August 18, 2016

voa-amharic

 

 

 

 

(አቻምየለህ ታምሩ)

ይድረስ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ጋዜጠኛ አዳነች ፍስሀዬ

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ ካለሽበት ቦታ ይድረስሽ። በዛሬው እለት ማለትም ረቡዕ ነሐሴ ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. «በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ውይይት» በሚል ርዕስ በአሜሪካ ድምጽ የአማርኛው ክፍል ብርሀኑ መንግስቱን፣ አለማንተ ገብረሥላሴና ገላውዲዮስ አርአያን ጋብዘሽ ስለወልቃይት ያቀረብሽውን ዝግጅት በጥሞና ተከታትየዋለሁ። ይህንን ግልጽ አስተያየት እንድጽፍልሽ የገፋፋኝ ምክንያት አንቺ አዘጋጅና አቅራቢ ሆነሽ ባሰናዳሽው በዚህ «የምሁራኖች» የውይይት መድረክ ላይ ይዘሽ የቀረብሽው የግል አቋምና የተሳሳተ ግንዛቤ አመክንዮ የሌለው መሆኑን በመታዘቤ በጉዳዩ ላይ ጥናት እንዳደረገ ሰው ምናልባት የተሳሳትሽው የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነሽ ከሆነ በሚል ስህተትሽን ታርሚ ዘንድ እርምት ለመስጠት ነው። (በVOA ሰኞ ነሃሴ 11 እና ረቡዕ ነሃሴ 17 2008 ዓ.ም. የተደረጉትን ውይይቶች ክፍል 1 እና ክፍል 2 ከዚህ ጹሁፍ መጨራሻ ላይ ማዳመጥ ይቻላል።)

«ወልቃይት የትግራይ ነው» የሚለውን አቋምሽን ለማንበር ቢያንስ ሶስት ስህተት የሆኑ መነሻዎችን ጠቅሰሻል። የመጀመሪያው መነሻሽ «የወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ የቦታ ስሞች <የትግርኛ ስሞች> መሆናቸውን» ያነሳሽበት መከራከሪያሽ ነው። ሁለተኛው መከራከሪያሽ «ወልቃይቶች ትግርኛ ቋንቋ ስለሚናገሩ ወደ ትግራይ መካለል አለባቸው» ያልሽው ሲሆን ሶስተኛው ምክንያትሽ ደግሞ «የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮምቴ አባል የሆነው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና ሎሎችም የወልቃይት ተወላጆች የሆኑ የኮሚቴው አባላት ከወያኔ ጋር ሆነው ደርግን መታገላቸው ትግሬ ያደርጋቸዋል» በማለት ያቀረብሽው ነው።

በመጀመሪያ «ወልቃይት የትግራይ ነው» እንድትይ ያስቻለሽን የቦታ ስያሜዎች አመክንዮሽን እንመልከት። ይህንን «አመክንዮ» የኒዮርኩ ገላውዲዮስ አርአያ ለኔ ግብረ መልስ በጻፈውና ትግራይ ኦንላይን ባሳተመው «Beyond Ethnocentric Ideology and Paradigm Shift for a Greater Ethiopian Unity» ጽሁፉ ላይ አንስቶት ነበር። እኔም ለዚህ ደካማ መከራከሪያ «Forceful Annexation, Violation of Human Rights and Silent genocide: A Quest for Identity and Geographic Restoration of Wolkait-Tegede, Gondar, Amhara, Ethiopia» በሚል በጻፍሁት ሰፊ አርቲክል በቂ መልስ ሰጥቸው ነበር። ለጊዜው አንቺ ባነሳሽው «መከራከሪያ» ላይ ያለኝ አስተያየት እንዲህ የሚል ነው።

በቅድሚያ አንቺና ገላውዲዮስ አርአያ የወልቃይት፣ጠገዴና ሁመራ የተወሰኑ የቦታ ስያሜዎች የትግርኛ ስሞች ናቸው የምትሏቸው የአካባቢ ስሞች የትግርኛ ስሞች ሳይሆኑ የግዕዝ ስያሜዎች መሆናቸው ግንዛቤ ይያዝ እላለሁ። ሲቀጥል ስሞቹን የትግርኛ ስሞች እንኳ አድርገን ብስወስድ ተመሳሳይ ስሞች በመላው ኢትዮጵያና ኤርትራ ውስጥ አሉና የናንተ መደምደሚያ ገዢ ሀሳብ አይደለም። የቦታ ስም የማንነት መገለጫ ከሆነ ኦጋዴን ያለው ቀብሪ ዳህር የትግራይ መሬት ሊሆን ነው ማለት ነው። የቦታ ስሞ የማንነት መገለጫ ከሆነ ኤርትራ ውስጥ ያሉ የትግርኛ የቦታ ስሞች ሁሉ የትግራይ ክልል አካል ሊሆኑ ነው ማለት ነው። በእውነቱ እንደዚህ አይነቱ መነሻ ውሀ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም። እንደዚህ አይነት መከራከሪያ በየትኛውም ህልዮት ትርጉም ያለው ድምዳሜ ላይ አያደርስም።

ይህ የአንቺና የገላውዲዮስ መከራከሪያ በቀላሉ ፉርሽ የሚሆነው በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አካባቢዎች የግዕዝ፣ የአማርኛና የአረብኛ ስሞች መሆናቸውን ስናስታውስ ነው። ለምሳሌ የሚከተሉት የቦታ ስሞች በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ውስጥ የሚገኙ የአረብኛ ስም ያላቸው ቦታዎች ናቸው። ሞይ ካድራ [ማይ ካድራ አላልሁም]፣ ቧኸር፣ህለትግርሽ፣ረውያን፣ አብደላፊ፣ በዋል፣ ኋጃ፣ ሎግዲ፣ ህለጂን፣ ሁመራ፣ ህለትሚማ፣ አደባይ፣ ሸሪፋ አህመድ፣ ሸሪፋ ጎላ፣ኑጓራ፣ ገላዕዘራብ፣ ገላዕነሀር፣ መቻቺ፣ እምባራኪድ፣ አበጡር፣ መዋለድ፣ ወዘተ…ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የአረብኛ የቦታ ስሞች ናቸው። ከአረብኛ ስሞች በተጨማሪ በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ፍየል ውሃ፣አወራ፣አፅመጥንት፣30አይን፣ወፍ አርግፍ፣ባናት፣ ወይ እናት [በወያኔ አውሮራ/ድቭዥን ተብሎ የተቀየረ]፣ ማክሰኞ ገብያ [በወያኔ ወደ ከተማ ንጉስ የተቀየረ]፣አንድ አይቀዳሽ፣ ወዘተ… የአማርኛ ስም ያላቸው የቦታ ስያሜዎች ናቸው።

እና በአንቺና በገላውዲዮስ አርአያ «አመክንዮ» መሰረት ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ውስጥ ያሉት እነ ሞይ ካድራ፣ ቧኸር፣ ህለትግርሽ፣ ረውያን ፣ በዋል፣ ኋጃ፣ ሎግዲ፣ ህለጂን፣ ሁመራ፣ ህለትሚማ፣ አደባይ፣ ሸሪፋ አህመድ፣ ሸሪፋ ጎላ፣ኑጓራ፣ ገላዕዘራብ፣ ገላዕነሀር፣ መቻቺ ፣ እምባራኪድ፣አበጡርና መዋለድ፣ ወዘተ የአረብኛ ስሞች ስለሆኑ የሱዳን መሬቶች መሆን አለባቸው ማለት ነው? ስም የማንነት መገለጫ ከሆነ በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ያሉት እነ ፍየል ውሃ፣ አወራ፣ አፅመጥንት፣ 30አይን፣ ወፍ አርግፍ፣ባናት፣ ወይ እናት፣ ማክሰኞ ገብያ፣ አንድ አይቀዳሽ፣ ወዘተ… የመሳሰሉት የአማርኛ ስሞች ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራን የአማራ አያደርጓቸውም ማለት ነው? ኦጋዴን ውስጥ ያለው ቀብሪ ዳህር ቃሉ ትግርኛ ስለሆነ የትግራይ መሆን አለበት ማለት ነው? በናንተ መከራከሪያ መሰረት አክሱምና ተምቤን የሚሉት ስሞች አገውኛ ስለሆኑ ግዛቶቹ የአገው ምድር አካል መሆነ አለባቸው ማለት ነው? እስቲ መልሽልኝ? እነዚህን አራት ጥያቄዎች እናንተ ወልቃይትን፣ ጠገዴንና ሁመራን ለትግራይ ለማድረግ በተነሳችሁበት በዚህ የመጀመሪያው አመክንዮ ማዕቀፍ ትይዩ መሰረታዊ የሎጂክ ህጎችን ሳትጥሺ ከፍ ብዬ ያነሳኳቸውን አራት ጥያቄዎች ከመሰሽልኝ የተነሳሽበትን ሀሳብና የደረስሽበትን ድምዳሜሽን አገዛሻለሁ።

