ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ

ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ

(EMF) ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ – በብራዚል የሚገኘውን ኢትዮጵያዊ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን ለመታደግ በማናቸውም ግዜ ወደ ሪዮ ለመሄድ መዘጋጀቱን ገለጸ። ዶ/ር ሼክስፒር ይህን ከገለጸ በኋላ በርካታ የስልክ ጥሪዎች ያስተናገደ መሆኑን አልሸሸገም። ከደረሱት የስልክ ጥሪዎች በተጨማሪ፤ እሱ ያደረገው አንድ የስልክ ጥሪ ለየት ያለ ነበር። አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን አግኝቶ ያናገረው መሆኑን ነው በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ ድረ ገጽ የገለጸው።

እንደዶ/ር ሼክስፒር ገለጻ ከሆነ፤ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በተደጋጋሚ የሚያስፈልገው ነገር ካለ ወይም ያጋጠመውን ነገር ሲጠይቀው፤ “እስካሁን ምንም ችግር የለም” የሚል ተደጋጋሚ መልስ የሰጠው መሆኑን  ለድረ ገጻችን አሳውቋል።

“ብራዚል የአትሌቱን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ብታስገድደውስ?” ለሚለው ጥያቄያችን ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ሲመልስ፤ “ብራዚል የአለም አቀፉን የስደተኞችና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስምምነቶችን የፈረመች አገር ናት። በመሆኑም አትሌቱን ወደ ኢትዮጵያ አሳልፋ የምትሰጥበት ሁኔታ አይታየኝም። ሆኖም በአስቸኳይ የህግ ሰዎች ጉዳዩን በመያዝ ለብራዚል መንግስት ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የኢትዮጵያ ደህንነት አባላት የብራዚልን መንግስት አስቀድመው ካሳመኑ፤ ሁኔታዎችን ወደኋላ መመለስ ሊያስቸግር ይችላል።” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል።

“አትሌቱ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? በስልክ ስታናግረው ፍላጎትህን ለአትሌቱ ገልጸህለታል?”

ዶ/ር ሼክስፒር – አዎ   በህግ በኩል ልወክለው እንደምችል ነግሬዋለሁ።

ጥያቄ – ምን ምላሽ ሰጠህ?

ዶ/ር ሼክስፒር – እስኪ ላስብበት ብሎኛል። ነገ ስንገናኝ ፍላጎቱን ማወቅ እችላለሁ።

ጥያቄ – አሁን በዚያ አካባቢ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ካላገኙት ሊያጋጥመው የሚችለው አደጋ ይታይሃል?

ዶ/ር ሼክስፒር – ይህንንም ተነጋግረናል። (የተነጋገሩትን ከገለጸልን በኋላ፤ “አሁን ግን ዝርዝሩን ለአደባባይ የሚወጣ አይደለም” ብሎናል።)

ጥያቄ – የሚቀጥለውን መልካም ዜና መቼ እንጠብቅ?

ዶ/ር ሼክስፒር – ነገ የሚለኝን ሰምቼ የአውሮፕላን ቲኬት እቆርጣለሁ። ተሳክቶ የምሄድ ከሆነ፤ አትሌት ፈይሳም ወደዚህ ከመጣ፤ ከአምላክ እርዳታ ጋር ቀሪው ጉዳይ የተሳከ እንደሚሆን አምናለሁ።

በዶ/ር ሼክስፒር በኩል አዲስ ነገር ካለ፤ተከታትለን ማቅረባችንን እንቀጥላለን፡

ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ከዚህ ቀደም… የአትላንታው ዳዊት ከበደ ወየሳ (ኢ.ኤም.ኤፍ)፤ ወደ ኢትዮጵያ ይተላለፍ በነበረው ትንሳኤ ሬድዮ አዘጋጅ ሳለ፤ የወቅቱ ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ፣ ሚስታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ ስብሃት ነጋ፣ በረከት ስምኦን እና ሌሎች አስር ያህል ባለስልጣኖች በቨርጂንያ ፍርድ ቤት ክስ መስርተውበት እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ዶ/ር ሼክስፒር ለጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ወየሳ ጠበቃ በመሆን፤ ኢህአዴግ በብዙ መቶ ሺህ ዶላር የቀጠራቸው አሜሪካውያንን መርታቱ የሚዘነጋ አይደለም። በቅርቡም ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራ የኢትዮጵያን አየር መንገድ አውሮፕላን ስዊዘርላንድ አሳርፎ እጁን ሲሰጥ፤ በጠበቃነት ለመቆም ፈልጎ በተደጋጋሚ ለስዊዘርላንድ መንግስት ጥያቄ ቢያቀርብም፤ የስዊ መንግስት ጥያቄውን ውድቅ ያደረገበት መሆኑ ይታወሳል።

ምንጭ     _   ኢትዮ ሜዲያ ፎረም