Wednesday, 29 June 2016 12:37
ኢሳያስን ማስወገድ፣
“የማናውቀው መጨረሻዎች መጀመሪያ ሊሆን ይችላል?!”
አቶ ዘሪሁን ተሾመ
የዓለም ዓቀፍ ሠላምና ደህንነት ባለሙያ
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፍልስፍና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም ዓቀፍ ሠላምና ደህንነት በተለይ በአፍሪካ ሰርተዋል። የፖለቲካ ፀሐፊና ትንታኔዎችን በማቅረብ ይታወቃሉ።
በሐምሌ 1999 ዓ.ም. ኩርኮራ የሚል ስያሜ ያለው መጸሐፍ አሳትመዋል። የመጸሐፉ ዋና ትኩረቶች የኤርትራ ጉዳይ፣ የልሂቁ ሚና፣ የማንነት ፖለቲካ በዘመናዊት ኢትዮጵያ በሚሉ ርዕሶች ላይ ነው። መጽሐፉ መግቢያ ላይ ይህ ሰፍሯል፣ “ለዓመታት ወይም ለተወሰነ ወቅት ይዘው የቆዩትን እምነት መፈተሽ ህመም አለው። ድፍረትም ይጠይቃል። ማድረግ መቻሉ ደግሞ በግለሰባዊም ሆነ በማህበረሰባዊ ደረጃ ጠቀሜታ ይኖረዋል።”
በርግጥም እውነት ብለው የተቀበሉትን ወይም ያመኑትን መፈተሽ ከባድ ነው። ከዚህ ዕሳቤ ጋር በተያያዘም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የተያዙ እምነቶችን አቋሞችን ለመፈተሸ እንዲሁም ከባድ ነው። ይኽውም፣ ምንም ጦርነት፤ ምንም ሰላም የሌለበት (“No war No peace”) ከባቢያዊ ሁኔታዎች ለረጅም ጊዜ ተይዞ የቆየ ፖለቲካዊ እምነት ወይም መርህ ወይም አቋም ነው። ይህንን የፖለቲካ እምነት ወይም አቋም ወይም መርህ ለመፈተሸ ተከታታይነት ያለው ውይይቶች፣ ክርክሮችና ቃለ ምልልሶች ማድረግ አማራጭ ሃሳቦችን ለማዳበር ይረዳል። ለዛሬም ከአቶ ዘሪሁን ተሾመ ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
ከአቶ ዘሪሁን ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ ዋና ትኩረት ያደረገባቸው ነጥቦች፣ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት እንዴት መቀየር ይቻላል? የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስጋቶቻችን ተብለው የሚጠቀሱት ምንድን ናቸው? የኢሳያስን አገዛዝ ማስወገድ ያለው ትርፍ እና ኪሳራ ምን ይመስላል? እና ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችን ያካተተ ነው፡፡ ለንባብ አመቺ ነው ባልነው መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሰንደቅ፡– እየተደመረ ከመጣው የኢትዮ-ኤርትራ ፖለቲካዊ ውጥረት መታየት ያለባቸው አማራጮች ምንድን ናቸው ይላሉ?
አቶ ዘሪሁን፡-ጥያቄው ቀላል የሚመስለውን ያህል ውስብስብ ነው። ውስብስብ የሚመስለውን ያህል ቀለል እናድርገው ከተባለ ለመልስ ያህል የሚሆን ይገኝበታል። እንደመንግስትና እንደሀገር ለመምራት ኃላፊነት እንደያዘ ፖለቲካ ፓርቲ ሆነን ስንገምተው ግን ውስብስብ አጣብቂኞች የተዋህዱበት እውነታ ነው። ይሄ እውነታ የኤርትራ ነፃነት አጋፋሪ ሆኖ በትጥቅ ትግሉ ዘመን የተጓዘው እና ለኤርትራን ነፃነት የታገለውን ያህል ድህረ ነፃነቷ ኤርትራ ምን ትመስላለች ብሎ ፍኖተ ካርታውን ሰርቶ ያልተዘጋጀ ግን ወታደራዊ የበላይነቱን ተቆናጥጦ በድንገት በግንቦት 1983 ዓ.ም.የመጣ በመሆኑ ነው።
ሰንደቅ፡– በድንገት ሲሉ ምን ለማለት ፈልገው ነው?
