Wednesday, 22 June 2016 12:32

በይርጋ አበበ

 

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የሙያ ዘርፎች መካከል ከፍተኛ የሰራተኛ ቁጥር የሚይዘው የትምህርቱ ዘርፍ ነው። በትምህርት ሚኒስቴር ስር ከሚካሄዱ የትምህርት ተቋማት (አንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ደረጃ እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት) ውስጥ ከሚያስተምሩ መምህራን መካከል ከ420ሺህ በላይ የሚሆኑት በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የታቀፉ መሆናቸውን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዮሃንስ በንቲ ይናገራሉ። አባል ከሆኑት የሚልቅ መጠን ያላቸው መምህራን ደግሞ የማህበሩ አባል ሳይሆኑ አገራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። በዚህም መሰረት የመንግስት ተቀጣሪ የሆኑ መምህራን ብቻ እስከ አንድ ሚሊዮን ሊደርሱ እንደሚችሉ ይገመታል።

ለላፉት ረጅም ዓመታት የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ዝቅተኛ በመሆኑ አስተማሪዎች ስራቸውን በተገቢው መልኩ እየሰሩ አይደለም የትምህርት ጥራቱ እያሽቆለቆለ መጥቷል እና ሌሎች ተመሳሳይ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ስንክ ሳሮች በተደጋጋሚ ለአገሪቱ ገዥ ፓርቲ ለኢህአዴግ ሲቀርቡለት ቆይተዋል። በአንድ ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በኢሲኤ አዳራሽ ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ መሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ “የመምህራን ደመወዝ ዝቅተኛ በመሆኑ በትውልድ ቀረጻው ሂደት ላይ እንቅፋት ሆኗል። መንግስታችሁ የአስተማሪዎችን ደመወዝ የሚያሻሽለው መቼ ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

አቶ ኃይለማሪያም ከተቃዋሚዎች ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “አስተማሪው ደመወዙ ስላነሰ ብቻ በትውልድ ቀረጻ ሂደቱ ላይ ሆን ብሎ ሊቀልድ ይችላል የሚል እምነት የለንም። ዋናው የአስተማሪው ሙያዊ ዲሲፕሊን ጉዳይ ነው” ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት። በቅርቡ ደግሞ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ካቢኔ ለአስተማሪዎች መጠኑ “ዳጎስ” ያለ የደመወዝ ጭማሪ እና ተጨማሪ ጥቅማጥቅሞችን የሚያስጠብቅ ውሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል። የአስተማሪዎቹ ደመወዝም ከነበረው የሲቪል ሰርቫንት ደረጃ በአስር እርከን የተሻለ ሲሆን ለአዲስ አበባ አስተማሪዎች የቤት አቅርቦትና የትራንስፖርት ወጭዎችን እንደሚሸፍን የሚገልጸው የትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ አስትማሪዎች ደግሞ የቤት መስሪያ ቦታ የሚያገኙበትን እድል እንደሚያመቻች አስታውቋል።

የአስተማሪዎች ደመወዝ ጭማሪ በዚህ ወቅት ለምን መደረግ አስፈለገ? ጭማሪው በመንግስት ካዝና እና በአገሪቱ የገበያ ሁኔታስ ምን አይነት ተጽእኖ ያሳድራል? የደመወዝ ጭማሪው “ወደቀ” ለሚባለው የትምህርት ጥራትስ ምን ጠቀሜታ ይኖረዋል? የሚሉትንና ሌሎች ሀሳቦችን በመያዝ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል።

መጠኑ ያልተገለጸው የደመወዝ ጭማሪ እና

የመንግስት መግለጫ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2008 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ 128 መምህራንን እና በዘርፉ አካባቢ ያሉ ባለሙያዎችን የእውቅና እና የገንዘብ ሽልማት አበርክቶላቸው ነበር። በወቅቱ ባደረገው የሽልማት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ በሰጡት አስተያየት አስተማሪዎችን መደገፍ የመንግስት ፍላጎት መሆኑን ገልጸው ለስራቸው ተነሳሽነት እንደሚኖረውም ተናግረው ነበር። ከዚህ በተማሪም በተለይ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ “መምህራን እስከዛሬ ሲያነሱት የነበረውነ ቅሬታ የፈታ ነው” ሲሉ በሰጡት አስተያየት የአስተማሪዎች ደመወዝ ቀድሞ ከነበረው ላይ ማሻሻያ በማድረግ ከመጭው ሀምሌ 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ የአስተማሪዎች ደመወዝ በአስር እርከን የሚጀምር መሆኑን ተናግረው ነበር።

