በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አስተያየት ላይ  አስተያየት

welkait

ምሁርን መተቸት ይቻላል? ይቻላል እንደምትሉ በማመን መቀጠሌ ነው። አዎ ደሞም የሚቻል ይመስለኛል። በኛ ሀገር ነውር ሆኖ የሚያስቀጣው መንግስትን መተቸት እንጂ በሌላው ማንኛውም ሰው ሃሳብ ላይ ሃሳብ ቢሰጡ ክፋት የለውም። እርግጥ ከፖለቲካ ውጭም ቢሆን መተቻቸት የለመድነው ባህል ስላልሆነ ሲተች የሚወድ ብዙ ሰው የለም። ለነገሩማ የብልሹ ፖለቲካ ባህላችን ምንጭ ይኼው አሳዛኝ ማህበራዊ አስተሳሰባችን አይደል? ብቻ ፕሮፌሰር በክርክር የሚያምኑ በሳል ምሁር እንደሆኑ ስለማምን ያለስጋት በሃሳባቸው ላይ ሃሳብ ልሰነዝር ደፈርኩ።

ፕሮፌሰር፥ወልቃይት የማነው? የማይረባ ጥያቄ፥ በሚል ርእስ በብሎጋቸው ያወጡትን በጎልጉል ድረገፅ ላይ ካነበብኩ በኋላ የሚደገፍም የሚነቀፍም ነጥብ አገኘሁበት። በአንድ በኩል ጥያቄው በዘር ሳይሆን ባገር መነፅር ሊታይ ይገባል። ወልቃይት የትግራይም ያማራም ሳይሆን የኢትዮጵያ ነው ማለት በተለይ የጎሰኝነትን መርዘኛ ፖለቲካ ለምንፀየፍ ሰዎች ምቾት ይሰጣል። ምናልባትም ለ25 አመታት ከዘረኝነት ሸሽቶ ግን ደግሞ የዘረኝነት ጦስ ሰለባ በመሆን ፍዳውን ሲቆጥር የኖረውን ያማራ ህዝብ በቁጭትና በንዴት ዘረኞች ባዘጋጁለት የዘረኝነት ወጥመድ እንዳይገባ ለመከላከል ይጠቅም ይሆናል። እኔም ብሆን ወልቃይትን ሱዳኖች ወሰዱት እስካላሉኝ ድረስ አማራ ሰፈረበትም ትግሬ, ዖሮሞ ያዘውም ጉራጌ አያሳስበኝም።

ወልቃይት በትግራይ አስተዳደር ስር እንዲሆን የተፈለገበት ምክንያት አስተዳደራዊ ሳይሆን ጎሰኝነት መሆኑ ሲታሰብ ግን ወልቃይት የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ያማራም ነው ለማለት ያስገድዳል። ዘረኛው መንግስት ወልቃይት ወደትግራይ ቢጠቃለል ላስተዳደር ያመቻል ቢለን ይገባን ነበር። ወልቃይቶች ትግርዎች ናቸው፦ ስለዚህ ወልቃይት የትግራይ ነው ሲል ግን ራሱ በቆረጠው ዱላ ከመከላከል ሌላ አማራጭ የሚኖር አይመስለኝም። ከዚህም ሌላ ክርክሩ ወልቃይት የትግራይ ነው ወይስ የኢትዮጵያ የሚል አይደለም። በተግባር የቀረበው ጥያቄ አካባቢው ያማራ ክልል ነው ወይስ የትግራይ የሚል ነው። ወልቃይት ያማራም የትግሬም ሳይሆን የኢትዮጵያ ነው የሚል ክርክር ማቅረብ ምርጫ ውስጥ የሌለ መልስ ነው። ምርጫው ውስጥ የሌለ መልስ መስጠት ደግሞ ነጥብ ስለማያሰጥ በዚህ ክርክር ላይ ለፕሮፌሰር ነጥብ አልሰጠኋቸውም። እርሳቸውም ቢሆኑ በመምህርነት ዘመናቸው ምርጫው ውስጥ የሌለ መልስ ለሰጠ ተማሪ ነጥብ የሰጡ አይመስለኝምና በዳኝነቴ አይቀየሙም።

በመጨረሻም በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ከአቶ መለስ ጋር ያደረጋችሁትን ያማራ አለ የለም ክርክር ሰምቼ በሃሳብቆ ተስማምቼ ነበር። ምክንያቱም በኔም የትውልድ አካባቢ ?አማራ? የሚለው ቃል የሃይማኖት እንጂ የዘር ወይም የጎሳ መጠሪያ ስላልነበረ ነው። ከ25 አመታት በኋላ ግን ሃሳብዎን ያለመለወጥዎን ስረዳ አቶ መለስን አመሰገንሁት። ምክንያቱም እሱ አማራን በፈጠረበት ዘመን አማራ እንደአማራ ያልነበረ ቢሆንም ከ25 አመታት የግፍና ጭፍጨፋ ዘመን በኋላ ግን አማራ ሳይወድ በግዱ የራሱን ማንነት ፈጥሯል። ኢትዮጵያዊነት ብቻውን ከሞት እንዳላዳነው ሲረዳ ለራሱ ተጨማሪ ስም ለማውጣት ተገዷል። እናም ዛሬ አማራ አለ። አማራ ባይኖር ኖሮ አማራ አይሞትም ነበር። በገዢው መንግስት ፊታውራሪነት በየክልሉ ያለቀው ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን አማራም ነበር። እናም አማራ ዛሬ ሲጠሩት ወይ ለማለት ተገዷል። ሌሎች በስሙ እየጠሩ አለህ ሲሉት ለኢትዮጵያ ሲል ብቻ የለሁም ቢል አንድ እግሩን ጅብ እየበላው አጠገቡ የተኛውን ጓደኛውን፥ እባክህ አትንቀሳቀስ፤ ጅብ ታስበላኛለህ፥ ያለውን ፈሪ ያስመስላል። እና ፕሮፌሰር ይቅርታ ያድርጉልኝ እንጂ በጠንካራ ያንድነት ስሜትዎ ባደንቀዎትም በዚህ ክርክር ላይ ግን አላሳመኑኝም። ረጅም እድሜ እመኛለሁ።

ህሩይ ደምሴ

zobar2006@gmail.com

ምንጭ         _       “ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ


Leave a Reply