አቶ ዘሪሁን፡- በድንገት ስል ኤርትራ ከነገ አንፃር ታሳቢ ያላደረገ ወደስልጣን ከመጣው ፓርቲ ባሕሪና ተሞክሮ ጋር ይያያዛል። የሚያጠነጥነውም በአንድ ሰው ዙሪያ ሲሆን እሱም በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዙሪያ ነው። ይኽውም በእሱ ማንነት እምነት አስተሳሰብ ዙሪያ የተቃኘ ነው። ፕሬዝደንቱ ተቀናቃኞቻቸውን በቅድመ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አስወግደው የድህረ ነፃነቷ ኤርትራ በአፍሪካ ጂዖፖለቲካዊ ማዕቀፍ ውስጥ እና ወቅቱ እየተለወጠ ይመጣ የነበረው የአዲሱ የግሎባል ዘመን ምን መሆን አለበት ብለው ጥያቄ ያነሱትንም አብረው ውጠው የመጡበት ሒደት ነው ያለው። ይህ አንድ ማዕቀፍ ነው።
ከዚህ ውስጥ ፕሬዝደንት ኢሳያስ እና የቅርብ ሰዎቻቸው ይዘው የወጡት የኤርትራን ነፃነት በጦርነት እንዳዋለድነው የድህረ ኤርትራ ነፃነቷን እና እጣፈንታዋን አቅጣጫ በዋናነት በወታደራዊ ጡንቻ እና በወታደራዊ ጦረኝነት ላይ በተመሰረት አካሄድ እናዋልደዋለን የሚል በዘመነ ግሎባላይዜሽን ፅንሰ ሃሳብ ውስጥ ምሽገኛ ብሔርተኝነት (defensive nationalism) ሁሉንም በጠላትነት አድርጎ ኤርትራን ከሁሉም የተለየችና የተነጠለች ነች። ለዚህም የበቃችሁ በጡንቻዋ ነው ብሎ የሚያስብ በአመዛኙ ወደ ዘረኝነት ጥላቻ ለመጋባት የቀረበ የብሔርተኝነት ዕሳቤ ላይ ተመስርቶ የተቃኘ ነው።
ሰንደቅ፡– ይህንን የጦረኝነት አመለካከቱት የሚገልጽ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻል ይሆን? የኢትዮጵያ እና የኤርትራን ግንኙነትንስ እንዴት መቀየር ይቻላል?
አቶ ዘሪሁን፡- በመጽሐፌ ላይ እንደጠቀስኩት፣ እስከ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ድረስ የሚሄድ የኢኮኖሚ የበላይነትን የኢሳያሱ በድህረ ኤርትራ ሲያቅድ ያንን ያቀደው ለማሳካት የስኳር ንግድ አስፋፍቼ፣ ነዳጅ አውጥቼ፣ እርሻዎች አስፋፍቼ ወይም ኤርትራ የታደለችውን የባሕር ሃብት አበልጽጌ ብሎ ሳይሆን በሳህል በርሃ ከፈፍ ውስጥ ተቀምጦ የነበረው ሰራዊቴ የምርት መሣሪያ እና የኢንቨስትመንት ካፒታሌ ሆኖ እሔዳለው ብሎ የሄደበት ሂደት ነው።
የዚህ ውጤት ደግሞ ጅቡቲን ኢትዮጵያን ሱዳንን ቀይ ባሕርን ተሻግሮም የመንን የነካካ ነው። ይህንን የባሰ የሚያደርገው ይህንን መሰል አስተሳሰብ ብቅ ያለበት ዓለማችን በአንድ በኩል ሉላዊነት የምንለው የበላይ ዕሳቢያዊ ማዕቀፍ እየሆነ የሀገራት እና የመንግስታት የአለማችን ሒደት ሆኖ በአመዛኙ ካፒታሊስት ተከል የሆነ የዓለማችን ርዕዮተዓለም ቅኝት የበላይ የሆነበት እሱንም ተገዳዳሪ የሆኑት የሚሞግቱ አማራጮች በቻይና በብራዚል ወይም ብሪክስ ተብለው የሚጠሩ በሌላ በኩል ይህንን ሉላዊነት ከባቢያዊ ተከል ወይም ብሔርተኛ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ፈተና እየያዘ የመጣበት መሆኑ ነበር።