ሌላው ያነሳሽው አመክንዮ አልባ መከራከሪያ «ወልቃይቶች ትግርኛ ስለሚናገሩ ወደ ትግራይ ክልል መካለል አለባቸው» በሚል የደረስሽበት ድምዳሜ ነው። እስቲ ልጠይቅሽ ጋዜጠኛ አዳነሽ፡- አንቺ አሜሪካን አገር ስትኖሪ እንግሊዝኛ አቀላጥፈሽ ትናገሪያለሽና እንግሊዛዊ ነሽ ማለት ነው? መለስ ዜናዊ አማርኛ ከመናገር አልፎ ቅኔ ሳይቀር ይቀኝበት ነበርና አማራ ነው ማለት ነው? አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አማርኛ ይናገራልና አማርኛ የሚናገረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ አማራ ነው ማለት ነው? ሱዳን ድንበር አካባቢ የሚኖሩ የወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ሰዎች አረብኛ ይናገራሉ፤ አረብኛ ስለተናገሩ ሰዎቹ አረብ ወይንም ሱዳናዊ ናቸው ማለት ነው? ጎንደር ውስጥ ቅማንቶች አሉ። 42 ቀበሌዎችን ማዕከል ያደረገ ልዩ ወረዳ መስርተዋል። የልዩ ወረዳው የመስሪያ ቋንቋ ደግሞ አማርኛ ነው። እና ቅማንቶች አማርኛ ስለተናገሩ አማሮች ናቸው ማለት ነው? እኔ ትግርኛ እችላለሁ፤ ትግሬ ነኝ ማለት ነው? እስቲ ትግርኛ የቻለ ወልቃይቶች ሁሉ ትግሬ የሚሆኑ ከሆነ አማርኛ የሚናገሩ ወልቃይቶች ሁሉ አማራ የማይሆንበትን አመክንዮ አስረጅኝ?

«ወልቃይት የትግራይ ነው» ብለሽ ለመደምደም ያነሳሽው ሶስተኛውና የመጨረሻው መከራከሪያሽ ደግሞ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮምቴ አባል የሆነው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱና ሌሎች የወልቃይት ተወላጆች የሆኑ የኮሚቴው አባላት ከወያኔ ጋር ሆነው ደርግን መታገላቸውን ነው። ይህ መከራከሪያ በውነቱ ውሃ ካለመቋጠሩም ባሻገር የወያኔን የትግል ታሪክ ላነበበ ሰው አስቂኝ ትርክት ነው። ውድ አዳነች፡- ህወሀት ውስጥኮ አይደለም የአማራ ተራ ወታደርና የኮሚሳር መሪ ይቅርና ከአስራ አንዱ የህወህት መስራቾች መካከልኮ አንዱ አማራ ነበር። ምናልባት ይህንን ታሪክ አታውቂው ይሆናል። መቀሌ በሚገኘው የህወሀት «ሰማዕታት» አዳራሽ ብትሄጂ ከህወሀት አስራ አንዱ መስራቾች መካከል ወረድ ብዬ ታሪኩን የምነግርሽን አማራ ስም ታገኝዋለሽ። አስገደ ገብረ ሥላሴም «ገሀዲ» ብለው በጻፉት መጽሀፋቸው አማራውን የህወሀት «ቼ ጎቬራ» አውስተውታል።

አማራው የህወሀት መስራች አብተው ታከለ ይባላል። አብተው የተወለደው በ1929 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ 774 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተንጣለለችው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ 118 ኪሎ ሜትር ርቀት ገባ ብላ በምትገኝው ድብ በሐር ውስጥ ነው። ድብ በሐር በደባርቅ ወረዳ የምትገኘው ከተማ ስትሆን ከአምስት ሺ በላይ ኗሪዎች እንደሚኖሩባት ከአስር አመት በፊት የተካሄደው የህዝብና የቤት ቆጠራ ውጤት ያሳየል። የድብ በሐር ከተማ በርካታ ሰዎች በደርግ የግፍ አገዛዝ ከተወረወሩበት ሊማሊሞ ገደል ስር ትገኛለች። በህወሓት ታሪክ ውስጥም ጉልህ ስፍራ ሊይዝ የሚገባውን፤ ነገር ግን አመድ አፋሽ የሆነን አብተውንም አፍርታለች።

ስለአብተው የታገለለት፣ የደማለት፣ የቆሰለለት፣ የወጣለት፣ የወረደለት… ድርጅት ህወሀት ታሪኩን አልዘከረለትም። አብተው እድሜው ሲጎረምስ ከድብ በሐር በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው የሽሬ ከተማ ሄደ። ኑሮውን በዛው አደረገ። የሽሬ ከተማ ግምጃ ቤት ሀላፊ የሆኑትን የባላባራስ አፅባሀ ልጅ ወ/ሮ አለም አፅበሀንም አግብቶ ሶስት ጉልቻ መሰረተ። ባለንባራስ አፅበሀ የሌላኛው የህወሓት መስራች ስሁል አየለ [ገሠሠ] አጎት ናቸው። ይሄ ሁኔታም አብተው እና ስሁል እንዲቀራረቡ መንገዱን ከፈተላቸው። እናም ከእለታት አንድ ቀን «የትግራይ ህዝብን ከአማራ ጭቆና ለማላቀቅ እና ነፃይቱን ትግራይ ለመፍጠር» ድርጅት መመስረቱ አስፈላጊ እንደሆነ ተወያዩ፤ እንደ ዘመኑ ደንቆሮ ትውልድ አብተው ምንም እንኳ አማራ ቢሆንም፤ ‹‹የተጨቆነ ካለማ…›› ሲል ለመታገል መወሰኑን አስገደ ገብረ ሥላሴ በመጽሀፋቸው ያስነብቡናል። እናም አብተው ከሌሎች 10 የትግራይ ልጆች ጋር በመሆን ወደ ደደቢት በረሃ አመራ። አስራ አንድ ሆነው ስድስት አሮጌ መሳሪያ ታጥቀው ዱር ቤቴ አሉ። እናም በደደቢት በርሀ ህወሓትን አማራው አብተው ከአስር ትግሬዎች ጋር አብሮ መሰረተ።
እነዚህ አስራ አንድ የመጀመሪያው በረሃ የገቡና ህወሀትን የካቲት አስራ አንድ ቀን 1967 ዓ.ም. የመሰረቱ ታጋዮች በስም ስንዘረዝራቸው የሚከተሉት ናቸው፡- ስሁል አየለ [ገሰሰ]፣ አረጋዊ በርሀ፣ ስዩም መስፍን [አምባዬ]፣ ግደይ ዘርአፅዮን [ፋንታሁን]፣ አጋዚ ገሰሰ [ዘርኡ]፣ አስፋሐ ሐጎስ [ሙሉ]፣ ፀሀዬ ካሕሳይ [አረፈአይኔ]፣ ምስጋና ቡርሀ [ካሕሳይ]፣ ቀለበት ታዬ [ንጉሴ]፣ አስገደ ገ/ስላሴ [ወ/ሚካኤል] እና አብተው ታከለ [ሚካኤል] ይባላሉ። እነዚህ ሰዎች የህዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ መስራቾች ናቸው። ነገር ግን ከእነሡ አንዱ የትግራይ ተወላጅ አይደለም። አማራ ነው። ከፍ ብዬ እንዳልሁት አማራው አብተው ታከለ ነው። ደደቢት በረሃ አብረውት የገቡ ጓደኞቹ ትግሬዎች የትግል ስም አውጥተውለት ‹‹ሚካኤል›› ሲሉ ሰየሙት።

ሆኖም ግን ህወሓት የአብተውን መስዋትነት ካደው። ዘረኛው ወያኔ አብተው ታከለ አማራ ስለሆነ ከህወሓት መስራቾች ታሪክ ዝርዝር ውስጥ በመደለዝ መስዕዋትነቱን ነጠቀው። በእጅጉ የሚያስገርመው ትግራይ በቆመው የሰማዕታት ሀውልት ስር የአስሩ የህወሀት መስራቾች ስም እና ፎቶ አለ። የአብተው ታከለ ግን ስሙ አለ፣ ፎቶው ግን የለም። ይህ ሰው ፎቶ የለውም እንዳይባል ደርግ ከወደቀ በኋላም በህይወት ነበር። እስከ 2000ዓ.ም. በጎንደር ደባርቅ፣ ደብ በሐር ከተማ ከባለቤቱ ጋር ይኖር ነበር። የአራት ልጆችም አባት ነው። ከዚህ አለም ያለፈው በአንጀት ድርቀት ተሰቃይቶ ነው። አብተው ከስምንት አመት በፊት የሚንከባከበው አጥቶ ህይወቱ አለፈ። አማራው የህወሓት ቼ ጉቬራ የታገለለት ድርጅት ህወሀት አንድም ቀን ሳይጠይቀው ከዚህ አለም በሞት ተለየ። የሰራው ታሪክም የአማራ ብሄር ተወላጅ በመሆኑ ብቻ ተቀበሮ እንዲቀር የተፈረደበት- አማራው የህወሀት ቼ ጉቬራ።

ከህወሓት መስራቾች ውስጥ የተወሰኑት መጽሐፍ ፅፈዋል። ከአስገደ ገብረ ሥላሴ በስተቀር አረጋዊ በርሄ፣ ገብሩ አስራትም ሆነ ግደይ ዘራፅዮን በመጽሐፋቸውም ሆነ ቃለ ምልልስ በሚሰጡበት ጊዜ ስለአብተው አማራነት ነግረውን አያውቁም። የብአዴን መስራቾችም ስለዚህ ጉዳይ ሲያነሱ አልተሰሙም። ስለማያውቁ ነው እንዳይባል በደንብ ያውቃሉ። ምናልባት ህወሓት የጠላውን መጥላት፣ ህወሓት የወደደውን መውደድ የሚለው ያልተፃፈው የህወሓት ህግ አስሮአቸው ሊሆን ይችላል።

አየሽ ጋዜጠኛ አዳነች፡- ከህወህት ጋር መታገል የግድ ትግሬ አያደርግም። የህወሀት መስራቹ አብተው ታከለ አማራ ነው፤ ግን ከህወሀት ጋር ታግሏል። አብተው ከህወሀት ጋር የታገለው ደርግን ለመጣል እንጂ ትግሬ ለመሆን ስላልነበረ ደርግ ከወደቀ በኋላ አብተው ወደ ትውልድ ስፍራው ድብ በሐር ተመልሶ አማራ ሆኖ ኖረ! መቼም ከህወሀት መስራቾቹ አንዱ አማራ መሆኑን ስትሰሚ ተራ ወታደር ሆነው የታገሉት እነ ኮሎኔል ደመቀም ሆነ ሌሎች የወልቃይት አማሮች በተራ ወታደርነትና በኮሚሳር መሪነት ከህወሀት ጋር ደርግን ለመጣል ስለታገሉ እነሱ «እኛ አማራ ነን» እያሉ ከህወሀት ጋር ስለታገላችሁ የግድ ትግሬ ሁኑ ማለት ነውር እንደሆነ የምትገነዘቢ ይመስለኛል። ስለዚህ ከወያኔ ጋር መታገል ትግሬ አያደርግምና እነኮሎኔል ደመቀ ከወያኔ ጋር ስለታገሉ «አማራ አይደሉም፤ ትግሬ ናቸው» ያልሽው መከራከሪያ ክብደት እንደማያነሳ ከህወሀት መስራቹ ከአብተው ታከለ የህይወት ታሪክ መረዳት የቻልሽ ይመስለኛል።

ከወያኔ ጋር መታገል የግድ ትግሬ እንደማያደርግ ሁለት ተጨማሪ ታሪካዊ አብነቶችን ልጨምር። በቅርቡ «The Eritrean Liberation Front: Social and Political Factors Shaping Its Emergence, Development and Demise, 1960-1981» በሚል ሚካኤል ወልደ ጊዮርጂስ ተድላ የጻፈውን የሁለተኛ ዲግሪ ቴሲስ እያነበብሁ ነበር። የሚገርምሽ ጀብሀ ውስጥ ተዋጊ የነበሩ የወልቃይት ልጆች ነበሩ። መቼም እነዚህ የወልቃይት ሰዎች ከጀብሀ ጋር ስለተዋጉ ኤርትራውያን ናቸው የሚል መከራከሪያ የምታነሽ አይመስለኝም። ሁለተኛው አብነት አንቺ የምታውቂው የማነ ጃማይካ ነው። የማነ ጃማይካ ወያኔን ሊሰልል በሻዕብያ ተልኮ ህወሀት ውስጥ ሰጥሞ የቀረ ወዶ ገብ ነው። የማነ ጃማይካ ከወያኔ ጋር ሆኖ ደርግን ስለተዋጋ የኢትዮጵያ ትግሬ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ እነ ኮሎኔል ደመቀም ከወያኔ ጋር ደርግን መዋጋታቸው መታየት ያለበት እንደ አማራው አብተው ታከለና እንደ ኤርትራዊው የማነ ጃማይካ ነው።

አዳነች:- ከፍ ብዬ ያነሳሁት አመክንዮ ሁሉ አንቺ ካነሳሻቸው መከራከሪያዎች አንጻር እንጂ ወልቃይት የአማራ መሆኑን የሚያስረዳ የታሪክ ማስረጃ አጥቼ አይደለም። እንዴውም ከሰሞኑ ከአስራ አራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ ደርግ ስልጣን መጨረሻ ድረስ ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ የማንና በየትኛው የአስተዳደር መዋቅር ስር እንደነበሩ የሚያሳዩ ከ40 በላይ የታሪክ ሰነዶችንና ከ15 በላይ ካርታዎችን ከጥንታዊ መጽሀፍቶች ሰብስቤ ሰፋ ያለ አርቲክል በመጻፍ በኢንተርኔት ለቅቄያለሁ። የአርቲክሉ ርዕስ ከፍ ብዬ የጠቀስሁት ነው። ምናልባት ስለወልቃይት ያለሽ የተሳሳተ ግንዛቤ ከወገናዊነት ያልመነጨ ከሆነ የሰበሰብኋቸውን ከ700 ዓመታት በላይ የሚሸፍኑ የታሪክ ድርሳኖችና የካርታ ማስረጃዎች ብዙ ሳትወጪና ሳትደክሚ የኔን አርቲክል በማንበብ ብቻ ስለወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ ታሪክ የጠራ አመለካከትና ግንዛቤ እንዲኖርሽ ታነቢው ዘንድ በአክብሮች ጋብዝሻለሁ።

ሰናይ ጊዜ!

(በVOA ሰኞ ነሃሴ 11 እና ረቡዕ ነሃሴ 17 2008 ዓ.ም. የተደረጉትን ውይይቶች ክፍል 1 እና ክፍል 2 )

ምንጭ    ወልቃይት ዶት ኮም

Leave a Reply