Saturday, 18 June 2016 13:03

Written by  አለማየሁ አንበሴ

 • በዓለም አቀፍ ህግ የአሰብ ወደብን ማስመለስ እንችላለን…
• ኢህአዴግ ህገ መንግስቱን እየሸረሸረ ነው
• የኢሳያስ መንግስት መወገድ አለበት

መንግስት ሰሞኑን በኤርትራ ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡ አሁንም እንደ ቀድሞው ጭልጥ ወዳለ ጦርነት የምንገባ ይመስልዎታል?  ለመሆኑ የሁለቱ አገራት የድንበር ግጭት እንዴት ነው ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኘው?
ሁለት ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛ ከኤርትራ እንደ ኤርትራነቷ የሚመጣ ችግርን፣ በሁለተኛ ደረጃ ጂኦ ፖለቲክሱን መሠረት አድርጐ ማየት ይቻላል፡፡ አሁን መንግስት እየሰጠ ያለው መልስ ኤርትራን እንደ ኤርትራ በማየት ብቻ ነው። ያው እኛ እያደግን ነው፤ ኤርትራ በቀውስ ውስጥ ነው ያለችው፤ ስለዚህ ተመጣጣኝ የሆነ እርምጃ እየወሰድን እናቆመዋለን የሚል ነው፡፡ ይሄ እንደኔ መሰረታዊ ስህተት ያለበት ነው፡፡ ኤርትራ ብቻ ለኢትዮጵያ ስጋት ወይም ጠላት አይደለችም። ግን አሁን ያለው የኤርትራ መንግስት ተላላኪ ነው፤ገንዘብ ያገኘበት የሚሄድ ነው፡፡ ገንዘብ ካገኘ ወደ ሣኡዲ ይሄዳል፤ ካላገኘ ደግሞ ወደ ኢራን፣ ብቻ ገንዘብ ወዳገኘበት የሚሄድና ተልኮ ፈፃሚ የሆነ መንግስት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ ነፃ ሀገር ነች፤ በኤርትራ የውስጥ ጉዳይ መግባት የለብንም፤ ግን እሷም በኛ ጉዳይ እንድትገባ እድል መስጠት የለብንም፡፡ በተለይ በታጠቀ ሃይል ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሙከራ በሚደረግበት ጊዜ ይሄ መንግስት አቅም እንዲኖረው መፍቀድ የለብንም፡፡ ይሄ በኤርትራ ታጥሮ ሲታይ ነው። በአጠቃላይ ግን ከጂኦ ፖሊቲክስ አንፃር ሲታይ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሱዳን ላይ ሠፊ ኢንቨስትመንት አላቸው፤ ድጋፍም እያደረጉ ነው። አረቦቹ በሶማሊያ፣ በጅቡቲም የራሣቸው እቅድ አላቸው፡፡ በኤርትራም የአሰብን ወደብ ከመጠቀም አንስቶ የራሣቸው እንቅስቃሴ አላቸው፡፡ ኤርትራ መረማመጃ ልትሆን ትችላለች፡፡ የኤርትራ መንግስት ይሄ ሁሉ ተልዕኮ እያለው፣የኛ መንግስት ተመጣጣኝ እርምጃ ነው የምወስደው ማለቱ አስቂኝ ነው የሚሆነው፡፡ በአንድ በኩል ለ18 አመታት በዚያ በኩል እየደማን ነው ያለነው፡፡ ብዙ ሰው አልቋል። ጦርነት ሲከፍቱ ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን የሚሉት፣ እኔ እንደሚመስለኝ ከኛ ወገን 200 ሰው ከሞተ፣ ከነሱ 1000 ከገደልን ይበቃል እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ እያደረግን እስከ መቼ እንቀጥላለን? ሃገራችንን ለማፍረስ በይፋ የተናገረ መንግስት፣ ኤርትራ ውስጥ እንዲኖርስ ለምን እንፈቅዳለን? መፍቀድ የለብንም፡፡
ምን ማድረግ ይቻላል…?
ፖለቲካዊ ጥናቶች ተጠንተው የኢሣያስ መንግስት መውደቅ አለበት፡፡ የኤርትራ ጉዳይ የራሣቸው የኤርትራውያን ጉዳይ ነው ይሄን እናከብራለን፡፡ ነገር ግን ለኛም ለነሱም ይሄ መንግስት ስጋት ነው፡፡ በረዥም ጊዜ ታቅዶ፣ ይሄ መንግስት የሚወድቅበት ነገር መፍጠር አለብን፡፡ ሶማሊያ አልሸባብን ለማስወገድ እንደገባነው ማለት ነው፡፡ ሶማሊያ ሄደን ካጠቃን፣ አስመራ ሄዶ ማጥቃት ሃጢያት አይሆንም። ራሳችንን መከላከል ነው፡፡ በቃ የኤርትራ መንግስት እንደ አልሸባብ ለደህንነታች ስጋት ነው ካልን፣ አልሸባብ ላይ ያረፈው ጡንቻ የሻዕቢያ መንግስት ላይም ማረፍ አለበት፡፡ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ ስልት ጉዳዩን መመልከት አለብን፡፡
ይሄ ምን ያህል አዋጪ ነው? ኤርትራን የበለጠ ወደ ቀውስ አይከታትም?
መጀመሪያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ አንድ መገንዘብ ያለብን ጉዳይ፣ ኤርትራ ውስጥ ያለው መንግስት የወደቀ ነው፡፡ አሁንም በሆነ መንገድ ሊወድቅ ይችላል፡፡ የፈራነው መምጣቱ አይቀርም፡፡ እንደዚህ አይነት መንግስት ኤርትራ ውስጥ እንዲኖር መፍቀድ የለብንም፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የማትከጅል ሀገር መፍጠር አለብን፡፡ ከኤርትራ ህዝቦች ፀረ – አገዛዝ ትግል ጋር በመሆን፡፡
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች “የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ ነው” የሚል አቋም በመያዝ፣ ሥልጣን ላይ ሲወጡ ወደቡን እንደሚያስመልሱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በአሰብ ጉዳይ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
እንግዲህ የማስተርስ ትምህርቴን አጥንቼ መመረቂያ ፅሁፌን እስክሰራ ድረስ የነበረኝ አቋም አሰብ የኤርትራ ነው የሚል ነበር፡፡ እኛ የማንንም ሀገር መሬት መውረር የለብንም የሚል አቋም ነበረኝ። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም ዳግም ኢትዮጵያ እንዳትወረር ጠቅላላ መደምሰስ አለብን፤አሰብን ግን መያዝ የለብንም የሚል ነበር አቋሜ፡፡ አሰብ ከተወሰደብን በኋላ የኛ መብት ምንድን ነው? የሚል ጥናት አደረግሁኝ፡፡ በጥናቱ ሂደት ግን አለማቀፍ ህግ እኛ በወደቡ የመጠቀም መብት እንዳለን አረጋግጦልኛል፡፡ ከህግ አኳያ መብት አለን፤በኔ ጥናት ሉአላዊ የሆነ መብት አለን፡፡ አሁን በዚህ ሃሳብ ውስጥ ነኝ፡፡
አሰብን እንዴት ነው ማስመለስ የሚቻለው?
መጀመሪያ የሻዕቢያን ጉዳይ መፍታት አለብን፡፡ በሁሉም የፖለቲካ ስራዎችና ድርድሮች፣ አለማቀፍ ህጎችን በመጠቀም ማስመለስ ይቻላል፡፡ በሰላም ብቻ ነው ማስመለስ ያለብን የሚለው አይሰራም፤ የሁሉም እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ ጡንቻ የዚያ አካል ነው፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ ባድመ ተፈርዶላታል፤ ግን ጡንቻ ስለሌላት መብቷን ማረጋገጥ አልቻለችም፡፡ ግን ኪሳራውን ለመቀነስ ድርድርን ማስቀደም መልካም ነው፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራን ሰላም ለመመለስ እርቅ አማራጭ አይሆንም?
በእርግጥ ኤርትራና ኢትዮጵያ በኮንፌደሬሽንም በፌደሬሽንም አንድ የሚሆኑበት ሁኔታ ነበር። የኢሳያስ መንግስት ነው ኢትዮጵያን በመውረር ያንን እድል ያበላሸው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ የሚሆኑበት ወርቃማ እድል ይፈጠር ነበር፡፡ ይህ የሚሆነው በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ፍላጎት ነው፡፡ ኢሳያስ ግን ይሄን ወርቃማ እድል አበላሽቶታል፤ስለዚህ የኢሳያስ መንግስት እያለ እርቅና ሰላም የሚኖር አይመስለኝም፡፡ እርቅ ስንል ኢሳያስና አቶ ኃይለማርያም እርቅ እንዲያደርጉ አይደለም፤ የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው። ይሄ ደግሞ የኢሳያስ መንግስት እያለ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ኤርትራን በጦርነት ለመግጠም በቂ አቅምና ዝግጅት አላት ብለው ያስባሉ? ከወታደር ቁጥር ጀምሮ በጦር ስልጠና ኤርትራ እንደምትልቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኤርትራ መንግስት ሌላውን አገራዊ ሃላፊነቱን ወደ ጎን ትቶ፣ ወታደራዊ አቅሙን ሲገነባ ነው የኖረው ይባላል——
በመጀመሪያ ፊዚካል የወታደር ወይም የአውሮፕላን አሊያም የታንክ ቁጥር አይደለም ጦርነት የሚያሸንፈው፡፡ ጦርነቱ ፍትሃዊ ነው አይደለም የሚለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኤርትራን ያለ አግባብ ለመውረር ከሄደች ለማሸነፍ ያስቸግራታል፤ ፍትሃዊ ስላልሆነ፡፡ ከዚያ በኋላ የወታደራዊ ዶክትሪኑ ወሳኝ ነው፡፡ ማን ነው የሚያሸንፈው ለሚለው ጥያቄ፣ ፍትሃዊነት መልስ ይሰጣል፡፡ ፍትሃዊ ከሆንን፣ ኤርትራ ኢትዮጵያን መቋቋም አትችልም፡፡
ሰሞኑን መንግስት በሶማሊያ ከአልሻባብ ታጣቂዎች የተሰነዘረውን ጥቃት በአስተማማኝ ሁኔታ መክቻለሁ ብሏል … በሶማሊያ ያለው ሁኔታ መጨረሻው ምን ይመስልዎታል? የኢትዮጵያ ሰራዊት በሶማሊያ ያለውን እንቅስቃሴና ውጤቱን እንዴት ነው የሚገመግሙት?
