራኘ በዚያ ትውልድ ውስጥ በሠፊው እናገኛለን። ሕልምና ውጥን አልሠምር ብሎ፣ የነበረው እንዳልነበረ፣ የታሠበው እንዳልታሠበ ሆኖ ያልተጠበቀው ክስተት ሲመጣም በመፅሃፉ ውስጥ እናገኛለን። ክፍሉ ታደሰ አብዛኛዎቹ የትግል አጋሮቹ በሕይወት የሉም። እርሱ ውስጥ ያለው ትዝታቸው፣ ርዕያቸው፣ መስዋዕትነታቸው ነው። ክፍሉ የታሪክ አደራ አለበት። የነዚህን ውድ ጓደኞቹን የሕይወት ውጣ ውረድ የመዘከር ሐላፊነትና አደራ አለበት። ሌት ተቀን ስለ እነሱ ያስባል፤ ያነባል፣ ይፅፏል። አሁን ደግሞ ለአመታት ሲሠበስበው የቆየውን ታሪካቸውን አደራጅቶ በውብ የትረካ ክሂሉ ኢትዮጵያ ሆይ… እያለ  ያወጋናል።

ክፍሉ ታደሰ በጓደኞቹ ደም ምድሯ ስለረሠረሠው ኢትዮጵያ ወደ ኃላም፣ ወደ ፊትም እየሔደ ታሪኳን ያወሣናል። ብዙ የኢሕአፓ አባላት ከነ ንፁሕ አእምሮአቸው፣ ከነ ቅን ልቦናቸው፣ በእናት አገራቸው ፍቅር ወድቀው ሕይወታቸውን ሰውተዋል። ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ ነውና የአበው ብሒል፣ ጓደኛቸው ክፍሉ ታደሰ በመኖሩ ምክንያት እነሡም ሕያውያን ሆነዋል።

አሁን ያለችው የዛሬዋስ ኢትዮጵያ? የዚያ ሁሉ መስዋዕትነት ውጤት ናት? ለሐገር ለወገን ሲባል በቁርጠኘነት መቆም፣ አገርን ለዲሞክራሲና ለነፃ አስተሣሠብ ማብቃት ላይ የወጣቱ፣ የምሁሩ አስተዋፅኦ ምንድን ነው? የወጣቱና የምሁሩ ቦታ የቱጋ ነው? ምን እየሠራ፤ ምን እያከናወነ ነው?ታሪክ ድሮ አብቅቷል ወይስ ገና ይሠራል? የክፍሉ መፅሀፍ ብዙ ቁም ነገሮችን ያነሣሣል።

የመጪዋ ኢትዮጵያም ተስፋ ምንድን ነው? እንደ ጨው ዘር በአለም ላይ የተበተነው ኢትዮጵያዊ እና ገና የሚሰደደው ሕዝብ መጨረሻው ምንድን ነው? የኢትዮጵያ አብዮት ከተቀጣጠለ 40 አመታት አለፉ። እሣቱ አልበረደም። መጨረሻው ምንድን ነው? “ኢትዮጵያ ሆይ…” በተሠኘው የክፍሉ መፅሃፍ ውስጥ ብዙ ነገር እናገኛለን። ሐገራችንንም እናውቃለን። ያን ትውልድንም እንዘክረዋለን።

የክፍሉ ታደሰ ያ ትውልድ፣ ዛሬ እድሜው ከስልሳ በላይ ነው። ያለፈውን ዘመን ቁጭ ብሎ የሚያይበት የሚገመግምበት ወቅት ነው። የወጣትነት ተፍለቅላቂ ስሜት ሀገሩ ኢትዮጵያ ላይ በፍቅር እንዴት እንደጣለው የሚያስብበት ወቅት ነው። ከፍቅሩ ብዛት ያለመውንና ያጎደለውን በሰከነ መንፈስ የሚዳኝበት ዘመን ነው። ለምድራዊ ሩጫና ግር ግር ችላ ብሎ ኢትዮጵያ ስለምትባለው ግዙፍ ሕሊናዊ ምስል የሚያስብበት ወቅት ነው። ክፍሉ ታደሰም “ኢትዮጵያ ሆይ…” በሚለው በዚህ መጽሀፉ እውነተኛና ሕሊናዊ ፍርድ ለመስጠት ያዘጋጀው ጽሁፉ ነው። ሰው አለምን ሁሉ ትቶ ለሀቅ እና ለሕሊናው መኖር ሲጀምር የሥነ-ልቦና ምሁራን Self-actualization ይሉታል። ስለዚህ “ኢትዮጵያ ሆይ…” የተሰኘው ይህ መጽሀፍ በውስጡ ሚዛናዊ ዳኝነትን የያዙ ሀሳቦችን እንዳካተተ አምናለሁ።

