Wednesday, 03 August 2016 14:34

በይርጋ አበበ

 

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ በዘመነ ኢህአዴግ መንበረ ስልጣን አምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ተካሄደ። የምርጫውን መጠናቀቅ ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገው መረጃ የምርጫ ውጤት ኢህአዴግ (ህወሓት ብአዴን ኦህዴድ እና ደኢህዴን) በሚወዳደርባቸው አራቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች (ትግራይ አማራ ኦሮሚያ ደቡብ ክልሎችና አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች) ኢህአዴግ መቶ በመቶ የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፉን አስታወቀ።

ከላይ የተጠቀሰው የምርጫ ውጤት በተገለጸ ስድስት ወራት ሳይሞላ በኦሮሚያ ክልል የፌዴራል መንግስቱንና የክልሉን መንግስት መዋቅር ሳይቀር መረበሽ የቻለ ህዝባዊ ቁጣ ተነሳ። የአዲስ አባበ ዙሪያ ማስተር ፕላንን ተከትሎ በተነሳ ህዝባዊ ቁጣ በርካታ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገው አልፈዋል። ይህን የህዝብ ቁጣ መንግስት “የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠረው ነው። በጊዜ መፍትሔ እንሰጠዋለን” ማለቱ የሚታወስ ነው።

በኦሮሚያ የተነሳው አመጽ ሳይበርድ በሰሜን ጎንደር (አማራ ክልል) በተነሳ ሌላ ህዝባዊ ቁጣ አካባቢው እየታመሰ ይገኛል። በተለይ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ የተነሱ ጥያቄዎችን መንግስት የያዘበት መንገድ ለጥያቄ አቅራቢዎቹ የተሰጠው ምላሽ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት የማንነት ጥያቄ ያቀረቡት ኮሚቴዎች ደጋግመው ገልጸዋል። በተለይ ሀምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የጸጥታ ሀይሎች እና የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎች መካከል በተከፈተ ተኩስ አካባቢው ከመረበሹም በላይ በከተማዋ ውጥረት ነግሶ መሰንበቱ ይታወሳል። ከዚህ ክስተት በኋላ በጎንደር ከተማ እና አካባቢዋ (አብዛኛው ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች) በተለያዩ የክልሉ ውስጣዊ ችግሮችና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገለጸ። ሰልፉን የሚያስተባብረው አካል ባይኖርም ሰልፉ ግን ሀምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተላለፈ ጥሪ ተገለጸ።

ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ ከ15 ያላነሱ መፈክሮችን ይዞ ቁጥሩ እጅግ በርካታ ህዝብ በተገኘበት ሀምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ተካሄደ። የአማራ ክልል መንግስት “እውቅና አልሰጠሁትም” ብሎ በጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ምን አለ? በሰላማዊ ሰልፉ የተሰሙ የህዝብ ድምጾች ምን ይላሉ? ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ በቀጣይ የአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን ፋይዳ አለው? እና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦችን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ለሰላማዊ ሰልፉ የሰጠው አስተያየት

ጎንደር ላይ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ የአማራ ክልል ገዥ ፓርቲም ሆነ የፌዴራል መንግስት ሰልፉን ኃላፊነት ወስዶ ያስተባበረ አካል አለመኖሩን ገልጸዋል። ሰልፉም እውቅና እንዳልተሰጠው ገልጸዋል። የአማራ ክልል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ “የተነሳው ጥያቄ የማንነት እና የድንበር ብቻ አይደለም። በጣም ብዙ ጥያቄዎች ናቸው የተጠየቁት። የወልቃይትን ጥያቄ በተመለከተ የማንነት ጥያቄ መጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብት ነው። ይህ ጥያቄ ሲጠየቅ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማንኛውንም ጥያቄ መጠየቅ በዚህ አገር ክልክል አይደለም። የክልሉ መንግስት ይህን ያምናል። የወልቃይት ጥያቄ በተመለከተ ግን የተጠቀሰው አካባቢ የሚገኘው በትግራይ ብሔራዊ ክልልዊ መንግስት ውስጥ ነው። ስለዚህ የትግራይ ክልል መንግስት ጥያቄው ይቀርብለትና ምላሽ ይሰጣል። የሚሰጠው ምላሽ ጠያቂዎቹ በፈለጉት መልክ ካልሆነ በህገ መንግስቱ አግባብ ጥያቄው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ይቀርባል። ስለዚህ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የወሰነው ብይን ተፈጻሚ ይሆናል። ስለዚህ የአማራ ክልል በየትኛውም አካባቢ የተጠየቀ ማንኛውም ጥያቄ ህገ መንግስታዊ እስከ ሆነ ድረስ ህገ መንግስታዊ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል እና ከዚያ ባሻገር ግን የህግ ጉዳይ ለአማራ ክልል የሚቀርብ ጥያቄ አይደለም። ምክንያቱም ይህ ጥያቄ የሚነሳበት ክልል ያለው የአማራ ክልል ስላልሆ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከህዝቡ የተነሱት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ የክልሉ መንግስትም በአጭርና በረጅመ ጊዜ የሚፈታቸው ናቸው ሲሉ ነበር ለአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን አጄንሲ የገለጹት።

 በሌላ በኩል የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ሰላማዊ ሰልፉ እውቅና የሌለው መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ህዝቡ ላሳየው ጨዋነትና ሰልፉ በሰላም ለመጠናቀቁ ምስጋና አቅርበዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ይዘት

ሁለቱ የብአዴን ሰዎች ከላይ የተጠቀሰውን ቢናገሩም ጎንደር ላይ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡት ሰዎች ይዘዋቸው የወጡትን መልዕክቶች ከተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስንመለከት ግን ከአቶ ንጉሱ አስተያየት በተለየ መልኩ ሆነው አይተናቸዋል። ወደ 15 የሚጠጉ መልክዕቶችን በባነር አሰርተው ይዘው የታዩት ሰላማዊ ሰልፍ የወጡት ዜጎች ቅሬታቸው ወይም ለሰልፍ እንዲወጡ ያስገደዳቸው አቶ ንጉሱ እንደገለጹት በመልካም አስተዳደር ላይ ሳይሆን በዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶች ላይ የሚያጠነጥኑ እንደሆነ ነው መረዳት የሚቻለው።

ከማህበራዊ ሚዲያዎች በተመለከትነው የሰላማዊ ሰልፈኞቹ ፎቶ ግራፍ ላይ እነዚህን ጥያቄዎች ይዘው መውጣታቸውን ተመልክተናል። “የህግ የበላይነት ይከበር፣ ወልቃይት አማራ ነበር አሁንም አማራ ይሆናል፣ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የሞት ስቃይ እና እስር ይብቃ፣ አማራነት ይከበር፣ የህወሓት የበላይነት ይቁም፣ የህዝብን ጥያቄ መጠየቅ ሽብርተኝነት አይደለም፣ በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድም እና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው፣ በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም፣ የአማራ ህዝብ አሸባሪ አይደለም፣ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደረገው ጅምላ ግድያ ይቁም፣ አገራችንን ለሱዳን አሳልፈን አንሰጥም፣ ያለአግባብ ከየቤታቸው እየታፈኑ የተወሰዱ ወንድሞቻችን ይመለሱ፣ ታሪካዊ ድንበራችን ተከዜ ወንዝ ነው፣ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ይፈቱ” የሚሉት ይገኙበታል።

የትግራይ ህዝብ እና የህወሓት ጉዳይ

ባሳለፍነው እሁድ ጎንደር ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከመካሄዱ አምስት ወራት በፊት በወልቃይት ጠገዴ ነዋሪ የሆኑ የትግራይ ክልል ተወላጆች “እኛ ትግሬ እንጂ አማራ አይደለንም” ሲሉ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣታቸው ይታወሳል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ለዘመናት አብሮ ከኖረው የአማራ ብሔር ተወላጆች ጋር መጠነኛ መቃቃር ውስጥ ገብቷል።

ሌላው የሁለቱ ብሔረሰቦች የቅርብ ጊዜ ቅራኔ ማሳያ ደግሞ በቅርቡ ጎንደር ላይ በተካሄደው የጸጥታ ሀይሎች እና የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎች መካከል በተነሳው የተኩስ ልውውጥ ማግስት ጎንደር ከተማ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ንብረት በህዝቡ የወደመበት ይጠቀሳል። እነዚህ ሁነቶች የተፈጠሩት ከህወሓት ጋር ቅራኔ ያላቸው ወገኖች የትግራይን ህዝብ ከፓርቲው ጋር ደብሎ የማየት ጉዳይ ነው። ይህ ደግሞ የሚያመለክቱት አዝማሚያ ጥሩ አለመሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

ባሳለፍነው እሁድ በጎንደር ከተማ ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ይዘዋቸው ከወጧቸው መፈክሮች መካከል አብዛኞቹ በቀጥታም ይሁን በተዘዋወሪ በህወሓት ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። የህወሓት የበላይነት ይቁም ከሚለው መፈክር ጀምሮ የአንዳንድ ነባር የህወሓት ተጋዮችን ምስል ይዘው የተቃውሞ ቃላትን ከመጻፍ የደረሰ ተቃውሞ ያሰሙት በህወሓት ላይ ነው። እነዚህን ጥያቄዎች በደንብ መመልከቱ የሚገባ ይመስለናል። ምክንያቱም አሁን ያለውን ስርዓት ወደ ስልጣን እንዲበቃ የትግራይ ክልል ህዝብ ሚናው ከፍተኛ እንደነበረ ይታወሳል። በ1997 ዓ.ም ተካሂዶ በነበረው ሶስተኛው ዙር ምርጫ እንኳ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በየክልላቸው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲሸነፉ በትግራይ ክልል የሚወዳደረው ህወሓት ግን አንድም የክልል እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ሳያጣ ነበር የተመረጠው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በህወሓት ላይ ተቃውሞ የሚያነሱ ሀይሎችም ሆኑ ሰዎች በተደጋጋሚ ህወሓትን ከትግራይ ክልል ህዝብ ጋር ደምረው ሲመለከቱት ይታያሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸውን ሲያቀርቡ ህወሓት በአገሪቱ ላይ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ብልግና እና በአገር ሉዓላዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ ክስተቶችን የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የአገሪቱ ዜጋ ሲቃወም አይታይም እያሉ ነው። በዚህም የተነሳ ህወሓትን የሚቃወምም ሆነ የሚጠላ ሁሉ የክልሉን ህዝብ ከፓርቲው ጋር አብሮ ሲፈርጀው ይታያል። በቅርቡ ለአፍሪካ ቀንድ ምህዋረ ድር (ሆርን አፍሪካን ድረ ገጽ) ላይ በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውሶች ላይ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ያቀረቡት የቀድሞው የህወሃት ታጋይ ሌተናንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ የሚከተለውን ሀሳብ አስፍረዋል።

“የትግራይ ህዝብ ይህ አሁን ያለውን የፖለቲካ ስርዓት ለማምጣት ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን ታግሎ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ነው። በመሆኑም እስካሁን ድረስም ሆነ ለወደፊቱም ስርዓቱን ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ከማድረግ አንጻር ያለው ድርሻ ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ እንደህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅሙ የሚከበርለት በህገ መንግስት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲገነባ ስለሆነ። ……… በመሀል አገር ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች በትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ይንጸባረቃል። የትግራይ ህዝብ በስርዓቱ እላፊ ተጠቀሚ እንደሆነ ተደርጎ ይወራል ይታያልም” ሲሉ ጽፈዋል።

ጄኔራሉ ይህ አዝማሚያ ለአገርም ሆነ ለክልሉ ህዝብ የማይበጅ መሆኑን አስረድተው ከገለጹ በኋላ የትግራይ ህዝብ ከዚህ አይነት ስሜት የጸዳ አስተሳሰብ በህዝቡ ላይ እንዲኖር የትግራይ ህዝብ ሊጫወት ስለሚገባው ሚና የራሳቸውን ምልክታ ሲያስቀምጡ “የትግራይ ህዝብ የስልጣን ዘመኑን በጸጥታ ሀይሎች ድጋፍ የሚያራዝም በየጊዜው ከህዝብ እየተነጠለና በህዝብ እየተጠላ የሚሄድ የፖለቲካ ስርዓት ጠባቂ እና ተከላካይ ነው መሆን ያለበት ወይስ ሌላ ምርጫ አለው? የትግራይ ህዝብ የሚወስደው የፖለቲካ አቋም ምን መሆን አለበት?” በለው ይጠይቃሉ። ጄኔራል ጻድቃን አያይዘውም “በእኔ አመለካከት እና እምነት የትግራይ ህዝብ የሰብአዊና የፖለቲካዊ መብቶች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ የህዝቦች አንድነት በፍትህ ላይ የተመሰረተ የህዝብ መብት ጥበቃ ይህንን መሰረት አድርጎ የሚመጣ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና እና ማህበራዊ ልማት ለማምጣትና እነዚህ መብቶች ጥልቀት ኖሯቸው  ተግባር ላይ እንዲውሉ የሚታገል መሆን አለበት እላለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

ቀጣይ የመንግስት ምልሽ

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለየ መልኩ አገሪቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በሚያስብል መልኩ ፖለቲካዊ ውጥረቶች እየሰፉ መጥተዋል። የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ ማለት ነው። ለእነዚህ ቀውሶች መፍትሔው ደግሞ በመንግስት እጅ ላይ እንደሆነ ይታመናል። በዚህ በኩል እነዚህ ቀውሶች ነገ ውለው አድረው አገሪቱን እና ዜጎቿን ዋጋ ከሚያስከፍሉ ደረጃ ከመድሰራቸው በፊት ምን መደረግ አለበት ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል።

ስንደቅ

Leave a Reply