ኄኖክ የሺጥላ

adolph hitler

adolph hitler

ሂትለርም በመጨረሻው ሰዓት ሞት ፈርቶ ነበር ። እናም አዋቂ አስጠርቶ « መቼ ነው እኔ ሂትለር የምሞተው ?» ብሎ ይጠይቃል ። አዋቂም « አንተማ የምትሞተው የአይሁዶች በዓል ዕለት ነው » በማለት ይመልስለታል ። በመልሱ የተገረመው ሂትለርም « እንዴት ?» በማለት ይጠይቀዋል ። አዋቂውም « እንዴቱን ተወው ፥ ብቻ አንተ የሞትክ ቀን ለአይሁዶች በዓል ስለሚሆን ነው !» ብሎ መለሰለት ይባላል ።

የኢትዮጵያዊያን እውነተኛ ዘመን መለወጫ ተቃርቧል ። ጨፍጋጋው የባርነት ሰማይ ፥ በግፍ ዶፍ ፥ በጥላቻ ቁር ፥ በዘረኝነት ሃሩር ሲጠብሰን ፥ ሲለበልበን የነበረበት ዘመን ላይመለስ ሊሄድ ጓዙን ጠቅልሎ ፊቱን ወደመቀበሪያው ጉድጓድ አዙሮ እንደታረደ በግ አለሁ ለማለት እየተንፈረጋጠ ነው ። ሞት አይደል! ያንፈራግጣል !

ትንፋሽ ሲወጣ አመድ መጫር እና መሬት መሞንጨር የባለነብሶች ሁሉ ባህሪ ነው !

አዲስ ዘመን ፥ አዲስ ትንሳኤ ፥ አዲስ ብርሃን ። አበባየሆሽ ! አደይ ላንተ ለውንድሜ ! ሰርዶ ለኔ ለወንድምህ ! እንደ ማህሌት እንደ ድጓ በነፍስ ከናፍር ለምስምህ ! ላንተ ላራሽ ገበሬው ፥ አደይ ይሁን ላገር አርማው ፥ ለአባ ዲጋ ፥ ለአባ ነጋ ፥ ለአባ ቢያ ፥ ለአባ መላ ፥ አደይ ይሁን ለህዝቡ ሁላ ! ልንል ፥ የሰውነት መስከረም ሊጠባ ፥ ጀግኖች እንደ አደይ አበባ በየ ዱሩ ፥ በየ ገደሉ ፥ በከተማ ፥ በገጠሩ እየተዋደቁ ነው ። ለአዲሱ አመት ፥ ሃያ አምስት አመት ሙሉ ሳይጠባልን ፥ ልባሽ ማንነት ሲጋት ለነበረው ሰውነታችን፥ በደም ገፀበረከት ፥ በታጋዮቻችን የ እንቁጣጣሽ ትንሳኤ ሞት ፥ የወያኔን መቃብር ፈንቅለን ልንነሳ ፥ በጥቂት የቀናት እርምጃዎች ውስጥ ቆመናል !

ኢትዮጵያዊነት ከደብሩ ፥ ከተራራው ፥ ከጋራው ፥ ከገመገሙ ፥ ከምድር እምብርት ማረፊያ ፥ ከጥግ ከወጋግራው ፥ እጣን ከሚያለቅሰው ጫካ ፥ ሙጫ ከሚተፋው ጢሻ ፥ ቡና ከተሸከመው መንደር ፥ ጣዝማ ማር ካረገዘው ዋሻ ፥ ከሶፍ ኡመር እስከ እርጣሌ ፥ ከባሌ ፥ እስከ ሃረርጌ ፥ ከ ኮንሶ እስከ ደንካሌ ፥ ከ ቢቸና እስከ ባሌ እምቢ ብሏል ፥ አዲስ ዘመን ይሁን ብሏል ፥ በቃኝ ብሏል ፥ ይህ የኢትዮጵያዊያኖች አዲስ አመት ነው ። ይህ የኛ በአል ነው ። እንዴት ቢሉ ወያኔ የሚሞትበት ቀን ነውና !

በመጨረሻም

የሚታገል ህዝብ ይወድቃል ፥ ይሞታል ፥ ይታሰራል ፥ ይገደላል ፥ ግን በፍፁም አይሸነፍም !

ድል የህዝብ ነው !