እውን ሐበሻና ፊደሎቹ ከደቡብ ዓረብያ ፈልሰው የገቡ መጻእያን ወይም ውሑዳን ናቸውን?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
ethiopia old map
June 25, 2014 07:13 am By Editor 3 Comments
የሥነ ልሳን ወይም የሥነ ቋንቋ linguistics ተመራማሪዎች  ፊደልን ለመጀመሪያ ጊዜ ፈለሰፉ የሚሏቸው ከፊሎቹ ሱመራዊያን አሁን ኢራን በሚባለው አካባቢ እንደሆነ ሲናገሩ ከፊሎቹ ደግሞ በግብጽና በሜሶፖታሚያ እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይህ እንዳልሆነ በሌላ ጊዜ በሚገባ እናየዋለን፡፡ እነኚህ ምሁራን የእኛን የግዕዝ ወይም የአማርኛ ፊደላትን ከደቡብ ዓረቢያ ባሕር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ በገቡ አፍሮ ዓረቦች ወይም ኢትዮ ሴማዊያን አማካኝነት ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ሃያ ዘጠኝ መሠረታዊ ፊደላትን ይዘው ገቡ በማለት ይናገራሉ፡፡
እንደመረጃ አድርገው ከሚያቀርቧቸውም ውስጥ አንድ ሁለቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴማዊ ቋንቋ የሚናገሩ ብሔረሰቦች መኖራቸውና እነኚሁ ብሔረሰቦች ደግሞ በመልክ ከሌላው አፍሪካዊ የተለዩ ስለሆኑ መጤዎች እንጂ ነባር አይደሉም ይላሉ፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ድምዳሜ የሚያደርሳቸው ደግሞ መስፈርት አድርገው የያዙት የገዛ አስተሳሰባቸው ነው፡፡ እንደነሱ እምነት ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሁሉ የግድ ከመካከለኛው ምሥራቅ መፍለስ አለበት፡፡ ልብ ቢሉ ግን ኩሻዊውም ራሱ ከየት ፈለሰና ? ምክንያቱም ሴምም ካምና ልጁ ኩሽም ያፌትም የአንድ ሰው የኖኅ ልጆች ናቸውና፡፡ በአንድ ቋንቋ ይግባቡ የነበሩ ቤተሰቦች ናቸውና፡፡ ዘፍ. 0.1 – V1
ስለዚህ በአንድም በሌላም ምክንያት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ መፍለስ ግድ ሳይል ሴማዊም ሆነ ኩሻዊ ሌላም የቋንቋ ቤተሰብ በነሱ ግምትና እምነት በማይጠብቁት ቦታ ወይም በተለያዩ ስፍራዎች በነባር ሕዝብ ዘንድ የመነገር አጋጣሚ ይኖራል ማለት ነው፡፡ ኩሻዊ ቋንቋ እስያ ውስጥ እንዳለ ሁሉ ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑ መልካቸው አፍሪካዊ አይደሉም አፍሮ ዓረቦች ናቸው ለሚሉት ደግሞ አንድም እንዲህ የሚሉበት ምክንያት ሴማዊ ቋንቋ በመናገራችንም ነውና መልካቸው ከአፍሪካዊያን የተለየ ሁሉ ከደቡብ ዓረቢያ የግድ የፈለሰ መሆን አለበት ማለታቸው የተሳሳተ መሆኑን የሚያረጋግጠው አገውኛና ሌሎች በጎንደርና በጎጃም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍልም ያሉ ኩሻዊ ቋንቋ የሚናገሩትስ ? ነገር ግን እነሱ ከደቡብ ዓረቢያን ፈልሰው የገቡ ሕዝቦች ናቸው ከሚሏቸው ጋር ምንም ዓይነት የመልክ ለውጥ የሌለባቸው ማለት ነው ይሄንን እንዴት ሆኖ ሊሉ ይሆን ? ምክንያቱም ኩሻዊ ቋንቋ የነባር ሕዝብ ቋንቋ ነው ይላሉና፡፡