አያሌ የኢሕአፓ አባላት ዛሬም አሉ። ነገር ግን ታሪካቸውን ሲጽፉና ለትውልድ ሲያስተላልፉ አይስተዋልም። ያ ደግሞ የራሱን የታሪክ ክፍተት እያመጣ ነው። በተቃራኒው ወገን የነበሩት የደርግ አባላትና ሌሎች የታሪኩ ተካፋይ ያልነበሩ ሰዎች እንደልባቸው ካለ ሚዛናዊ ብእር የሚያሳትሟቸው ጽሁፎች ትልቁን ታሪክ እያደበዘዘው እየመጣ ነው። የክፍሉ ታደሰ “ኢትዮጵያ ሆይ…” መጽሀፍ እነዚህን እየተምታቱ የመጡ የታሪክ አጻጻፎችን ሁሉ የሚያጠራ ነው። ከዚያ ንጹህ ምንጭ ነው የሚያጠጣን።

የኢሕአፓ ትውልድ በታሪክ ውስጥ ክፉኛ የተጎዳ ነው። ሕልሙ እውን ባለመሆኑ የተነሳ የትም ተበታትኖ፣ ተሰዶ የሚኖር ነበልባል ትውልድ ነው። ከ40 አመታት በላይ ከሐገር ወጥተው የሚማስኑ። እንደወጡ በስደት በሞት የተለዩ አያሌ ናቸው። ወጥተው የቀሩ ውድ ትውልዶች። ባተሌ ትውልዶች። ክፍሉ በዚህ መጽሀፉ እነርሱንም ያስታውሰናል። እንደው ለመነሻ ይሆነን ዘንድ የያ ትውልዱ ባለ ግርማ ሞገስ፣ ባለቅኔውን ኃይሉ ገ/ዮሀንስን/ ገሞራውን/ እናንሳ። ኃይሉ 40 አመታት ሙሉ በስደት የኖረ። በስደት የሞተ። ግን እንዲህ ገጠመ፡-

ባያውቁት ነው እንጂ – የእኔን ቋሚ ንግርት፣

በተወለድኩበት ነው – የምቀበርበት፣

ሌላ ቦታ ሳይሆን – በትውልዴ መሬት።

አስቀድሞም ቢሆን – እትብቴ ተቀብሯል፣

ቀሪውም አካሌ – በርግጥ በክብር ያርፋል።

ሲንከራተት ኖሮ – አካሌ የትም ምድር፣

በስተመጨረሻ – የሚያርፍበት አፈር፣

ከተወለድኩበት ነው – በክብር የሚቀበር።

በመቃብሬም ላይ – በስተ ግርጌ በኩል፣

“እኔም እንደርስዎ – ሕያው ነበርኩ!” የሚል፣

በትልቅ ቋጥኝ ላይ ተቀርፆ ይፃፋል።

ይሔ ሁሉ ንግርት – ከወዲሁ ታውቋል፣

ከዚያ ርስት ለመንቀስ – ታዲያ እንዴት ይቻላል?!