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሶማሊያ ድረስ ዘልቆ የሀገራችንን ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚደገፍ ነው፡፡ አሁን ብቻ ሳይሆን በ1998 እና 99 ዘልቆ በገባበት ጊዜ የኢትዮጵያን ደህንነት ለማረጋገጥ መዝመት ነበረበት፡፡ ያኔ እኔ በአሜሪካ ወታደራዊ ህግና አለማቀፍ ህግ እየተማርኩ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ በገባበት ጊዜ በተማሪዎችና በአስተማሪዎች መካከል ሰፊ ክርክር ነበር፡፡ ኢትዮጵያ መግባት አለባት የለባትም የሚለው ብዙ አከራክሮናል፡፡ በወቅቱ ባቀረብኩት ጽሁፍ ኢትዮጵያ ዘልቃ መግባቷ ተገቢ ነው የሚል አቋም ነበር ያንፀባረኩት፤አሁንም ያ አቋሜ እንዳለ ነው፡፡ ዛሬ በሰላም እንድንኖር እዚያ ያለው መከላከያ ኃይላችን እያደረገ ያለውን ነገር በክብር ነው የማየው፡፡
በቅርቡ እንግዲህ የተፈፀመውንም ሰምቻለሁ፤ የመከላከያ ኃይላችን ለወሰደው የአፀፋ እርምጃ ላመሰግነው እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ መሃል ግን እዚያ የተሰዉ የኛ ወታደሮችና የጦር አመራሮች አስክሬናቸው ወደ ሀገር መጥቶ በክብር እንዲቀበሩ መደረግ አለበት፡፡ ሌላው ሰራዊቱ ከሶማሊያ  መቼ ነው የሚወጣው የሚለው ስልት ከወዲሁ መነደፍ አለበት፡፡ ይሄ ከሌለ ለረዥም ጊዜ ጦርነት ውስጥ መቆየት ሊኖር ይችላል፡፡
መንግስት በጦርነቱ የተሰዉ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ቁጥር ገልጾ አያውቅም፡፡ በኢራቅና አፍጋኒስታን ውጊያ ላይ የሞቱ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አገራቸው ተወስደው በታላቅ ወታደራዊ ክብርና ሥነሥርዓት ነው የሚቀበሩት፡፡ የእኛ ምስጢራዊ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
ከትጥቅ ጊዜ ጀምሮ ያለው ልምድ፣ በክብር የሚያርፉት እዚያው በተሰዉበት አካባቢ ነው፡፡ በየሄዱበት የመቅበር ነገር ነው የነበረው፡፡ ትክክል ይሁን አይሁን ባላውቅም የተሰዉ ወታደሮች  ቁጥር መግለፅ ከሞራል አንፃር አስቸጋሪ ነበር የሚል አመለካከት ነበር፡፡ ይሄ ልምድ እስካሁን ዝም ብሎ የቀጠለ ይመስለኛል፡፡ እኔ ግን ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ የተከፈለውን ዋጋና የተገኘውን ድል አውቆ ማመዛዘን ይኖርበታል፡፡ ይሄ መብት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ቁጥሩን መደበቅ ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡ በይፋ ቁጥሩ መታወቅ አለበት። ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ድል ብቻ ሳይሆን ኪሳራውንም መመዘን አለን፡፡ ለህዝቡ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የሰው ህይወት ትልቁ ኪሳራ ነው፡፡ እዚህ መጥተውም በክብር አስከሬናቸው ማረፍ ይገባዋል። ለቤተሰቦቻቸውም ድጋፍ መደረግ አለበት፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከታታይ በሚያቀርቧቸው ጽሁፎች፣ በመንግስትና በገዥው ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችቶች እየሰነዘሩ ነው፡፡ በመንግስት ላይ ጎልተው የሚታዩ ዋነኛ ችግሮች ምንድን ናቸው? እርስዎም የአቋም ለውጥ ላይ ያሉ ይመስለኛል—-
መቼም የአቋም ለውጥ የማያደርገው ድንጋይ ብቻ ነው፡፡ እኔ ከመጀመሪያውኑ ስታገልላቸው ለነበሩ አላማዎች፣አሁንም በፅናት ቆሜያለሁ ነው የምለው፡፡ ገዥው ፓርቲ ነው ከትግሉ አላማዎች ወደ ኋላ እየተንሸራተተ ያለው፡፡ የ25 ዓመት ጉዟችንን ስናየው፣ ይሄን ልንገመግም እንችላለን፡፡ ግን በቅርቡ እንኳ ያለውን የ10 ዓመት ጊዜ ብናይ፣ 97 ምርጫ ለኛ አንድ ወርቃማ እድል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ዲሞክራሲያዊ ጉዞ በከፍተኛ ደረጃ የገባበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በገዥው ፓርቲም በተቃዋሚውም በኩል በነበሩ ችግሮች ምክንያት ያ ተኮላሸ፡፡ በፊት ኢህአዴግ በተወሰነ ደረጃ ህዝቡን ያከብር ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ህዝብን መፍራት ጀመረና ህዝብን ማሳመን ሳይሆን መቆጣጠር የሚል አቅጣጫ ያዘ፤ ስለዚህ የተለያዩ ህጎች አወጡና ዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን ማፈን ተያያዙ። እንግዲህ የኔ አቋም መነሻው ከዚህ ነው፡፡ ከህገ-መንግስቱ በመነሳት ነው አቋሜን የማንፀባርቀው። ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ መስፋት አለበት ነው የኔ አቋም፡፡ ኢህአዴግ የሚመዘነው በህገ-መንግስቱና በራሱ ፖሊሲ ነው፡፡ በኔ አመለካከት፤ ኢህአዴግ አሁን ህገ-መንግስቱንም እየሸረሸረ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱን በተሟላ መንገድ ተግባራዊ እያደረገ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚካሄዱ ምርጫዎች ማሳያ ናቸው። በ1997 ምን አይነት ሁኔታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ህዝቡ እድል ሲያገኝ ማንን እንዴት እንደሚመርጥ ያሳየበት ምርጫ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም 96.6 በመቶ ነበር ገዥው ፓርቲ ያሸነፈው፡፡ በ2007 ደግሞ መቶ  በመቶ ሆኗል፡፡
በ1997 የምርጫ ውጤት፤ ተቃዋሚዎች አዲስ አበባን ሲያሸንፉና በክልሎችም ያልተገመተ ድርሻ ሲያገኙ፣ ኢህአዴግ እንደ ድል ከመቁጠር ይልቅ ሽንፈት አድርጐ ቆጠረው፡፡ ከሕገ – መንግሥታችን ከራሱ ፕሮግራም አንፃር ድል ነበር። ግን ተደናገጠ፡፡ (ተቃዋሚዎቹም ቢሆኑ ያገኙትን ድል ተቀብለው፣ ለዚያ ያመቻቸላቸውን ህዝብና ኢህአዴግ አመስግነው እንደመቀጠል ተንጠራሩ። የመሪዎቻቸውን የግል ፍላጐት ለማሟላት ሲሉ በአቶ ልደቱ አያሌው የሚመራውን ኢዴፓ ምክር ትተው ተወራጩ፡፡ የአገሪቱን ሰላምና እድገት ከማሰብ ይልቅ በጊዚያዊ ስሜት ተነስተው ነጐዱ፡፡
በዚህም  ከዴሞክራታይዜሽን አንፃር የተገኘውን ወርቃማ ዕድል የኢትዮጵያ ህዝቦች ተነጠቁ፡፡ ኢህአዴግ በመጀመሪያ የአዲስ አበባ ከተማን ስልጣን ወደ ፌደራል በከፊል ከመውሰድ ጀምሮ ያኛው ወርቃማ ዕድል ተመልሶ እንዳይመጣ የተለያዩ እርምጃዎች ወሰደ፡፡ የተቃዋሚ መሪዎችን ሰብስቦ ከማሰር ጀምሮ የተለያየ የህዝቦች አደረጃጀት እና አሰራር አመጣ፡፡
የፌደራል ተቋሞች የውጭ ጉዳይ፣ የመንግስት ሚዲያ፣ ወዘተ ዳኞችም ሳይቀሩ ከክልሎች አምጥቶ አስገባ፡፡ የሲቭል ሰርቫንቱን ሙያተኛነት የሚገድል ውሳኔ ነበር፡፡ ህዝብን ማሳመን ሳይሆን ህዝብን መቆጣጠር በመሆኑ የፓርቲ አባሎች ሲመለምል ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ በማተኮር በሚልዮኖች መለመለ፡፡ ሲቪል ሰርቫንቱ በብቃት ሳይሆን በአባሎቹ ተሞላ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ “A” ከማምጣት ከኢህአዴግ “C” ማግኘት ይሻላል ተባለለት፡፡
አንደምታው መሰረታዊ ነው፡፡ ምርጫ ለመቆጣጠር የአንድ ለአንድ አሰራር ዘርግቶ፣ የያንዳንዱን ዜጋ መመዝገብ በተዘዋዋሪም ኢህአዴግን የመረጠ መሆኑን ለማረጋገጥ ተንቀሳቀሰ። (አሁን አንድ ለአምስት ሆኗል፡፡)
በአጠቃላይ ሐቀኛ ተቃዋሚዎችና ተቃውሞን ለማፈንና ለማዳከም ልዩ ልዩ ስራዎች ተሰሩ፡፡ (የፓርላማ ስነ ስርዓት፣ የፓርቲዎች ሕግ) ወዘተ…
ዴሞክራሲያዊ ምሕዳሩ እየጠበበ ሄደ፡፡
እርስዎ በብዕርዎ የሚታገሉት በዋነኝነት ምን ዓይነት ለውጥ እንዲመጣ ነው?
ለሕገ መንግስቱ በተሟላ መንገድ መተግበር የአቅሜን ያህል እታገላለሁ፡፡ ምክንያቱም ሕገ – መንግስቱ የአገራችንን ችግር የሚፈታና የሁሉም ሕጐች የበላይ በመሆኑ የማክበርም ግዴታ ስላለብኝ ነው፡፡ በተጨማሪም ከወጣትነቴ ጀምሮ የታገልኩለትን ዓላማ የሚያንፀባርቅና የህዘቦች መስዋእትነት ውጤት ነው፡፡ በተለይም እኔ ስታገልበት የነበረው በህወሓት መሪነት የትግራይ ህዝብ በከፈለው እጅግ ከፍተኛ መስዋእትነት እንዲሁም፣ በተሰውት ጀግኖች፣ (በተደጋጋሚ በተቃጠሉ መንደሮች፣ በአውሮፕላን ድብደባ ወዘተ) የመጣ ውጤት በመሆኑ ሕገ መንግስቱን የማስጠበቅ ጉዳይ እንደሌላው ታጋይ ሞራላዊ ግዴታ አለብኝ ስለምል ነው፡፡
ኢህአዴግ የጀመረው መልካም አስተዳደር የማስፈን ዘመቻን በተመለከተ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እኔ አንደኛው የምቃወመው፣ ለምሳሌ የመልካም አስተዳደር ጉዳይን መንግስት ከቢሮክራሲ ጋር ያየዋል፤ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ፖለቲካዊ ነው፤ የዲሞክራሲ ማጣት ውጤት ነው፡፡ ችግሩ የሚጀምረው ከላይኛው አመራር ነው፡፡ እላይ ከተስተካከሉ ከስር ይስተካከላል፡፡ የወረዳውንና የቀበሌውን እያሰሩ፣ እላይ ያሉት እርስ በእርሳቸው ሳይገማገሙ ሳይተጋገሉ ያሉበትን ሁኔታ አጥብቄ እቃወማለሁ፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ መተጋገል የለም፡፡
በቅርቡ በድረ-ገፆች በተሰራጨ ፅሁፍ፤ “ደርግነት እየመጣ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል…ምን ለማለት ፈልገው ነው?
ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየጠበበ ነው፡፡ በተለይ ከ97 ጀምሮ ያሉትን ነገሮች ስናያቸው፣ ህጎች የሚባሉት ተግባራዊ ሲደረጉ የሰውን ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ለማፈን ነው። አንዳንድ ሰዎች የኢህአዴግን መንግስት በብዙ መልኩ ዝርክርክ ነው ይሉታል፡፡ አንድ ውጤታማ የሆነበት ጉዳይ ቢኖር፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብትን ማፈን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ፣ የዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ተቃውሟቸውን የማሰማት መብቶችን—ስናይ እየጠበበ ነው የመጣው፡፡ አሁን ደግሞ የሲቪል አስተዳደሩ አልቻለም፤ ተዳክሟል የሚባል ነገር ሲመጣ፣ አንዳንድ የወታደር መሪዎች፤ “እኛ እንሻላለን፤እኛ ጥሩ ነው ያለነው፤የደከመው ሲቪሉ ነው; እያሉ በአደባባይ መናገር ጀምረዋል፡፡ ደርግነት የሚመጣው እንግዲህ ሲቪሉ መግዛት ሲያቅተውና “ወታደሩ እኔ እሻላለሁ” ማለት ሲጀምር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እየጨለመ የመጣው ዲሞክራሲ፣ ወደለየለት አምባገነንነት ያመራል ማለት ነው፡፡
ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየጠበበ ደርግነት እያቆጠቆጠ፣ በመንግስትም ከመንግስት ውጪም ማፍያዎች እየታዩ ነው ስል፡ “ብዙ ሰዎች አንተ አትፈራም እንዴ? ሊገድሉህ ሊያስሩህ ይችላሉ” ይሉኛል፡፡ ለስጋታቸው አመሰግናለሁ፡፡ በተዘዋዋሪ መንገድ ግን መታገል አለብህ እያሉኝ ነው፡፡ ሃሳቡን በሠላማዊ መንገድ የገለፀ ሰው ጥቃት ይፈፀምበታል ካላችሁ፣ ይሄ ነገር ሊኖር እንደሚችል ሳላውቀው አይደለም ወደዚህ የገባሁት፡፡ መጀመሪያ በ “ካራክተር አሣስኔሽን”፣ ከዚያም የተለያዩ ጥቃቶች ሊፈፀሙ ይችላሉ፡፡ እንግልት… መሞት… መታሰር ያስፈራል፡፡ ያስጠላልም፡፡ እኔ ከሁሉም የምፈራው ፈርቶ በቁም መሞትን ነው፡፡ ፈርቶ የህሊና እስረኛ መሆንን ነው፡፡ በተለይ ወጣቶች ከዚህ የህሊና እስርና በቁም መሞት በላይ ምንም እንደሌለ ተገንዝበው መታገል አለባቸው፡፡
በትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፈውን ሜቴክ በመጥቀስ፣ ኢኮኖሚውና ኢንዱስትሪው በወታደሩ ቁጥጥር ስር መዋሉ ትክክል አይደለም ብለው የሚቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ ከህግ አኳያ ሲታይ፣ ሜቴክ ወታደራዊ ተቋም አይደለም፡፡ ወታደራዊ መሪዎች ያሉበት የሲቪል ተቋም ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ስለዚህ ወታደራዊ ተቋም ሳይሆን የራሱ ሰውነት ያለው ተቋም ነው፡፡ ግን በህብረተሰቡ ዘንድ ይህ ግንዛቤ የለም፡፡ አብዛኛው ሰው የመከላከያ ተቋም እንደሆነ ነው የሚያስበው፡፡ ለሰው ሜቴክ ተጠሪነቱ ለመከላከያ ነው የሚመስለው፡፡ በእርግጥ የመከላከያ ታንክና የሜቴክ ገንዘብ ከተጨመረበት በጣም አደጋ ነው የሚሆነው፡፡
ከዚያ በላይ ግን የሚያሳስበው ዝርክርክነቱ ነው፡፡ ባለፈው ፓርላማ፣ በስኳር ፕሮጀክቶች ላይ የቀረበው እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም፡፡ ገና አንድም ነገር ሳይጀመር ሙሉ ገንዘብ መስጠት ምን ማለት ነው!? 2005 ላይ ማለቅ የነበረበት ፕሮጀክት እስካሁን ሲዘገይ፣ መንግስት ጉዳዩን በሚገባ ማየት አለበት፡፡ ስለዚህ ከፓርላማው ብዙ እንጠብቃለን። ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ብዙ እንጠብቃለን፡፡ ተጣርቶ ለህዝብ መቅረብ አለበት። ለመሆኑ ፀረ- ሙስና ኮሚሽን ይሄ ሁሉ ሲሆን የት ነበር? ከዚህ ጉዳይ በመነሳት ጠቅላላ ስርአቱንም መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ማየት ይጠይቃል፡፡ እኔ እንደሰማሁት ሜቴክ ወደ 275 ቢሊዮን ብር ነው የሚያንቀሳቅሰው። ይሄ ነገር በህግና ስርአት ካልተመራ አደገኛ ነው፡፡ መንግስት ይሄን መገምገም አለበት፡፡ ጥሩ ከሰራ ጥሩ ሰርቷል ማለት፣ ካልሰራ ደግሞ ማስተካከል አለበት፡፡ ሜቴክ የመከላከያ ተቋም ነው የሚሉ ሰዎች፣ብዙ ጊዜ እንደ ስጋት የሚገልፁት፣ ጠመንጃና ገንዘብ ሲገናኙ አደገኛ መሆናቸውን ነው፡፡
ኢህአዴግ ያለፈውን ሥርዓት አስወግዶ ሥልጣን ሲይዝ፣ የደርግን ወታደራዊ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ማውደሙ ተገቢ አልነበረም፤ባለው ላይ መቀጠል ነበረበት የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ አዲስ መንግስት በመጣ ቁጥር ሁሉንም አፈራርሶ ከዜሮ የመጀመር ባህል አገሪቱን ክፉኛ ይጎዳታል—-የሚል ሃሳብ ይንጸባረቃል፡፡ በዚህ ጉዳይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
እዚህ ላይ ሁለት ነገር ነው መታየት ያለበት፡፡ አንደኛው በሀገራች በአጠቃላይ ሲታይ፣ “ለውጥ” እና “ቀጣይነት” በሚለው መርህ አይደለም የምንሄደው። ደርግ የኃይለ ሥላሴን መንግስት ሲጥል ጠንካራ የነበሩትን ነገሮች በሙሉ አፍርሶ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ደርግን ስናስወግድ፣ ደርግና ሌላውን ነገር በተሟላ መንገድ ለይተን አይተነው ነበር የሚል እምነት የለኝም፡፡ መዋቅሩ አስቸጋሪ ስለነበር መቀየር ነበረበት፡፡ ነገር ግን የተሰሩ በጎ ነገሮችን ያየንበትና የተቀበልንበት መንገድ ችግር ያለበት ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ ያለፈን ስርአት በጎ ነገር የመቀበል ልማድ በሀገሪቱ የለም፡፡ ይሄ መስተካከል ያለበት ነው፡፡
በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች፣እርስዎ በጀነራል ሳሞራ የኑስ ላይ የሰነዘሩት አስተያየት መነጋገሪያ ሆኗል …
አዎ! አንድ ጓደኛዬ፤ “ህወሓት ከሌለ ይሄ ህዝብ አይኖርም ይባላል” ብሎ ጠየቀኝ፡፡ “ኧረ እንዲህ ያለ ነገር የለም” አልኩት፡፡ “ኧረ የድሮ ጓደኛህ ነው ያለው” አለኝ፡፡ በእርግጥም ሊንኩን ነግሮኝ የተባለውን ሳነብ ማመን አልቻልኩም፡፡ ባለፈው የግንቦት 20 በዓል ላይም የቀረበው ነገር አጨቃጫቂ ነው፡፡ “የሀገራችን ችግር በህወሓትና በኢህአዴግ ብቻ ነው የሚፈታው” የሚል የምርጫ ቅስቀሳ ለምን እንደጀመሩ አይገባኝም። ድርጅት ድርጅት ነው፤ህዝብ ህዝብ ነው፡፡ ያ ድርጅት ከሌለ፣ ህዝብ የለም ማለት የሚያስኬድ አይደለም። የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 87 ምን እንደሚል የታወቀ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ኢህአዴግ ከሌለ አይኖርም ማለት እብሪት ነው፡፡ ኢህአዴግንም ህወሓትንም የፈጠረው ህዝብ ነው እንጂ እነሱ ህዝብን አልፈጠሩም፡፡ በወቅቱ ጀነራሉ ይሄን ንግግር ሲያደርጉ፣ ከመድረክ ተሳስተዋል ያለ ሰው አልነበረም፡፡ ጀነራሉ የራሳቸው አስተያየት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንዲሉ ሕገ – መንግስት አይፈቅድላቸውም፡፡
በኔ አመለካከት ጀነራል ሣሞራ ለመንግስትና ለህዝቡ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ያለው ነገር የጠቅላይ አዛዡ የአቶ ሃይለማርያም ስራ ነው የሚሆነው። መተካት ካለባቸው ግን በጀነራል ፃድቃን መሆን የለበትም፡፡ እሣቸውም የሚፈልጉት አይመስለኝም፡፡ ጀነራል ፃድቃን በአመራር ብቃታቸው የተመሠከረላቸው፣ በሄዱበት ጥሩ አመራር መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በመከላከያ ውስጥ በጀግንነትና በብቃታቸው የተመሠከረላቸው ወጣት የጦር አዛዦች ስላሉ መተካት የሚያስፈልግ ከሆነም በነሱ ነው መተካት የሚኖርበት፡፡
እርስዎና አንዳንድ የቀድሞ አመራሮች፣በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የምትሰነዝሩት ወደ ስልጣን ለመመለስ ፍላጎት ስላላችሁ ነው ይባላል፡፡ እርስዎ ተመልሰው ሥልጣን ለመያዝ ያስባሉ?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳንድ ጊዜ ኮንስፓይሬሲ ቲዎሪ ይበዛበታል፡፡ መስፍናዊ ዳራ አለው፡፡ ደርግ የፈጠረው ጫና አለ፡፡ አሁንም የሚፈጠር ጫና አለ። ስለዚህ ሰው በአገሩ ጉዳይ ላይ የመሰለውን ሃሳብ ሲያቀርብ፣ ቁም ነገሩ ምንድን ነው? የሚለውን በተሟላ መንገድ ሳያይ የራሱ ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡ ለራሱ ስልጣን ፈልጎ ይሆን? የሚል ጥያቄም ያነሳል፡፡ በራሴ በኩል እኔ የማንም ከለላ የለኝም፤ የማንንም ከለላ አልፈልግም፡፡ የሀገራችን ሁኔታ ያሳስበኛል፤ ህገ መንግስቱ ያወጀልን መብት አለ፡፡ ይሄን መብቴን ተጠቅሜ በተቻለኝ መጠን ከጥናት ተነስቼ ያለኝን ሃሳብ አቀርባለሁ፡፡ በተረፈ እኔ ወደ ስልጣን የመመለስ ምንም አይነት ሀሳብ የለኝም፡፡ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ በምርምር ሀገሬን የማገልገል ፍላጎት ነው ያለኝ፡፡ ስልጣን ብፈልግ ኖሮ መሞዳሞድ ነበር የሚጠበቅብኝ፡፡
ጀነራል ሰሞራ በጄኔራል ፃድቃን መተካት አለባቸው ብለው አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች አሉ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው?
እንግዲህ 25 ዓመት ነው የቆየነው፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የሰራዊቱ የብሄር መመጣጠን እየተስተካከለ መጥቷል የሚል ግምት ነው ያለኝ። ወታደራዊ አመራሩም (chief of staff) የትግራይ ተወላጆች ርስት መሆን የለበትም፡፡ ከተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች በብቃታቸውና በጀግንነታቸው እዚያ ደረጃ ላይ መድረስ የሚችሉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ለትግራይ ህዝብ የሚጠቅመው ከብሄር ብሄረሰብ የተውጣጣ ብቁ አመራር ሲኖር ነው፡፡ የትግራይ ልጅ ስልጣን ላይ ስለተቀመጠ አይደለም፡፡
በዚህ ዓመት ከወትሮ በተለየ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ቀውሶች ተከስተዋል፡- በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብ፣ በትግራይ—-ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶች ነበሩ፡፡ የእነዚህ ቀውሶች ምክንያት ምን ይመስልዎታል?
እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች ምንጫቸው፣ አንደኛው የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች መንግስት በተሟላ መንገድ መፍታት አልቻለም፡፡ ሁለተኛ ከሙስና ጋር በተያያዘ ያሉት ችግሮች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ገምግሞ ማስተካከል ከተቻለ ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ በመንግስት የላይኛው አመራር ያለውን ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ በሚገባ መፈተሽ ያስፈልጋል። ህገ-መንግስቱ እስከተከበረ፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እስከተከበሩ ድረስ፣ ህገ-መንግስታዊ ተቋማት ስራቸውን በሚገባ መስራት እስከቻሉ ድረስ፤ ፓርቲና መንግስት የተለያዩ መሆናቸው ታውቆ አሰራሩ በዚህ እስከተለወጠ ድረስ ችግሮችን መፍታት አይገድም፡፡
ችግሮችን የቢሮክራሲ ብቻ አድርጎ ከታየ ግን አደገኛ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ በዋናነት ኢህአዴግ ከህዝቡ ጋር ሆኖ ተቃዋሚዎቹን አሳትፎ፣ አሁን ያለውን ፖለቲካዊ ቀውስ መፍታት አለበት። የወታደሩ ተፅዕኖ መቆም አለበት፡፡ ወታደሩ ወደ ካምፑ መግባት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ቀውሱ የመፈታቱ እድል ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አለኝ።
አሁን ለውጥ በሚፈልጉና በማይፈልጉ ኃይሎች መካከል ያለው ግጥሚያ ፍንትው ብሎ ወጥቶ መጥራት ይኖርበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በየጊዜው በሚያነሷቸው ሃሳቦች፣ ለውጥ ፈላጊ መሆናቸውን የሚያሳዩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በተግባር ግን የሚውሉ አይደሉም። በተግባር የማይውሉበት ምክንያት እነዚህን ሃሳቦች የሚያኮላሽ አንድ ያልተደረሰበት ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ይሄ መፈታት ይኖርበታል፡፡ ቀውሶቹ የመጡት ከዲሞክራሲ ጥያቄ፣ ከፍትህ ፍለጋ፣ ብልሹ አስተዳደርና ሙስናን ከመቃወም ነው። አንዱ ችግር ኢህአዴግ ህዝብ መስማት ማቆሙ ነው፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ህዝቡን የግድ ማዳመጥ አለበት፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የብሄር ቅራኔዎች የሚፈጥሯቸው ግጭቶች በተደጋጋሚ ይታያሉ። የፌደራሊዝም መምህር እንደመሆንዎ፣መፍትሄው ምንድን ነው?
ህገ መንግስቱ ለአውሮፓውያን (እንደ ስፔን ላሉ ሀገራት) ተምሳሌት የሚሆን ጭምር ነው፤ ችግሩ ያለው ህገ መንግስቱን መተግበር ላይ ነው። ይህቺ ሀገር በ1983 ዋዜማ የነፃ አውጭዎች ሀገር ነበር የምትባለው፡፡ ይሄ ህገ መንግስት የብሄር ብሄረሰቦችን መብት በማስከበርና ችግሮችን በመፍታት በኩል ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ የፌደራል ሥርዓቱ ሙሉ ለሙሉ በህገ መንግስቱ መሰረት ተግባራዊ ሳይደረግ ሲቀር ግጭቶቹ ሊመጡ ይችላሉ። ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ሽግግር ሲደረግ እነዚህ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ አሃዳዊ ስርአት ይሁን ቢባል ደግሞ የባሰ ነበር፡፡ እንደ ዩጎዝላቪያ መበታተን ሊመጣ ይችል ነበር፡፡ ይሄ ህገ መንግስት ዋና ችግሩ በሚገባ ተግባራዊ አለመደረጉ ነው፡፡ እስካሁን በመጠኑም ቢሆን ይሄን ፌደራላዊ ስርአት በእግሩ ለማቆም ጥረት ሲደረግ ነበር፤ አሁን ግን ወደ ኋላ እየተመለስን ይመስለኛል፡፡
ለወደፊት ምን አይነት ስርዓት ይፈጠራል ብለው ነው ተስፋ የሚያደርጉት?
የኔ ተስፋ የተገኘውን ሰላም እና እድገት ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ በቀጣይነት በማስፋት እንዲጐለብት ነው፡፡
አሁን በኦሮሚያ ይህን በሌሎች እየተቀጣጠለ ያለው የህዝብ መነሳሳት በሰላማዊ መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና “ጠያቂ” ህዝቦች እንዲኖሩ ፀረ – ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን እና ሙስናን እና ፍትሕ መጓደልን በጽናት የሚታገሉ ሲያስፈልግም ገዥው ፓርቲ እና በሱ የሚመራውን መንግስት በሰላማዊ ተፅእኖ ማስገደድ ሲችሉ ነው፡፡ ለዚሁም ሁሉም እንቅስቃሴ በሰላም እንዲሆን እና የነሱ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ለግላቸው ለመጠቀም ሁከት የሚጥሩትን ለመንግስት አሰልፎ በመስጠት ጭምር እንደታገሉ ነው፡፡
ሲብል ሶሳይቲ አሁን ካለው እንቅልፍ ተነስቶ ያለውን ሙሁራዊ ዓቅመ፣ ገንዘብ ትስስሩ መሰረት አድርጐ የተገኘውን በአምና እድገት የተጠናከረ መንገድ እንዲቀጥል በተሟላ መንገድ እንዲታገል ነው፡፡
ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ ድርጅቶች ካላቸው Crisis ሰላማዊ መንገድ ተጠናክረው ወጥተው ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ ለማስፋት ያለውን ሰላም እና እድገት እንዲቀጥል ነው፡፡
ወጣቶች በተለይ ምሁር በኛ ትውልድ የሚመሩት ድርጅት በወረራ በመቆጣጠር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲሰይዙት አልያም የራሳቸው ድርጅት ፈጥሯል፡፡ Change and continuously በማመን የተገኘውን ሰላምና ዕድገት አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲቀጥልበት ነው፡፡

አዲስ አድማስ

Leave a Reply