በእነዚህ ሙግቶች መካከል አማራጭ ርዕዮተዓለሞች አንሰው የመጡበት የኒዮ እና የሊብራል ርዕዮተ ዓለማዊ አሸናፊ ሆኜ ወጣሁ ያለውን ያህል እነፎኪያማ “The end of History” ያሉት የታሪክ መጨረሻ የካፒታሊዝም ድምዳሜ ያሉትን ያላሳየበት ሊያሳይም ያልቻለበት በመሆኑም፤ በተፈጠረ ዕሳቤያዊና ርዕዮተዓለማዊ ክፍተቶችን በተለያየ መንገድ የሚገለጽ አክራሪነቶች በዋናነት ደግሞ ሐይማኖታዊ ጠቀስ አክራሪነት የርዕዮተዓለማዊውን ክፍተቶች እየሞላ የመጣበት፤ ይሄንን ርዕዮተዓለም ታጥቆ አካባቢያዊ የማሕበረሰብ ግንኙነቶችን እንቀርፃለን የሚሉ እነአልቃይዳ ዛሬ ላይ ደግሞ አይ.ኤስ.አይ.ኤስ በአካባቢያችን ካየኸው አልሸባብን ኢስላሚክ ጀሃድ እና ሌሎች የመሳሰሉት ብቅ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው፤ የእነኢሳያስ ጥያቄ የሚመጣው። ለዚህም ነው፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትን እንዴት እንቀይረው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ይሄንን ዓለማቀፋዊና አህጉራዊ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ይጠይቃል። ምክንያቱም ከዚህ ተነጥለን የወጣን አይደለንም።
ሰንደቅ፡– ካስቀመጡት ትንታኔ አንፃር የአጭር ጊዜ ሥጋቶች ተብለው የሚቀመጡት የትኞቹ ናቸው?
አቶ ዘሪሁን፡- በፖለቲካ ስትራቴጂክ ነገሮችን ስትነድፍ የምትፈልገውን የምታስቀምጠውን ያህል የምትፈልገው እውን ሊሆን የሚችልበትን እና ያለህን አቅም አንድ ማገናዘብ የአጭር ጊዜ ትርፍና ኪሳራውን ከስትራቴጂክ ጥቅም ትርፍና ኪሳራው ጋር እንዴት ይመጋገቡልኛል? የአጭር ጊዜ ጉዳቴን ዋጥ አድርጌ የረጅም ጊዜውን የመውሰዱ ዋጋ የቀነሰ ነው ወይ ብለህ ትመርጣለህ።
በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ስንመጣ የአጭር ጊዜ ተገቢ ስጋቶቻችን የምንላቸው በተለያየ አጋጣሚ በወታደራዊ አቅሙ በቀጥታ ወረራ የማካሔድ ጥርሱ የበፊቱ አይነት ስለት የሌለው ሻዕቢያ ይህንን ሊተኩለት የሚችሉና ሊያዘምታቸው የሚችሉ የተለያዩ ኃይሎች እንዲሁም እሱ እንደሥርዓት ከምዕራባዊ ኤርትራ በሚገርም ጭካኔ ገና ሳያቆጠቁጡ የመታቸው አሁን ላይ ግን እንደገና ሊያቆጠቁጡ ቢሉ በተወሰነ ደረጃ አላየዋችሁም የሚላቸው ምክንያቱም ለራሱ ዋስትና አድርጎ የሚመለከታቸው ኃይሎችንም ይጨምራል። ይህም ሲባል፣ እኔ ከሌለው የሚገጥማችሁ እነዚህ ናቸው የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ያልተለመደ ምህረቱን የቸራቸው አደገኛ ኃይሎች ናቸው።
የአስመራ ቴሌቪዥንን ብንወስደው ተዋፅፆ ምን እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ ግብፅ ከሙባረክ በኋላ የገባችበትን ሁኔታዎችን የሚያሳዩ እንዲሁም የሶሪያን ፖለቲካዊ ቀውሶች የሚዳስሱ ናቸው። ይህ አንዱ የኤርትራ መንግስት አካሄድ ነው። አልሸባብ ግንቦት ሰባት እና ሌሎችንም በመጠቀም የማስተንፈሻ ስልት አድርጎ ለአጭር ጊዜ የሚጠቀምባቸው ናቸው። ይህም የአጭር ጊዜ ስጋታችን ነው።
ሰንደቅ፡– ከስትራቴጂካዊ ፍላጐቶች አንፃር ያሉትስ ስጋቶች ምንድን ናቸው?