fidellበመሆኑም የእነኚህ የዓለም አቀፍ ምሁራን መስፈርት እና ፍረጃ ጠለቅ እና ሰፋ ያለ መሆኑ የሚያጠራጥር ከግላዊና ቡድናዊ ፍላጎትና አመለካከት የጸዳ አቋምና መስፈርት እንዳልሆነ ይታያል፡፡ ለምሳሌ አማርኛን የወሰድን እንደሆነ ግእዝ ውስጥ የሌሉ ሌሎች ሴማዊያንም ያልነበራቸውን ከጊዜ በኋላ ከእሱ የወረሷቸውን እነ ሸ፣ ቸ፣ ጨ፣ ኘ፣ ጀ፣ አምስት የኩሽ የድምፅ ቤቶች አሉት፡፡ በተጨማሪም ከሴማዊያኑም ከኩሻዊያኑም የሌለ የራሱ ብቻ የሆነ “ዠ” የሚባል የድምፅ ቤትም አለውና አማርኛን አፍን ሞልቶ ሴማዊ ማለት አይቻልም ኩሻዊ ማለትም እንዲሁ፡፡
ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ የእኛ ምሁራንም ከላይ የገለጽኩትን የባዕዳኑን ትንታኔ አምነው በመቀበል እነሱም ሲያናፍሱት ይስተዋላሉ፡፡ እንደእነሱ አባባል ግዕዝ ባሕር ተሻግረው የገቡት “አፍሮ ዓረቦች” ወይም “ኢትዮ ሴማዊያን” እና ነባሩ የኩሽ ነገድ ሕዝብ በመዳቀል የፈጠሩት ቋንቋ ነው በማለት ይናገራሉ፡፡ የሀገር ውስጥ ምሁራን ፊደሎቻችንን የአማርኛ ፊደላት መባሉን አይስማሙም እንደእነሱ እምነት “ፊደላቱ የግዕዝ እንጂ የአማርኛ አይደሉም አማርኛ ከግዕዝ ተውሶ ነው” በማለት ግራ የተጋባና የተምታታ እርስ በእርሱ የሚጋጭ እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንዲህ ማለቴ እነኚህ ምሁራን የግዕዝ ቋንቋ ባሕር ተሻግረው የገቡት “ኢትዮ ሴማዊያንና” ከነባሩ የኩሽ ነገድ ጋር በመዳቀል የፈጠሩት ቋንቋ ነው ብለው ካመኑና ሃያ ዘጠኙ መሠረታዊ ፊደላቱን ባሕር ተሻግረው ይዘውት የገቡት የኢትዮ ሴማዊያኑ ከሆኑ ፊደላቱ የአማርኛ እንጂ የግዕዝ አይደለም ማለታቸው እንደሆነ ልብ አላሉትም፡፡ ምክንያቱም በግልጽ እንደሚታወቀው አማርኛ ከኢትዮ ሴማዊያኑ ቋንቋዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛውም ነውና፡፡
በመሆኑም ግዕዝ ባሕር ተሻግረው የገቡት ኢትዮ ሴማዊያንና ነባሩ የኩሽ ነገድ በመዳቀል የፈጠሩት ቋንቋ ነው ብለው ካመኑ ፊደላቱ የአማርኛ መሆኑንም ሳያወላውሉ ማመን ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ እነአለቃ ታዬ፣ እነተክለጻድቅ መኩሪያ፣ እነሀብተማርያም ማርቆስ፣ የመሳሰሉት ምሁራንም ቀዳማዊ ክብረ ነገሥትን፣ የአክሱም ነገሥታትን ስሞችን፣ በአክሱም ሰዎች ዘንድ ያሉ ትውፊታዊ መረጃዎችን እና የውጪ ምሁራን የጻፏቸውን መጻሕፍት ዋቢ በማድረግ አማርኛ ቋንቋን ቅ.ል.ክ. አንድ ሺህ ዓመታት በፊት ይነገር የነበረ ቋንቋ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ በመሆኑም የአማርኛ የፊደል ገበታ የሚለው ሥያሜ የሚቆረቁራቸው ሥያሜ ሊሆን አይገባም ማለት ነው፡፡ እነኚህ ምሁራን አፍሮ ዓረብ የሚለውን ቃል እና ሳባዊያን የሚለውን ቃል እያቀያየሩ ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ፡፡ እንደእነርሱ ግምት ንግሥተ ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥት ሳትሆን የደቡብ ዓረብ ወይም በአሁኑ አጠራር የመን ተብሎ የሚታወቀው አካባቢ ንግሥት ናት ብለው ያምናሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማለትም ሳባ ኢትዮጵያዊት መሆኗን የሚያረጋግጡ ከበቂ በላይ መረጃ አለንና ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