(ኃይሉ ገ/ዮሐንስ – በግጥም ልተንፍስ ጥር 20/2006 ዓ.ም)

ይሄው ታላቅ ባለቅኔ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ የኢትዮጵያ አለመረጋጋትና ለዜጎችዋ አልመች ማለትዋ ምክንያት አጣለት። የችግር አዙሪት ከኢትዮጵያ አልወጣ አለ። ምናልበት እርግማኑ ይሆን ብሎ አሰበ። ኢትዮጵያ ተረግማለች። ማን ረገማት? ገሞራው ስለዚሁ እርግማን በጥር ወር 1993 ዓ.ም ለታተመው ኢትዮጵ መጽሄት እንዲህ አለ፡-

“….አበው እንደሰጡኝ ምላሽ ከሆነ “የማይፋቅ መርገምት አለብን!” የሚል ነው። የወረደብንን መርገምትም ምንነት ሲያብራሩ ከትላንትናው ምእተ አመት መገባደጃ ምዕራፍ ዘመን ላይ ይጀምራሉ። ከነገስታቱ የነ አፄ ቴዎድሮስ እርግማን፣ የነ አፄ ዮሐንስ፣ የነ አፄ ምኒልክ፣ የነ አፄ ኃይለ ስላሴ፣ ከሕዝባውያኑ ደግሞ የነ አቡነ ጴጥሮስ፣ የነ በላይ ዘለቀ፣ የነ መንግስቱ ነዋይ፣ እርግማን ይጠቅሳሉ።

“ቴዎድሮስ ሐገር አንድ ላድርግ ብለው ቢነሱ ክህናት  ሳይቀሩ በመስዋዕት ውስጥ የእባብ ጭንቅላት አድርገው ሊገድሏቸው እንደሞከሩና በተለይም ለመንገስ ሲሉ የራሳቸው ሀገር ሰው የሆኑት አፄ ዮሐንስ የጠላት ጦር /እንግሊዞችን/ መቅደላ ድረስ እየመሩ አምጥተው ሊያስገድሏቸው ሲዘጋጁ በማወቃቸው “ይችን የኢትዮጵያ ኩሩ ነፍስ የውጭ ጠላት አይገድላትም!” ብለው፣ ራሳቸው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሊገድሉ ሲሉ፣ “ኢትዮጵያ ወንድ አይብቀልብሽ!!!”  ብለው ረግመዋታል።

“ቀጥሎም ኢትዮጵያን ከመጣባት ወረራ ለማዳን ከደርቡሽ ጋር አፄ ዮሐንስ በተፋጠጡ ጊዜ የሸዋው አፄ ምኒልክና የጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖት ለእርዳታ እንዲደርሱላቸው ጠይቀው ባለመምጣታቸው የጦርነቱ አውድ ገብተው አንገታቸው ተቆርጦ ከመሞታቸው በፊት” ኢትዮጵያ ዘር አይብቅልበሽ” ብለው ረግመዋል።

“ከዚያም አፄ ምኒልክ እንደ ልጃቸው ያዩት የነበረውን የልጅ ልጃቸውን አቤቶ ኢያሱን ለማንገስ ፈልገው “ልጄን ተቃውሞ ለዙፋኔ የማያበቃ ቢኖር ጥቁር ውሻ ይውለድ!” ብለው በመርገማቸው ያው እንዳየነው ንጉስ ተፈሪ ኢያሱን ገድለው ዙፋኑን ቢወርሱ ያን ፋደት የደርግ ጥቁር ውሻ ወልደው አንድ ንፁህ ትውልድ አስበሉ። ራሳቸው ንጉስ ኃይለስላሴም በተራቸው ከሞቀ ዙፋናቸው ወርደው 4ኛ ክፍለ ጦር ታስረው ሳሉ ምግብ ተመግበው ከጨረሱ በኋላ ታጥበው ፎጣ ለማድረቂያ ሲሰጣቸው እምቢ ብለው ጣቶቻቸውን ወደ ታች አድርገው የታጠቡበትን ውሃ እያንጠባጠቡ “ይህን አስተምሬው የከዳኝን ትውልድ ደሙን እንዲህ አንጠብጥብልኝ..!” እያሉ መርገማቸውን ያየ የሰፈሬ ሰው በደብዳቤ ገልፆልኛል።