አቶ ዘሪሁን፡- ይህ ጥያቄ የሚቀርበው ለገዢው ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን ማንም ነገ ይህንን መንበረ ስርዓት ተርክቦ ምክንያቱም ጂኦግራፊ ስለማይቀየር ይህንን ሁኔታዎችን ማኔጅ አድርጎ አመራር ሰጥቶ ይዞ መሔድ ያለበት ፓርቲ ስትራቴጂካዊ ፍላጐቶቻችን ምንድን ናቸው የሚለውን ማየት ይጠበቅበታል። ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶቻችንን ምንድን ነው? በአንድ በኩል የዘወትር ጦርነትም አንፈልግም። በሌላ መልኩም ምንም ጦርነት ምንም ሰላም የሚለውን ሁኔታም አንፈልግም። የሁላችንም ስትራቴጂካዊ ጥቅማችን ሊከበር የሚችለው፤ ዛሬ ላይ የፈጠርነውን አቅም ቆም ብለህ ካየኽው ከጦርነት ሽክርክሪት እረሳችን አርቀን እልሃችንን ንዴታችንን ዋጥ አድርገን ልንቆጥበው በቻልነው ጥሪት ነው። እንዲሁም ከሞት ከተረፉ ልጆቻችን ጭምር ነው። ስለዚህም ጠንካራነት እየዘለሉ ማንንም መምታት የሚችል ጦር ሰራዊትና መከላከያ ባለቤት መሆን አይደለም። ማንም ዘሎ ቢፈልግም እንዳይነካህ የሚያደርግ ቁመናን መላበስ ነው። ይህንን ቁመና መላበስ የሚቻለው ኢኮኖሚያዊ አቅም መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው። ፖለቲካዊ መደላደልህ የተመቻቸ ሲሆን ነው።
ስለሆነም መጠየቅ ያለብን አንድ መሰረታዊ ጥያቄ የኤርትራን ጉዳይ ስናነሳ፤ ኢሳያስን ዛሬ ላይ ማስወገድ ከማቆየቱ ጋር ሲነጻጸር እዳው የከፋ ነው ያልከፋ ነው የሚለውን መጠየቅ ነው። እኔ እንደዘሪሁን በአንድ በኩል ተግዳሮታችን የአጭር ጊዜ ስጋት ነው። በሌላ መልኩ ትግራይን እንደ ክልል ወስደን ካየነው፤ በድንበሩ አካባቢ ትልቅ ንግድ እና እንቅስቃሴዎች የነበረበት ነው። ይህ ንግድ እና እንቅስቃሴ በአካባቢዎቹ ማሕበረሰብ የሚካሔድ ቤተሰባዊ ባሕላዊ ቁርኝታዊ ትተኽው በኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ብታየው ብዙ ጉሮሮዎችን የደገፈ ሒደት ነበር። ለብዙ ሰዎች የሥራ እድል የፈጠረ ነበር። ዛሬ ይህ የለም። ተጨማሪ የሥራ እድሎች መፍጠር የሚችሉ ኢንቨስተሮች አለመረጋጋትን አይመርጡም። ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ሊገመት የሚችል ፖለቲካዊ መረጋጋት ወታደራዊና ደህንነታዊ መረጋጋት ያለበትን አካባቢ ይመርጣሉ። በዚህ ረገድ የአጭር ጊዜ ስስ ብልታችን ነው። ዝም ብሎም እንዲሽከረከር ከፈቀድንለት እኛም ላይ የሚያሳርፈው ተፅዕኖ አለ።
ሰንደቅ፡– የገለጹት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከረጅም ጊዜ ፍላጎቶች አንፃር እንዴት ማስቀመጥ ይቻላል?