የአገራችን ምሁራንም ይህን ብለው ማመናቸው አሳዘነን እንጂ የባዕድ ምሁራንስ ከዘረኝነት እና ከቅናት የተነሣ የኢትዮጵያ የሆነን ነገር ሁሉ አሌ ማለትን ወይም ማስተባበልን ጉዳዬ ብለው ከያዙት ከራርመዋል፡፡ ሳባን ብቻ አይደለም፡፡ እንደእነሱ እምነት የጎንደር አብያተ መንግሥታትን፣ የቅዱስ ላሊበላን ውብና ድንቅ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናትን፣ የአክሱም ሐውልትን የኢትዮጵያውያን ሥራዎች ሳይሆኑ የሌላ አገር ሰዎች ሥራዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ የዜማው ሊቅ፣ ዘርዓያዕቆብ ፈላስፋውን፣ አሁን ደግሞ በቅርቡ ጃንሆይን ወይም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን በአጠቃላይ ዋኖቻችንን ኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ ትንሽ ከቆዩ ደግሞ እነአበበ ቢቂላ፣ እነ ኃይሌ ገብረሥላሴንና በስደት ሀገር ድንቅ ድንቅ ሥራ እየሠሩ ያሉና ሠርተው ያለፉ ኢትዮጵያውያን ምሁራንንም ኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑ አድርገው ሊያወሩ እንደሚችሉ ካላቸው ልምድ በመነሣት መገመት ይቻላል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ለቅሪት ዘአካል ጥናት (archeology) ለሥነሰብእ ጥናት (anthropology) እና ለሥነቋንቋ ወይም ለሥነልሳን (linguistics) ጥናቶች እና ለመሳሰሉት በምንጭነትና መላምት ጠቋሚነት የማይተካ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡ እነኚህን የታሪክ ምሁራን የሚያደናግራቸው እና የሚያሳስታቸው ነገር ንግሥተ ሳባን ዓረባዊት ናት ግዕዝንም ከነፊደሎቹ የደቡብ ዓረቢያ ነው ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸው ነገር የንግሥተ ሳባና የግዕዝ ፊደላት የታሪክ አሻራዎች እና ትውፊቶች በዓረብ ሀገሮች መገኘታቸው ነው፡፡ እንዲያው ግራ ተጋቡ ሲላቸው እንጂ በሳባ ጊዜም ይሁን ከሷም በፊት ከእሷም በኋላ በተለያየ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ አብዛኛውን የመካከለኛው ምሥራቅን ወይም ሳውዲአረቢያን እና የመንን ከፋርሶችጋር በመፈራረቅ ትገዛ እንደነበር የራሳቸው የዓረቦችና የምዕራባዊያኑ ትውፊታዊ መረጃዎችና መዛግብት ሳይቀር የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡ እነሱ ካሏቸው መዛግብቶች አንዱም እንኳን እነሱ ኢትዮጵያን መግዛታቸውን የሚናገር የታሪክ መጽሐፍ ወይም ትውፊታዊ መረጃ የለም፡፡ እነሱም ይሄንን ብለው አያውቁም ይህ በሆነበት ሁኔታ ሳባ የየመን ንግሥት ብትሆን ኖሮ እኛ ከሰው ሀገር ንግሥት ጋር ፍቅር ላይ የምንወድቅበት እና ንግሥታችን ናት ብለን ድርቅ የምንልበት አንዳችም ምክንያት ባልነበር፡፡ ማንነታችንም ይሄንን የሚፈቅድ አይደለም፡፡
የፊደሎቻችንና የግዕዝ ወይም የአማርኛ አሻራዎች እዚያ አካባቢ የመገኘታቸው ምክንያት ማለትም ምሁራኑን ፊደሎቻችንና ግዕዝን ወይም አማርኛን ከደቡብ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግሯል የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ያደረጋቸው እንዲህ የመሆኑ ብቸኛው ምክንያት ይኸው ነው፡፡ እሱም እንዳልኩት ሀገራችን ለረዥም ጊዜ ከፋርስ ጋር በመፈራረቅ አካባቢውን ትገዛው ስለነበረ በቅኝ ግዛቱ ወቅት በአንድም በሌላም ምክንያት ቋንቋውንና ፊደላቱን የማወቅ እና የመገልገል ዕድል ስላጋጠማቸው እንጂ እሴቱ ወይም ሀብቱ የእነርሱ ሆኖ ወደ እኛ ተሻግሮ አይደለም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ይህ ሀብት አሁንም ድረስ በእጃቸው በተገኘ ወይም እየተገለገሉበት በተገኙ ነበር፡፡ ነገር ግን ሀብቱ ወይም እሴቱ የቅኝ ገዢ ሀገር በመሆኑና እንደቅኝ ተገዢነትም ለቅኝ ገዢያቸው በነበራቸው ጥላቻ ወይም ለቅኝ ገዢያቸው እሴቶች በነበራቸው የባዕድነት ስሜት ወይም ሥነ-ልቡና ምክንያት የቅኝ ገዢ ሀገር እሴት ወይም ሀብት የሆነውን ቋንቋና ፊደላትን እየተገለገሉበት እንዲቆዩ ሳያደርጋቸው ቀርቷል፡፡ ወይም ደግሞ ይህንን በማድረግ ማለትም አሁንም ድረስ እየተገለገሉበት ባለመቆየታቸው የራሳቸው እንዳልሆነ አስመስክሯቸዋል፡፡ እናም ቅኝ ግዛቱ ሲያከትም በግድም ይሁን በውድ በፊደላቱ የመገልገላቸው ነገር አብሮ ሊያከትም ችሏል፡፡ የቀረ ነገር ቢኖር ፊደላቱ እዚያ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበሩ የሚያመለክቱ ቅሪቶች ብቻ ነው፡፡shebamiles1
በዚሁ አጋጣሚ ሳልጠቅሰው ለማለፍ የማልፈልገው ነገር ቢኖር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚከፈቱ የንግድ ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማትና የሥራ ሒደቶች “ሸባ” እና “ሱባ” በሚል ሥያሜ እየተጠሩ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር “ሳባ” ማለት ሲችሉ ለምን “ሸባ” ና “ሱባ” እንደሚሉ እንኳን በምክንያት ማስረዳት አለመቻላቸውን ከ6 ዓመታት በፊት ካነጋገርኳቸው በቅርብ ላገኛቸው ከቻልኳቸው በዚሁ ስም ከተጠሩ ድርጅቶች ተረድቻለሁ፡፡ ስገምት ግን እንደመሰልጠን ቆጥረውት ይመስለኛል ልክ እንዳልሆነ በማስረዳትም ሥያሜአቸውን እንዲያስተካክሉ ጥረት አድርጌ ነበር ድርጅቶቹ ሀሳቡን ወይም አስተያየቱን ቢያምኑበትም “የተመዘገብነውና የንግድ ፈቃድ ያወጣነውም በዚሁ ስም ስለሆነ እንደገና ወደኋላ ተመልሰን ለማስተካከል ብንሞክር ብዙ ነገሮችን ያበላሽብናል” በሚል ሰበብ ሥያሜያቸውን ለማስተካከል እንደማይችሉ አረጋገጡ፡፡
