ከ ኆኅተብርሃን ጌጡ

 

-ለ 25 ዓመታት የተገነባዉ የዘረኝነት ግንብ በመፈራረስ ዋዜማ ላይ

ቀኑ ዓርብ ነሐሴ 12 ቀን 2016 ነበር። የትዕይንተ ሕዝቡ መገናኛ ማዕከል ቦታ ዋናዉ ባቡር ጣቢያ አካባቢ ነዉ። በተጠቀሰዉ የሰልፉ መጀመሪያ ሰዓት ኢትዮጵያዉያን አካባቢዉን አጥለቀለቁት። ፍራንክፈርት ከተማ በአረንጟዴ፣ ቢጫና ቀይ ኅብረ-ቀለም ባለዉ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ደምቃና ተዉባ ትታያለች። ከሁሉም የጀርመን ከተሞች በመምጣት ፍራንክፈርትን ከኢትዮጵያ ከተሞች አንደኛዋ አስመስሏት ዉሏል። መነኮሳትና ቀሳዉስቱም ልብሰተክህኗቸዉን ደርበዉ ሰልፉን አድምቀዉታል። የሴቶች እህቶቻችንም ቁጥር ከሁልጊዜዉ በተለየ ቁጥሩ አይሎ የታየበት ብቻ ሳይሆን፣ ቁጭትና ሀገራዊ ስሜታቸዉም ከፊታቸዉ ላይ ይነበብበት የነበረ ሰልፍ ነዉ። የሰልፉ መጀመሪያ ፍራንክፈርት ዋናዉ ባቡር ጣቢያ ሆኖ፣ መዳረሻዉ ሄሰን ቲሌቪዥን ጣቢያ ( Hessischer Rundfunk) እንዲሆን ነዉ የተዘጋጀዉ። ይህም የሆነበት ምክንያት የትዕይንተ ሕዝቡ (የሰላማዊ ሰልፉ) መደረግ ዓላማዎች ለጀርመን ሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን እንዲተላለፍ ለማድረግ የታሰበበት እንደሆነ የሰልፉ አስተባባሪዎች በአፅንኦት ይናገራሉ። ካለፈ ተመክሮ በመነሳት ሚዲያዎች ወደ እኛ የማይመጡ ከሆነ፣ እኛ ወደ ሚዲያዎቹ በመሄድ የሰልፉ ዓላማ ወደምንኖርበት ሀገር ሕዝብ ጆሮ መድረስ ስላለበት ሂደን በራቸዉን መክፈት አለብን በሚል ዘዴ የታሰበ እንደነበር አዘጋጆቹ ጨምረዉ ይናገራሉ። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢም የዓይን ምስክርነት ይሰጥበታል። ይህ ብቻም አይደለም። የሰላማዊ ሰልፉ መነሻና መድረሻ የቦታ ርቀት ወደ 6 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ሲሆን በዚህ ረዥም የእግር ጉዞ ግራና ቀኝ ሰልፈኛዉን እየተመለከተ ለሚገኘዉ የከተማዋ ኗሪ በጀርመንኛና በእንግሊዘኛ ቑንቑዎች የተዘጋጁትን የሰልፉን ዓላማዎች የሚገልፁትን መፈክሮች በበቂም ለማደል እንደታቀደ ጊዜዉ አጭር ቢሆንም የታሰበበት ሰልፍ እንደነበርና እንደተሳካም አዘጋጆቹ አበክረዉ ይናገራሉ። ይህም በመሆኑ በጀርመንኛ ቑንቑ ተፅፎ በተበተነዉ ፅሁፍ ማለትም … Wie lange werden Diktatoren, die die eigene Bevolkerung umbringen noch von Deutschland und der EU unterstutzt ???? …. የገዛ ሕዝባቸዉን ለሚገሉና ለሚጨፈጭፉ አምባገነኖች ማለትም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ መንግሥታት የጀርመን መንግሥትና የኤዉሮፓ ህብረት እስከ መቼ ነዉ እርዳታቸዉንና ድጋፋቸዉን የሚቀጥሉት? የተሰኙ መልዕክቶች ተላልፈዋል። ይህ ዓይነቱ መልዕክትም ታክስ ከፋዩ ሕዝብ የሀገሩን መንግሥት ለምን ብሎ እንዲጠይቅ የሚያስችለዉ አቀራረብ የሰላማዊ ሰልፉ አቅም መሆኑን በተግባር ለማሳየት ተሞክሯል። በዕለቱም ምሽት በጀርመን አገር ሁለተኛዉና ትልቁ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማለትም ZDF (Zweites Deutsches Fernsehen) እና ሰልፉ የተካሄደበት የሄሰን ክፍለ ሀገር ዋንኛ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሆነዉ ሄሲሼር ሩንድፉንክ (Hessischer Rundfunk) ኢትዮጵያዉያን ለምን ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እንዳስፈለጋቸዉ ተገቢ በሆነ መንገድ በዜና መልክ የሚዲያ ሽፋን አግኝቶ፣ ለጀርመን ሕዝብ መቅረብ ችሏል። ዓላማዉም ይህ ነበር እንጅ ለመዋጋት አልነበረም።

ታዲያ የሰላማዊዉን ሰልፍ ዜና ላዳመጠና የሰልፉን የትዕይንተ ሕዝብ ትርጉም ምንነት ከመነሻና እስከ መዳረሻ ለተከታተለ፣ ኢትዮጵያዊ ብዙ ነገሮች በአእምሮው ብልጭ ይሉበታል። በመጀመሪያ ደረጃ ያን ያህል ረዥም መንገድ ሰልፈኛዉ ሲጟዝ ፖሊስ ግራና ቀኝ ቆሞ የመኪና መንገዶች ሰልፈኛዉ እስኪያልፍ እየተዘጉ ነዉ። ዲሞክራሲ ባደገበት አገር ሕዝባዊ ሰልፍ ከብር አለዉ። አሽባሪዎች ተብለን አልተፈረጅንም። በሻዕቢያ ተላላኪነትም አልተጠረጠርንም። የአጋዚ ጦር በቦታዉ ስላልነበር መሞት ቀርቶ መገፍተር የደረሰበት ሰልፈኛም አልነበረም። አደለም መገፍተር በግልምጫ የታየም አልነበረም። እነሱ በቦታዉ ኖረዉ ቢሆን ኖሮ፣ ፍራንክፈርት በሚገኘዉ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ቆንስል አጠገብ ሰልፈኛዉ ሲያልፍ አንድ ቆራጥ ወጣት ኢትዮጵያዊ የእነሱን ኦፊሴላዊ ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከቆንስላዉ ቢሮ ጎን የመስቀል እርምጃ ሲወስድና ሲያዉለበልብ፣ ያለምንም ጥርጥር ቢያንስ መጠነኛ የሰዉ ሕይወት ማለፉ አይቀሬ ነበር። እና ማደግና የዲሞክራሲ ማበብ ለሰልፍም ሆነ ለሕዝባዊ ጥያቄዎች መልሱ ጥይት አይደለም። የእኛ መሪዎች የዲሞክራሲን ቃል ባፋቸዉ ደጋግመዉ ይጠሩታል እንጅ ከተግባሩ ጋር ግን አይተዋወቁም። ማወቅም አይፈልጉም።

ለሃያ አምስት ዓመታት የተገነባዉ የዘረኝነት ግንብ በመፍረስ ዋዜማ ላይ እንደሚገኝ ኢትዮጵያ ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገር ከሚኖረዉ ሕዝባችን አንደበት የሚነገረዉ የሰሞኑ የሰላማዊ ሰልፎች መልዕክት አንድ እራሱን የቻለ የምሥራች ዜና ነዉ። በዕለቱ በፍራንክፈርቱ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ይስተጋቡ ከነበሩት መፈክሮች መካከልም …አማራም፣ ኦሮሞም አንድ ነዉ፣ የጋራ ሀገሩም ኢትዮጵያ ነች፣ ያለፈዉ አኩሪም ሆነ አሳፋሪ ታሪካችን የጋራችን እንጅ፣ የአንድ ወገን ዕዳ አይደለም፣ በየቦታዉ የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች በሕዝብ ይሁንታ ይፈታሉ እንጅ፣ በጫካዉ የወያኔ ሕግ አይዳኙም፣ የፖለቲካ ደመኛችን ወያኔ እንጅ፣ የትግራይ ሕዝብ ምንጊዜም ወገናችን ነዉ ወዘተ…. የተሰኙ መፈክሮች በአማርኛና በኦሮሞኛ ቑንቑዎች ሲስተጋቡ ዉለዋል። ያለምንም ጥርጥር ኢትዮጵያዊነት አሽንፎ እየወጣ ነዉ። ትናንት ለጎሪጥ በመተያየት ሁሉም በየፊናዉ ያደርገዉ የነበረዉ ሰልፍ ቀርቶ፣ ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን ትዕይንተ ሕዝብ ስናደርግ ከዚህ የበለጠ ገዥዉን መደብ የሚያሸማቅቅ የፖለቲካ ድል ምን አለ? የሃያ አምስት ዓመቱ የፖለቲካ መዘዉር ኢትዮጵያዊነት እንዲኮስስ ተደርጎ፣ በምትኩ፤ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ሱማሌነት፣ ትግሬነት፣ ስልጤነት….ወዘተ እንዲነግሱ በማድረግ ኢትዮጵያዊነታችን ሆን ተብሎ እንዲደበዝዝ ስዉር የፖለቲካ ደባ ተሰርቷል። ይህን ዘገባ እያዘጋጀሁ እያለሁ ጎረምሳዉ የመንግሥት የኮሜኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ማለትም በእሱ አነጋገር በጣም ተናዶ፣ (… እሳትና ጭድ የሆኑ አስተሳሰቦች ሁላችንም አንድ ነን በተለይም አማራም፣ ኦሮሞም አንድ ነዉ) የሚለዉ የወቅቱ የኢትዮጵያዊነትን አሸንፎ የመዉጣት ድል የሚያንፀባርቀዉ መልዕክት … እንዴት አንድ ሊሆኑ ይችላሉ? በማለት በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ብስጭቱ ከፊቱ ላይ ይነበብ ነበር። ጋዜጠኞቹ ሰዉየዉን እንዴት ይመለከቱት እንደነበር ለተከታተለ ሰዉ ይህ ሰዉ በዕዉኑ ጤነኛ ነዉን? ይሉ እንደነበር ያለማጋነን ከፊታቸዉ ማንበብ ይቻላል። ጋዜጠኞቹም አሳዘኑኝ። የሚያምኑበትን ሳይሆን በእንጀራ ምክንያት መንግሥት እንዲባል የሚፈልገዉን ማዘጋጀት ስላለባቸዉ መግለጫዉን እየተከታተሉ ለጎሪጥ በመተያየት ይጎሻሸሙ ነበር። እንዳይሳሳቁ ካሜራዉ ያጋልጣቸዋል። የሆድ ሕመም ሆኖባቸዉ፣ የማይቻል የለም ቻሉት። እነሱም አንድ ቀን ነፃ ይወጣሉ። ሁሉም ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋንና ተመስገን ደሳለኝን መሆን አይችሉም። እንደ ሻማ ቀልጦ ለሌሎች መብራት የመሆን መስዋዕትነት ግለሰብም ሆነ ትውልድ ቁጥሩ ገፍ አይደለም። ይህ ጥቂቶች የሚታደሉት በደም የሚፃፍ የታሪክ አሻራ ነዉ። መፅሃፉ …የተጠሩ ብዙዎች የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸዉ… እንደሚለዉ መሆኑ ነዉ። መስዋዕትነቱም እንደዚያዉ ነዉ። ሁሉም አይታደለዉም። አይደፍረዉምም።

የሰሞኑ በየሀገሩ የሚደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች የሀገር ቤቱ እንቅስቃሴ ነፀብራቆች መሆናቸዉ ለሁላችንም ግልፅ ነዉ። በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊም የተፈጠረባት ምድር ሀገሩ ፣ የተወለደበት ቤተሰብ፣ ያደገበት ቀዪ ሁሉም አካባቢ በጥይት እየነደደ መሆኑን ጧት ማታ ያስተዉላል። በዓይን በብሌኑ እያየ ለማመን እስከሚያቅተዉ ይከታተላል። እንደ ሰዉ ለሚያስብ አርፎ መቀመጥን አይመርጥም። የወገን ደም እየፈሰሰ በር ዘግቶ መቀመጥ፣ አባባሉ እራሴንም ይጨምራል የኅሊና ቁስል እየሆነ ከመኝታ ያባንናል። በመብት ማስከበርና በነፃነት ጥያቄ ድርድር ባለመኖሩ የሕዝቡ ጥያቄ መብታችን ይከበር ነዉ። ባለብዙ ብሄረሰቧ ሀገር ባንድ ጥቂት አናሳ ቡድን ተቀፍድዳ እየተገዛች ስለሆነ፣ ይህ ይብቃና የሁላችንም ሀገር መሆኗ በተግባር ይረጋገጥ ነዉ ጥያቄዉ። ገዥዉ መደብ ግን …የብሔረሰቦቿን መብት አስከብሮ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መንግሥት ከእኛ የተሻለ ሰለሌለና ስለማይመጣም ዝምብላችሁ ሰጥለጥ ብላችሁ ተገዙ…. ነዉ የሚለዉና የግል ጡሩምባዎቹ በሆኑት ኢቲቪና የኢትዮጵያ ራዲዎች ጧት ማታ የሚለፍፈዉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በኢቲቪ የምትቀርብልን ኢትዮጵያና እኛ በዓይናችን ብሌን የምንመለከታት መሬት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ እናንተ እንደምትነግሩንና እናንተ እንደምታቀርቧት ሆና ስለማናገኛት የጥቂቶች የምድር ገነት ለብዙኃኑ የምድር ሲኦል የሚያደርግ የዘር ፖለቲካ መርሆን አቁሙና ለእኛ ለሁላችን ሀገር የሆነች ኢትዮጵያ ትኑረን ነዉ። ይህ ዕዉን ሊሆን ከቻለ ደግሞ የጥቂቶች ሀገር መዝረፍና በሃያ አራት ሰዓት ሚሊዪነር መሆን የሚችሉበት ዘመን ለያከትም ነዉ። አናሳዉ ቡድን በትረ ሥልጣኑን ለብዙሃኑ ሊያስረክብ ነዉ። አሳዳጁ ተሰዳጅ ሊሆን ነዉ። አሳሪዉ ታሳሪ ሊሆን ሊገደድ ነዉ። አንደኛዉ የበኩር፣ ሌላኛዉ እንደ እንጀራ ልጅ መብት የመታየት መኖር ሊያከትም ነዉ። በገዛ ሀገሩ የመንገድ ዳር ለማኝ ሆኖ፣ የሌሎችን ፎቅ የሚቆጥርበትና ወደ ሰማይ አንጋጦ የሚመለከትበት ጊዜ ማክተሚያ ሊደርስ ነዉ። ይህ ግን በሰላም የማይታሰብ ነዉ። ግድያዉ መፍትሄም ባይሆን ለቀጣይነቱ በየቦታዉ ርችቶች እየታዩ ነዉ። አንድ ገበሬ ሽንኩርት ጭኖ ወደ ገበያ ሲገሰግስ አህያዉ ከተማዉ አካባቢ ስትደርስ ለገመችበት። ጭራሽ መንቀሳቀስ አቆመች። ይኽዉ ገበሬ የግድ ካልተራመድሽ ብሎ አህያዋን ባልተወለደ አንጀቱ በዱላ ይቀጠቅጣት ጀመር። ይህን የተመለከተ የአካባቢዉ አልፎ ሂያጅ መንገደኛ …ጌታው እንዲያዉ ለመሆኑ ሕሊና የለህም ተዉ አትቀጥቅጣት፣ ነፍሷ መዉጣት እኮ ነዉ የቀራት ሲለዉ፣ አይ ጌታየ! ኀሊናስ የለኝም ጨርሻለሁ፣ ወደ ገበያ የምወስደዉ ሽንኩርት ብቻ ነዉ የቀረኝ። እሱንም ይኽዉ መንገድ ላይ እያስቀረችዉ ነዉ..? እንዳለዉ ባለጊዜዎች የሚታያቸዉ ሟቹ ሳይሆን የደራዉ የሀገር ዘረፋ ገበያቸዉ ነዉ።

እስኪ ማን ይሙት የአንድ ሀገር ሕዝብ ከዳር እዳር ተንቃስቅሶ ለመብቱና ለነፃነቱ መከበር ከእንግዲህስ ይብቃ ብሎ የመንግሥት ለውጥ እንዲደረግ በሰላማዊ እምቢተኝነት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ …ባለቤት የሌላቸዉ አመፆችና እንቃስቃሴዎች በየቦታዉ እየተደረጉ… ብሎ ማፌዝና ስለሆነም መንግሥት ሰላም የማስከበር ሕገመንግሥታዊ ኀላፊነት ስላለበት… በሚል መመሪያ የጅምላ ግድያ በሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ ማድረግ ተገቢ ነበርን? ያዉም የሕዝብ ብሶት ወለደኝ ከሚለዉ ኢሕአዴግ። ደግሞስ በአንድ ሀገር እንቅስቃሴ ከሕዝብ በላይ ምንስ አለና ነዉ ባለቤታቸዉ የማይታወቁት እንቅስቃሴዎች በማለት ሕዝባቢዉን አመፅ ለማጣጣልና ቦታ ላለመስጠት መንግሥታዊ ሽወዳ የሚደረገዉና የሚቀለደዉ። በሽወዳ 25 ዓመታት አልፈዋል። ብሔረሶቦችን እርስ በርስ በማጋጨት የሥልጣን ዕድሜን ማራዘም ተችሏል። ግን አሁን ጊዜዉ አከተመ። ማጣፊያዉ አጠረ። እንዲህ ዓይነቱ የፖለቲካ ጨዋታ የተበላ ቁማር ሆኗል። ሕዝቡ ኦሮሞም አማራም አንድ ነዉ ብሎ ዘመረ። በቅርብ ጊዜ የምናየዉ ዕዉነታ ቢኖር ኦሮሞዉና አማራዉ ብቻ ሳይሆን አንድነታቸዉን የሚገልጹት፣ በሀገሪቱ የሦሥተኛነትን ቁጥር ይዞ የሚገኘዉና አኩሪ ታሪክ ያለዉ የትግራይ ሕዝብም በከንቱ የፈሰሰዉ የኦሮሞ፣ የአማራ ወንድሞቻችን ደም የእኛም ደም ነዉ ብሎ እንደሚነሳና በእሱ ስም የሚነግዱትን የፖለቲካ ነጋዴዎች አቁሙ! ከኢትዮጵያ ሕዝብ የሚነጣጥለንን ስዉር የፖለቲካ ጨዋታ ምዕራፍ ዘግታችሁ ብሔራዊ የአንድነት አጀንዳ ክፈቱ! አለበለዚያ …ዉጉዝ ከመ አርዮስ… ከእናንተ ጋር አይደለንም እንደሚላቸዉ ጥርጣሬ ሊገባን አይገባም። ይህ ዕዉን የሚሆንበትን ጊዜ ለማቃረብ ደግሞ ሁላችንም የየአቅማችንን የቤት ሥራ እንሥራ። ከፋፋይ የዘር ፖለቲካን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፍነንና ገንዘን እንዳይነሳ አድርገን እንቅበረዉ። ማቅ እናልብሰዉ። ይጥቆር። ያንጊዜ ኢትዮጵያዊነት አብቦ ይፈካል። ኢትዮጵያዊነት ይነግሳል። የገዥዎቻችንም ዓላማ ይከሽፋል። ከሥር መሠረቱም ይናጋል። በየቦታዉ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች መምሕር በቀለ ገርባም ሆነ ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ ብርቅዬ የነፃነት አርበኞቻችን እንጅ፣ አሽባሪዎች አይደሉም በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ያስተጋባዉም መልዕክቱ ጥልቅ የሚሆነዉ ለዚህ ነዉ። እነ እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ እነ ተመስገን ደሳለኝ የሰላማዊ ትግል ቀንዲሎች እንጅ የጥፋት ዘመን መልዕክተኞች አለመሆናቸዉን ሕዝቡ በአንደበቱ ምስክርነቱን የሚቸራቸዉም ለዚህ ነዉ። አብርሃ ደስታ ከእስር ቢፈታም በትግራይ ተወላጅነቱ ሳይወገንለት የሥርዓቱ ሰለባ ሆኖ መሰቃየቱን አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ የማይዘነጋዉ የቅርብ ጊዜም ትዝታ ነዉ።

በሁሉም ሕዝባዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች መንግሥት ገታራ አቑም ባይወስድ ኖሮ፣ ሀገራዊ መፍትሔዉ በሀገሪቱ የብሔራዊ ዕርቅ መዉረድ ነበር። ለእራሳቸዉም የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ ለሀገሪቱ መድኀንና አንድና አንድ የፖለቲካ ፈዉሱ አሁንም ብሔራዊ ዕርቅ ከሁሉም አማራጮች የቀዳሚነቱን ሥፍራ ከመዉሰድ እንደ ብቸኛ መፍትሄም ባይወሰድ (ስለዘገየ) የአማራጭነቱ ሚና ጉልህ ሥፍራ ይኖረዋል። ግን የቤተ መንግሥቱ ወንበር አንድ ጊዜ ከተቀመጡበት ላለመልቀቅ አዚም ያለዉ ይመስለኛል። ኀሊና ይጋርዳል። ዓይን ያዉራል። ለሕዝብ የተገባዉ ቃል ሁሉ ይረሳል። የማሰቢያ ጭንቅላትም ይደፈናል። ለዚህም ነዉ አንድ የወሎ ገበሬ በኢሕአዴግ የሥልጣን መጨበጥ ዋዜማ ሰሞን ነፃ ባወጡት የሰሜን ወሎ አካባቢ በተደረገ ስብሰባ፣…ነፃ አዉጭዎች ነን ካላችሁማ ምን ይደረግ፣ እስኪ ደግሞ እናንተን እንያችሁ… ግን እናንተም አሁን ማር ሆናችሁ ቀርባችሁን በሁዋላ እንደ ደርግ እሬት እንዳትሆኑብን… በማለት ነበር ነቢዩ ገበሬ አስቀድሞ የነገራቸዉ። ወጣም ወረደ፣አልታደልንም። ደም ካልተገበረ በሰላማዊ መንገድ መሠረታዊ ለዉጥን ማምጣት አልተቻለም። ይህ ዕድል በ 1997 በቅንጅት ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት አመለጠ። አሁን የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይሆኑ ሕዝብ በቃኝ ብሎ ተነሳ። ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማሳወቅ እንጅ፣ ሕገመንግሥታዊ ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልገንም አለ። በሕገመንግሥቱ ላይ የሰፈረዉ ሰንደቅ ዓላማም ሕዝቡ የሚቀበለዉ አይደለም ብሎ ከዳር እስከዳር የቀድሞዉን ባንዲራ ይዞ ወጣ። ባጭሩ በተዘዋዋሪ መንገድ ሕዝቡ ሕገመንግሥቱን እንደማያምንበትና እንደማይቀበለዉም መልዕክቱን አስተላለፈ። ይህ ብቻም ሳይሆን የሀገሪቱ የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ ሕገመንግሥቱ ስለሆነ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕገመንግሥቱን የሀገሪቱ መመሪያ ገዥ ሕግ አድርጎ እንደማይቀበለዉ አሳወቀ። ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን ይኽዉ እኛ በሕገመንግሥታችን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለማክበር በባንዲራዉ መካከል በተለያዩ ሕብረ ቀላማት አስዉበን የብሔር ብሄረሰቦችን እኩልነት መብት በሚያስከብር መልኩ ያወጣነዉን ሕገመንግሥት በመጣስ ጠባቦችና ትምክህተኞች (ኦሮሞዎችና አማራዎች ለማለት) ጨቁነዉ ሊገዙህ ተነስተዉብሃል የሚል የማደናገሪና ከፋፋይ ቅስቀሳ ከማድረግ ወደሁዋላ እንደማይል ሳይታለም የተፈታ ነዉ። እንዲያዉ ለነገሩ …ዶሮን ሲያታልሏት… ካልሆነ፣ በዓመት አንድ ጊዜ የሰንደቅ ዓላማና የብሔረሰቦች ቀን በዓል እያከበሩ ማስጨፈር የብሔረሰቦች እኩልነት ተከብሯል ለማለት ያስደፍራል? በዚህ መታለልም ለመገዛት አምችቷል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ምናልባት አንዳንድ የዋሆች የወልቃይት የአማራን የማንነት ጥያቄ ለሰሞኑ እንቃስቃሴ እንደ ምክንያት ሊቆጥሩት ይችላሉ። የወልቃይት ኗሪዎች ቀያቸዉን ከተነጠቁበት ጊዜ ጀምሮ በየማሳቸዉ እያንጎራጉሩ፣

እናንተም እረሱ እኛም እናርሳለን፣

መኽር (ሰብል) ሰብሳቢዉን አብረን እናያለን።

እያሉ የዉስጥ አንጀታቸዉ አርሮ ዓመታትን አሳልፈዋል። ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያጤነዉ የሚገባዉ፣ወያኔዎች ከኢትዮጵያዊነት ሌላ የተለየ አመለካከት ከሌላቸዉ መጀመሪያዉኑ ገና ጫካ እያሉ፣ ለምን ከዉጭ አገር ጋር ወልቃይትን ወደ ትግራይ በማጠቃለል ለምሳሌ (ከሱዳን) ወሰን አስፈለጋቸዉ? መንግሥት ከሆኑ በሁዋላስ ለምን በትግራይና በጎንደር መካከል ወሰኑ ወደ ቀድሞዉ (ተከዜ) እንዲመለስ አላደረጉም? ጎንደርም፣ ትግራይም የኢትዮጵያ ግዛቶች ናቸዉ የሚል ዕምነት ቢኖራቸዉ ኖሮ፣ ይህ ጥያቄ ይህን ያህል ደም አፋሳሽ መሆን አልነበረበትም። አሁንም የተደበቀ ዓላማ እንዳላቸዉ ለአንዳፍታም መጠራጠር የማያስፈልገዉ እዉነታ ነዉ። ወጣ ወረደም ሰበቡ የወልቃይት የአማራ የማንነት ጥያቄ ሆኖ ብቅ ይበል እንጅ፣ መሬት ላይ የሚነበበዉ ዕዉነታ በሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት ከደርግም እየባሰ ስለመጣ፣ ብሶት የወለደዉ ሆኖ የመጣ መንግሥት መሆኑንም ስለዘነጋ፣ የሃያ አምስት ዕድሜዉም ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ሊያደርገዉ ስላልቻለ፣ የተሰጠዉ የሙከራ ጊዜም ስላለፈ፣ የብሔራዊ ዕርቅ በሩንም ክርችም አድርጎ ስለዘጋ፣ ባጭሩ መንግሥታዊ አስተዳደሩን ስላላወቀበትም ወደ መጣበት ባይመለስም ከሥልጣን ይዉረድ ነዉ ጥያቄዉ። በጣም የሚያስገርመዉ እኮ ሰሞኑን በየቦታዉ በሚካሄዱት የገዥዉ መደብ የአዉራ ካድሬዎችም ሆኑ የሌሎች ዉሎ ገብ ካድሬዎች የስብሰባ መድረኮች ላይ የሚንፀባረቁት ዲስኩሮች በእኛ ጊዜ ከሞተዉ በደርግ ጊዜ የተገደለዉ ይበልጣል እየተባለ፣ የሰዉ ልጅ ሞት (ግድያ) ቁጥር/አኀዝ መብዛትና ማነስ እንዴ ዲሞክራት መንግሥትነት የመለኪያ መመዘኛ ሆኖ እየቀረበ ነዉ። አኀዝን የምንጠቀምበት ብዙዉን ጊዜ ለኢኮኖሚ ዕድገት ማነፃጸሪያነት ነበር እንጅ ለሞት የሰዉ ቁጥር ብዛት ማወዳደሪያነት እስታትስቲክስ አልነበረም። እና ይህ የጤነኝነት አካሄድ ነዉ ትላላችሁ ወገኖቼ? ገሰሰዉ እንግዳ የሚባል ፀሐፊ ይመስለኛል …ታሪክ አጉዳፊዉ የአልባንያ ደብተራ… በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃዉ መፅሃፍ …ደርግም፤ ወያኔም ሁለቱም ገዳይ መንግሥታት ናቸዉ። አገዳደላቸዉ ግን የተለያየ ነዉ። ደርግ ጅል መንግሥት ስለነበረ በስም ጠቅሶ እነገሌን፡ እነገሌን ገድያለሁ ብሎ ማታ በሬድዮና በተሌቪዥን መግለጫ ይሰጣል። ወያኔዎች ደግሞ እራሳቸዉ ይገሉና …እንዲያዉ ለመሆኑ ማን ይሆን የገደለዉ ብለዉ ከሟች ቤተሰቦች ዘንድ መጥተዉ፣ ዓይናቸዉን በጨዉ አጥበዉ ለቅሶ ይደርሳሉ በማለት የዉስጥ ማንነታቸዉንም ስለሚያዉቅ ትክክለኛ ባሕርያቸዉን በሚገባ ገልጾታል። አለመታደልም ሆኖ በገደሉት ሰዉ ቁጥር ብዛትና ማነስ ካለፈዉ የተሻሉ ዲሞክራሲያዊ መንግሥትነታቸዉን እየለኩበት ነዉ።

ሀገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ አገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች ዓላማቸዉ አንድና አንድ ይመስለኛል። የሕዝቦቿ እኩልነት የተረጋገጠባት፣ ሁሉም ዜጎቿ የእኛ ሀገር ናት የሚሏት ኢትዮጵያ ትገንባ ነዉ ማሳረጊያዉ። የመንግሥት ለዉጥ በተደረገ ቁጥር፣ ሥልጣን ላይ ላለዉ መንግሥት ብቻ የሚጠቅም ብቻ ሕገመንግሥት በየጊዜዉ የሚወጣባት አገር ሳትሆን፣ ሀገር የምትመራበት፣ ሕዝብ የሚተዳደርበት፣ መንግሥትም ለሀገርና ለሕዝብ ተጠያቂ የሚሆንበት እንጅ ከሀገርና ከሕዝብ በላይ ሆኖ፣ ሕዝብ ለሚያሸብር ሕገመንግሥት በተግባር ላይ የማይዉልባት ሀገር እንድትኖረን፣ ባጭሩ የአንድ አገር ሕዝብ በአፈሙዝ የሚገዛበት አገር ከመሆን ዘመን ነፃ ሆነን የመኖር መንግሥታዊ ባሕል እንገንባ ነዉ እንቃስቃሴዉ። በትረ ሥልጣን የጨበጠዉ ወገን ደግሞ በግሉ ሚዲያዎች ከእኔ የተሻለ መንግሥት ሊመጣም ስለማይችል የእኔን የፖለቲካ ቀመር ተቀብላችሁ፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተጠምቃችሁና ቆርባችሁ ከኖራችሁና ከተገዛችሁ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የመቀጠል ዕድሏ ሰፊ ነዉ። አለበለዚያ የሀገሪቱ ማጣፊያ ያጥራል፣ እኛም ከሌለን ሀገሪቱ ትበታተናለች እየተባልን ነዉ፣ እየተስፈራራን ያለነዉ። ሕዝቡ ግን በደማችን ነፃነታችን ይከበራል እንጅ፣ ከእናንተ በደጅ ጥናት የሚገኝ የዜግነት የመብት ከበሬታ እንደማይገኝ እናዉቃለን እያለ ነዉ ድምፁን ከፍ አድርጎ እያስተጋባ የሚገኘዉ። ይህ የተራራቀ ፅንፈኛ አመለካከት እንዴት ይታረቅ? ነዉ ጥያቄዉ። የፍራንከፈርቱ ሰላማዊ ሰልፍ ዓላማም ከሕዝቡ ጥያቄዎች ጎን በመሰለፍ ለሚኖርበት ሀገር የተለያዩ ተቑማት መልዕክቱን ማስተላለፍ ነዉ። ይህንንም በተሳካ ሁኔታ አካሂዷል። ባጭር ጊዜ ዉስጥ በተደረገ መሰናዶ ፍራንክፈርት አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ቁጥሩ በርከት ያለና ትርጉም ያለዉ ትዕይንተ ሕዝብ በማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሙን በተግባር አሳይቷል። ለሚኖርበት ሀገር መንግሥትና ሕዝብም ዓላማዉን በትክክል አሳዉቑል። ወሳኙ የሀገር ቤቱ ትግል መሆኑ ቢታወቅም፣ በየሀገሩ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎችም የራሳቸዉ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸዉ ሊዘነጋ አይገባዉም።

Leave a Reply