(ኢ.ኤም.ኤፍ – የዳዊት ከበደ ወየሳ ዘገባ)
በኢትዮጵያ ውስጥ፤ መንግስት በህዝብ ላይ የሚፈጽመው የጥቁር ሽብር ድርጊት ብዙዎችን ከማሳዘን አልፎ ቁጣን የቀሰቀሰ፤ ብዙዎችም ለመብታቸው እንዲቆሙ እያደረገ ነው። ህዝቡም በራሱ ግዜ ሰላማዊ ሰልፍ ከመውጣት ጀምሮ፤ ሳይፈራ ሃሳቡን በአደባባይ ማንጸባረቁን ቀጥሏል። ዛሬ ኢትዮጵያዊው ፈይሳ ሌሊሳ በሪዮ ኦሎምፒክ 2ኛ ሲወጣ፤ ሁለት እጆቹን በማጣመር “ታስረናል” የሚለውን ምልክት ሲያሳይ፤ ብዙዎች ወርቅ ያሸነፈ ያህል በመቁጠር ደስ ተሰኝተዋል። ይህም በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያው ደፋር አትሌት የሚያሰኘው ይሆናል።

ፈይሳ ወደ ስቴድየም ሲገባ

ፈይሳ ወደ ስቴድየም ሲገባ

ወደ ስቴዲየም ከገባ በኋላም የኢትዮጵያ ህዝብ ሰንደቅ አላማ የሆነውን ንጹህ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ በመልበስ ደስታውን ገልጿል። ፈይሳ ሌሊሳ አረንጓዴ እና ቢጫ ጄርሲ፤ ከቀይ ቁምጣ ጋር በማድረግ ኢትዮጵያዊነትን ይበልጥ አንጸባርቋል። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን በመሳሪያ ሲቆጣጠር ፈይሳ ሌሊሳ ገና የአምስት ወር ልጅ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ መጥፎ አገዛዝ ውስጥ አድጎ የስርአቱን አስከፊነት ሳይፈራ በማንጸባረቁ በብዙዎች ዘንድ ከበሬታ እንዲያተርፍ ያደርገዋል። ሌላው ቀርቶ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አፈና በዚህ መልኩ ማንጸባረቁ እና የውጭ አገር ሚዲያ ሽፋን ብዙዎችን አስደስቷል።
አትሌት ፈይሳ ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ ወክሎ ሲሮጥ የመጀመሪያው ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ በ2010 የሮተርዳም ማራቶን፤ በ2ሰአት፡06ደቂቃ ሲያሸንፍ፤ እድሜው ገና 20 አመቱ ስለነበር፤ የመጀመሪያው ወጣት አሸናፊ የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት ነበር። በአሜሪካ የቺካጎ እና የኦስተን ግማሽ ማራቶን በማሸነፍ ይታወቃል።
ከላይ እንደገለጽነው.. ዛሬ በተደረገው የሪዮ ኦሎምፒክ የመዝጊያ ዝግጅት ላይ ከኬንያዊው አትሌት ቀጥሎ 2ኛ ሲወጣ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የሙስሊም ህብረተሰብ፣ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ፤ መበደሉን ለማሳየት የሚጠቀምበትን የሁለት እጆች ጥምረት በማሳየት ነበር ወደ ስቴዲየም የገባው።

የፈይሳ ታላቅ መልእክት - ታስረናል! ታፍነናል!

የፈይሳ ታላቅ መልእክት – ታስረናል! ታፍነናል!

በኦሎምፒክ ታሪክ ውስጥ… በ1968 የሜክሲኮ ኦሎምፒክ ወቅት፤ በጥቁር አሜሪካ አትሌቶች ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ የተፈጸመው ድርጊትም ተመሳሳይ ነበር። ቶም ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ በአሜሪካ ውስጥ በጥቁሮች ላይ የሚደረገውን የዘር መድልዎ አጥብቀው ያወግዙ ነበር። ወደ ሜክሲኮ ሲሄዱ በጉዳዩ ላይ ተዘጋጅተውበት ነበር። በደረት ላይ የሚለጠፈውን የሰብአዊነት ባጅ እና ጥቁር ጓንት ይዘው ነበር የሄዱት። አሸናፊነታቸው ታውቆ ሜዳሊያቸውን በክብር ከተቀበሉ በኋላ የአሜሪካ ባንዲራ ሲሰቀል፤ አንገታቸውን ደፍተው “ጥቁር ኃይል ነው” የሚለውን የእጅ ምልክት በስቴዲየሙ ውስጥ አንጸባረቁ።

ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ አንገታቸውን ደፍተው “ጥቁር ኃይል ነው” የሚለውን የእጅ ምልክት በስቴዲየሙ ውስጥ አንጸባረቁ።

ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ አንገታቸውን ደፍተው “ጥቁር ኃይል ነው” የሚለውን የእጅ ምልክት በስቴዲየሙ ውስጥ አንጸባረቁ።

በዚህ ድርጊታቸው ምክንያት በወቅቱ ወቀሳ እና ድጋፍ አስተናግደዋል። ሁኔታዎች ካለፉ በኋላ ግን ቶሚ እና ጆን ካርሎስ በአሜሪካ ታላቅ ከበሬታን አትርፈዋል። ሁለቱም… ለጥቁሮች ነጻነት ላደረጉት ታላቅ አስተዋጽኦ በተለያዩ ግዜያት ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል። በ2008 የሲድኒ ኦሎምፒክ ልዩ ጥናታዊ ፊልም ሲዘጋጅ ባለታሪኮቹ ሁለቱ የኦሎምፒክ ጀግኖች ነበሩ። በቅርቡም በሳን ሆዜ ዩኒቨርስቲ ሃውልታቸው ቆሟል።
በዚህ አጋጣሚ አንድ ነገር እንጨምር። ፖዲየሙ ላይ አብሯቸው የነበረው አውስትራሊያዊ አትሌት ኖርማን ለሁለቱ አሜሪካውያን ዘላቂ ጓደኛቸው ሆኖ ነበር። እጁን እንደነሱ ወደ ላይ ባያነሳም፤ እነሱ የሰጡትን የሰብአዊነት ባጅ ደረቱ ላይ በመለጠፍ፤ ለጥቁር አሜሪካውያን ያለውን አጋርነት አሳይቷል። የአውስትራልያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በኖርማን ድርጊት ተናዶ ከሚቀጥለው የሙኒክ ኦሎምፒክ ሰርዞታል። በዚህ ምክንያት ጥቁሮች በሙሉ “አውስትራልያ የምትሳተፍ ከሆነ፤ በሙኒክ ኦሎምፒክ አንገኝም” አሉ። ውዝግቡ እየተካረረ ሲሄድ፤ አውስትራልያ ራሷ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የኦሎምፒክ አትሌቶቿን ከሙኒክ ኦሎምፒክ አገደች። (ታሪኩና ውዝግቡ ብዙ ነው።) አውስትራልያዊው አትሌት ኖርማን በ2006 ህይወቱ ሲያልፍ፤ ሁለቱ አሜሪካውያን በቀብሩ ስነ ስርአት ላይ በክብር ተገኝተው ነበር።

ለሁለቱ አሜሪካውያን የቆመላቸው የክብር ሃውልት - ሳን ሆዜ

ለሁለቱ አሜሪካውያን የቆመላቸው የክብር ሃውልት – ሳን ሆዜ

አሁን ሃውልታቸው በሳንሆዜ ዩኒቨርስቲ ከተመረቀ በኋላ የኖርማን ምስል የለም። ቦታው ለሌላው ህዝብ የተተወ ነው። ሰዎች ፎቶ መነሳት ሲፈልጉ፤ ኖርማን ቆሞ የነበረበት ፖዲየም ላይ በመቆም ፎቶ ይነሳሉ።
ዛሬ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይደረግ፤ ጋዜጠኞች ሃሳባቸውን በነጻ እንዳይገልጹ፤ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የመረጣቸውን ህዝብ እንዳይመሩ በማድረግ ህዝቡ ምሬት ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ነው። አፈና እና ጫናው በርትቷል። ፈይሳ ሌሊሳም ይህን የታፈነ ጩኸት ለአለም ስላስደመጠ፤ ትልቅ ክብር እና ምስጋና ያሻዋል። ወደፊት… ከእለታት በአንዱ ቀን እንደ ቶሚ ስሚዝ እና ጆን ካርሎስ ሃውልቱ በክብር ይቆምለታል – አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ።

=================

ከውድድሩ በኋላ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ፈይሳ ሌሊሳ እጁን ለምን እንዳጣመረ ተጠይቆ የሰጠውን መልስ የፈረንሳዩ ሌኬፕ፣ ያሁ ኒውስ እና ተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በዚህ መልኩ ይዘውት ወጥተዋል

ቃለ ምልልሱን ይመልከቱ

feyissa