Posted on June 25, 2016 
 ለዜጐች ሰብዓዊ መብትና የኑሮ ዋስትና ደንታ የሌለው፣ነፃ የፖለቲካ እንቅስቃሴንና የሃሳብ ነፃነትን የሚያፍን አምባገነኑ የኢሕአዴግ መንግሥት ተአማኒነት የለውም!
ከመድረክና ሰማያዊ ፖርቲ የተሰጠ መግለጫ

የኢሕአዴግ መንግሥት ባለፉት 4 ወራት ውስጥ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ዞኖች የሚኖረው ሕዝብ፣ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የወልቃይትና እንደዚሁም የቅማንት ሕዝብ እና በደቡብ ክልላዊ መንግሥት የኮንሶ ሕዝብ፣ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በሕጋዊ መንገድ ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ጥያቄዎችን በማቅረባቸው የመከላከያ ሠራዊት ጭምር በማሠማራት፣ድብደባ፣ግድያና እሥራት በመፈፀም የሕዝባችንን መብቶች ገፍፎና ረግጦ ለመግዛት ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ መውሰዱ ይታወሣል፡፡ በዚህ ሂደትም ዜጐቻችን ከቀዬአቸው እንዲሰደዱ፣ንብረቶቻቸው እንዲወድሙና ለእንግሊት እንዲዳረጉ አድርጓል፡፡ ባለፉት 4 ወራት በፀጥታ ሀይሉ የተፈፀሙትን እነዚህን ኢ-ሰብዓዊና ዘግናኝ እርምጃዎች ገለልተኛ አጣሪ አካል ተቋቁሞ እንዲያጣራና የምርመራውን ውጤት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ማሕብረሰብ እንዲገለጽ መድረክና ሰማያዊ ፖርቲ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ጥያቄያቸው ኢትዮጵያ በተቀበለችው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች አግባብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይኸውም፤ ኢትዮጵያ የተቀበለችውን በዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀጽ 6/1 ላይ የተጠቀሰውን፤ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች መንግሥታት እነዚሁኑ በቃል ኪዳኑ የተረጋገጡትን መብቶች በግዛታቸው የማክበር፣የማስከበርና የሟሟላት ግዴታ እንዳለባቸው በአንቀጽ 2/1 እና 2 የተደነገገው ነው፡፡ ጥያቄአችን የኢሕፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 14 “ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰሰ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው” የሚለውን የሀገሪቱን ሕገ መንግሥተዊ ድንጋጌ ኢሕአዴግ መጣሱን ከመገንዘብ የተነሳም ነው፡፡ እንደዚሁም የኢሕአዴግ አምባገነናዉ እርምጃዎች ኢትዮጵያ የተቀበለችውን የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር አንቀጽ 20/1 “ሁሉም ሕዝቦች የራሳቸውን የፖለቲካ ዐቋም ይወሰናሉ፤ኤኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ልማታቸውን ራሳቸው በነፃነት በመረጡት ፖሊሲ መሠረት ያካሂዳሉ” የሚለውንም የጣሱ መሆናቸውን በማጤንም ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያም እነዚህን ድንጋጌዎች የተቀበለችና በሕገ መንግሥቷም ያስፈረች ሀገር እንደመሆኗ መጠን የእነዚህን ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች የማክበር፣ የማስከበርና የሟሟላት ግዴታ ተጥሎባታል፡፡ ዳሩ ግን፣በአገሪቱ ውሰጥ ባለፉት 4 ወራት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ መንግሥት በሀይል ለመደፍጠጥ የወሰደው እርምጃ አግባብነትና በሕዝብ ሕይወትና ንብረት ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ አካል ማቋቋም ከኢሕአዴግና ከመንግሥቱ የሚጠበቅ ሆኖ እያለ፣ ኢሕአዴግ ግን የማጣራቱን ሥራ ራሱ መርጦና ሹሞ ለዓላማው ማስፈፀሚያነት ባስቀመጠው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን /ኢሰመኮ/ እንዲካሄድ ማድረጉ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለሕገ-መንግሥቱ ያለውን ንቀት ከማሳየቱም በላይ የፈፀመውን ወንጀል ለመደበቅ የተወሰደ እርምጃ ከመሆን አይድንም፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ፣ የተጠቀሰው ኢሰመኮ፣የመብት ጥሰቶች የተፈፀሙት በሰማን ጐንደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በ19 ዞኖች በሚገኙ 178 ወረዳዎችና በሌሎችም አካባቢዎች ሕዝቦች ላይ ሆኖ እያለ፣ ምርመራ ተብዬው ግን የተካሄደው በሰማን ጐንደርና በኦሮሚያ ክልል፣ለዚያውም በአራት ዞኖች ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ይህም የኢሰመኮ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የማጣራት ሥራ የማስመሰል እንቅስቃሴ ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ መድረክ ባለው መረጃ መሠረት በሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ምክንያት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ብቻ የተገደሉት ዜጐች ብዛት፣ ሁለት መቶ ዘጠና ሁለት /292/ በስም ተለይተው የሚታወቁና ማንነታቸው ያልታወቀ 41/ አርባ አንድ/ ዜጐች በድምሩ ከሶስት መቶ ሰላሣ ሦስት /333/ በላይ ሆኖ እያለ እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች የሟቾች ቁጥር 400 እንደ ደረሰ መዘገባቸው እየታወቀ ፣ኢሰመኮ ግን ባለፈው ሣምንት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ የሟቾችን ቁጥር በእጥፍ ያህል አሳንሶ ወደ 173 /አንድ መቶ ሰባ ሦስት/ ከማውረዱ በተጨማሪ ይባስ ብሎ፣በሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ወቅት የነበረውን የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሃይል አጠቃቀም ሁኔታ አስመልክቶ በሰጠው ብይንም፣ የፀጥታ ሃይሎች የወሰዱት እርምጃ “አስፈላጊና ተመጣጣኝ ነው” ብሎታል፡፡ ይህ ብያኔው ኢሕአዴግንና መንግሥቱን እንዲሁም ጭፍጨፋውን የፈፀመውን የፀጥታ ሃይል ከተጠያቂነት ነፃ ለማደረግ የተወጠነ ተግባር እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ ስለሆነም፣ኢሰመኮ ባለፉት 4 ወራት ውስጥ በሀገራችን የተከሰቱትን ሰብዓዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ቀውሶች አስመልክቶ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረበው ሪፖርት ተአማንነትና ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

