Wednesday, 22 June 2016 11:41

በይርጋ አበበ

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ስር በሚገኙ ሶስት ወረዳዎችን የሚያዋስነው የጉና ተራራን ከእንስሳት ንክኪ እና ከእርሻ ለመከለል የተካሄደው እንቅስቃሴ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ተቃውሞ ገጠመው። ተኩስ ተከፍቶም መጠነኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እዘዝ ዋሴ ላይም ጉዳት እንደደረሰ ቢገለፅም፤ የዞኑ ኮምኒኬሽን ቢሮ ግን አስተባብሏል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከሰንደቅ ጋዜጣ በስልክ ጥያቄ የቀረበላቸው የደቡብ ጎንደር ዞን ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀኔ “የተወራው ከእውነት የራቀ እና ግነት የበዛበት ነው” ሲሉ መልሰዋል። አቶ ጥላሁን “እንደሚታወቀው ጉና ተራራ የ44 ምንጮች መገኛ ሲሆን ተራራውን ሶስት ወረዳዎች (ፋርጣ፣ ጋይንት እና እስቴ ወረዳዎች) የሚያዋስኑት ሲሆን አካባቢ ተፈጥሯዊ ደህንነቱ እንዲጠበቅ ለማድረግ በክልል ደረጃ እና በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ አማካኝነት ተጠንቶ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ተካሂዶበት በስምምነት የተወሰነ ውሳኔ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም ግን ተቃውሞ የተነሳው ደኑን እንዲጠብቁ በተመረጡ ጥበቃዎች ምርጫ መሆኑን የገለጹት አቶ ጥላሁን “እኛ ያላመንባቸው ጥበቃዎች ናቸው የተመረጡት ስለዚህ ውሳኔውን አንቀበልም ብለው ነው ጠብ የቀሰቀሱት። በዚያ ላይ ደግሞ በእለቱ ጠቡን የቀሰቀሱት ግለሰቦች በስካር መንፈስ ተነሳስተው ነው። በግጭቱ ምክንያት ተኩስ ተከፍቶ ጉዳት ደርሷል የተባለው የተጋነነ ነው። ዋና አስተዳደሪ አቶ እዘዝ ላይ ጉዳት ደረሰ የተባለውም ሀሰት ነው”ብለዋል። ደኑ እንዲካለል ያስፈለገበትን ምክንያት የተጠየቁት አቶ ጥላሁን “በክልል ደረጃ ተወስኖ የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ጥናት ያደረገበትና እንዲከለል የተወሰነበት ምክንያት አካባቢው እንክብካቤ ሳይደረግለት ለረጅም ዓመታት በመቆየቱ ጉዳት ስለደረሰበት በምንጮቹ ላይ የመድረቅ ስጋት ተደቅኖባቸዋል። እንክብካቤ ካልተደረገለት ታሪካዊነቱ ስለሚጠፋ የደኑን ታሪካዊነት ለማስጠበቅ ነው” ብለዋል።

ደኑን ለመከለል የታሰበው ኢህአዴግ ከደርግ ጋር ባካሄደው ጦርነት ወቅት ትልቅ ድል የተጎናጸፈበት በመሆኑ ነው። በዚያ ላይ የደኑ መካለል ሲሰራ የገበሬዎችን የግል መሬት የሚነካ ስለሆነ ነው ጠቡ የተነሳው ይባላል። ይህን እንዴት ያዩታል? የሚል ጥያቄ ለአቶ ጥላሁን ቀርቦላቸው ነበር።

ለጥያቄው መልስ የሰጡት አቶ ጥላሁን “ፖለቲካ ማለት እኮ ለህዝብ ጥቅም መስራት እንጂ ሌላ አይደለም። ሆኖም ደኑን ማካለል ያስፈለገው የደኑን ታሪካዊነት ለማስጠበቅ እንጂ ሌላ ዓላማ የለውም። ሌላው ተቃውሞ ያነሳው ህዝቡ ሳይሆን የተወሰኑ ግለሰቦች ናቸው እንጂ ህዝቡ ተቃወመ የሚያስብል አይደለም” ብለዋል። አቶ ጥላሁን አያይዘውም “የአርሶ አደሮችን መሬት ይነካል የተባለው በፍጹም ስህተት ነው። አርሶ አደሮቹ በህገወጥነት ሲያርሱት ቆይተዋል እንጂ የመሬቱ ባለቤት ሆነው አይደለም” በማለት መልሰዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply