Wednesday, 29 June 2016 12:35
ማብቂያ ያጣው የኤርትራዊያን ሰቆቃ
በመዋዕለ ንዋይ ብልጽግና፣ በህዝቦች አስተዳደር (ዴሞክራሲ)፣ በሰላምና መረጋጋት፣ እንዲሁም በፍትሃዊ የፍርድ ስርዓትና የሀብት ክፍፍል እጦት ከሚቸገሩ የዓለማችን ዜጎች መካከል ቅድሚያውን የሚይዙት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዜጎች ናቸው ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም። ለ44 ዓመታት ከፊውዳሉ የአጼ ኃይለስላሴ አስተዳደር በኋላ ለ17 ዓመታት በወታደራዊ የደርግ መንግስት ስር የቆየችው ኢትዮጵያ ላለፉት 25 ዓመታት ደግሞ በሌላ አብዮታዊ አምባገነን መንግስት ስር ትገኛለች። ለ30 ዓመታት በአንድ አምባገነን መሪ ስር የምትገኘዋ ሱዳንም ሆነች ረጅም ጊዜ ከወሰደ የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ራሷን ከሱዳን ገንጥላ “ነጻነት አገኘሁ” ያለችው ደቡብ ሱዳን መገኛዋ እዚሁ ምስራቅ አፍሪካ ነው። ዴሞክራሲ ሲያልፍ የማይነካቸው የሚባሉት እንደ ጅቡቲ እና ኬኒያም ሆነ መረጋጋት የተሳናት ሶማሊያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ አገራት ናቸው።
ከላይ ከተጠቀሱት አገራት በባሰ መልኩ ፍጹም አምባገነን መንግስትን አቅፋ የያዘችው አገር ደግሞ ኤርትራ ነች። “የአፍሪካ ሲንጋፖር እንሆናለን” ሲሉ የማይጨበጥ ተስፋ ለዜጎቻቸው ቃል የገቡት ምስራቅ አፍሪካዊው አምባገነን መሪ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን አገራቸው በኢኮኖሚ እድገት ሲንጋፖር ሳይሆን Single poor (የተረሳች እና የተገለለች ድሃ) አገር ወደ መሆን እየተሸጋገረች ስትሆን ዜጎቿም እግራቸው ወደመራቸው የዓለማችን ክፍል ከመሰደድ ወደኋላ አይሉም። እነዚህ “ብኩናን” ዜጎች እግራቸው ወደመራቸው የዓለማችን ክፍል ሲሰደዱ የሚያርፉባቸው አገራት መንግስታትም ሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኤርትራዊያኑ ልዩ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዜጎቹ አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ወይም ከኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ወደ ተሻለ ማንኛውም የአፍሪካ አገር ሲሰደዱ ገና ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ መድረሻቸው ድረስ የሚገጥማቸው ፈተና ቃላት ከሚገልጹት በላይ በመሆኑ ነው። ይህን የተመለከቱት ዓለም አቀፍ ተቋማትም ማንኛውንም ጠይም የቆዳ ቀለም ያለው ስደተኛ ሲያገኙ ከየት እንደመጣ ከጠየቁት በኋላ “ከኤርትራ ነው” ብሎ ከመለሰላቸው በቀላሉ የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኝ ያደርጋሉ። ይህ የሆነው በኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ምክንያት ነው።
ሰሞኑን የዓለም አቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት የኤርትራን መሬት “ህያዋን ፍዳቸውን በመሬት የሚከፍሉባት አገር” ሲል ገልጿታል። በአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ህልውና እንዳይኖር በመደረጉ ምክንያት አገሪቱ ከኤርትራ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ሻዕበያ) በስተቀር ሌላ ፓርቲ የላትም። የመገናኛ ብዙሃን ህልውናም በገዥው ኢሳያስ አፈወርቂ በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ ከመኖር አይቆጠርም። ከዚህ ሁሉ የባሰው ደግሞ በአገሪቱ በተዘረጋ የአፈና እና ጥርነፋ ስርዓት ምክንያት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የአቶ ኢሳያስ ተችዎች የገቡበት እንዳይታወቅ ተደርጓል ሲል ነው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ይፋ ያደረገው። ይህም በመሆኑ አገሪቱን “የምድር ሲኦል” ሲል ይገልጻታል።
