እንደሚታወቀው የትግራይ ወያኔ(ህወሃት) በ1972 ዓ/ም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የወልቃይት፤ የጠገዴና ጠለምትን ሕዝብ ዘር በማጽዳትና በማጥፋት እስከ አሁን ይህን የኮሚቴው መግለጫ እስካወጣንበት ሰአት ድረስ ቀጥሎበት እንደሚገኝ ግልጽ ነው።ይህን ፀረ-ሕዝብና መርዘኛ የመስፋፋት ፍላጎቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሲባልም ሴት፤ ሕፃን ፤ወጣትና ሽማግሌ ሳይለይ ወገኖቻችን በጅምላ ተጨፍጭፈዋል፤ታስረዋል፤በእሥር እንዳሉ እንዲሞቱ ተደርጓል፤የትውልድ ቀያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ተደርጓል ፤ ሐብት ንብረታቸው ተቃጥሏል ተዘርፏል ፤ ርስት ጉልታቸውን ተነጥቀዋል፤በርካታ የቀንድና የጋማ ከብት በኃይል ተወርሷል ፤ ደን መንጥሮ ጭራሮ ሰብሮ ያቀናነውን ለምና ውሃ ገብ መሬቱን ተነጥቋል።
ይህ ሁሉ ሲሆን ደራሽ ወገን ባይገኝም የወልቃይት፤ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ከላይ ከፍ ብለው የተጠቀሱት ጭካኔ የተሞላባቸው አረመኔያዊና ፋሽስታዊ ርምጃዎች ቢወሰዱበትም አሜን ብሎ እጅ እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም።ትግሉን በተለያዩ ስልቶች ቀጥሎ ዛሬ ላይ ደርሷል።ይህን ሀቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳምሮ ያውቀዋል።ድምፃችን ከፍ አድርገን የምንጮኸውም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ጉዳይ የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ነው። በተለይም የአማራ ብሄር ሕዝብ በእኛ ላይ የተሠነዘረው ጥቃት የራሱም ጥቃት እንደሆነ ሊያምንበትና ለመፍትሄው ሊረባረብ ይገባዋል።
ከሳለፍናቸው አምስትና ስድስት ወራቶች ቀደም ብሎ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚፈቅደው መብት መሠረት የአማራ ብሔር የማንነቱን መብት ለማስከበር ከሕዝብ በተመረጡ ከአብራኩ በተወለዱ ልጆቹ አማአካኝነት ኮሚቴ ተመሥርቶ ሥራውን በይፋ እያንቀሳቀሰው ይገኛል።እስከ አሁን የተገኘ ፍታሃዊ ምላሽ ባይኖርም ኮሚቴው የአማራ ብሔር ሕዝብና የመላውን ኢትዮጵያዊ ሕዝብ ድጋፍ በመጠየቅ የተነሳበትን የአማራ ብሔር ማንነት መብት ለማስከበር እጅግ ተጠናክሮ እንዲወጣና ጥያቄው መልስ እንዲሰጠው ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ የሆኑና ጉዳዩ የሚያገባቸው መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት በማቅረብ ድምጹን ከፍ አድርጎ በማሰማት ላይ ይገኛል።
ይሁን እንጅ ሕገ-መንግሥቱን ተገን አድርገው የሕዝቡን ጥያቄ እንዲያቀርቡ የተወከሉ ወንድሞቻችን ይህን ጥያቄ ለምን አነሳችሁ ተብለው በእሥራት ላይ ይገኛሉ። የተያዙበት ምክንያት አግባብ የሌለው በመሆኑ ለፍርድ ቤት ጉዳዩ ቀርቦ ፍርድ ቤቱ በነፃ ቢያሰናብታቸውም ልዩ ልዩ ምክንያቶችን በመፍጠር በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ተደርጓል።ስለዚህ ወንድሞቻችን በአስቸኳይ እንዲፈቱና ያቀረብነው ጥያቄም አግባብ ያለውና የማንነት ጥያቄ ስለሆነ በሕገ-መንግሥቱ የሠፈረው ደንብ ስለሚፈቅድ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህን ጉዳይ አትኩሮት እንዲያደርግበትና በውል እንዲያጠናው በትህትና እንገልጽሳለን።
እኛ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆችም ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኮሚቴያችን የእኛን ሁለገብ ድጋፍ እንዲያገኝ በማለት መጀመርያ በዚህ ዓመት በጥር ወር የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች የኮሉምቦስ ነዋሪዎችን ስብሰባ ጠርተን ኮሚቴ ተመርጦ የሕዝብ ፊርማ አሰባስቦ ለኤምባሲው በአካል የሰጠ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ሚያዝያ 30/2008 ዓ/ም በኮሎምቦስ ኦሃዮ የሚገኙ የጎንደር ተወላጆችን ለስብሰባ ጠርተን በስብሰባው ላይ በህዝብ ላይ የደረሱ ችግሮች እየደረሱ ያሉትንም በማንሳት በጋራ ከተወያየን በኋላ ኮሚቴው በሰው ኃይል ተጠናክሮ እንዲወጣና ኢትዮጵያ ለሚገኘው ኮሚቴ ያላሰለሰ ድጋፉን እንዲሰጥ በማለት ስብሰባው የተጠናቀቀ ሲሆን ይህ ኮሚቴም ከሕዝብ የተጣለበትን አደራ ተሸክሞ ግዳጁን ለመወጣት አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ሕጋዊ የሆነውና በሕዝብ የተመረጠው ኮሚቴ ይዞት የተነሳውን ጥያቄ አግባብ ባለውና ፍትሃዊ ምላሽ እንዲያገኝ እየሄደበት ያለውን መንገድ በጣሰና ወደ ግጭት ሊያስገባ በሚችል መልኩ በእነዚህ ከፍ ብለው በተጠቀሱት አካባቢ በሚኖር ሕዝብ ስም የሚወጡ ጹሁፎችንም ሆነ በራዲዮና በቴሌቪዥን የሚቀርቡ ዜናዎች የወልቃይት ጠገዴና የጠለምትን ሕዝብ ወይም በሰሜን አሜሪካ የሚንቀሳቀሰውን ኮሚቴ እንደማይወክል እየገለጽን በተጨማሪ በትሕትና ለማሳሰብ የምንወደው ዛሬም ነገም የመላውን አማራ ሕዝብና የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ እንዳይለየን ነው።
በዚህ ጉዳይ ዙርያ በየትኛውም ቦታ በሕዝብ ከተመረጠው ኮሚቴ ውጭ በዚህ አካባቢ ሕዝብ ስም አጀንዳ ይዞ የሚቀርብ ወገን ካለ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን ሕዝብ ወክሎ ሳይሆን ራሱን ወክሎ እንደቀረበም እንድታውቁት እያልን ስለ አካባቢው ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራችሁ ከተፈለገም የኮሚቴውን ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኮሚቴውን በማነጋገር አስፈላጊውን ግንዛቤ ማግኘት እንደሚቻል አክለን ለመግለጽ እንወዳለን።
ይህ ጉዳይ ወላጆቻችን አድዋ ላይ የተቀዳጁትን ድል ለመበቀል በቅጥረኛነት ስንቁን ሰንቆ ጠላቶቻችን የሰጡትን ትጥቅ ታጥቆ የተነሳ አገር በቀል ጣሊያን ጋር የሚካሄድ ትንቅንቅ መሆኑን በሚገባ አውቀን የተነሳንበት ስለሆነ በግር ግር የሚካሄድ ነገር ሁሉ ከትርፉ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ስኬታማ ለማድረግ እውነታውን ከመገንዘብና ከመቀበል አልፎ ሌላ ትርጉም እንዳይሰጠው መግለጽ እንወዳለን። በመጨረሻም በሰላም እየተካሄደ ያለው ፍትሃዊ የመብት ጥያቄ ተጠያቂው ወገን ህወሃትና የትግራይ ክልል አውቀው በሩን እስከሚዘጉት ድረስ በዚሁ መንገድ እንሄዳለን በሩን ከዘጉት በኋላ ግን ይህ አሁን ብዙዎች የሚፈልጉት ግጭትም ሆነ ጦርነቱ አይቀሬ ስለሆነ ያኔ እንደርስበታለን።
በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ኮሚቴ።
ምንጭ ወልቃይት