Wednesday, 24 August 2016 14:18
“አንድ ፓርቲ ሕዝቡን ስላወያየ ለውጥ አይመጣም”
አቶ ገብሩ አሥራት
“የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት አለበት”
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርኸ
በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ፊኒፊኔ ዙሪያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ንቅናቄ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተዛምቶ ያለፈው የትምህርት ዘመን የተጠናቀቀው በውጥረት ነበር። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ተቃውሞ ወደ ትምህርት ቤቶች በመዛመቱ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎት ቆይቷል።
በትምህርት ዘመኑ ማጠናቀቂያ ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው ፈተናም በማህበራዊ ድረገፅ ተለቆ ፈተናው እስከመራዘምና ሌላ ፈተና እስከመሰጠት የደረሰውም በዚሁ ምክንያት ነበር። መንግስት በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንዲበርድ ለማድረግ ሁለት እርምጃዎችን የወሰደበት ሁኔታ ነበር። የመጀመሪያው የተቃውሞው መነሻ የሆነው የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንዲቀር ማድረግ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኦሮሞ አባገዳዎች ጋር ውይይት አድርገው የግጭቱ ሰለባ ለሆኑ ዜጎች ካሳ የሚከፈል መሆኑን የመግለፃቸው ሁኔታ ነበር። በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማብረድ እነዚህ እርምጃዎች በመንግስት ከተወሰዱ በኋላም ቢሆን ተቃውሞው በክልሉ ተስፋፍቶ ታይቷል።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ይህ ነው የሚባል መቋጫ ባላገኘበት ሁኔታ ሌላኛው አለመረጋጋት የተከሰተው በአማራ ክልል ጎንደር ነበር። በአካባቢው የመጀመሪያው አለመረጋጋት የተፈጠረው ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአካባቢው የዜጎችን ህይወት ያጠፋ፣ ንብረት ያወደመና የአካባቢውንም ነዋሪዎች ለመፈናቀል የዳረገ መጠነ ሰፊ ግጭት እስከ መከሰት ደርሷል። ከዚሁ ከማንነት ጥያቄ ጋር የተነሳው ውዝግብ ወደ ሙሉ መረጋጋት ገብቶ በግጭቱ የተፈናቀሉ የአካባቢው ነዋሪዎች በተሟላ ሁኔታ ወደቀያቸው ባልተመለሱበት ሁኔታ ከወልቃይት ጋር በተያያዘ በጎንደር የተከሰተው ውጥረት ወደ ሰላማዊ ሰልፍና ግጭት ብሎም ወደ ቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ ተቀይሮ ሰንብቷል። የጎንደሩ ሰላማዊ ሰልፍ ባህርዳርን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች ከመስፋፋቱም ባሻገር ቀደም ያለው የኦሮሚያ የተቃውሞ ሰልፍም እንዲያገረሽ አድርጓል። በጎንደር የተጀመረው የቤት ውስጥ አድማ ወደ ባህርዳር ከተማ መስፋፋቱን ተከትሎ ከተማዋ ባለፉት ሦስት ቀናት ጭር ያለች መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁለት ምሁራንን አነጋግረናል። የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራርና የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ገብሩ አስራትና ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ ናቸው። ሁለቱም ምሁራን ከችግሮቹ በመነሳት መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ሀሳቦች ሰጥተውናል። የሰጡትም ሀሳብ የሚከተለውን ይመስላል።
አቶ ገብሩ አስራት
በእኔ በኩል አሁን እየታየ ያለው ችግር ስርአቱ የፈጠረው ችግር ነው የሚል አስተያየት ነው ያለኝ። ብዝሀነት ባለባት አገር መፈናፈኛ መታጣቱ አንድ ፓርቲና አገዛዝ መሆኑ አንዱ የችግሩ ምንጭ ነው። ዜጎች ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶቻቸውን የተነጠቁበት፣ በአጠቃላይ አፈና የበዛበት በመሆኑ ይህ መፈናፈኛ መታጣቱ የፈጠረው ችግር ነው። መፍትሄውም መፈለግ ያለበት ከዚህ በመነሳት ነው። ለዚህ ችግር መፍትሄ በማፈላለጉ ረገድ የፖለቲካ ሰዎች፣ የሲቪል ማህበረሰቡና ሌሎች በዚች አገር ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በነፃነት ድምፃቸው የሚሰማበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው መፍትሄ መምጣት የሚችለው። መፍትሄው ሊገኝ የሚችለው መንግስትም ራሱ የአንድ ፓርቲና ቡድን አገዛዝ መሆኑ ቀርቶ ሌሎችንም የሚያሳትፍበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው።
እስከአሁን ድረስ እየታየ ባለው አካሄድ የሚታየው ብዝሀነት ባላት አገር መንግስት ሁሉንም ነገር ቀፍድዶ ይዞ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን የሰፈነበት ሁኔታ ነው። ፓርቲው ከመንግስት አሰተዳደር ቁጥጥር አልፎ የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሳይቀር ቀስፎ የያዘበት ሁኔታ ይታያል። ስለዚህ ይህ አካሄድ ካልተለወጠ በስተቀር በዚች ሀገር ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም። ይህም በገዢው ፓርቲ በጎ ፈቃድ ብቻ የሚፈፀም ሆኖ አይታየኝም። አመራሮቹ ላገር አሳቢ ከሆኑ ይሄንን ጉዳይ አሁን አጥብቀው ሊያስቡበት ይገባል። አገር እየተበጣበጠ ከሚፈርስና ለእነሱም የማይበጅ ሁኔታ ከሚፈጠር ከወዲሁ መነጋገሩ ተገቢ ይመስለኛል።
ሰኞ ምሽት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ባወጣው መግለጫ ከህዝቡ ጋር እንወያያለን ብለዋል። ይህ ላለፉት 25 ዓመታት ሲኬድበት የነበረ መንገድ ነው። ይህ ፋይዳ የለውም። ሚዲያው በነፃነት ሲሰራ፣ የራሳቸው የምርጫ ውክልና ያላቸው ፓርቲዎች ተጠናክረው በመንግስት ስርዓት ውስጥ ተሳታፊ መሆን ሲችሉ እንጂ ለውጥ የሚመጣው፤ አንድ ፓርቲ ህዝቡን ስላወያየ አይደለም። ስብሰባና ውይይትን በተመለከተ ሁልጊዜም ከታች እስከላይ አመራሮቹ በስብሰባ እንደተጠመዱ ነው። ሆኖም ጠብ ነገር የለም። ይሄ ህዝብን እያወያየን መፍትሄ እናመጣለን የሚለው አካሄድ ላለፉት 25 ዓመታት ተሄዶበት መፍትሄ ያላመጣ ጉዳይ ነው። ህዝብ ሰብስቦ መስበክ የመሰረታዊው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ መሰረታዊው መፍትሄ ወደ ዋና ዋናዎቹ የፖለቲካ መፍትሄዎች ማምራት ብቻ ነው። ይህም የዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት ጉዳይና የዜጎች የነፃነት ጉዳይ ነው።
የመልካም አስተዳደር ችግር እየተባለ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጉዳይ ከጀርባቸው ወሳኝ ጉዳይ አለ። የሙስናም ሆነ የመልካም አስተዳደር መፈታት የሚችለው ህዝቡ በነፃነት ተደራጅቶ መታገል ሲችል ብቻ ነው። ሆኖም የህዝቡን ነፃነት አፍኖ፣ ነፃ ሚዲያዎችን መፈናፈኛ አሳጥቶ፣ ከእኔ በቀር ለዚች አገር አሳቢ የሚል አስተሳሰብን ይዞና አገሪቱ በአንድ ሳንባ እንድትተነፍስ በተደረገበት ሁኔታ ፈፅሞ ለውጥ ሊመጣ አይችልም። እንደውም የመልካም አስተዳደርና የሙስና ምንጩ ይህ ነው። በእኔ አስተያየት ኮሮጆ የሰረቀና፣ የህዝብ ድምፅ የሰረቀ ሰው ገንዘብ ከመስረቅ ወደኋላ ሊል አይችልም።
መንግስት ራሱ እንደሚያምነው በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የመዘፈቅ ሁኔታ አለ። ሙስናውም ቢሆን በግል ሳይሆን ተደራጅቶ ዝርፊያ በሚፈፀምበት አገር ፕሬስን የመሰለ ብርሀንን ከልክሎ በጨለማ እውነትን እንፈልግ ማለት ፈፅሞ የማያዋጣ አካሄድ ነው። አሁን የፖለቲካውን ምህዳሩ አስፍቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሚዲያው በነፃነት እንዲሰራ ሲደረግ ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሄ ማግኘት የሚቻለው።
በዚች አገር እኮ ለዘብተኛ ፓርቲዎች፣ ለዘብተኛ ሚዲያዎችና ለዘብተኛ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ችግሮችን በተደጋጋሚ እያነሱ መፍትሄ እንዲሰጠው ሲጎተጉቱ ቆይተዋል። አሁንም ይህ ከ20 ዓመታት በላይ የቆየ ጥያቄ መፍትሄ ሳያገኝ ቀርቷል። ለዘብተኛው አካል ተቀባይነት ማጣጡ ብቻ ሳይሆን መንገዱም እንዲዘጋበት መደረጉ አሁን ላለው ፅንፈኛ አመለካከትን ለያዘ ሀይል በርን ከፍቷል። እነዚህ አካላት “እንነጋገር ለዚች አገር በጋራ መፍትሄ እንፈልግ” ሲሉ ቦታ ማጣታቸው ነው ይህ አሁን እየታየ ያለ ችግር ሊከሰት የቻለው። ይህ በበርካታ ሀገራት የታየ እውነታ ነው። ሰላማዊው መንገድ ከተዘጋ ሊነሳ የሚችለው በየትኛውም አቅጣጫ አክራሪና ፅንፍ አመለካከትን የያዘው ኃይል እንዲፈጠር ማድረግ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ ሰላም ሊኖር አይችለም። ገዢው ፓርቲ እኔ ባልኩት መንገድ ብቻ በሚልበት ሁኔታ ፅንፍ አስተሳሰብ ካለው አጋር ጋር ሌላ ትግል ነው የሚፈጠረው። አሁን እየታየ ያለው ምልክትም ይህ እውነታ ነው።
ለዘብተኛ አመለካከት ያለው አካል ከተዘጋ ቀጣዩ መንገድ የሚሆነው በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች አመለካከቶች አክራሪ አመለካከት ያለው ኃይል እንዲፈጠር ማድረግ ነው። የፓርቲው አመራሮች አሁንም መፍትሄ ለመፈለግ እየሞከሩ ያሉት የተፈጠረውን ችግር በሚያካርር መልኩ በመሆኑ አሁንም ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸ
አሁን ህብረተሰቡ እያነሳቸው ያሉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህ ጥያቄዎች በርካታ ናቸው። ለምሳሌ የኦሮሚያ ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ ነው። ይህ ጉዳይ በተለይ ገበሬዎች ከቦታቸው ከተነሱ በኋላ የሚሰጣቸው የካሳ መጠን እና መንግስት ቦታውን ተረክቦ በሊዝ ሲያስተላለፍ የሚያገኝበት ገቢ ፈፅሞ የተራራቀ ነው። ይህ በአፋጣኝ ዛሬ ነገ ሳይባል መስተካከል መቻል አለበት። ይህ ጉዳይ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ባሉት የኦሮሚያ ከተሞች ላይ ብቻ የሚታይ ችግር ሳይሆን አሁን በስፋት እየተካሄደ ባለው የአዲስ አበባ መልሶ ማልማት ጋርም በተያያዘ ዜጎች ከነባር ቦታቸው እየተነሱ የሚያገኙት ገቢና መልሰው የሚሰፍሩበት ቦታ ጉዳይ ቅሬታ እያስነሳ ነው። ይህ ቅሬታ መፍትሄ ካላገኘ አሁንም ቢሆን ሌላ ተጨማሪ ችግርን ይፈጥራል። ልማት ስንል እኮ እየተነጋገርን ያለነው ስለህዝብ ነው። ይህ ከሆነ አንዱን በቀላል ካሳ አፈናቅሎ ሌለውን በቦታው መተካት ፍትሃዊነት አይኖረውም።
ይህ የችግሩ አንድ አካል ነው። ብዙ መፍትሄ የሚያሻቸው ችግሮች እንዳሉ መታወቅ አለበት። የሙስና የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር ጉዳይ ተደጋግሞ ሲነሳ ይታያል። መፍትሄው ሀገሪቱን በሚያስተዳደርው ገዢ ፓርቲ ብቻ ይመጣል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ሲቪክ ማህበራት ሲጠናከሩ፣ ነፃው ፕሬስ እየዳበረ ሲሄድና ሌሎች ፓርቲዎችም የሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ምህዳር እየሰፋ ሲሄድ ብቻ ነው መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው። ፓርቲው በግምገማና ህዝብን በማወያየት መፍትሄ አመጣለሁ የሚለው ጉዳይ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም። መንግስት በራሱ መዋቅራዊ አሰራርና በግምገማ ሊያገኛቸው የማይችል በርካታ ችግሮች እንዳሉ መታወቅ አለበት። ይህ ተፈጥሯዊ ነው። መፍትሄው ፕሬሱ እንዲጠናከር በማድረግ የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ እንዲጠናከር ማድረግ ነው። ዜጎች ሀሳባቸውን በሚዲያ እንዲያንሸራሽሩና በራስ መተማመንን እንዲያዳብሩ ማድረግ ነው። የፕሬስ ህጉም መሻሻል ካለበት ጠንካራ የሚዲያ ካውንስል ተፈጥሮ በአንድ መልኩ የሚዲያ ራሳቸውን በራሳቸው እያረሙ የሚሄዱበት አሰራር በሀቀኝነት መፈጠር መቻል አለበት። በሌላ መልኩ ይኸው የፕሬስ ካውንስል በፕሬስ ህጉ አላሰሩ ያሉትን አንቀፆች ለቅሞ በማውጣትና በማጥናት ለፓርላማ ቀርቦ መሻሻል የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር መቻል አለበት። ስለዚህ መንግስት በራሴ የመልካም አስተዳደርን ችግርና ሙስናን እዋጋለሁ ማለቱ ብዙም መንገድ አያስኬደውም። ግልፅነት እንዲኖር ማድረግ፣ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ሚዲያውን ዋነኛ ተዋናይ የሚሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል። በጎ ፈቃደኝነቱ ካለ ፕሬሶች በራሳቸው ባጀት የምርመራ ጋዜጠኝነት ያካሂዳሉ ማለት ስለሚከብድ፤ የአቅም ግንባታ ማድረግንም ይጠይቃል። በአጭሩ መንግስት “ሚዲያው የእኔ አጋር ነው” ብሎ ማመን መቻል አለበት። ከሰብአዊ መብት ድርጅቶችም ጋር ያለው የመንግስት ግንኙነት መሻሻል መቻል አለበት። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች በመፍትሄነት የሚታዩ ናቸው።
ስንደቅ