አቶ ዘሪሁን፡- ከረጅም ጊዜ አንፃር ከወሰድነው፤ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶቻችንን ሊያዛባ የሚችል በኢሳያስ የሚገፉም ሆነ በኢሳያስ ሊገፉ የማይችሉም ሒደቶች አሉ። አንደኛው፣ ዛሬ ላይ አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. ከኢራቅ ከፋሉጃ ነገ ከሞሱል እየወጣ ነው። እንዲሁም ከሶሪያ እየወጣ ነው። ጦራችንን አሰማርተን ለራሳችን ደህንነት ስንል እንዲሁም ለጎረቤታችን ሶማሊያ ደህንነት ሳይቃጠል በቅጠል ብለን መድረስ ካለብን አሁን ነው ብለን በገባንበት ሒደት ትኩረታችን ያደረግንበት አልሸባብ ለአይ.ኤስ.አይ.ኤስ. ታማኝነቱን የሰጠ ድርጅት ነው። እዚህ ውስጥ ኢሳያስ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የሚያደርጋቸው ትብብሮችና እንቅስቃሴዎች በአንድ በኩል አሉ።
አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. በራሱ የሚያደርጋቸውም አሉ። ለምሳሌ ሊቢያ ከሶስት ዓመታት በፊት የነበረችው ሊቢያ አይደለችም። መሐመድ ጋዳፊን መገላገል ከመሐመድ ጋዳፊ የተሻለ ዋጋ ለሊቢያዊን የማያስከፍል ነገር አመጣ ወይ? አላመጣም። በርግጥ ዛሬ ላይ ሰርጥ መሐመድ ጋዳፊ ለአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ ተነስቶ መቀመጫ እንድትሆን የገነቧት ከተማና ቦታ፣ ዛሬ ላይ አይ.ኤስ.አይ.ኤስ. ዋናዋና ኮማንደሮች አዲስ ቤዝ ተደርጋ ሌላ የውጊያ ቀጠና ሆናለች። ስለሆነም በአፍሪካ ቀንድ አልሸባብን በአንድ በኩል ይዘህ በሌላ በኩል እነዚህን የአጭር ጊዜ ስስ ብልቶቻችን ወታደራዊ የበላይነታችን ጠብቀን ሌላ ኢኮኖሚያዊ ማረጋጊያና ማላሻ መንገዶችን ድንበር ላይ ላሉ ዜጎቻችን ለትግራይ እና ለአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎችን እየሰጠን የመሔዱ ዋጋ ይሻላል? ወይንስ ይህን አይነት ቀመር ባለበት የተደራጀ ውህድ የፖለቲካ ክፍል በሌለበት ቢያንስ ደግሞ ውህድ እንኳን ባይሆን ግልፅ ራዕይ ያለው በተከፋፈለ ደረጃ ቀጣይዋ ኤርትራ ምን ትምሰል የሚለውን ጠበንጃ በመማዘዝ ባሕል ተሞክሮ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል ተሞክሮ ሊያካሂድ የሚችል ፖለቲከኛ በሌለበት፣ የምዕራብ ኤርትራ ጉዳይ በአመዛኙ ለአክራሪ እስላማዊያን እንቅስቃሴ ክፍት ሆኖ ኢሳያስም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ፍልስፍናው ሊያጠፋቸው እየቻለም ሊያደርቃቸው እየቻለም ያላደረቃቸው፣ ሊያደርቃቸው ቢፈልግም ማድረቅ ያልቻላቸው የእነዚህ ኃይሎች ባሉበት እንዲሁም በእነሱ ውስጥ ወጥነት በሌለበት አይነት ኢራቅ ሶሪያ ላይ እንደምናየው ለብዙ ቦታዎች ተከፋፍለው ባሉበት ሁኔታ ኢሳያስን ወታደራዊ አቅሙ ስላለን ብንነካው ምንድን ነው ትርፋችን? በምስራቅ በኩል የገጠመችን ሶማሊያን በሰሜን በኩል መድገምን ቢሆን የምንሸከመው ነገር ነው ወይ?