ከዚህ ተቋም ሪፖርት በኋላ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ብኩናን ኤርትራዊያን ታዲያ የአገራቸውን መንግስት ተቃውመው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል። በአሜሪካ፣ በጀርመን እና በሌሎች አገሮች የተቃውሞ ሰልፍ ማካሄድ የቻሉት ኤርትራዊያን፤ መንግስትን ለሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በተከለከለባት ኢትዮጵያም በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ ፊት ለፊት እና በትግራይ ክልል በሚገኘው ሽመልባ የስደተኞች ጣቢያ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። እኛም የኤርተራዊያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ተከትሎ ከስደተኞቹ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
የተቃውሞው ሰልፍ ይዘት እና የሰልፈኞቹ ስሜት
ቁጥራቸው ከ150 – 200 የሚደርሱ የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ዜጎች በተለምዶ ቄራ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር “ገነት ሆቴል” በር ላይ ተሰብስበው በቡድን በቡድን እየሆኑ በተንቀሳቃሽ ካሜራዎቻቸው ፎቶ ይነሳሉ። ከጎናቸው ደግሞ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን የሚያወግዙ “በትግርኛ፣ አረብኛ እና እንግሊዝኛ” ቋንቋዎች የተጻፉ የፕላስቲክ ወረቀቶች ተከምረዋል። የፕላስቲክ ወረቀቶቹ መፈክር መሆናቸው ነው። አረብኛውን እና ትግርኛውን ማንበብ ባንችልም በእንግሊዝኛ የተጻፉት መፈክሮች “አቶ ኢሳያስ ለፍርድ ይቅረቡ፣ በኤርትራ ምድር ከዚህ በኋላ አምባገነን ስርዓት ይብቃ፣ የአፍሪካ ህብረት ጥያቄያችንን ተቀብሎ እንድንሰለፍ ስለፈቀደልን እናመሰግናለን እና ነጻነት ለኤርትራዊያን” የሚሉ ይገኙበታል።
በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ መናገር የማይችሉትና ቃለ መጠይቅ ለመስጠትም ብዙም ፈቃደኛ ያልሆኑት ኤርትራዊያኑ ቃለ መጠይቅ እንዲሰጡ ሲጠየቁ የማይፈቅዱበትን ምክንያት ሲናገሩ “እኛ እዚህ ስለ ኢሳያስ አገዛዝ ክፉ ነገር ብንናገር አገራችን የሚገኙ ቤተሰቦቻችን አደጋ ላይ ይወድቃሉ” ሲሉ ነው የሚመልሱት። ያም ሆነ ግን ስማቸው እንዳይጠቀስ ወይም ምስላቸው እንዳይወጣ ከጠየቁ በኋላ ለቃለ ምልልስ ፈቃደኛ የሆኑት አስተያየት ሰጪዎች ሲናገሩ “በዚያ ያለው (በኤርትራ) የአፈና ስርዓት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በየትኛውም አገር የሌለ የባርነት አስተዳደር ነው። ከዚያ ለማምለጥ ነው አስከፊውን የእግር ጉዞ አድርገን ለስደት የተዳረግነው” ሲሉ ይናገራሉ። አስተያየት ሰጪዎቹ አክለውም “በዚህ አጋጣሚ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ብሶታችንንና ጭቆናችንን ተመልክቶ ከጎናችን እንዲቆም ነው የምንጠይቀው። አቶ ኢሳያስ እና አስተዳደራቸው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንሻለን” ሲሉ ተናግረዋል።
የአቶ ኢሳያስ አስተዳደር እና የግል ባህሪያቸው
በአስተያየት ሰጪዎቹ አንደበት
አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በትግል ዘመናቸውም ሆነ በስልጣን መንበራቸው ላይ ከተቀመጡበት ጊዜ ጀምሮም ቢሆን ያልተለወጠው ባህሪያቸው “አምባገነንነታቸውና ፈላጭ ቆራጭነታቸው ነው” ተብለው ይታማሉ። እንዲያውም አቶ ኢሳያስ አፈወርቂም ሆነ አስተዳደራቸው ከኤርትራ ህዝብ ይልቅ ለራሳቸው የሚጨነቁ እንደሆነ በስፋት የሚነገርባቸው ሲሆን በክፉ ዐይን የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ “ጸብ ያለሽ በዳቦ” እንደሆኑ ይገልጻቸዋል። ከዚህም አለፍ ብሎ ለቀጠናው አስጊ እና አደገኛ ሀይል ነው ሲል ይተቻቸዋል።