በጣም የሚያሳዝነው ግን አሁን ደግሞ የመንግሥት ድርጅት የሆነውና እንደ ሀገር አምባሳደር የሚቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ “ሸባ ማይልስ” በሚል ሥያሜ ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ የበረራ ደንበኝነት አገልግሎት ዘዴ መዘርጋቱን በብዙኃን መገናኛ ማለትም በሬዲዮ (በነጋሪተ ወግ) እና በቴሌቪዥን (በምርአየ ኩነት) ባሰራጨው ማስታወቂያ አይተናል ሰምተናል፡፡
ከአርኪዮሎጂ (ሥነ-ቅሪት ዘአካል) እና ከአንትሮፖሎጂ(ሥነ-ሰብእ) ጥናትና ምርምር በተጨማሪ የሥነልሳን ጥናት የአንድ አካባቢ ቋንቋ ሥነልሳን የዚያን አካባቢ ሕዝብ ማንነት ለማወቅ ዋነኛ መለኪያ ነው፡፡ እንግዲህ ችግሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ “ሸባ” እና “ሱባ” የሚለው ቃል ዓረቢክ ነው፡፡ የእኛ ቋንቋ “ሳባ” ነው የሚላት፡፡ በአማርኛና በግዕዝ የተጻፉ መጻሕፍትም አንዳቸውም እንኳን “ሸባ” የሚል ቃል ተጠቅመው አያውቁም፡፡ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስም የአማርኛውና የግዕዙ “ዓረብ” የሚለውን ቃል የእንግሊዝኛው “ሸባ” በማለት ሲጠራው የአማርኛውና የግዕዙ “ሳባ” የሚለውን ደግሞ የእንግሊዝኛውም “ሳባ” በማለት ነው የሚጠራው፡፡ ለምሳሌ መዝ.፸፩፣፲  psalm 72÷10
ይህም ማለት ደግሞ የእንግሊዝኛው “ሸባ” ማለት “ዓረብ” ማለት ነው ማለቱ ሲሆን የእኛ ሰዎች ይህንን ቃል ማለትም “ሸባ” ወይም “ሱባ” የሚለውን ቃል “ሳባ” ለማለት መጠቀማቸው የሳባን ማንነት ኢትዮጵያዊት ናት ወይስ የመናዊት? የሚለውን ለመወሰን ቋንቋዎቻችንን የሚያጠኑትን እና የሚመረምሩትን የሥነልሳን (Linguistics) ባለሙያዎችን የተሳሳተ ድምዳሜ እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡ እነሱ ይህ አጠራር አዲስ የመጣና እንዲህ በማለታቸው የሚያስከትለውን ችግር በማያውቁ ሥልጡን መሀይምናን አማካኝነት አሁን በቅርቡ ወደሀገራችን መምጣቱን ሳያውቁ ቃሉን ከእነዚህ ሰዎች አንደበት በመስማታቸው ብቻ የተሳሳተ ድምዳሜ ያደርሳቸዋል፡፡ “ሳባ”ን “ሸባ” ወይም “ሱባ” ብለን በመጥራታችንም ሳባን የእኛ ናት ለሚሉት የመኖችም ጥሩ ማስረጃና እንዲህ የሚሉትንም የእኛን ሰዎች ጥሩ ምስክሮች ያደርጋቸዋል፡፡ በመሆኑም ሲጀመር በቋንቋችን ያማረና በታሪካችንም ትልቅ ሥፍራ የያዘውን “ሳባ” የሚለውን ስም ሸባ ወይም ሱባ የምንልበት አንዳችም ምክንያት የለምና እንዲህ በማለት እየጠሯት ያሉትን ሰዎች እና ድርጅቶች በማስረዳት ከስሕተታቸው እንዲታረሙ እንድናደርግ መልእክቴን ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ አመሰግናለሁ፡፡
እንደ ኢትዮጵያዊ እንዲህ ዓይነት ስሕተት መሥራት በጣም ጸያፍ አሳፋሪና፣ አኩሪ ማንነትን መካድ ወይም ከማንነት መሸሽ በመሆኑ በተመሳሳይ በሌሎች ቃላትና ሥያሜዎች ላይም እንዲሁ ዓይነት ስሕተት በሰፊው ይስተዋላል እና ምነው ወገኔ ወርቅ የሆነ ማንነት እያለህ መናኛ የሆነውን የባዕድን ማንነት ወይም መለያ ሙጥኝ ማለትህ? በስንት ድካምና መሥዋዕትነት ድንቅ የሆኑትን መለያዎችህን ያነጹ ጽኑዓን አባት እናቶችህ ይህንን ነውርህን ቢያዩ ምንኛ እንደሚያፍሩብህና እንደምታስከፋቸውም ልብ ብለኸው ታውቅ ይሆን?፡፡
ወደቀደመው ነገራችን ስንመለስ ቀደም ሲል እንዳልኩት መጽሐፍ ቅዱስ የያዛቸው መረጃዎች ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ባሻገር ለታሪካዊ ክሥተቶች ጥናትና ምርምር ለአጥኚዎችና ተመራማሪዎች ዓይነተኛ ግብዓት ነው፡፡ ቅ.ል.ክ. ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የተናገረውን ቃል እንመልከት፣ የዚህችን ሀገር ሥረመሠረትና ማንነት ለመረዳት ይበጃል፡፡ ኢሳ.፲፰ን ስናነብ በዚሁ አጭር ምዕራፍ ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ የተጻፈን ቃል እናገኛለን፡፡ ቃሉም “እናንት ፈጣኖች መልእክተኞች ሆይ ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደሆነ ወገን ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሒዱ” ይላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ኢትዮጵያና ግብጽ በመሆናቸው ይህ ቃል በትክክል ለኢትዮጵያ ይሁን ለግብጽ ማንን ለመግለጽ እንደሆነ ግልጽ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ቃሉን ልብ ብለው ቢመለከቱት ግን ቃሉ በትክክልም ኢትዮጵያን የሚገልጽ እንደሆነ ይረዳሉ፡፡ “ወንዞች ምድራቸውን ወደ ሚከፍሉት ሕዝብ” በማለት ከ ዘጠኝ እስከ ዐሥራሁለት  በሚደርሱ ታላላቅ ወንዞቿ ምድሯ የሚከፈለው ኢትዮጵያ እንጂ በወንዞች ሳይሆን በአንድ በዓባይ ለዚያውም በእኛ ወንዝ ብቻ ምድሯ የሚከፈለውን ግብጽ አለመሆኗን ይረዳል፡፡ ይህ ጥቅስ የሀገራችንን ታሪክ፣ ልዕልና ክብር ኃያልነት ወይም አጠቃላይ ማንነት ተጠቅልሎ የተያዘበትና የተገለጸበት ቃል ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሀገራችን ውጪ በእንደዚህ ዓይነት ቃል የተገለጸ ሀገር የለም፡፡
ethiopic oceanሀገራችን ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጥንታዊ የአውሮፓ ታሪክ ጸሐፍትም ጭምር ገናና ታሪኳ በስፋት የተገለጸበት አጋጣሚ አለ፡፡ የጥንቱ የአውሮፓዊያኑ የዓለም ካርታ አትላንቲክ ውቂያኖስን ከሁለት ቆርጦ ደቡቡን ክፍል “የኢትዮጵያ ውቂያኖስ” ብሎ ይጠራው ነበር፡፡ በምሥራቁም ዓለም ከታሪክ እንደምንረዳው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕንድን አልፋ እስከ ቻይና የባሕር ጠረፍ ድረስ ትገዛ እንደነበረ መዛግብት ቢያስረዱም አሁን ያለንበት እና የወደቅንበት ማጥ ይህንን ገናናና የከበረ ታሪክ የሚሰማውንና የሚያነበውን ሁሉ እውነት የነበረ እና የተደረገ መሆኑን እንዳያምን ወይም እጅጉን እንዲጠራጠር ሲያደርገው ይታያል ወይም ይስተዋላል፡፡ አንዳንዴም እንዲያውም “አይ ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች እንጅ ይህችማ ልትሆን አትችልም” በማለት በድፍረት ያለሐፍረት እስከመናገርና እስከ መጻፍ ሲደረስ ይታያል ለዚያውም ከኢትዮጵያዊያንም ጭምር፡፡ ነገር ግን ያቺ ገናናና ልዕለ ኃያላን የነበረችው ሀገር በእርግጥም ይህች ዛሬ ወድቃ የምናያት አገራችን ኢትዮጵያ መሆኗን መጽሐፍ ቅዱስ የምትገኝበትን መልክዐምድራዊ ቦታ ጭምር እንዲህ ባለ ቃል ይገልጻል፡፡ “የሁለተኛውም ወንዝ ስም ግዮን ነው፡፡ እሱም የኢትዮጵያን ምድር ይከባል”  ዘፍ. 2፡13 በማለት፡፡ በመሆኑን ግዮን ወይም ዓባይ ከኢትዮጵያ ውጭ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውስጥ ፈልቆ ምድሯን የሚከባት ወይም የሚዞራት ሀገር ያች ማለት ኢትዮጵያ ናት ስለሆነም ምንም የሚያደናግር ወይም የሚያምታታ ነገር የለም፡፡
እርግጥ ነው ትላንት የነበረችው የኢትዮጵያ አካለመጠን ወይም የቆዳ ስፋት ዛሬ ያለችው ኢትዮጵያ ብቻ እንዳልሆነች በዚህ ዘመን ያለን ኢትዮጵያዊያን የዓይን ምስክር በመሆንም ጭምር የምንረዳው እና የምናውቀው ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ያቺ ትላንትና የነበረችው ግዙፏና ኃያሏ ኢትዮጵያ የግዛት አካሏ እየተቀነሰ እየተቀነሰ የሚቀነሰው የራሱን ስም እያወጣ ሲሔድ ኢትዮጵያ የሚለው ስም አሁን ያለችው ኢትዮጵያ መጠሪያ ሆኖ ቀረ፡፡ ይሄ መሆኑ ደግሞ ጥንት የምትታወቀዋ ያቺ ገናና ባለሰፊ ግዛት ኢትዮጵያ ትባል የነበረችው ሀገር ምንም እንኳ የግዛት አካሏ ሰፊና ግዙፍ ቢሆንም በወቅቱ ዋና ማዕከሉ ግን ይች አሁን የምናውቃት ኢትዮጵያ እንደነበረ አሁን ድረስ ስሙን ይዛ መቆየቷም አንዱ ማረጋገጫ ነው፡፡ በመሆኑም የጥንቷ ኢትዮጵያ ገናና ታሪክና እሴቶች ሁሉ የማዕከሉ ወይም አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ሀብት መሆኑ እርግጥ ነው ማለት ነው፡፡ ወይም የሚያሻማ ጉዳይ አይሆንም ማለት ነው፡፡
አሁን ቀደም ሲል ወደአነሣነው የነቢዩ ኢሳይያስ ቃል ልመለስ እና “ወደ ረጅምና ወደ ለስላሳ ሕዝብ” ረጅም አለ እንጂ እረጃጅም አለማለቱን ልብ ይሏል፡፡ እንዲህ ማለቱም ሊናገር የፈለገው የሕዝቡን ታሪክ እርዝማኔ እንጂ የሰዎቹን የቁመት እርዝማኔ አይደለምና፡፡ “ለስላሳ” አለ ጠባእዬ ሕዝቡን ሲገልጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላምና በፍቅር ለመጣው ሁሉ ያለውን ፍቅርና አቀባበል ሲገልጽ፡፡ “ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደሆነ ወገን” እንግዲህ ትልቁ ነገር ይህ ነው፡፡ ከላይ ያልነው ወይም የጠቀስነውን በዓለም ታሪክ ጸሐፍት እንደነ ሄሮዱቶስ እንደነ ሆሜር ባሉት ዘንድ የተነገረውን የጥንቷን ገናና ኢትዮጵያን ታሪክ ከዚህ ጋር ያያይዟል፡፡ ነቢዬ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ከክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመታት በፊት ምን አለ “ከመጀመሪያው አስደንጋጭ ወደ ሆነው ወገን” የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነት ታሪክ ከማንም የቀደመ መሆኑን ሲያጠይቅ “ከመጀመሪያው” አለ “ወገን” ማለቱ በአምልኮተ እግዚአብሔር እንደምንዛመድ ለማጠየቅ፡፡ ከዚያም ቀጠለና “ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ ሒዱ” አለ፡፡ “ወደሚሰፍርና ወደሚረግጥ” ማለቱ ለጊዜው በዘመኑና ከዚያም በፊት የነበረውን ታሪኩን ሲናገር ነው ፍጻሜው ደግሞ በጌታ ምጽአት መቃረቢያ የምትኖረውን በብዙ የትንቢት መጻሕፍት የተነገረላትን ኃያሏን ኢትዮጵያን መግለጡ ነው፡፡ “ወንዞችም ምድራቸውን ወደሚከፍሉት ሕዝብ” አለ ወንዞች ብሎ የበርካታ ወንዞች ባለቤት መሆኗን ሲናገር፡፡ “ምድራቸውን” አለ ያ ታላቅና ገናና ያንን ሁሉ ታሪክ የሠራ ሕዝብ ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሶ ምንትስ እንደሚሉት ቀባጣሪያን ዲስኩር ሳይሆን ከመጀመሪያውም መሠረቱ እዚያው መሆኑን ከየትም ስደተኛ መጻተኛ ሆኖ የገባ አለመሆኑን ሲያጠይቅ ሲያረጋግጥ “ምድራቸውን” አለ፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይህ ማለት ግን ከደቡብ ዓረቢያ ፈልሰው ወደ ሀገራችን የገቡ ወገኖች ጨርሶ የሉም ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል፡፡ ከሴማውያንና ከኩሻውያን ከሌሎችም ነገዶች ከደቡብ ዓረቢያም ይሁን ከሌሎች የተለያዩ ሥፍራዎች 1ኛ. ቅኝ ገዥ ቅኝ ከሚገዛቸው ሀገሮች ወታደሮችን በገፍ የማጋዝና ላለበት ጦርነት የማሳተፍ ልማድ ነበርና ከፈርዖኖች ጋር በነበረን ጦርነት ምክንያት በውትድርና 2ኛ. በባርነት 3ኛ.በስደት እና በሌሎችም ምክንያቶች ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ወገኖች አሉ፡፡ ባሕልና ቋንቋቸውም ሲታይ ከመጡበት ሥፍራ ካሉ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው፡፡ ከጊዜ ብዛት ባሕል ቋንቋቸውን ቀድሞ የግዕዝ ተናጋሪ ከነበረው አማርኛ ተናጋሪ ወይም አማራ ከሚባለው ሕዝብ ባሕልና ቋንቋ ጋር ማስተሳሰር እና ከሀገሪቱ እሴቶች ጋር ለመዋሐድ ችለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ከላይ እንዳልኩት ባሕል ቋንቋቸው ሲታይ ከመጡበት ሀገር እና ሕዝብ ባህል ቋንቋ ጋር ያለውን አንድነት በግለጽ ማየት ይቻላል፡፡ እነዚህም ሕዝቦች ከፊሎቹ በወቅቱ የመንግሥት አስተዳደር ማዕከል ከነበረችው አክሱም እና በዙሪያዋ ሲገኙ ሌሎቹ ደግሞ በሀገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች ይገኛሉ፡፡ እናም እንግዲህ መጻሕፍት ሳይቀር የሚፈሯት የዚህች ሀገር ታሪክ በጥቂቱም ቢሆን ነገር ግን ግሩምና ስስት በሌለበት አጭር ቃል በኢሳ.08 እንዲያ ታስሮ ተቀምጧል፡፡

— 
You received this message because you are subscribed to the Google Groups “IHAPA_Democraciawie-Mederek” group.
To unsubscribe from this group and stop receiving emails from it, send an email to ihapa_democraciawie-mederek+unsubscribe@googlegroups.com.
For more options, visit https://groups.google.com/d/optout.

Leave a Reply