ግድግዳ ልንሰራ አንችልም። አጥር ልንሰራም አንችልም።
ይህንን እንደዚህ አስቀምጠህ ደግሞ ባልተናነሰ መልኩ የሚመጣው የሺዓ እና ሱኒ ፉክክር በኢራን እና በሳዑዲ ዓረቢያ ዙሪያ በተሰባሰቡት በእነኩዌት አረብ ኤምሬት፣ ኳታር የመሳሰሉት ባሉበት እና እየተገፋ ያለው የአረቢያን ሰላጤ ፉክክሩ የከፋ ቢሆን እና አማራጭ ቢጠፋ የቀይባህርን የአረብ ባሕር የማድረግ እንቅስቃሴ የሚመስል በኢንቨስትመንት ከመግባት ባለፈ ወታደራዊ እግርን የኤርትራ ቀጠናዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ እነአሰብን የመሳሰሉ ቦታዎች የማስገባቱን ስሌት ስታመጣ ምን አይነት ዝግጁነትን መጠበቅ አለብን? ከዚህ ዝግጁነት እኛ የምንፈልገው አካሄድ እስከሚመጣ ድረስ ምን አይነት ሥራዎች መስራት አለብን?
እዚህ ላይ ጥሩ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ይኸውም አሜሪካ ኢራቅን አሁን ላለችበት ሁኔታ ያበቃቻት በወታደራዊ መስክ ድል ማድረግ አቅቷት አይደለም። አሜሪካ በወታደራዊ ሜዳ መስክ በጦርነት ኢራቅን አሸንፋለች። ኢራቅን ግን መቆጣጠር አልቻለችም። ምክንያቱም የኢራቅን መልሶ ግንባታ ብሔራዊ ፕሮጀክትን እንደ አንድ የውጪ ሁለተኛ ኃይል እሷ መሪና ዘዋሪ ሆና ማካሔድ አትችልም። የኢራቁ የአሜሪካ ውድቀት ትምህርት ይህ ነው። ልዕለ ኃያሏ አሜሪካ በትሪሊዮን ዶላር አፍስሳ የኢራቅያዊያን የሳዳም ጥላቻን ወደ አሜሪካዊያን ፍቅር መገልበጥ አልቻለችም። እነ አርዛቃዊን ማስቆም አልቻለችም። ስለሆነም ከዚህ አንፃር የኤርትራን ጉዳይ ብናየው ኢሳያስን ማስወገዱ ቀላሉ ስራ ሊሆን ይችላል። ኢሳያስን ማስወገድ ግን የመጨረሻ ሳይሆን፣ የማናውቀው መጨረሻዎች መጀመሪያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ስሌታችን ላይ ይህንንም ማጣጣም ያስፈልጋል።
ሰንደቅ፡– በኤርትራ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ክፍት መሙላት የማን ድርሻ ነው? የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የግድ በኤርትራ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ክፍተቶቹ መሞላት አለባቸው የሚለውን ዕሳቤ እስከመቼ ድረስ አዋጪ ሆኖ ይቀጥላል?