በመሆኑም፣ ባለፉት 4 ወራት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በሙሉና በሌሎች አካባቢዎች ሕዝቦች ላይ የተፈፀሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የንብረት ውድመቶች እንደዚሁም የፀጥታ ሃይሎች የሃይል አጠቃቀም ሁኔታ በገለልተኛ አጣሪ አካል ተጣርቶ ውጤቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ማሕበረሰብ በይፋ እንዲገለጽ መድረክና ሰማያዊ ፖርቲ በድጋሚ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡ በጠቃላይም በሕገ ወጥ አግባብ ታስረው የሚገኙ አባሎቻችንና ደጋፈዎቻችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም አበክረን እናሳስባለን፡፡

ከዚህ ሌላ፣ ከ4 ወራት በፊት በተነሣው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ምክንያትና ሃሳብን በነፃ ለመግለጽ ባደረጉዋቸው ጥረቶች ምክንያት የታሠሩ የመድረክና ሰማያዊ ፖርቲ አመራሮችና ታጋዮችን እንደዚሁም ጋዜጦኞችንና ጦማሪያንን በየማረሚያ ቤቶቹ ከሌሎች ታሳሪዎች እየለዩ በጨለማ ቤት በኢሰብዓዊ ሁኔታ እያሠሩ የማሰቃየቱ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡

እንደዚሁም በሐዲያ ዞን በጐምበራ ወረዳና በጃጁራ ከተማ በሶሮ ወረዳ የመድረክን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከፍተው የሚንቀሳቅሱትን ታጋዮች የጽ/ቤቶቻችውን ንብረቶች በመዝረፍና ቤት ያከራዩትንም ባለንብረቶች ጭምር አስሮ በማሰቃየትና ከዚያም አልፈው፣በሕገወጥነት ከዐቅም በላይ የሆነ ገንዘብ በዋስትና እንዲያስይዙ በማስገደድና ቅ/ጽ/ቤቶቾችን መዝጋታቸውን እየኮነንን፣ ይህም ኢ-ሕገመንግሥታዊ ዕኩይ እርምጃቸው በአስቸኳይ እንዲቆም አበክረን እንጠይቃለን፡፡
በሌላ በኩልም ሰሞኑን “ህገ ወጥ” ግንባታዎች ናቸው ተብለው በተለያዩ አካባቢዎች የዜጐችን መኖሪያ ቤቶች የማፍረስ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ በምርጫ የተሳተፉና ገዢውን ፖርቲ ይቃወማሉ የተባሉት የመድረክና የሰማያዊ ፖርቲ አባላትም የዘመቻው ሰለባ ሆነዋል፡፡ ለአብነት ያህል በጂማ ዞን በሰርቦ ከተማ የአባሎቻችንና የደጋፊዎቻችን ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ ይኸው የዜጐችን መጠለያ ቤቶች የማፍረሱ ዘመቻ በአዲስ አበባም ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ በሳሪስና በቦሌ ቡልቡላ ወረገኑ በተባለ አካባቢ ወደ 2000 የሚጠጉ ቤቶች እንደፈረሱ ሲነገር አፈጻፁሙን በመወቃም በተፈጠረው ግጭት ሰባት ወንዶችና ሶስት ሴቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውና ቤተሰቦቻቸውም መበተናቸውን ጉዳት የደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪ የነበሩት ይናገራሉ፡፡