የደመወዙን በአስር እርከን መጨመር የገለጹት የትምህርት ሚኒስትሩ የገንዘቡን መጠን እንዲገልጹልን ከሰንደቅ ጋዜጣ በስልክ ጠይቀናቸው ነበር። ሆኖም አቶ ሽፈራው ይህን አሃዝ ለመንገር ጊዜው አሁን እንዳልሆነ በመግለጽ ስልኩን ዘግተውታል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በቅጽ ሶስት ቁጥር አስር የሰኔ ወር እትም መጽሄቱ ላይ የቢሮው ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ ስለ አስተማሪዎች የደመወዝ ጭማሪ መንግስታቸው ለአስተማሪዎች ከዚህ ቀደምም መጠነ ሰፊ የድጋፍ ስራ ሲሰራ መቆየቱን የገለጹ ሲሆን ለአብነት ያህልም የአስተማሪዎቹን የሙያ እና የክህሎት ማሻሻያ እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ከሰርተፊኬት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አስተማሪዎችን ትምህርትቸውን እንዲያሻሽሉ በመደረጉ በአጠቃላይ 2 ሺህ 729 መምህራን በእድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አስተማሪዎች ከደመወዝ ጭማሪው በተጓዳኝ ሌሎች ፓኬጆችን (የቤት እና የትራንስፖርት አቅርቦት) ቢሮው ማመቻቸቱን ገልጸው በቀጣይነትም የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አጋጣሚም እንደሚያመቻች አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ አምስት ሺህ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸው የተገለጸ ሲሆን በቀጣይነትም ተጨማሪ 19 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የሚገነቡ መሆኑም ተያይዞ ተገልጿል።

ስለደመወዝ ጭማሪው የመምህራን ማህበር አስተያየት

ከ420 ሺህ በላይ መምህራንን በአባልነት እንደያዘ የሚነገረው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የአባላቱንና የባለሙያዎቹን ጥቅምና መብት በማስጠበቅ በኩል ትችቶች የሚደርስበት ቢሆንም መንግስት በቅርቡ ያስተላለፈውን ውሳኔ ቀደም ብሎ ማህበራቸው ሲጠይቀው የቆየ መሆኑን ይናገራሉ። አቶ ዮሃንስ “ቀደም ሲል ደጋግመን ስንጠይቀው የቀየ ጉዳይ በመሆኑ የምናውቀውና የምንጠብቀው ውሳኔ ነበር” በማለት ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ሆኖም መንግስት አሻሽየዋለሁ ስላለው የአስር እርከን ጭማሪ የደመወዝ ማሻሻያ ጉዳይ ይጨመራል የተባለውን የገንዘብ መጠን ማወቅ እንዳልቻሉ ሲናገሩ “አሁን ብንናገር በይፋ ሲገለጽ ከሚገለጸው መጠን ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ስለሚችል ያኔ እንገልጻለን” ሲሉ መልሰዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር በአገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን የሰራተኞች ደመወዝ እርከንን የማሻሻል ስራ እንደሚሰራ በቅርቡ ሚኒስትሯ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የ11 ወር እቅድ አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት ተናግረው ነበር። አሁን መንግስት ማሻሻያ አድርጌያለሁ የሚለው የመምህራን ደመወዝ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ከሰንደቅ ጋዜጣ የቀረበላቸው አቶ ዮሃንስ ሲመልሱ “ይህ (የመምህራን የደመወዝ ጭማሪውን) ከዛ ጋር ግንኙነት የለውም ራሱን የቻለ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

የደመወዝ ጭማሪውን ባለሙያዎች እንዴት ያዩታል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለረጅም ዓመታት ያስተማሩትና ከአገር ውጭም በአሜሪካን አገር ሲያስተምሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ተመልሰው በምርምር ስራ ላይ ያሉት ዶክተር ፍሰሃ አስፋው የደመወዝ ጭማሪውን አስመልክቶ ሙያዊ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር። ዶክተር ፍሰሃ “በመጀመሪያ የአስተማሪዎች ችግር ምንድን ነው የሚለው ጥያቄ ተለይቶ መታወቅ አለበት። የአስተማሪዎች ችግር ደመወዝ ብቻ አይደለም የችሎታ ማነስ ችግርም አለ። አስተማሪዎች ሙያቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ ሳያደርጉ ዝም ብሎ የደመወዝ ጭማሪ ማድረጉ የፖለቲካ ጨዋታ ብቻ ነው የሚሆነው። እንደዚህ ስልህ ግን ደመወዝ አይጨመር እያልኩ አይደለም ማለት የፈለኩት ቅድሚያ ለብቃታቸው ማሻሻያ ይሰጥ ነው” ይላሉ።

ዶክተር ፈሰሃ “በአሁኑ ወቅት የትምህር ጥራት እና የአስተማሪነት ዋጋ ወርዷል” ከሚሉት ወገን መሆናቸውን ጠቅሰው ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከአስተማሪነት አመላመሉ እንደሆነ ይናገራሉ። ዶክተር ፍሰሃ “ድሮ አንድ የተማረ ሰው ያልተማረን ህዝብ እንዲያስተምር ሲታጭ ማስተማር ይችላል ወይ ተብሎ ግምገማ ይደረግለታል። ግምገማው ትኩረት የሚያደርገው በእጩ መምህሩ የትምህርት ብቃት የማስተማር ችሎታ እና የትምህርት አቀባበል ላይ ነው። በዋናነት ትኩረቱም በእጩ መምህሩ የእንግሊዝኛ አማርኛ እና ሂሳብ ትምህርቶች ላይ ያለው ብቃት ላይ ነው። ይህ ሁሉ ግምገማ ከታየ በኋላ ነው ወደ መምህርነት ኮርስ የሚገባው። ይህ በመሆኑም ምክንያት አስተማሪው ለሙያውና ለተማሪዎቹ ክብር ይኖረዋል” ብለዋል። አሁን ስላለው ሁኔታ ሲናገሩም “የአሁኑ ጊዜ አስተማሪ ውሎው ከተማሪዎቹ ጋር በመሞዳሞድ አልባሌ ቦታ ነው የሚገኘው። የሚያስተምራቸውን ተማሪዎችም ውሎ እና እንቅስቃሴ የሚከታተል አይደለም። አስተማሪው ራሱ ትምህርት የሚያስፈልገው ነው። በአጭሩ አሁን ሙያው ወርዷል” ይላሉ።

ሙያው ወርዷል ሲሉ ምክንያቱ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? ተብለው ተጠይቀው ነበር። ዶክተር ፍሰሃ “ችግሩ የሚመነጨው ከመሰረቱ ነው። መንግስት ትኩረት ያደረገው ከትምህርት ተደራሽነት ላይ እንጂ ጥራት ላይ አይደለም። መዳረሱ ጥሩ ቢሆንም የማዳረሱ አቅም ሳይኖር ለማዳረስ መሞከር የትምህርቱን ጥራት እንዲወርድ ያደርገዋል። ገና ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ማድረግ ካልተቻለ የአስተማሪዎቹ ጥራትም አይሻሻልም። ምክንያቱም አስተማሪ የሚሆኑት ከዚያ ያልጠራ የትምህርት ፖሊሲ የወጡ ተማሪዎች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።

የአስተማሪዎች ደመወዝ አለመሻሻል በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል ተብሎ ይነገራል። በእርሰዎ እይታ አሁን የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ይህን ችግር ሊቀርፍ ይችላል ብለው ያስባሉ? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ “ገንዘብ እኮ እውቀት ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ደመወዝ መጨመሩ በእርግጥ አስተማሪዎችን ከተማሪዎቻቸው ጋር ከመሞዳሞድ ሊያወጣቸው ይችላል። አሁንም ደግሜ የምነግርህ ከደመወዝ ጭማሪው በፊት ጥራቱ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ነው” ሲሉ መልሰዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply