Wednesday, 17 August 2016 13:23
በይርጋ አበበ
የኢትዮጵያ ምድር ፖለቲካዊ የሰላም አየር እየተነፈሰ አይደለም። በየቦታው የባሩድ እና የሞት ሽታ የተላበሰ አየር እየነፈሰ ነው ብሎ መናገር ባይቻልም አሁን ያለው ድባብ ግን ከላይ የተጠቀሰው አጋኗዊ ገለጻ እውነት የማይሆንበት ምክንያት የለም ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በሚያስብል መልኩ እና በኦሮሚያ ክልል ሁሉም ቦታዎች የተነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች እና አገሪቱን እየገዛ ያለው ኢህአዴግ ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ እየወሰደ ያለው የአጸፋ እርምጃ ሀይልን የተላበሰ መሆኑ ነው። ባለፉት አራት ሳምንታት ብቻ አገሪቱ ውስጥ ከመቶ በላይ ንጹሃን ዜጎች እና በርካታ የጸጥታ ሀይሎች ህይወት ማለፉን አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል።
በአማራ ክልል የተነሳውን የማንነት ጥያቄ እና በአሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣ በተመለከተ በክልሎቹ አብዛኞቹ ቦታዎች በየሳምነቱ ሰላማዊ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። በእነዚህ ሰልፎች ላይ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ከመሆናቸውም በላይ ለአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመትም ተከስቷል። እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ በአገሪቱ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ካሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መግለጫ ሰጥተዋል። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አገሪቱ ውስጥ ለተነሳው ግጭትና ግጭቱ ላስከተላቸው ቀውሶች ተጠያቂው አገሪቱን በብቸኝነት እየገዛ ያለው ኢህአዴግ ነው ሲሉ ተናግረዋል። የፓርቲዎቹን መግለጫ እና በመግለጫው ወቅት ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
የአገሪቱ ፖለቲካ ከአሁኑ ወቅት ቀደም ብሎ
የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሁን የተነሳው አገራዊ ቀውስ እንደሚነሳ ቀደም ባሉት ጊዜያት ጀምሮ ምልክቶች እንደነበሩ ይገልጻል። ፓርቲው “የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና በቅርቡ ደግሞ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ እስከተፈጠረው ከፍተኛ ቀውስ ድረስ ጉዳዮችን እየተከታተለ ፓርቲችን መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል” ሲል አስታውቋል። የኢዴፓ መግለጫ አክሎም “በዚህ ግጭት እና ተቃውሞ የሀገሪቱ ቀውስ ተባብሶ እንደ ሃገርም እንደ ህዝብም ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ከመክፈላችን በፊት መንግስት ህዝቡ እና መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የፖለቲካ ኃይሎች በተገቢው መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት ስናስተላለፍ ቆይተናል” ብሏል።
መድረክ በበኩሉ አሁን የተነሳው ግጭትና ቀውስ ሊነሳ እንደሚችል ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ለመገናኛ ብዙሃንና ለራሱ ለመንግስትም ሲያሳውቅ መቆየቱን ገልጿል። ፓርቲው “ላለፉት 25 ዓመታት ኢትዮጵያን በብቸኝነት ሲገዛ የቆየው የኢህአዴግ መንግስት ማሳሰቢያዎቻችንን አልሰማም በማለት እና ለጥያቄዎቻችን መልስ ባለመስጠት አሻፈረኝ ብሎ በትዕቢት በመሞላት በህዝብ እና በሀገር ላይ ጥፋት ማድረሱን ቀጥሎበታል” ብሏል።
ሁለቱ ፓርቲዎች በየመግለጫዎቻቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ “አጣብቆኝ”የፖለቲካ አለመረጋጋት እያመራች መሆኗን ያስታወቁ ሲሆን አሁን ላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ትልቁ ምክንያትም ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ ባለማግኘታቸው ነው ሲሉ ገልጸዋል። በተለይ መድረክ በመግለጫው አገሪቱ አሁን ላለችበት ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ናቸው ያላቸውን የቆዩ ችግሮች ሲገልጽ “ህዝባዊ እምቢታዎች ክስተት በቅርቡ የተከሰቱ ብቻ ሳይሆን ላለፉት 25 ዓመታት በኢህአዴግ እየተካሄዱ የቆዩ በህዝቦች ላይ የደረሱ የመብት ረገጣዎች ክምችት ውጤቶች ናቸው” ይላል።
ሰሞንኛው የአገራችን ፖለቲካዊ ቀውስ መጠን
ይህ ጽሁፍ እየተዘጋጀ በነበረበት ቀን ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት (ከእሁድ ነሀሴ 9 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ ማክሰኞ ነሃሴ 11 ቀን 2008 ዓ.ም) ድረስ በጎንደር ከተማ ከቤት ያለመውጣት አድማ ህዝቡ በማወጁ ከተማዋ ከማንኛውም ህዝባዊ እንቅስቃሴ ውጭ ሆና ሰንብታ ነበር። ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ በደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እንዲሁም በደቡብ እና ሰሜን ጎንደር ዞን የተለያዩ ከተማዎችም ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። በአንዳንድ የሰሜን ወሎ ከተሞች ደግሞ ለሰላማዊ ሰልፍ ከወጣው ህዝብ ጎን ለጎን የከተማዎቹ አስተዳደሮች ኃላፊዎች ህዝቡን ወደ ሰልፍ እንዳይወጣ የወጣውም በጊዜ እንዲመለስ በድምጽ ማጉያ ሲቀሰቅሱ እንደነበረ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በኦሮሚያ ክልልም ቢሆን ውጥረቱ እንደጠነከረ ነው።
የወቅቱን የአገሪቱ ሁኔታ በተመለከተ ኢዴፓ እና መድረክ ሲገልጹ “አገራችን ወደማትወጣው ቀውስ እየገባች ነው” ሲሉ ነበር ያስታወቁት። ኢዴፓ “አሁን በሀገራችን ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ነው ያንዣበበው” ሲል መድረክ በበኩሉ “ዛሬ ታላቂቷን ሀገራችንን ከማትወጣበት አረንቋ ውስጥ እየከተታት ይገኛል” በማለት አስታውቋል። “ኢህአዴግ በሀይል እንጂ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለህዝቡ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ባህሉም ባህሪውም አይደለም” ያለው መድረክ “የሃገራችን ችግሮች እየተከማቹ እና እየገዘፉ መጥተው ዛሬ ከሚገኝበት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ሲል የወቅቱን የአገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ የሚገኝበትን ደረጃ ገልጾታል።
የመድረክ ኃላፊዎች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ከጋዜጠኞች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል “በተለያዩ ከተሞች የተነሱት የህዝብ ጥያቄዎች የልማት ጥያቄዎች ናቸው ለእነዚህ ደግሞ መንግስት መልስ እንደሚሰጥባቸው እየተናገረ ባለበት ሰዓት እናንተ ግን ትልቅ አገራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄ አድርጋችሁታል። እውነት ጥያቄው እንደምታስቡት ከባድ ነው ወይ? የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰሞኑን በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥቃት መጠን ለማጣራት የላከውን አጣሪ ቡድን የኢትዮጵያ መንግስት እንዳልተቀበለው አስታውቋል። የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑን መግለጫ እንዴት ታዩታላችሁ? በሰላማዊ ሰልፉ ምክንያት ህይወት ጠፍቷል ጉዳትም ደርሷል። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ምክንያት ለሆነው ሰላማዊ ሰልፍ ተጠያቂው ማን ነው? በአማራ ክልል የተነሳው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነትን ጥያቄ በተመለከተ መድረክ በተለይም የመድረኩ አባል ፓርቲ ዓረና ትግራይ ጥያቄው መመለስ ያለበት በምን መልኩ ነው ይላል?” የሚሉት ይገኙበታል።
የመድረኩ ኃላፊዎች ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን ጨምሮ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል። “በመጀመሪያ ደረጃ ለ25 ዓመታት ስልጣን ላይ ያለን መንግስት በልማት ምክንያት ህዝቡ የልማት ጥያቄ ይዞ ሲወጣ የሚያሳየው የመንግስትን አስቦ እና አቅዶ የመስራት ችግር እንዳለበት ነው። ሁልጊዜ ድልድይ እና መንገድ ሰራንላችሁ ወይም ከፍተኛ የቻይና እዳ የተሸከመን ባቡር አመጣንላችሁ ከማለት ለልማት ጥያቄዎቹ በራሱ በጊዜ መልስ መስጠት አለመቻሉ የመንግስት ችግር ነው። ከዚህ ውጭ አንተ እንደምትለው (ጠያቂውን ጋዜጠኛ) የህዝቡ ጥያቄ የልማት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹትም ከ200 በላይ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ የወጣ ህዝብ ጥያቄው ቀላል ነው ልትለው አትችልም” ሲሉ ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያወጣውን መግለጫም መድረክ የሚደግፈው መሆኑን የገለጹት የመድረክ ኃላፊዎች “በሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ተጠያቂው ኢህአዴግ እና ኢህአዴግ ብቻ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ በወቅቱ በቦታው ተገኝተው መልስ የሰጡት የመድረኩ ምክትል ፕሬዚዳንትና የፋይናንስ ኃላፊው አቶ ካህሳይ ዘገየ “ኢህአዴግ የማንነት ጥያቄ ተፈቷል እያለ ቢደሰኩርም መቀሌ ላይ ተካሂዶ በነበረው የፓርቲው ጉባዔ ላይ ግን ሁለቱ አጎራባች ክልሎች ጥያቄውን ይመልሱ ብሎ ማለፉ የተመለሰ የማንነት ጥያቄ አለመኖሩን ያሳውቃል። የወልቃይትን ጉዳይ በተመለከተም ዓረና ግልጽ የሆነ አቋም አለው። እሱም የህዝቡን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታት በህዝበ ውሳኔ (Referendum) መፈታት አለበት ብሎ ያምናል” ሲሉ መልሰዋል።
የባለቤት አልባዎቹ ሰልፎች ተጠያቂ
ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ከተካሄደ እና ያለምንም የጸጥታ ችግር ከተጠናቀቀ በኋላ (ሰልፉ ሁከትና ጥፋት ሳያደርስ መጠናቀቁን የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ በአማራ መገናኛ ብዙሃን ነው የገለጹት) በተከታታይ በየሳምንቱ የእረፍት ቀናት ተመሳሳይ ሰለፎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች (መድረክ ከ200 በላይ ከተሞች ናቸው ይላል) ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። እነዚህን ሰልፎች መንግስት “ባለቤት አልባ ሰልፎች” ሲል ገልጿቸዋል። በእነዚህ ሰልፎች ምክንያትም ዜጎች መሞታቸውንና በአካላቸው ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጸው መንግስት ከሰልፉ ጀምርባ በውጭ አገር እና አገር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃቸው እንዳለበት አስታውቋል።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት መድረክ እና ኢዴፓ ግን “የችግሩ ምክንያት ኢህአዴግ ነው” ሲሉ ተከላክለዋል። ሰላማዊ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግስት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ ሰልፍ እንዳያሳውቁ በመከልከሉ ህዝቡ በራሱ ጊዜ በብሶት ያካሄደው ሰልፍ መሆኑን ተናግረዋል። ለጠፋው የሰዎች ህይወት መልስ የሰጠው የመድረክ መግለጫ “ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ጥያቄዎቹን አንግቦ ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት መብቱ የሆነውን ህዝብ በሀይል ለመደፍጠጥ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደፎከሩትም አልቀረ የሰሞኑን ሀገራዊ ትርምስ እና የዜጎች እልቂት አስከትለው እኛም ሁኔታውን በከፍተኛ ሀዘን እና ምሬት ለመታዘብ ተገድደናል። በመላው ኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል ጎንደር እና ባህርዳር ከተሞች ለደረሰው የዜጎች እልቂት ኃላፊነቱ ከኢህአዴግ መንግስት ውጪ ሊሆን አይችልም” ብሏል።
የተቀመጠ የመፍትሔ ሀሳብ
ኢዴፓ “ችግሮቹን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ጊዜው አልረፈደም” ያለ ሲሆን መፍትሔ ይሆናል ያለውን ሃሳብም አቅርቧል። በኢዴፓ የቀረበው የመፍትሔ ሃሳብ “አሁን በሃገራችን ህልውና ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከልና ወደ ዘላቂ መረጋጋት ውስጥ ለመግባት ሁሉም ወገን ከምንጊዜውም በበለጠ የኢትዮጵያን ህዝብ ፍላጎት እና ጥቅም ሊያስጠብቅ በሚችል መልኩ በኃላፊነት ሊንቀሳቀስ ይገባል” ብሏል። ፓርቲው ጨምሮም “የወቅቱን የሃገራችንን ሁኔታ እና ለዘመናት በሃገራችን ፖለቲካ ስር እየሰደደ የመጣውን የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ያለመተማመን፣ የቂም በቀልና የመገዳደል ስሜትን የማስወገድ እና የሀይል የስልጣን ሽግግርን ወደ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለመለወጥ የሚያስችል ታሪካዊ መሰረት ለመፍጠር ብሔራዊ እርቅ ወሳኝ ነው” ብሏል። ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም ወገን ኃላፊነት በተሰማው መንገድ መንቀሳቀስ እንዳለበት የገለጸው ፓርቲው የግሉም ሆነ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ሚዲያው የሃገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥል ቅስቀሳ ታቅበው ለሃገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲንቀሳቀሱ የገለጸ ሲሆን “የመንግስት መገናኛ የአንድን ወገን አሰልቺ ቅስቀሳ ብቻ ማቅረባቸውን ትተው የሁሉም ወገን ሃሳብ የሚስተናገድበት መድረክ እንዲፈጥሩ” ሲል ኢዴፓ መልዕክቱን አስተላልፏል። የሃይማኖት ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እና በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎችም ለብሔራዊ እርቅ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ኢዴፓ ጨምሮ ገልጿል።
መድረክ በበኩሉ “ህዝባችን ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት አስቸኳይ ምላሽ በመስጠት ሁኔታዎችን እንዲያረጋጋ። መላው የሃገራችን ህዝቦች እና ለሀገራችን ፖለቲካ ችግሮች የተለያዩ መፍትሔዎች የሚያቀርቡ ወገኖች ሁሉ ኃላፊነትን በተላበሰ መልኩ ዘላቂ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ፍለጋ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪያችንን እንስተላልፋለን” ብሏል። መድረክ ጥሪ ያቀረበላቸው የትኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆነ ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ (በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትንም ያጠቃልላል? ተብሎ ተጠይቋል) መልስ የሰጡት የፓርቲው አመራሮች “ለሀገራችን ሰላም የሚያመጣ ከሆነ ከማንኛውም ፓርቲ ጋር ውይይት መካሄድ አለበት” ሲሉ መልሰዋል።
መድረክና ኢዴፓ ሁለቱም በአጽዕኖት ጥሪ ካቀረቡባቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች መካከል የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚለው ይገኝበታል። ሁለቱ ፓርቲዎች የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከኢህአዴግ ጋር ሲሰሩ (ድጋፍ እና እርዳታ ሲሰጡ) ኢህአዴግ በአገሪቱ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን በደል ታሳቢ እንዲያደርጉ ተማጽነዋል። ለዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። መድረክ እና ኢዴፓ በየፊናቸው “ፖለቲካዊ ስጋት ያጠላበት” ያሉት የኢትዮጵያ ምድር ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት እንደተፈጠረ ገልጸው መፍትሔ ያሉትንም በዚህ መልኩ አስቀምጠውታል።
ስንደቅ