እነዚህ “በሕገ ወጥነት” ቤት ገንብተዋል የተባሉት ዜጐች፣ ቤት መሥሪያ ቦታ የማግኘት መብታቸውን ለመጠቀም በሚመለከታቸው መንግሥተዊ መ/ቤቶች ለረጅም ዓመታት ሲንከራተቱ ቆይተው ተስፋ ቆርጠው በቀድሞ የመሬት ባለይዞታዎች የተሠሩትን ደሳሳ ጉጆዎች በመግዛት፣ለኑሯቸው በሚመች መልኩ ሠርተው፣ መብራትና ውሃ እስከ ማስገባት የደረሱ ሁሉ ያሉበትና ግብር እየገበሩ ከአምስት ዓመታት በላይ በቦታው ላይ የኖሩ ሁሉ እንዳሉበት ታውቋል፡፡ መሬት የሕዝብና የመንግሥት እንደመሆኑ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ሁሉም የከተማ ነዋሪ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ /መሬት/ በነፃ ባገኘበት ሀገር እነዚህ ዜጐች ከአምስት ዓመታት በፊት በሠሩዋቸው ቤቶች መኖራቸው እንደከባድ ወንጀል ተቆጥሮ ግምት ሳይከፈላቸውና አማራጭ ሳይዘጋጅላቸው በከፍተኛ ጭካኔ ሥርዓት አልባ በሆነ ሁኔታ ቤቶቻቸውን ማፍረስ፣ ፀረ ሕዝብነት በመሆኑ መድረክና ሰማያዊ ፖርቲ እርምጃውን አጥብቀን እየኮነን፣ ድርጊቱ በአስቸኳይ እንዲገታና እስካሁን በተፈፀመባቸው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጐች መንግሥት ተገቢውን ካሣ እንዲከፍላቸውና እንዲያቋቁማቸው አበክረን እንጠይቃለን፡፡ በተመሣሣይ ሁኔታ የልማት ተነሺዎች የሚባሉ ዜጐችን ከቦታቸው ከማስነሣት ሂደት ጋር ተያይዞ፣የይዞታ ሰነድ ባለቤቶችና ሰነድ አልባ ተነሺዎች በሚል ፈሊጥ፣በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ እየተባለ በሚጠራ አካባቢ ቁጥራቸው 180 የሆነ አባወራ የቤት ባለቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ስለሌላችሁ ካሣና ምትክ ቦታ አይሰጣችሁም መባሉ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ እንደጣላቸው ታውቋል፡፡ በአ.አ. ከተማ ውስጥ እጅግ በርካታ ቤቶች ሰነድ አልባ መሆናቸው ስለሚታወቅ የይዞታ ማረጋገጫ ኖረ፣ አልኖረ ዜጐች ሜዳ ላይ መጣል ስለሌባቸው ለእነዚህም ዜጐች ችግር አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን፡፡ መንግሥት ይህንን ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል በሀገሪቱ ዜጐች ላይ መፈፀሙ ብቻ ሳይሆን የሚገርመው፣በብዙ ሚሊዮኞች የሚገመት ዜጐች ጥረው ግረው ያፈሩትን የሀገር ሀብት ማውደሙ ጭምር ነው፡፡

በመጨረሻም፣መላው ሰላም ወዳድና ዴሞክራሲ ናፋቂ ሕዝባችን፣ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በወገኖቹ ላይ እያደረሰ ያለውን በደል በመቃወም ለሕግ በላይነትና መልካም አስተዳደር በሀገራችን የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለማምጣት የተያያዘውን ሰላማዊ ትግል ከምን ጊዜውም በላይ ተግቶ እንዲቀጥልበት ጥሪ እናደርጋለን፡፡
ድል ለሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ትግላችን!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ እና
ሰማያዊፓርቲ
ሰኔ 17 ቀን 2008 ዓ/ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply