በትናንትናው እለት ታቅዶ የነበረው የአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ እንደታሰበው ሊካሄድ አልቻለም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች እና መላ ምቶችን የሚያመላክቱ ጽሁፎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። አዲስ አበባን የጦር ቀጠና ያስመሰላት የሰራዊቱ በጎዳና ላይ መፍሰስ የገዥውን ፓርቲ ልብ ትርታ መለክያ መሆኑን ግን ሁሉም ይስማሙበታል። የቀድሞ ፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሠይፉ ማሩ “የአዲስ አበባው ‘ሰልፍ’ በሚል በእኔ እምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ በስኬት በመከናወን ላይ ነው“ ሲሉ የዞን ዘጠኝ ጦማሪው በፍቃዱ ሃይሉ “መሬት ላይ የተሠራ ነገር የለም” ባይ ነው። ጋዜጠኛ አብርሃ ደስታ ደግሞ “ሰልፍ የወጣው ህዝብ ሳይሆን ፌደራል ፖሊስ ነበር። ህዝብ ሰልፍ ይወጣል ሲባል ሰልፉን ለማፈን ወታደር ወጣ። ” ይለናል። የሶስቱንም ሙሉ አስተያየት ከዚህ በታች አቅርበናል።
የአዲስ አበባው “ሰልፍ” – ግርማ ሠይፉ ማሩ
በእኔ እምነት ዛሬ በአዲስ አበባ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ በስኬት በመከናወን ላይ ነው፡፡ ጠሪዎቹም የተጠራባቸውም እንዴት እንደሚገመግሙት ባላውቅም ማለቴ ነው፡፡
ቅዳሜ ቀን ሙሉ በዋና ዋና የከተማ ቦታዎች የውጭ ወራሪ የመጣ ይመሰል ከተማዋ በሠራዊት ተወራ ውላ ምሸቱን ሰዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ በፍተሻ ሰም ሲዋከቡ ነበር፡፡ ይህ ፍተሻ መቼም ፖሊሶቹ ሰራ ከምንፈታ ብለው ሳይሆን ጌቶቻቸው ባደረባቸው ጭንቀት ምክንያት አንድ ነገር እንዳይፈጠር በመስጋት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡
ቤቴ ስገባ መንገዱ ሁሉ ተወጥሮ ፖሊሶች በፍተሸ ላይ ናቸው፡፡ ለማነኛውም እውቅና ሳይጠየቅ የተሰጠው ሰልፍ በመንግሰት በኩል እውቅና እንዳገኘ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም ማስፈቀድ የሚባል ህግ በሌለበት ካልፈቀድን ህገወጥ ነው አሉ እንጂ ህዝቡ ወጥቶ ምን እንደሚል መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ ይጠቅማቸው ነበር፡፡
ዛሬም እሁድ ሚያዚያ 30/97 በሚያስታውስ ሁኔታ ዶፍ እስኪወርድ ድረስ ከተማዋን የወረራት ሠራዊት ዞር አላለም ነበር፡፡ እነዚህ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች መቼም ወንድሞቻችን መሆናቸው ነው፡፡ የትላንት የቀኑ ቅዝቃዜ፣ የማታው ቆፈን የሚያሲዝ ብርድ እንዲሁም የቀኑ ብርድና ዝናብ እንደሚያስመርራቸው ጥርጥር የለወም፡፡
ጉዳይ ሀገር ሊወር ከመጣ ጠላት ጋር ቢሆን በሆታና በጭፈራ የሚታለፍ ነው፡፡ በጀግንነት ለመወጣት ከውስጥ ደም የሚሞቅበት ነው፡፡ የገዛ ወንድምና እህት ብሶቱን ለማሰማት እንዳይወጣ መጠበቅ ሲሆን ግን የሚቻል አይደለም፡፡ ደም አያሞቅም፣ ጀግና አስብሎ አያሸልምም፡፡
ሠራዊቱን ያሰጨነቀ፣ ማነኛውም የደህንነት ሰራተኛ ከወትሮ በተለየ በተጠንቀቅ፣ ካድሬዎች ከመደበኛ ስራቸው ውጭ ህዝብን እንቅስቃሴ እንዲከታተሉና ሪፖርት እንዲያደርጉ ያስገደደ፣ በተለይ በተለይ ደግሞ ገዢዎች በጭንቅ ውስጥ መሆናቸው ይፋ የሆነበት በመሆኑ ሰልፉ በስኬት ተከናውኖዋል ማለት ነው፡፡
በእርግጠኝነት የአዲስ አበባ አንድ አንድ ነዋሪዎች የሚሉትን በዜና እወጃ እንሰማለን …..
ጎበዝ ቤቴ ስገባ መንገዱ ሁሉ ተወጥሮ ፖሊሶች በፍተሸ ላይ ናቸው፡፡ ለማነኛውም እውቅና ሳይጠየቅ የተሰጠው ሰልፍ በመንግሰት በኩል እውቅና እንዳገኘ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ለማነኛውም ማስፈቀድ የሚባል ህግ በሌለበት ካልፈቀድን ህገወጥ ነው አሉ እንጂ ህዝቡ ወጥቶ ምን እንደሚል መስማት ብቻ ሳይሆን ማድመጥ ይጠቅማቸው ነበር፡፡
ሸገር ለምን አታምፅም? – በፈቃዱ ሀይሉ
ዛሬ ረፋዱ ላይ በመስቀል አደባባይ አለፍኩ። በርካታ የፌዴራል ፖሊስ መኪኖች እና መኮንኖች ቆመዋል። ለወትሮው በስፖርተኞች ውር-ውር ይደምቅ የነበረው ገጽታዋ ቆሌው ተገፎ ጭር ብላለች። ፖሊስ ከመቼውም የበለጠ ወደአደባባዩ በሚወስዱት መንገዶች ላይ በዝቶ ነበር። ቢያንስ ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ ይህን አይቻለሁ። ሌላው ቀርቶ ሰፈሬ መውጫ ላይ የሚቆሙት ሁለት ፖሊሶች ቁጥራቸው ወደ አምስት ማደጉን አስተውዬ ነበር። አዎ፣ ጥበቃው ከወትሮው የከረረ ነበር። ትላንት እና ከዚያ በፊት አፈሳ እንደነበርም ይታወቃል። አፈሳው በአካል የማውቀውን Sintayehu Chekolን ይጨምራል። ትላንት ቦሌ አካባቢ ፖሊስ ሰልፍ እንዳይወጡ ወጣቶችን ሲመክር አይቻለሁ። ማታ ላይ ወደቤቴ ስገባ በፖሊስ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ተፈትሻለሁ። ነገር ግን ይህ ሁሉ እንደሚሆን ቀድሞ አይታወቅም ነበር? በሕወሓት/ኢሕአዴግ ባሕሪ እንኳን ጠሪው ያልታወቀ ሰልፍ፣ ፓርቲዎች “ዕውቅና ያገኙበት” ሰልፍ ሲደናቀፍ አላየንም? የሰልፍ ቦታዎችን በፖሊስ መውረር እና አስቀድሞ ተሰላፊዎችን ማፈን የነበረና የሚኖር የኢሕአዴግ ባሕሪ ነው። ስለዚህ ዛሬ (ነሐሴ 15/2008) የተጠራው ሰልፍ በፖሊስ ተደናቀፈ የሚለው ምክንያት ተቀባይነት የለውም። ባይሆን ሌላ ምክንያት እንፈልግ።
፩) መሬት ላይ የተሠራ ነገር የለም!
ጎንደር ላይ የወልቃይትን (specific) ጉዳይ ሲያስተባብሩ የነበሩ የኮሚቴ አባላት እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ነበሩ። ኦሮሚያ ላይ የማስተር ፕላኑን (አሁንም specific) ጉዳይ ሲያስተባብሩ የነበሩ የቄሮ አባላት እና ሌሎችም ነበሩ። አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ራሱ እንደተጠራ መጀመሪያ የሰማሁት ሐሙስ ማታ ነው። እሱም አጋጣሚ ኢሳት ላይ “ሰልፉን ለማደናቀፍ ኢሕአዴግ አፈና ጀምሯል” የሚል ዜና ሲታወጅ ነው የሰማሁት። በማግስቱ ቃሊቲ የታሰሩ ወዳጆቼን ልጠይቅ ስሔድ “የእሁዱ ሰልፍ እንዴት ነው?” አሉኝ። የሰማሁትን ነገርኳቸው። ከዚያ በኋላም በአብዛኛው የሰማሁት የሆኑ ሰዎች በዚሁ ፍርሓት እንደታሰሩ ነው። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እዚህ ያሉ እና በአገዛዙ በጣም የተበሳጩ ጥቂት፣ በጣም ጥቂት ሰዎች ከመጻፋቸው በቀር ሌሎቹ በሐሰተኛ ሥም የሚጽፉ ወይም በውጭ አገር የሚኖሩ ናቸው ዜናውን ያስተጋቡት። በኔ አተያይ፣ በሐሰተኛ ሥም የሚጽፉት (እዚህ ያሉትም ቢሆኑ) ሰልፍ አይወጡም፤ በእውነተኛ ሥም መጻፍ ሰልፍ ከመውጣት የበለጠ አያስፈራም። እነዚያ በሥማቸው የጻፉት ደግሞ ይታፈሳሉ። ስለዚህ፣ ሰልፉን የማስተባበሩ ሒደት፣ ቢያንስ እኔ እስከማውቀው ድረስ መሬት የወረደ አልነበረም። ስለዚህ ሰልፉን የሚወጣ ሰው መኖሩ ቀድሞም አጠራጣሪ ነበር።
፪) ለአዲስ አበቤ ባዳ የሆኑ አጀንዳዎች
ሌላው ጉዳይ ሕዝብ ጋር የደረሰ ቅስቀሳም ሆነ ሰልፍ የሚያስወጣ አጀንዳ አለመኖሩ ነው። የኦሮሚያ ጉዳይ፣ ጥያቄው ብዙ ቢሆንም መነሻው [አዲስ አበባን ያስፋፋል የተባለው] ማስተር ፕላን መሆኑ ራሱ አዲስ አበባን ይገፋል። ብዙኃኑ አዲስ አበቤ ገንዘብ ካገኘ ሱሉልታ ወይም ሰበታ ላይ መሬት ገዝቶ ቤት መሥራት ነው ምኞቱ። የአማራ ጥያቄም ቢሆን ለአዲስ አበቤ ሩቅ ነው። አዲስ አበቤ ከኦሮሚያም ሆነ ጎንደር ሕዝቦች በተለየ ቅይጥ (heterogeneous) ነው፤ በቋንቋና ባሕላዊ ዳራ እንዲሁም ሃይማኖት አንድ ዓይነት (homogeneous) ሕዝብ ባለመሆኑ የቡድን ጥያቄ ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ የአዲስ አበባን ሕዝብ ሊያስተባብሩ የሚችሉት የግለሰብ መብት ጥያቄዎች ናቸው። የአዲስ አበቤን ብሶት በአጫጭር ቃላት አሽሞንሙኖ ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ሥራ አልተሠራም። “አማራ እና ኦሮሞ ወገኖችህ ናቸው” የሚለውም በቂ አይደለም። የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዙ ምሬቶች አሉበት፣ የብሔር ጭቆና ትርክት ግን አደባባይ አያስወጣውም። የራሱን ችግሮች ከነመፍትሔዎቹ ቁልጭ ባለ መልኩ (specifically) ይህ ነው የሚለው ይፈልጋል። በቡድን ጉዳይ፣ አዲስ አበቤ ቢቻል የብሔር ነገር ባይወራበት ይመርጣል። የኑሮ ውድነት እና በመስፋት ላይ ያለው የመደብ ልዩነት፣ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እና የመንግሥት ተቋማት ብልሹ አሠራር ወይም ሙስና የበለጠ ያሳስቡታል። እነዚህ ላይ ብዙ አልተባለም።
፫) ሰልፉን አገር ውስጥ ያለ አካል አልጠራውም
ቅስቀሳውን በብዛት ሲያደርገው የነበረው ኢሳት ቴሌቪዥን ሲሆን፣ ኢሳት አገር ውስጥ ያለው ተዳራሽነት በጣም ውሱን ነው። እርግጥ ኢሳት የሰልፉ አስተባባሪ ሌላ እንደሆነ ቢናገርም፣ ያንን አካል (በሥም እንኳ) የሚያውቀው አልነበረም። ከዚያም በላይ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ኢሳት በጠራው ሰልፍ ላይ የሚወጣ ወጣት አለ ብዬ አላምንም። ለዚህ አንዱና ቀላሉ ምክንያት ኢሳት የግንቦት ሰባት ልሳን ነው የሚለው ስጋት ነው። ሌላው፣ አዲስ አበቤ ሰልፍ እንዲወጣ እዚህ እንዳለ የሚያውቀው የሆነ ቡድን ሰልፉን መጥራት አለበት፤ ማለትም የሆነ የሚያውቀው ሰው ወይም ቡድን ሰልፉን አብሮት እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን አለበት። ስለዚህ የፈለገውን ያህል ምሬት እና ብሶት ቢኖርበትም የአዲስ አበባ ሰው ጥቂት ሆኖ ሰልፍ መውጣቱ በፖሊስ ቆመጥ ከመቀጥቀጥ በቀር የሚያተርፍለት ነገር ስላልነበር – አልወጣም። አደጋውን ለመጋፈጥ ደፍሮ እንዲወጣ ከተፈለገ አስቀድሞ የሚያውቀው፣ የሚያምነው አካል እንደሚወጣ እርግጠኛ መሆን ነበረበት ወይም ሊነገረው ይገባ ነበር። ይህ ግን አልሆነም፤ ሁሉም ሰው ‘ሌላ ሰው ይወጣ ይሆን?’ እያለ የማያውቀውን ሰው ይጠባበቅ ነበር።
እንግዲህ፣ በመንግሥት የማፈንና የማስፈራራት እርምጃ፣ እንዲሁም በተቃዋሚዎች የፍርሓትና የሽንፈት ታሪክ መብዛት መካከል ድንገት የተጠራው ሰልፍ በሰበቡ የታሰሩትን ልጆች ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በቀር ያተረፈው ነገር የለም። ያልተሳኩ የሰልፍ ጥሪዎች በመጪዎቹ የሕዝብ ንቅናቄዎች ላይ የራሳቸውን የ‘አንችልም’ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ። የተቃውሞ ሰልፍ በማንኛውም አደጋ መካከል ለመጥራት ከመወሰን በፊት፣ ‘ማንኛውንም አደጋ ተጋፍጦ ሰልፍ መውጣት ተገቢ ነው ወይ?’ ብሎ መጠየቅ ባይቻል እንኳ፣ ‘ማንኛውንም አደጋ ተጋፍጦ ሰልፍ ለመውጣት ፈቃደኛ የሆነ ሕዝብ አለ ወይ?’ ብሎ ማሰብ ያስፈልግ ነበር። ክሽፈቱ ብዙ ዋጋ ያስከፍላልና።
እንደመፍትሔ የምጠቁመው፣ መጀመሪያ ‘የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄዎች ምን፣ ምን ናቸው? የሚመለሱትስ እንዴት ነው?’ የሚለውን ማጥራት ነው። ቀጥሎ፣ ለነዚህ መልሶች መገኘት የሚሠራ/ሩ ቡድን/ቡድኖችን ማደራጀት ያስፈልጋል። በመጨረሻም፣ ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ። ያኔ፣ ሸገር፣ በጉያዋ አፍና የያዘችውን ፍም አደባባይ ትበትነዋለች ብዬ አምናለሁ። ያለዚያ ግን፣ በስሜት የሚገኝ ድል የለም።
ሰልፍና ዓመፅ! (የአዲስ አበባውን ሰልፍ በተመለከተ) – አብርሃ ደስታ
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ ሰለፍ ተጠርቶ እንደነበር ሰማሁ። ሰልፍ የወጣው ግን ህዝብ ሳይሆን ፌደራል ፖሊስ ነበር አሉ። ህዝብ ሰልፍ ይወጣል ሲባል ሰልፉን ለማፈን ወታደር ወጣ። ሰልፍ ሰለማዊ (ሕጋዊ) ወይ ዓመፅ ሊሆን ይችላል። መጀመርያ በህጉ የተፈቀደው (ወይ የሚፈቀደው) ሰለማዊ ሰልፍን ነው። ህዝብ ጥያቄውን ወይ ቅሬታውን ወይ ተቃውሞውን በሰለማዊ መንገድ የመግለፅ መብት አለው። ሰለማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት ነው። አንድ መንግስት ሰለማዊ ሰልፍን ከከለከለ ዓመፅን ፈቀደ ማለት ነው። ምክንያቱም ህጋዊ የሆነውን ነገር መከልከል ማለት ህጋዊ ያልሆነውን መፍቀድ ማለት ነው። ሰለማዊ ሰልፍን ለማፈን ከተጋ ሰለማዊ ያሆነውን መንገድ አበረታታ ማለት ነው።
ዛሬ በርካታ ፖሊሶች ሰለማዊ ሰልፈኞችን ለማሰርና ለመደብደብ ሲዘጋጁ ህዝብ መብቱን ተረግጦ ህጋዊው መንገድ ትቶ (ምክንያቱም አይተገበርም) ሌላኛው መንገድ (ዓመፅ) እንዲመርጥ እያስገደዱት ነው። ምክንያቱም ህዝብ ጥያቄ አለው። ጥያቄ ስላለው ነው ሰለማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚነሳው፤ ጥያቄ ባይኖረው ሰልፍ ለመውጣት አይነሳሳም ነበር። ህዝብ በሰለማዊ መንገድ (ሰለፍ) ጥያቄው እንዳያቀርብ በሐይል ማገድ፣ መከለከል ጥያቄው አይመልሰውም። ህዝቡ ሰልፍ ተከልክሎ ቢታፈንም ጥያቄው ይኖራል፣ አልተመለሰም። ስለዚህ ዓፈና ዓፈና እየወለደ የህዝቡ ብሶት ይገነፍልና ዓመፅ ወልዶ ጎርፍ ሆኖ ብዙ ህይወትና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ይሆናል።
ስለዚህ የዓመፅ ዋነኛ ምንጭ ዓፈና ነው። ዓፋኙ ማነው? ኢህ አዴግ ነው። ሰልፈኞችን በማፈን ከሰለማዊ መንገድ ወደ ዓመፅ መንገድ እንዲሸጋገር እያደረገው ነው። ስለዚህ ኢህአዴግ ማፈኑን እስከቀጠለ ድረስ ዓመፅ መነሳቱ ስለማይቀር በዓመፁ ምክንያት ለሚፈጠር ኪሳራ ተጠያቂው ራሱ ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ የዓመፅ መንስኤ ነው። የዓመፅ ምንጭ ጭቆና ነው። የጭቆና ምንጭ አምባገነን ስርዓት ነው። ጭቆና ባይኖር ዓመፅ አይኖርም ነበር። ሰለማዊ ሰልፍ ቢፈቀድ ዓመፅ አይኖርም ነበር። ሰለፍ ከተፈቀደ ሰው ለምን ያምፃል? ሰለማዊ ሰልፍ ካልተፈቀደለት ግን ዓመፅ ሌላው አማራጭ ያደርገዋል። ምክንያቱም ጭቅና ሲበዛ ይመራል፣ ከዓቅም በላይ ይሆናል። ከዓቅም በላይ ሲሆን ይፈነዳል፤ ሲፈነዳ ዓመፅን ይወልዳል። ስለዚህ ዓመፅን ለመከላከል ሰለማዊ ሰልፍን መፍቀድ ነው። ሰልፍን በጠመንጃ ሐይል ማገድ ዓመፅን መፍቀድ ነው።
….
ከአይን እማኞች
እኔና ብዙ ጉዋደኞቼ የዛሬውን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ቀጠሮ የያዝነው ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። ትላንት ቅዳሜ ማለት ነው ስንት ሰአት መገናኘት እንዳለብን ከተወያየን በኋላ ዛሬ በጠዋት ማልደን ተነሳን እናም በባቡር ሄደን እዛው አቢዮት አደባባይ መውረድ እንዳለብን ተነጋገርን ፣ ዳሩ ምን ያደርጋል ባቡሩ አንድ ፌርማታ ሲቀረው ፣ክቡራት ተሳፋሪዎቻችን ባቡሩ ከዚ ፌርማታ በዋላ አይንቀሳቀስም እናመሰግናለን የሚል መልክት በስፒከር አስተላለፈ። ተሳፋሪውም እንዴት እንደዚ እንደዚ ታደርጋላቹ ብለው በመውረድ ከባቡሩ ሹፌሮች ጋር ጭቅጭቅ ጀመረ፣<
በዚ ግዜ አንዱ ሹፌር በሩን ከፍቶ ምንም ማድረግ አንችልም ትዛዝ ተስቶን ነው ይቅርታ ብሎ ስውን ሊያረጋጋ ቢሞክርም ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል:: እኛም በእግራችን ወደ አብዮት አደባባይ ለመሄድ ስንሞክር ማንም ማለፍ አይቻልም ብለው ፌደራሮች መንገድ ዘጉብን ።
ሌላ አማራጭ መንገድ ስንፈልግም ነገሩ ተመሳሳይ ሆነ። ወደኋላም አንመለስም ብለን መጨረሻውን ለማየት እዛው አከባቢ አንድ ምግብ ቤት ገብተን ቁርስ አዘዝን እና እዛው ቆየን።
ከሰአታት የማለፍ ክልከላ በኋላ ክልከላው ስለቆመ ተበታትነን ወደዛው አመራን ፣ አቢዮት አደባባይ ያየነው የፌደራል ፓሊስ ፣እና የአዲስ አበባ ፓሊስ ፣እንዲሁም ሲቪል የለበሱ የስርአቱ ታማኝ አሽከሮች(የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች) ብዛት ለመቁጠር ያዳግታል ። እኛም በዛ በምናልፍበት ጊዜ ተፈትሸን መታወቂያ አሳይተን አልፈን ሄድን ።
በኋላ ለማጣራት እንደቻልነው በአራቱም አቅጣጫ ወደ አቢዮት አደባባይ የሚመጣውን ህዝብ በእንደዚ አይነት መልኩ አግደውታል ።
የመንገድ ትራንስፕፖርት ግቢ ውስጥ የተዘጋጁ አድማ በታኝ ፓሊሶች በጣም ብዙ በአይኔ አይቻለው:: ይሄ ሁሉ ወከባ ባለበት ነው እንግዲ እነ “ፋና እና ኢቢሲ” የአዲስ አበባ ህዝብ በሰላም ሲንቀሳቀስ ዋለ ብለው በዜናቸው የሚያፌዙብን።
አዲስ አበባ ታላቋ እስር ቤት ሆና ዋለች
እርግጥ ነው የአዲስ አበባ ህዝብ በትግራይ ወያኔ ይህ ቀረው የማይባል ግፍና በደል የተፈጸመበት ህዝብ ነው። የተወለደንትና ያደገብትን ሰፈር አጧል፤ ይሰራበት የነበረው የንግድ ቦታ ሁሉ ተወስዶበታል፤ተባሯል፤ ተገድሏል፤ እስር ቤት ታጉሯል። ላለፉት 25 አመታት እራሱ በመረጣቸው ሰወች ሳይሆን ወያኔ በሚሾምለት የወያኔ ሰወች(ጣሊያን እንዳደረገው የሮም የሙሶሎኒተወካይ አዲስ አበባን እንዲያስተዳድር መመደብ) ሲገዛና አስተዳደራዊ አድሎና በደል ፤ መፈናቀል፤ እስራት፤ እንግልትና ግድያ ሲፈጸምበት የኖረና አሁንም እየተፈጸመበት የሚገኝ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ በምንም መልኩ ወያኔን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ግንባር ቀደም ሆኖ እንደሚታገል ስራዉ ይመሰክራል።
አሁን በዚህ እሁድ ቀን የታየውና የሆነው፤ አንድ የወያኔ ጠበቃ እንደጻፈልኝ አዲስ አበባ ሰላም ዋለችህ ሳይሆነ፡ አዲስ አበበባ ታስራ ዋለች ነው እዉነታው ። የትግራይ ወያኔ የሃገሪቱን ሰራዊት በሙሉ ከያለበት በማንሳት ወደ አዲስ አበባ በማጓዝ ከተማዋን የጦር ቀጠና በማስመሰል፤ ማንም ሰው ወደዋና ጎዳና እንዳይወጣና የብሄር ማንነትን በመጠየቅ የመጨረሻዉን የዘር ማጥፋት እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን መቀመጫቸዉን አዲስ አበባ ዉስጥ ያደረጉ የዉጭ ሃገር መንግስታት ተወካዮችም አይተዋል። በዚህ እርምጃዉም ወያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላትና አጥፍቶ ለመጥፋት የተዘጋጀ እርኩስ ሃገር በቀል ነቀርሳ መሆኑን በግልጽ አረጋግጧል። ለዚህም ነው ሁኔታወች አስጊ ደረጃ ላይ መድረሳቸዉን በመግንዘቡ ለማምለጫ የሚሆኑ ፈጣን አመላላሽ አግልግሎት ሰጪ የጦር ሃይል በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ትዛዝ ያስተላለፈው። ይህ እርምጃው አዲስ አበባን ታላቋ የወያኔ እስር ቤት አድርጓት እንደዋለና በሰላም ተቃዉሞዉን ለመግለጽ የሚወጣን ህዝብ ፈርቶ የጦር አዋጅ በከተማው ላይ ማወጁ በመጀመሪያ መሸነፉን፤ ከዚያ በላይ ግን ተስፋ የመቁረጡንና የመጨረሻ እስትንፋስ እንደቀረችው ለአለም ህዝብ አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻና ኩሩ ህዝብ ነው፤ ነጻነቱን ከሁሉም በላይ ክብር የሚሰጥ ህዝብ ነው። በነጻነቱ ላይ ከሚመጣ ማንም ሃይል በህዪወቱ ቢመጣ ዪመርጣል። ነጻነት የሌለው ህዝብ የተሟላ ስብእናና ህይወት የሌለው መለስተኛ ህዝብ ነው። ነጻነት መንፈስ ነው፤ ነጻነት አስተሳሰብ ነው፤ነጻነት እምነት ነው፤ ነጻነት ኩራት ነው፤ ነጻነት ህወይትና ሰው መሆን ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ወያኔ የተነተቀውም ይሀንን ሁሉ ነው።
ትግሉ ዪቀጥላል!