ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በመተባበር በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለመጣል አሲረዋል የተባሉት የጦር መሪዎችና ባለስልጣናቱ፣ ባለፈው ሳምንት መታሰራቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ድርጊቱን የተቃወሙ ታጣቂዎች በመንግስት ፖሊሶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና ውጥረት መንገሱን ገልጧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስ ከመፈንቅለ መንግስት ሴራው ጋር ንክኪ አላቸው ያላቸውን በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን ማሰር መቀጠሉን የጠቀሰው ዘገባው፤ 12 ያህል የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊ ታጣቂዎች፣ ኡጋንዳ ፒዩፕልስ ኮንግረስ የተባለው ፓርቲ አባል የሆኑትንና በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉትን ዳን ኦላ ኦዲያ የተባሉ ግለሰብ ለማስለቀቅ፣ባለፈው እሁድ በፖሊስ ላይ ተኩስ በመክፈት ብጥብጥ መፍጠራቸውን ጠቁሟል፡፡
ባለፈው የካቲት ወር በተካሄደው የአገሪቱ ምርጫ የሙሴቬኒ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡትና የምርጫውን ውጤት በመቃወም ብጥብጥ አስነስተዋል በሚል ወደ ወህኒ የተወረወሩት ፎረም ፎር ቼንጅ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ዶ/ር ኪዛ ቢሲጂ፤ባለፈው ረቡዕ በአገር ክህደት ተከሰው በናካዋ ከተማ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፣ በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን የጠነሰሱት ኪዛ ቢሲጄ የተባሉ የአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እንደሆኑ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ በአገር ክህደት ከተከሰሱት ቢሲጂ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጾ፣ ቢሲጂ በመንፈንቅለ መንግስቱ ሴራ እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠሩን አስታውቋል፡፡
ቪኦኤ በበኩሉ፤ የአገሪቱ መንግስት ባለስልጣናቱን በመፈንቅለ መንግስት ሴራ ጠርጥሮ ማሰሩ በቀጣይም ከፍተኛ ብጥብጥ ሊፈጥርና አገሪቱን ወደ ከፋ ቀውስ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡
አዲስ አድማስ