አቶ ኢሳያስ ከላይ የተጠቀሰውን እኩይ ባህሪ የተላበሱ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡ ኤርትራዊያን ያረጋግጣሉ። ነገር ግን ከሌሎች ከብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች በተለየ መልኩ አቶ ኢሳያስ ሙስናን በመዋጋት በኩል ያወድሷቸዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ “ኢሳያስ ልጁ ያስተማረው እንደሌሎቹ የአፍሪካ መሪዎች ወደ ቻይና እና አሜሪካ ወይም ሌላ አገር ልከው ሳይሆን በአገራቸው ከሚገኝ የመንግስት ትምህርት ቤት ነው። ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላም ብሔራዊ የውትድርና ግዴታውን ከተወጣ በኋላ ነው ወደ ስራ ገብቶ የተመደበው። ይህ ደግሞ ሰውየው ሙስናን በመዋጋት በኩል የተሻሉ እንደሆነ ያሳያል። ነገር ግን ሙስናን በዚህ መልኩ ይጠየፉት እንጂ ለዜጎቻቸው በአገራቸው ተመቻችተው እንዲኖሩ እድል አልፈጠሩልንም” ሲሉ የአቶ ኢሳያስን ጉራማይሌያዊ ሰብዕና ይናገራሉ።
የቀንዱ አገራት ዜጎች ሁኔታ እና የኤርትራዊያን ሰቆቃ
በዓለም ላይ ከፍተኛ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው በመፈናቀል ግንባር ቀደም የሆኑት ሶሪያዊያን ናቸው። የመካከለኛው ምስራቅ ዜጎች ለከፍተኛ ስደት የተዳረጉት በአገራቸው የሰፈነው የለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንደሆነ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታውቋል። ከሶሪያ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የሚይዙት ደግሞ የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች በተለይም የኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ ዜጎች ናቸው።
የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች በስደት ምክንያት ቀያቸውን እንዲለቁ ምክንያታቸው የተለያዬ ቢሆንም በዋናነት ግን በአገራቸው ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እና የተሻለ ገቢ ፍለጋ እንደሆነ ይነገራል። ኤርትራዊያኑ ስደተኞች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት “የዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ያወጣውን ሪፖርት አቶ ኢሳያስ እንደማይቀበሉት ሲናገሩ ሰምተናል። አቶ ኢሳያስ ዜጎቹ የሚሰደዱት ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅትን ሪፖርት ተቃውመዋል። ነገር ግን አቶ ኢሳያስ ያልተረዱት ሰው በአገሩ ለመኖር ቢመቸው እናት አባቱን ጥሎ የሚሰደድ ይኖራል እንዴ? ማንም እኮ የተወለደበትን አገር አይጠላም። እኛም እንድንሰደድ ያደረገን በአገሪቱ ያለው መንግስት በነጻነት እንዳንሰራ ስላደረገን እንጂ የመሰደድ ፍላጎት ኖሮን ወይም እሳቸው እንደሚሉት አገራችን ካለው ኑሮ በተሻለ የገቢ ምንጭ ፍለጋ አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ።
ስደተኞቹ የአገራቸውን መንግስት አምባገነናዊ ባህሪ ሲገልጹ “አስተዳደሩ ብሔራዊ ግዴታ ማውጣቱ ክፋት የለውም (ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ አገሩን እንዲያገለግል የሚያስገድደው ስርዓት)። ነገር ግን ብሔራዊ አገልግሎቱን ከተወጣ በኋላ ሰዉ ሰርቶ መብላት አልቻለም። በበርሃ ይጣላል፣ እናት ከልጇ እንዲሁም ሚስት ከባሏ አይገናኙም። ይህ ነው የአገዛዙ ክፋት” ሲሉ ተናግረዋል።
