አምዶም ገ/ ስላሴ
ከለላው ማህበረሰባዊ በመሆኑ በቀላሉ የሚወገድ ነገር አይደለም። የትግራይን መንግስት ለመንቀፍ ስትነሳ “ተው እንጂ እነሱ ምን አደረጉ ችግሩ እኮ No War No Peace ነው፣ ሻዕብያ ነው፣ መለስ ነው” ይልሃል። ወይም የትግራይ ተወላጅ የሆነ የፌዴራል መንግስት አመራር ልንካ ብትል ደግሞ < ያምሃል እንዴ፣ በብኣዴን ልታስመታን፣ ነፍጠኛው ሊበላን፣ የኛው ናቸው ሌላ ሌላዉን አትነካም እንዴ? ይልሃል።
የብኣዴን ወይም የኣማራ ክልል መንግስት ብትነካ ደግሞ “የወያኔ ሴራ ነው፣ እነሱ ምን አደረጉ የህወሓት ተላላኪ አይደሉም እንዴ፣ አማራን ከስልጣን የማስወገድ እቅድ ነው እየፈፀምክ ያለሀው” ይልህና የመንግስታቱ ብልግና አይነኬ ይደረጋል። ተላላኪ ለመሆን ፍቃደኛ ከሆነም ከተላላኪነቱ ጋር አብሮ የሚመጣ ጥቅምና ሃላፊነት እንደሚሸከም አዉቆ አደል እንዴ እሚገባው ብትለው፤ ግድ የለም “ትንኞችን ትተህ ኣሳማው ህወሓትን ታገል” ይልሃል።
ዞር ብለህ ኦሆዴድን ብትነካ ደግሞ አይጣል ነው። “ኦሆዴድ በሙስና ተጨማለቀ፣ ህዝቡ በጣም እየተማረረ ነው፣ መጠየቅ አለባቸው” ስትል፤ “እህ… አሁን ገና ኦሮም በኢትዮጵያ ጢኒጥየ ስልጣን ተጋራና ዓይንህ ቀላ፣ ሓጎስ አደል እንዴ ቶላን የሚያሽከረክረው፣ ታሾፋለህ እንዴ” ይልህና ኦሮሞ በመሆኑ ከቅጥፈት ነፃ እንደሆነ በስመ ኦሮሞ ለዘራፊ ባለስልጣን ጥብቅና ይቆማል። ህወሓት አይደለም በሌሎች ክልሎች ገብታ ልትመራ ትግራይን ራሱ በቅጡ የምትቆጣጠር አይመስለኝም። ይህንንም ህወሓትን ምሽግ ሆኖ የመከላከል ስራ አድርጋቹህ እምትመለከቱ አትጠፉም፤ ምን ታደርጊዋለሽ አለ ዘፋኙ።
ደግሞ አሉ ትችትና ገንቢ ሂስን የሚያቀርቡ ዜጎችን እንዲያሸማቅቁ ተመድበው ከሃያ አራት ሰዓት ሃያ ሰባት ሰዓት ስም ሲያጠፉ፣ ሲሳደቡ፣ ስም ሲሰጡ የሚዉሉ፤ ባጭሩ መዳቢው ኣካል መጥፎ ስራ ላይ የመደባቸው ሚስኪኖች። እነሱ በራሳቸው ማሰብ ስለማይችሉ ሁሉም እንደራሳቸው የሚመስላቸው ለጥቅም የተሸጡ (Sellouts) ናቸው እነ ‘እንትና’።ብትናገር “እሱኮ ስላኮረፈ ነው፣ ጥቅሙ ስለተነካበት ነው፣ አጎቱን defend ለማድረግ ነው፣ ጏደኛዉን ለማስደሰት ነው” ወዘት ማለትን ያዘወትራሉ። ሃሳቡን ሳይሆን ሃሳቡን ያሰራጨው ኣካል ማንነት ማጠልሸት ይቀላቸዋል።
ይህንን ስራ በራሳቸው ተነሳሽነት የሚሰሩም አሉ፤ በብር እጥረት ወይም በስልጣን ጥማት፤ ዞሮ ዞሮ ፌስቡክ ዉስጥ ሲርመጠመጡ የሚዉሉ እባቦች አሉ ተጠያቂነት እንዳይሰፍን ሌት ተቀን የሚሰሩ።እነዚህ ማወቅ እንጂ ለመለወጥ መሞከር ትርፉ ልፋት ነው፤ መተዳደርያቸው ስለሆነ ንቆ ማለፍ ነው።በመንግስት እና በፓርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነው ከልባቸው ለበጎ ነገር የሚታገሉ ሰዎች መመስገን አለባቸው፤ ቁጥራቸው ትንሽ በመሆኑ ግን ሁሌም ይጠቃሉ። ከማናችንም በላይ እዉነተኛ መስዋእትነት የከፈሉም አሉ፤ ይሄንን ሃቅ መቀበል ሌሎችን ማበረታታት ስለሆነ መለመድ አለበት። አይዙዋቹህ ከጎናቹህ ነን ልንላቸው ይገባል።
ለማነኛዉም እንዲህ አይነት ኃላ ቀር አስተሳሰብ ለሙሰኛ አመራር ምቹ ሁኔታ ፍጥሮ ሌባን መንካት አስቸጋሪ እየሆነ ነው። ወደድንም ጠላንም እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ለሌቦች አሪፍ ምሽግ እየፈጠርን መሆናችን መታወቅ አለበት። ሌብነትን በብሄር ከለላ እየሰጠን የምንገነባው የጋራ አገር አይኖርም። ሁሉም ሌቦች ምሽግ ኣላቸው፤ ይህ ደግሞ በጣም ተምችቷቸዋል።