Wednesday, 15 June 2016 12:16

በ 

 ዜጎች በተለያዩ አረብ አገራት ለስራ ከተጓዙ በኋላ የሚደርስባቸውን ሰብአዊ ጥሰት ተከትሎ መንግስት ለስድስት ወራት የሚቆይ የጉዞ እገዳን ያደረገ ሲሆን ይህ እገዳ ከሁለት ዓመት በላይ ቆይቷል። ከእገዳው ቀደም ብሎ ፓስፖርት አውጥተው ወደ ተለያዩ አረብ አገራት መጓዝ  የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ወደ የኢምግሬሽንና ጉዳዮች ዋና መስሪያቤት በየጊዜው በፓስፖርት ፈላጊዎች እንደተጨናነቀ ነበር። እገዳውን ተከትሎ አካባቢው ጭር ብሎ የቆየ ሲሆን ፓስፖርት ማሳደስም ሆነ አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ መስሪያቤቱ የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ብዙም የተጋነነ አልነበረም።

ከተወሰኑ ጊዚያት በኋላ ግን ፓስፖርት የሚያወጡ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ከእገዳው በፊት የነበረው ወረፋ ተመልሷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፓስፖርት ለማውጣት የሚፈልግ ሰው ከሌሊቱ አስርና አስራአንድ ሰዓት ወረፋ መያዝ ያለበት መሆኑን በአካባቢው ካደረግነው ቆይታ መረዳት ችለናል። በርካታ ፓስፖርት ለማውጣት በአካባቢው ረዥም ሰልፍ የሚይዙ ዜጎች ወጣት ሴቶች ሲሆኑ በሰጡን ማብራሪያም አረብ አገር ለመሄድ ፓስፖርት የሚያወጡ መሆናቸውን ገልፀውልናል።

እገዳው መኖሩን ቢረዱም በሌላ ሶስተኛ አገር የሚሄዱ መሆናቸውን ገልፀውልናል። በርካቶች ኬኒያና ሱዳን ከሄዱ በኋላ ከዚያ በኋላ ወደተለያዩ አረብ አገራት የሚሻገሩ መሆኑ ታውቋል። በአካባቢው ፓስፖርት ለማውጣት ሰልፍ የሚይዙ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ስርዓት የማስከበሩን ስራ እየሰራ ያለው የአዲስ አበባ ፖሊስ መሆኑን በአካባቢው በነበረን ቆይታ መረዳት ችለናል። በዚሁ ዙሪያ መረጃ ለማግኘት ወደ ኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ቢሮ ለመዝለቅ ያደረግነው ሙከራ ሊሳካ አለቻለም።

ይሁንና በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ የሚኒስቴር ደኤታው አማካሪ የሆኑትን አቶ ተክሌ ተስፉን አነጋግረናል። አቶ ተክሌ በሰጡን ማብራሪያ መንግስት ወደ አረብ አገራት የሚደረገውን የስራ ጉዞ ላይ እገዳ የጣለ መሆኑን አስታውሰው ይሁንና አንዳንድ ዜጎች እገዳውን በመጣስ በህገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጡበት ሁኔታ እንዳለ መረጃው ያለ መሆኑን አመልክተዋል።

በህገወጥ መልኩ ከአገር ውጪ መጓዝ ቀደም ብሎም የነበረና ወደፊትም ቢሆን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሊውል ይችላል ተብሎ የማይታሰብ መሆኑን ያመለከቱት ሀላፊው በሶስተኛ አገር እያቆራረጡ ወደ ተለያዩ አገራት የሚሄዱ ዜጎች እንዳሉ መረጃው ከመኖሩም በሻገር አንዳንዶቹ ድንበር አቋርጠው ከአገር ሊወጡ ሲሉ በፀጥታ ሀይሎች እየተያዙ የሚመለሱበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል። “ህገወጥ ስደትን በመከላከሉ ረገድ የበርካታ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው” ያሉት አቶ ተክሌ በዚህ ረገድ የቀድሞው ፍትህ ሚኒስቴር የአሁኑ የፌደራል አቃቤ ህግ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው መሆኑን ገልፀዋል።

በዚህ ውሰጥ በተቋቋመ አንድ አካል ውስጥም ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሚሰራ አካል መሆኑን ገልፀውልናል። በርካቶች በቅርቡ የፀደቀው የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ወደ ስራ አለመግባቱ ዜጎች ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ አደርጓቸዋል የሚል አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን እንደ አቶ ተክሌ ገለፃ ህጉ የወጣው የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም በመሆኑ ዘገየ ሊባል አይችልም ብለዋል።

ከህጉ ባለፈ በቀጣይ ከተቀባይ አገራት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች፣ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና የማፅደቅ ስራ እንደዚሁም ለተጓዦች የሚሰጥ የስራ ስልጠናና ምዘና ስራ ላይ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል። እገዳው መቼ ይነሳል የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለመስጠት የሚያስቸግር መሆኑን ያመለከቱት አቶ ተክሌ፤ ዝግጅቶቹ ሲጠናቀቁ እገዳው የሚነሳ መሆኑን አመልክተዋል። ያም ሆኖ ህገወጥ ፍልሰትን በመከላከሉ በኩል ህብረተሰቡን ጨምሮ የሁሉም ባለድርሻ አካል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply