ኢሕአዴግና አጋሮቹ በአምስተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ማሸነፋቸው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተገልጾ፣ አዲስ መንግሥት በመሠረተበት ጥቂት ወራት የተነሳው ይኼው ተቃውሞ፣ በምርጫ ወቅትም ሆነ ከምርጫው ዋዜማ የተድበሰበሱ ነገሮች መኖራቸው ያጋለጠ ሲሆን፣ በተለይ ሥርዓቱ የአስተዳደር ቀውስ ውስጥ መግባቱ ያረጋገጠ ነበር፡፡
አቶ መለስን የተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ቀደም ሲል ድርጅቱ ባስቀመጠው የምርጫ ስትራቴጂ ተጠቅመው በአንዳንድ ወገኖች ተቀባይነት ባላገኘ የምርጫ ሒደት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ቀውስ የሚያትት ሪፖርት በይፋ ያቀረቡበት ዓመትም ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በስድስት ወራት ሪፖርታቸው በኦሮሚያ የተከሰተው ቀውስ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆን፣ መንግሥት በማናቸውም የውጭ ኃይሎች ላይ ማሳበብ እንደማይፈልግና በአጠቃላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከተከሰተው የአስተዳደር ቀውስ የመነጨ እንደሆነ ነበር ያስቀመጡት፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን ተቃውሞውን ለማብረድ በተወሰደው ዕርምጃ መንግሥት ከመጠን በላይ ኃይል ተጠቅሟል በማለት ይከሳል፡፡
ተቃውሞው የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም የተጀመረ ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው ከፍተኛ የሥራ አጥነት፣ የፍትሕ እጦት፣ ደኅንነትና ሌሎች ችግሮች ማሳያ እንደሆነ የመንግሥት እምነት ነበር፡፡ አንዳንድ ተቺዎችና ተቃዋሚዎች ለተቃውሞ መነሻ የሆነውና መንግሥት ያመነበት የአስተዳደር ቀውስ የዴሞክራሲ መታፈን መገለጫ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡ በመንግሥት ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለተፈጠረው ግጭት ምክንያትና በሰበቡ ሕይወታቸውን ላጡ ግለሰቦች በመንግሥት ስም ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ ለተጎጂ ቤተሰቦችም አስፈላጊ ካሳ ለመክፈል ቃል መግባታቸው ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መንግሥት ሁከቱን ለማብረድ የተጠቀመው ኃይል ተመጣጣኝና ከመጠን ያላለፈ እንደሆነ በምርመራው እንዳረጋገጠ በቅርቡ ለፓርላማ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ይኼው ሪፖርት ከቀረበና ጥያቄዎችም በተለያዩ አካላት መነሳት ከጀመሩ በኋላ ግን ሂዩማን ራይትስ ዎች ተቃራኒ ምልከታ ያለው ‹‹Such a Brutal Crackdown›› የሚል ርዕስ የሰጠው ሪፖርት አቅርቧል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ቀደም ካሉ ጊዜያቶች ጀምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሪፖርቱም በዚሁ በኦሮሚያ በተከሰተው ተቃውሞ ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል መንግሥት ካቀረበው ጋር ተፃራሪ ነው፡፡ ይኸው ሪፖርት ቀደም ሲል ግጭቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ያወጣቸው ከሁለት በላይ ሪፖርቶች ቅጥያ ሲሆን፣ በኦሮሚያ የተከሰተው ተቃውሞ ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ እንደነበር በመግለጽ መንግሥት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩሶ ከ400 በላይ ሰዎችን መግደሉ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ማሰሩንና መሰወሩን ያስረዳል፡፡
ለዚሁ ሪፖርት ከ25 በላይ ሰዎች ማነጋገሩን የሚያስረዳው ሂዩማን ራይትስ ዎች እስከ ያለፈው ግንቦት ወር በአካባቢው ተፈጸመ ያለውን ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሪፖርቱ አካቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ኃይልን ያካተተ ያለው በድርጊቱ የተሳተፈው የፀጥታ ኃይል ተቃውሞውን በማነሳሳት ሚና ነበራቸው ያላቸውን መምህራን፣ ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ የጤና ባለሙያዎችና የተቃዋሚ አመራሮችን ለእስር መዳረጉንም አካቷል፡፡
ለዚሁ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደ ዋና መነሻ ተደርጎ የሚወስደውን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ‹‹የዋና ከተማዋን ማዘጋጃ ቤት ድንበር ወደ ኦሮሚያ ክልል ድንበር የማስፋት ዕቅድ ነበረው፤›› በማለትም ይኼው ሪፖርት ይተቸዋል፡፡ ‹‹መፈናቀልን ያስከትላል፤›› በማለትም ያክላል፡፡ የኋለኛው ነጥብ በገለልተኛ አካላትና የሚዲያ ዘገባዎችም በብዛት የተንፀባረቀ ነበር፡፡
መንግሥት ተቃውሞን ለማብረድ በሚሞከርበት ወቅት 173 ሰዎች መገደላቸውን የተቀበለ ሲሆን፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን ከ400 ሰዎች በላይ መገደላቸውን በሪፖርቱ አካቷል፡፡ መንግሥት በአንዳንድ ቦታዎች ተቃውሞው በትጥቅ የታገዘ እንደነበርና አንዳንድ የፖሊስና የጦር መሳሪያ መጋዘኖችን ሰብረው በመግባታቸው አደጋው የከፋ እንዳይሆን ዕርምጃ መውሰዱን የገለጸ ሲሆን፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ግን ተቃውሞው ሙሉ ለሙሉ ሰላማዊ መሆኑንና የተገደሉትም አብዛኞቹ ዕድሜያቸው ከ18 በታች መሆኑ ያስረዳል፡፡
ሪፖርቱ በተጨማሪም የተቃውሞ ሠልፉ ተሳታፊዎች ገለልተኛ እንደሆኑ የሚያምኑባቸው እንደ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የመሳሰሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን በመዝጋት፣ መንግሥት ሐሳብን በነፃነት የሚገልጹበት መንገድን እንዳፈነ ይከሳል፡፡
በመጨረሻም ድርጅቱ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ምክረ ሐሳብ የሰጠ ሲሆን፣ መንግሥት በተቃውሞ ምክንያት ለእስር የዳረጋቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ አልያም በፍርድ ቤት አስቀርቦ ወንጀላቸውን እንዲያስረዳ ይጠይቃል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውም አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈላቸው የጠየቀ ሲሆን፣ እነዚህ ዕርምጃዎች በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦሮሞ ማኅበረሰብ መተማመን እንደገና እንዲፈጠር አስፈላጊ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡
ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተጠናከረና የተባበረ የጋራ ጫና መንግሥት ላይ እንዲደረግ የሚጠይቀው ይኸው ሪፖርት፣ ‹‹የኢትዮጵያ አፋኝ አስተዳደር የአገሪቱን የረዥም ጊዜ መረጋጋትና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እጅግ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ጥሏል፤›› ይላል፡፡
መንግሥት ገለልተኛ ባለው አካል ያጣራውን ሪፖርት ለፓርላማ አስቀርቦ ያፀደቀ ሲሆን፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለልተኛ ሊሆን እንደማይችል በመግለጽ ጉዳዩን በገለልተኛ የውጭ አካል እንዲጣራና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተከሰተ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ ዕርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፡፡
በኦሮሚያ አካባቢ ለተከሰተው ተቃውሞ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው በአዲስ አበባና ዙሪያዋ የሚካሄደው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ያለምንም ካሳ የኦሮሞ ተወላጆች ተፈናቅለዋል የሚለው ነው፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢንቨስትመንት ምክንያት ለሚነሱ ወገኖች በቂ ካሳ እንዲከፈልና በአካባቢው ላይ ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ አስፈላጊ ቅድመ ጥናት እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡
በምክረ ሐሳቡ በርካታ ጉዳዮች ያካተተው ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ በተለይ በተቃውሞው ላይ ሕገወጥ ግድያንና እስራት የፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ፣ በእስር ቤት የሚፈጸሙ ስቃዮችና ኢሰብዓዊ አያያዝን እንዲስተካከል፣ በሕግ ቁጥጥር ስላሉት ሰዎች ቁጥርና ማንነት በግልጽ ይፋ እንዲደረግ እንዲሁም በዚሁ ተቃውሞ ቀስቃሽነት ታስረው በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ ክስ የተመሠረተባቸው ክሳቸው እንዲነሳ ይጠይቃል፡፡
የሂውማን ራይትስ ዎች ይህንን ሪፖርት መንግሥት ካቀረበው ሙሉ ለሙሉ ተቃራኒ ሲሆን፣ ተቃውሞ በተከሰተበት ወቅት በተለያዩ ሚዲያዎች ይፋ የሆኑ፣ በሌሎች አካባቢዎችና ብሔሮች (በተለይ በአማራ ክልል) ስለተፈጸሙ ግጭቶች ያለው ነገር የለም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከቱ በጦር መሳሪያ ስለመታገዙም አያነሳም፡፡