ሐምሌ 30 እና ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ መለስተኛ መረጋጋት የታየበት ቢሆንም፣ በጎንደር ከተማ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተጠናክሮ መቀጠሉ ተሰምቷል፡፡

ይህ ሰላማዊ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ የመጣው መንግሥት በሰላማዊ ሠልፎች ላይ የኃይል ዕርምጃ በመውሰድ ዜጎችን እየገደለና እያሰረ በመሆኑ ነው ሲሉ፣ ምንጮች ለሪፖርተር አክለዋል፡፡

የቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማው እስከ ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ጎንደር ኤርፖርት የደረሱ ሁኔታውን ያልተገነዘቡ መንገደኞች ከኤርፖርት ወደ ከተማ ለመሄድ መቸገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ሰኞ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የተንቀሳቀሰ አንድ ባጃጅ ተሽከርካሪ ከጥቅም ውጪ መደረጉንም የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በአድማው ምክንያት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ሕይወት እንዳይጎዳ እርስ በርስ የመረዳዳት ተግባሮችን ለማከናወን እየሞከሩ ቢሆንም፣ ይህንን የሚያደርጉ ነዋሪዎችን ታጣቂዎች እንደ ወንጀል እየቆጠሩ ተግባሩን ለማስቆም ጣልቃ እየገቡ ነው ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

የጎንደር ተቃውሞ በዚህ መልኩ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነሐሴ 7 እና 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በተለያዩ የአማራ ክልሎች ተቃውሞው የመስፋፋት አዝማሚያን ለማሳየት ሞክረው ነበር፡፡ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው የተቃውሞ ሠልፎች የተካሄዱ ቢሆንም በፀጥታ ኃይሎች በአጭሩ ተበትነዋል፡፡ በዚህ ዕርምጃም የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰላማዊ ሠልፈኞች መኖራቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ለተወሰኑ ቀናት በደብረ ማርቆስ የትራንስፖርትና የሰዎች እንቅስቃሴ ቆሞ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምርያ ኃላፊ ኮማንደር አሥራት በለጠ ሰላማዊ ሠልፈኞቹን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ሰባት ሰዎች መጎዳታቸውን አምነዋል፡፡

በተመሳሳይ ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በደሴ፣ ደቡብ ወሎና በአማራ ክልል የኦሮሞ ማኅበረሰብ አስተዳደር ዞን በተለይም በባቲ፣ ከሚሴ፣ ሰንበቴ አካባቢዎችም የተቃውሞ ሠልፉ የመስፋፋት አዝማሚያ አሳይቶ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በእነዚህ አካባቢዎችም በፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ ሠልፈኞች መበተናቸውን፣ የሠልፈኞቹ ቁጥርም መጠነኛ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአማራ ክልል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ቀደም ሲል በነበሩት ሠልፎች ጥቃት የተሰነዘረባቸው መሆኑን ተከትሎ አካባቢውን ለቀው እየወጡ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በሥራ ላይ ባለው የፌዴራሊዝም አወቃቀር በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘው የወልቃይት ፀገዴ ማንነት የአማራ በመሆኑ ወደ አማራ ክልል ሊካለል ይገባል፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የጋራ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተነሳው ተቃውሞ አሁን መልኩን ቀይሮ ሌላ ገጽታ ይዟል፡፡

አገሪቱ በዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም መንግሥት የችግሩን መነሻ ለመለየትና መፍትሔውን ለማፈላለግ የሚታይ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለመሆኑ ትችት እየቀረበበት ይገኛል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናትም የተነሳውን የሕዝብ ተቃውሞ ያላቸው ግምገማ ከመልካም አስተዳደርና ከኢኮኖሚ ጥያቄ ጋር እያገናኙት ይገኛሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ ከአልጄዚራ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ያደረጉት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የተቃውሞው መነሻ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው በማለት የመንግሥትን ግምገማ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ በተለያዩ ሠልፎች የተንፀባረቁት መፈክሮች የዴሞክራሲ መብቶችን የሚጠይቁና የአንድ ብሔር የበላይነት የነገሠበት አገዛዝ እንዲያከትም የሚጠይቁ ናቸው፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ በአማራ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ ፓርቲያቸው ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ እንደሚፈታው ተናግረዋል፡፡

ነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫም ፓርቲው (ብአዴን) የመሪነት ሚናውን በመወጣት ችግሩን እንደሚፈታው ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕዝቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች ድብልቅልቅ ያሉ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ደመቀ፣ ‹‹መፍታት የሚቻለውን እየፈታንና እያስረዳን እንሄዳለን፡፡ የማይፈቱትን በምክንያት በማስረዳት መግባባትን እንፈጥራለን፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ብአዴንን ከሕዝቡ ለመነጠል የሚካሄዱ አሉባልታዎችን አውግዘዋል፡፡ ‹‹በብአዴን ውስጥ ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ እንኳን በፖሊት ቢሮ ውስጥ በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ልዩነት የለም፤›› ብለዋል፡፡

በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ኩማ ደመቅሳ በዚህ ጉዳይ ሰሞኑን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ለተቃውሞ መነሻ ናቸው በሚል መንግሥት የለያቸውን ምክንያቶች ጠቅሰዋል፡፡

ከተለዩት ችግሮች ውስጥ መልካም አስተዳደር፣ ሰብዓዊ መብትና ኪራይ ሰብሳቢነት ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ችግሮች ለአመፅ መነሻ መሆን አይችሉም ብዬ አምናለሁ፤›› የሚሉት አምባሳደር ኩማ፣ ጥያቄው ግን መቅረብ ያለበትና የሕዝቡ ጠያቂ መሆንና ጭቆናን አልቀበልም ማለት ሊበረታታ የሚገባው ተግባር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በተቃውሞው ውስጥ የተነሳው ጥያቄ የሕዝብ መሆኑን የሚገልጹት አምባሳደር ኩማ፣ ‹‹ብጥብጡ ግን የሕዝብ ነው ብዬ አላምንም፤›› ብለዋል፡፡ በዚህ ብጥብጥ አዘል ተቃውሞ ውስጥ በአማራም ሆነ በኦሮሚያ ክልሎች ጎልተው የወጡት ሁለት ኃይሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኦሮሚያ ውስጥ ከተቃውሞው ተጠቃሚ የሆኑ ራሳቸውን ላለፉት 40 ዓመታት ወደ ሥልጣን ለማምጣት የሚፍጨረጨሩ ቡድኖች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች የትጥቅ ትግሉ እንዳበቃ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መጥተው የሽግግር መንግሥቱን በመቀላቀል ሥልጣን ለመያዝ መሞከራቸውን፣ በሽግግር መንግሥት ወቅትም የሽግግር መንግሥቱን ቦርቡረው ሥልጣን የመያዝ ዕቅድ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡

ኦነግ መሠረታዊ መዋቅር በኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው ቢሆንም የኦነግን አስተሳሰብ ተሸክመው የፋፉ በርካታ ቡድኖች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከኦነግ ውጪ የኦሮሞ እስላማዊ ግንባር፣ ኦሮሞ አቦ የሚባሉ በቅርፅ የተለያዩ ነገር ግን ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

‹‹የሁሉም ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብን መገንጠል ነው፤›› ብለው፡፡ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ ነው፡፡ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ሁለተኛው ኃይል የታየው በአማራ ክልል መሆኑን ይህም፣ ‹‹ትምክህተኛው ኃይል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ኃይል ሲጀመርም ያለፈው ሥርዓት እንዳይፈርስ የሚፈልግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው ሲጠቀሙ፣ የሃይማኖት እኩልነት ሲሰፍን የተዋረደ አድርጎ የሚያይ ኃይል ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይችን አገር ያዋረደ አድርጎ የሚያይ ነው፡፡ ይች አገር ተበላሸች፣ ይህ ባንዲራ ተዋረደ ብሎ የሚያምን ኃይል ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል የዚህ ኃይል አንቀሳቃሽ የነበረው የመላው አማራ ሕዝቦች ድርጅት (መአሕድ) እንደነበር ያወሱት አምባሳደር ኩማ፣ ‹‹አሁን ደግሞ ግንቦት 7 ተብሎ መጥቷል፡፡ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት ከእነዚህ ኃይሎች ፍላጎት ጋር መደበላለቅ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ኩማ የሰጡትን አስተያየት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ግን፣ ለ25 ዓመታት በሥልጣን ላይ የተቀመጠ ፓርቲና መንግሥት የራሱን ሥርዓት በኅብረተሰቡ ላይ ማስረፅና ጠቀሜታውንም ማስረዳት ኃላፊነቱ ሆኖ ሳለ፣ የራሱን ሕፀፅ በኢትዮጵያ ውስጥ በሌለ መዋቅር ላይ መጠቆም ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹ትምክህተኛ የሚባል ኃይል ሊኖር አይችልም፡፡ ከኖረም አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ መቀየር ካልቻሉ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደሉም፤›› በማለት አስተያየት ሰጪዎች ይወቅሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ወጣት ማኅበረሰብ የኢሕአዴግ ትውልድ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሆና ሳለ፣ ከሥርዓቱ ካልተጣጣመ ችግሩ የሥርዓቱ ፈጣሪዎች ነው በማለትም ይከራከራሉ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ዜጎችን እያፈነ ነው፡፡ የኦሮሞ መሬትን እየተቀራመተ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም ጋዜጠኞችን በማፈን፣ የሚቀናቀኑትን በማሰር ሰላማዊ ትግል በአገሪቱ ውስጥ እንዳይኖር አድርጓል በማለት ወቅሰዋል፡፡

የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው የተቃውሞው መነሻ የሚሉት ዶ/ር መረራ ገዢው ፓርቲ በምርጫ ማሸነፉን ቢገልጽም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹የራሱን ዜጎች የሚገድል አሸባሪ መንግሥት ነው፤›› ሲሉም ተችተዋል፡፡