“እንዲሁም አባት ጴጥሮስ ለጠላት ጣልያን የሚገዛ ውጉዝ ይሁን! መሬቷም ሾክ አሜከላ ታብቅል! ብለው ሊረሸኑ አቅራቢ ረግመዋል። በላይ ዘለቀም መስቀያው አጠገብ እንዳለ “አንቺ ሀገር! ወንድ አይውጣብሽ!” ብሎ ተራግሟል። ጀኔራል መንግስቱም ከተሰቀለበት የተክለሃይማኖት አደባባይ ላይ ሕዝብ እየሰማው “አንቺ አገር..” ብሎ በማማረር ተራግሞ አልፏል። ወዘተ

“እንግዲህ እኛ የዛሬዎቹ ይህ ሁሉ የግፍና የደይን የፍዳና የመከራ የመቅሰፍትና የመአት ማዕበልና ናዳ የሚወርድብን ያን ሁሉ ርግማን ቆጥሮብን ይሆን?” / ኃይሉ ገ/ዮሐንስ ጥር 1993፣ ኢትዮጵ መጽሄት/

የኢትዮጵያ ነገር ግራ ያጋባል። ኃይሉ ገ/ዮሐንስ እርግማን አለብን ሲል፣ ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሾተላይ አለባት ይላል። ጸጋዬ ገ/መድህን በ1984 ዓ.ም ጽፎ ባዘጋጀው ሀሁ ወይም ፐፑ በተሰኘው ተውኔቱ፣ ነጋ እና አራጋው በተሰኙት ሁለት ገጸ-ባሕሪያት ስለ ኢትዮጵያ እና ዲሞክራሲዋ እንዲህ ይላል፡-

ነጋ

እናታችን ኢትዮጵያ ባሕላዊ ሾተላይ ናት መሰለኝ። ዲሞክራሲን በስድሳ ስድስት ወልዳ በላች። አስቀድሞም በሃምሳ ሶስት አስጨንግፏታል። ብትወልድም ብትገላገለውም ለዘለቄታ አያደርግላትም። የማሕፀን መርገምት አለባት። የዲሞክራሲ ሾተላይ ናት ኢትዮጵያ። በስድሳ ስድስትማ ወዲያው ማግስቱን መፈክር ተፎከረላት። ‘አብዮት ልጆቿን ትበላለች’ ተባለላት ተሸለለላት። የዲሞክራሲ ሾተላይ እናት፣ በላኤ ሰውነቷን መላው የአለም ሕዝብ አስጠንቅሮ አወቀላት።

ቢ-አራጋው፡-

ዛሬስ? ዛሬስ?

ነጋ፡

ዛሬማ አዲሱ ዲሞክራሲ ከተወለደ ገና ዘጠኝ ወሩ ነው። የሾተላይ ጥሪቷ ዳግመኛ እንዳጓጓት፣ በሕፃኑ የልደት ቀን ቤተሰቦቿ ካሉበት ተሰባስበው እንትፍትፍ አሰኝተው በመሃላ ቃል ገዝተዋታል። የሕፃኑ እርግብግቢት ገና በአራሱ፣ በሾተላይ አይኖቿ ተወግቶ እንዳይፈርስ፣ ቃለ-ምህላዋ እንዳይረክስ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዳይነግስ፣ ጨቅላ ዲሞክራሲያዊ አራስ ብሌኑ እንዳይፈስ ቤተሰቦቿ በተሰበሰቡበት እለት በምህላ ቃል ገዝተዋል። እናታችን በግዝት ተይዛለች።. . .

 /ሀሁ ወይም ፐፑ፣ ጸጋዬ ገ/መድህን/

ኢትዮጵያ የችግሮች ምስጢር ሆናለች። አልፈታ ያለ፣ የተተበተበ አንድ አዙሪት አለ። የክፍሉ ታደሰ ኢትዮጵያ ሆይ… መጽሀፍ ያንን አዙሪት ፍለጋ ይማስናል። በመጨረሻም የሚያገኘው ይመስለኛል።

Leave a Reply