በርካታ ኤርትራዊያን ዜጎች በኢትዮጵያ ወይም በሱዳንና በጅቡቲ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ከተሰደዱ በኋላ ከሚያገኙት ገቢ ላይ ሁለት በመቶ (2%) በኤምባሲያቸው በኩል ወደ ኤርትራ መንግስት ካዝና እንዲገባ ያደርጋሉ። በዚህ መልኩ የኤርትራን መንግስት የሚደግፉ ዜጎች ወደ አገራቸው የመግባትና የመውጣት መብት ይጎናጸፋሉ። የኤርትራ መንግስት ከፍተኛው የገቢ ምንጩም በዚህ መልክ ከዳያስፖራ የሚሰበስበው ገቢ እንደሆነ ይነገራል። ለመሆኑ ስደተኞቹ ከኤርትራ ከወጣችሁ በኋላ አቶ ኢሳያስን ብትተቹም ተመልሳችሁ በገንዘብ ትደግፋላችሁ። ይህ አይጣረስም ወይ? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። “ዋናው ነገር ለአገራችን የሚጠቅም ዘላቂ መፍትሔ መምጣቱ ላይ ነው እንጂ ከአገር መውጣትና መግባቱ ምንም ዋጋ የለውም። ይህን የሚያደርጉ ሊኖሩ ይችላል። እኔ ግን (ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በተናጠል የሰጡት ቃል ነው) ከአገሬ ተሰድጄ የአቶ ኢሳያስን አስተዳደር በገንዘብ የመደገፍ ፍላጎትም ሆነ ዓላማ የለኝም። ከአገሬ የወጣሁት ልጆቼን እንዳሳድግ ቤተሰቦቼን እንዳስተዳድር የሚያስችል አስተዳደር ስላጣሁ እንጂ የኢሳያስን መንግስት በገንዘብ ለመደገፍ አይደለም። ይህንን የሚያደርጉት (በገንዘብ እየደገፉ ወደ አገራቸው በነጻነት የሚገቡ እና የሚወጡትን) ምናልባት የአገዛዙ ደጋፊዎች ይሆናሉ ወይም ሌላ የራሳቸው ዓላማ ይኖራቸዋል ማለት ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
የኤርትራ ቀጣይ ጉዞ እና የአቶ ኢሳያስ እጣ ፈንታ
ኤርትራዊያኑ ስደተኞች “አቶ ኢሳያስ ለፍርድ ይቅረቡ” ሲሉ በተቃውሞ ሰልፋቸው ገልጸዋል። ይህን ጥያቄያቸውን ደግሞ ለአፍሪካ ህብረት ተወካይ አቅርበዋል። የአፍሪካ ህብረት ደግሞ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኝነት ፍርድ ቤትን ጣልቃ ገብነት ይቃወማል። የአፍሪካዊያን ጉዳይ ለአፍሪካዊን ሊተውላቸው ይገባል የሚለው የአፍሪካ ህብረት የኤርትራዊያን ስደተኞች የአገራቸው ፕሬዚዳንት በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲቀርቡላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ህብረቱ እንዴት ያየዋል? የሚለው ጉዳይ ለሌላ የውይይት አጀንዳ የሚከፍት ጉዳይ ነው።
ስደተኞቹ “ህጋዊ በሆነ መንገድ የኤርትራ አስተዳደር እንዲቀየር እንፈልጋለን። ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪያችንን የምናቀርበውም ይህን ጥያቄያቸንን ተቀብሎ መልስ እንዲሰጠን ነው” ሲሉ ነው የሚገልጹት። ይህንን ጥያቄያቸውን ያዳመጠው የአፍሪካ ህብረትም በኮሚሽነሯ ተወካይ አማካኝነት የኤርትራዊያኑን ጥያቄ በሚገባ እንደሚመለከተው አስታውቋል።
በ1983 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ የአገዛዝ ስርዓት መቀየሩን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል “የአፍሪካ ሲንጋፖር” እንሆናለን የሚል እምነት በሻዕቢያ መሪዎች ውስጥ ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን ባለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ ከዓለም ጭራዎች እንጂ መሪዎች ተርታ መመደብ አልቻለችም። ዜጎቿም ሆኑ ምሁራኗ እና ዳያስፖራው “ከኢትዮጵያ መገንጠላችን ያስገኘልን ጥቅም ምንድን ነው? ከደርግ በተሻለ የተጠቀምነውስ ምንድን ነው?” ሲሉ ደጋግመው እየጠየቁ ይገኛሉ። የኤርትራዊያን ተደጋጋሚ ጥያቄ ላለፉት 25 ዓመታት በጠንካራ የአምባገነን ጡንቻቸው የገዟትን የአቶ ኢሳያስን ወንበር ይነቀንቃል ወይስ አቶ ኢሳያስ አሁንም በስልጣን ላይ ይቆያሉ? የሚለው ጉዳይ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።
ኤርትራዊያኑ ስደተኞች በጽኑ የኮነኗቸው አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነመንግስታት (ኢጋድ) እና በአፍሪካ ህብረት ፊት የተነሳቸው ሲሆን በተለይ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ “ጸባጫሪ” እንደሆኑ ደጋግሞ ይገልጻቸዋል። ኢትዮጵያ የኢጋድም ሆነ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ ኤርትራዊያኑ ስደተኞች ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያካሂዱ መፍቀዷ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
ስንደቅ