አቶ ዘሪሁን፡- በዋናነት ኤርትራዊያን ናቸው። እነዚህን ኃይሎች ማገዝ ግን የማናፍርበት ብሔራዊ ጥቅማችን ነው መሆን ያለበት፣ የማንደብቀው። ሌላኛው አሁን እየመጣ ያለው ተጨማሪ ፖለቲካ ከብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ አካሔድ ቢሆንም ኢሳያስ አፈወርቂን በዲፕሎማሲያዊ ጫና ዞር የማድረግ ድርጊቶች ናቸው። ይህንን ልንጫወትበት የምንችለው ርቀት ረጅም አይደለም። የተወሰነ ደረጃ ድረስ ነው የሚሄደው፤ ምክንያቱም ኢሳያስ በቀላሉ መላመድ የሚችል ሰው በመሆኑ ሊቀበለው ይችላል። ይህ ግን የሞራል የበላይነት ነው። ዲፕሎማሲያዊ መድረኩን የሚያመቻቹ ምናልባትም ኤርትራ ኢሳያስ ካለ መኖር የምትችል አቅም እድልም ያላት የሚለውን ስዕል ለአብዛኛው ኤርትራዊ ማሳያ ነው የሚሆነው። ከዚህ ምሽገኛ ብሔርተኝነት ወጥተህ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛ ሀገር ሆነህ ከጐረቤት ሀገሮች ጋር የመኖር የተሻለ እድልህ የሰፋ ነው የሚለውን ሊያዩበት የሚችል የመሰባሰቢያ መድረክ ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህም በዋናነት ጉዳዩ የኤርትራዊያን ቢሆንም ባልተናነሰ መልኩ ደግሞ የጐረቤት ሀገሮችም ሥራ ነው።
እስከመቼ ድረስ አዋጪ ነው ለተባለው በፖለቲካ ትንታኔዎች ውስጥ በዚህ ቀን በዚህ ጊዜ ብሎ ማስቀመጥ ከባድ ነው። ወይም ከፖለቲካው ሳይንስ ወደ ጥንቆላው ዘመም ያለ የሚመልሰው ነው የሚሆነው። ማድረግ የሚቻለው በየጊዜው ባሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች መነሻ የተለያዩ ሴናሪዎችን በማስቀመጥ መፈተሸ ብቻ ነው። የዛሬው የኢትዮጵያ መንግስትና በአጭር ጊዜ እንተካዋለን የሚሉትም ማሰብ ያለባቸው የመጀመሪያ ሴናሪዮ፣ የአፍሪካ ቀንድ፣ የቀይ ባሕር አካባቢ፣ የመካከለኛውም ምስራቅ እና የዓለማችን ሁኔታዎች ይህንን ከሆኑ ምን አይነት ተግዳሮቶች እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችን አንድነታችን ቀጣይነታችን የሚጎዱ ስጋቶችን ሊፈጥሩ ይችላሉ? እነዚህን ስጋቶች ከወዲሁ በምን በምን አይነት ምስሎች ልንለያቸው እንችላለን? ምን ስናይ ምን ይገልጽልናል? ሲናሪዮ ሁለት፣ የኤርትራ መንግስት እኛ ከምንለው ውጪ የኤርትራ ኃይሎች ባልተደራጁበት ሁኔታ በራሱ ውስጣዊ ዳይናሚክስ ቢፈርስ ግን ደግሞ ከአፍራሾቹ የተረጋጋ ሁኔታ ለመፍጠር የሚችል ፖለቲከኛ በሌለበት ሁኔታ ቢከሰት ምንድን ነው የምናደርገው? እዚህ ውስጥ በአመዛኙ የሱኒ መር በሆነው የሳዑዲ አረቢያ እና የሌሎቹ ቢሆን ምንድን ነው የምናደርገው? እና ሌሎች ሁኔታዎችንም ከግምት ወስዶ በየጊዜው እየተዘጋጁ መሄድን ይጠይቃል። ስለዚህም ከእርምጃ በፊት ለሁሉ ነገር የሚመጥን እርምጃ የያዙ ዝግጁነቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተገቢ ነው።
ሰንደቅ፡– ኢሳያስ ከደቀነው አደጋ እኩል የመልካም አስተዳደር ችግሮች እና የአክራሪ ሐይማኖት አራማጅ ኃይሎች በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከተራ አባልነት እስከ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ድረስ እንደሰረጉ በስፋት ይታመናል። ይህን መሰል ፖለቲካዊ ቁመና የተላበሰ ሥርዓተ መንግስት ወደጦርነት በአንድ ልብ የመንቀሳቀሱ ጉዳይ እንዴት ይታያል?
አቶ ዘሪሁን፡- ዛሬ ላይ ባለን ቁመና ከኤርትራ መንግስት ጋር እምብዛም ብዙ ዝግጅት ሳናደርግ በየትኛውም ሁኔታ ብንገጥም የሚያቅተን ነገር አይኖርም።
ሆኖም ጦርነትን ማሸነፍ ከተወሰኑ የጦር ሜዳዎች ድል ባሻገር መሔድ አለበት። ያ ግልፅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ አከርካሪ የሚጠይቀውን ያህል ፖለቲካዊ ውህድነት እና ፖለቲካዊ ተደማጭነትን ይጠይቃል። ቀደም ላለው ጥያቄ ስመልስልህ በጨዋ ግን በደፋር ፖለቲካዊ እርምጃ የዛሬው ገዢ ፓርቲ በመልካም አስተዳደር እና በሙስና ይህንን ማላሻ ሆነው መጋቢም ተመጋቢም የሚሆኑ አክራሪያዊ አካሄዶችን ከወዲሁ መቅጨት ያለበት ከበደን ስለጠላ ነው ታደሰን ስለጠላ ነው ይህንን ፓርቲ በተንሸዋረረ መልኩ ስለምናየው ነው ከሚል ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ዋነኛ ምሶሶሰ የሆነውን ህላዊያቸውን የማስቀጠል ያለማስቀጠል የነገን እድልን ዛሬ ላይ ያረገዘና የተሸከመ በመሆኑ ነው።
ስለሆነም እያንዳንዱ ተሞክሮዎቻችን ተድበስብሰው የሚታለፍበት ሳይሆን ለምን? እንዴት? ምን ስለሆንን? በሚለው መልኩ መፈተሽ አለባት። ከዛሬ አርባ እና ሃምሳ ዓመታት በፊት ከነበረችው ኢትዮጵያ የተሻለ ዕሳቤ የታጠቅንበት ዕይታ ውስጥ ነን። የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሴራ ነው የሚለው ያረጀ ሆኖም በተወሰነ ደረጃ ልክ ከሆነ ትንታኔም ተላቀናል። ዋነኛው የብርታታችን የብሔራዊ ደህንነታችንም አደጋ ምንጭ ውስጣችን ነው ያለው ስንል፣ የፈለገውን ወታደራዊ አቅም ብንገነባም እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጎጆ የብሔራዊ መረጃ ጽ/ቤት ጆሮ የመከላከያችን ምሽግ እስካልሆነ ድረስ በታሪክ ካየናቸው እጣፈንታ የተለየ አይገጥመንም።
ስለሆነም የዛሬ የፖለቲካ ሊሂቅ በገዢነት ላይ ያለው በተወሰኑ ጉዳዮች ዙሪያ ዳተኝነት ቢያሳይም ይህንን የማየት የማያስችለው የፖለቲካ ድህነት አለበት ብዬ አላምንም። አለማመኑንም እመርጣለሁ። ይህንን ግን እንዳልሆነ የሚያሳዩን ነገሮች ካሉ የወላድ መካን አይደለንም እና ብዙ አማራጮች በእጃችን አሉ። ኢሕአዴግን ሁሉንም ባይሆን የተወሰኑትን እረፍት ሰጥተናቸው የቤት ስራዎቻቸውን እንዲሰሩ አድርገን እነዚህን የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶቻችንን የምንቆጣጠርበት እድል አናሳ ነው ብዬ አላምንም።
ስንደቅ