‪ግርማ ካሳ‬

የአዲስ አበባን ሰልፍ በተመለከተ

ዛሬ በአዲስ አበባ ሊደረግ ታስቦ የነበረው ሰልፍ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስዱ መንገዶችን ሁሉ አገዛዙ ስለዘጋና ቁጥሩ እጅግ በጣም ብዙ የሆነ የታጠቀ ሃይል በመረጨቱ ሳይደረግ ቀርቷል።፡

ሕዝብ ድምጹን የማሰማት ሙሉ መብት እንዳለው ሕገ መንግስቱ ይናገራል። ሆኖም ሕወሃት በድጋሚ በአዲስ አበባ ሕዝቡ ድምጹን የማሰማት መብቱ ገፏል።

የሕወሃት መሪዎች ብዙ ጊዜ እንደ አልጃዚራ ባሉ ሜዲያዎች እየቀረቡ ሕዝቡ ድምጹን የማሰማት መብት እንዳለው ይናገራሉ። ሆኖም ግን ሕዝብ ድምጹን እንዳያሰማ፣ አዲስ አበባ የጦር ቀጠና እንድትመስል ማድረጋቸው ሰዎቹ ምን ያህል በርግጥ ከሕዝቡ እንደተጣሉ የሚያመለክት ነወ።

አንዳንድ ወገኖች ያንን የአገዛዙ አፈና ሰብሮ ለምን እንደ ባህር ዳርና እንደ ጎንደር ህዝብ አልወጣም በሚል አላስፈላጊና እንጭጭነት ያለበት አስተያየትም ሲሰጡ እያነበብኩ ነው። ለነዚህ ወገኖች ዘጠና ሰባትን እና በቅርቡ ደግሞ አይሰስን በመቃወም በተጠራው ሰልፍ የነበረዉን ሁኔታ እንዲያስቡ እመክራቸዋለሁ። አሁን ብቻ አይደለም ሕወሃት አዲስ አበባ ሲገባ እንኳን. ይሄንን ዘረኛ አገዛዝ ከጅምሩ የተቃወመ ሕዝብ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ በአገዛዙ ከፍተኛ ስቃይ የደረሰበትና የመረረው፣ ለአገርና ለነጻነትም ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው።

ይልቅ የአዲስ አበባ ህዝብ ነቅሎ ለምንድን ነው ያልወጣው የሚል ጥያቄ በመጠየቅ ሁኔታዉን መረዳት ያስፈለጋል።

ሕወሃቶች የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰልፍ ስላልወጣ፣ “እኛን ደግፎ ነው፤ የጸረ-ሰላም ሃይሎችን ስለተቃወመ ነው” የሚልዝ ዝባዝንኪ ሊያወሩ ይችላሉ። በሜዲያቸው ትልቅ ሽፋን ሰጥተዉት። እኔ እነርሱን ብሆን ግን ዛሬ፣ ሕዝብ አልተነሳም ብለው ከሚመጻድቁ፣ ቢነሳ ኖሮ ግን ምን እንሆን ነበር ብለው፣ ለገ፣ ከነገ ወዲያ ሊነሳ እንደሚችልም በማሰብ በቶሎ ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጁ የሽግግር መንግስት በማቋቋም የአገር ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ እሰራ ነበር።የአዲስ አበባ ሕዝብ ነገሮችን እንዲያስተካክሉ ሌላ እድል እንደሰጣችው ቢያስቡት ጥሩ ነው።

የአዲስ አበባ ህዝብ ለምን ዛሬ ሰልፍ አልወጣም? በኔ እይታ ሁለት ትላልቅ ምክንያቶች ነው ያሉት፡

1. የአዲስ አበባ ህዝብ በበቂ ሁኔታ አልተደራጀም። በሶሻል ሜዲያ ሰልፍ ስለተጠራ ሰልፍ ይወጣል ማለት አይደለም። በባህር ዳርና በጎንደር የተደረጉ ሰልፎች፣ እዚያው በህዝቡ መካከል ያሉ ወገኖች ድርጅታዊ ሥራ ሰርተው ያቀረቡትን የሰልፍ ጥሪ ነው ፣ በሶሻል ሜዶያ የበለጠ ተደራሽነት እንዲኖረው የተደረገው። ሶሻል ሜዲያ አጋዥ እንጅ ወሳኝ አይደለም። የአዲስ አበባው ሰልፍ ግን የተለየ ነው። መነሻው ህዝብ ሳይሆን ሶሻል ሜዲያው ነው። በሶሻል ሜዶያ የተወሰኑ ዳያስፖራ ያሉ ሃይሎች በስሜት ሰልፍ ጠርተው፣ ሰልፉ ከተጠራ በኋላ ነው ሕዝቡን ለማደራጀት የተሞከረው። ትልቅ ስህተት ነበር። በዚህ መልኩ ህዝብ ሳይደራጅ በሶሻል ሜዶያ ዘመቻ፣ ወይንም በኢሳት ቅስቀሳ ለዉጥ እንደማይመጣም በሚገባ አስተምሮናል። ይሄ አንዱ ነጥብ ነው።

2. በአዲስ አበባ እንቅስቃሴ እንዲኖር ሕዝብ መደራጀት አለበት ካልን እንዴት ነው ህዝቡን የምናደራጀው የሚል ጥያቄ ይነሳል። ሕዝቡን ለማደራጀት ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄዎችም መስተናገድ አለባቸው። ኦሮሞ፣ አማራ የሚለው ሰሞኑን ፖለቲካችንን አጡዞታል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ኦሮሞ፣ አማራ የሚል ነገር፣ የዘር ነገር አይመቸውም። በዘር ዙሪያ የሚደረግ እንቅስቃሴን ለመደገፍ ይከብደዋል።

ትግሉ ተጀመረ እንጅ መጨረሻ አይደለም። የዛሬው ሰልፍ በመጠኑም ቢሆን በአዲስ አበባ ለሰልፉ ተብሎ በሜዳ የተሰሩ ሰራዎች አሉ። ይህ ሰራ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል አለበት ባይ ነኝ። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እየተመካከሩ፣ እየተነጋገሩ በየቀበሌዉና በየወረዳው መስባሰብ አለባቸው። ሁሉም ነገር የሚጀመረው ከሰፈር ነው። በዚህ መልክ በአጭር ጊዜ ውሱጥ ከህዝቡ ክራሱ ትልቅ ድርጅታዊ ጉልበት ያለው ሃይል ሊፈጠር ይችላል፡ ጎንደር የተደረገው እንደዚያ ነው።

እንግዶህ ወገኖች ..እንበርታ ….ትግሉ ይቀጥላል !!!!

Leave a Reply