Wednesday, 24 August 2016 14:22

ተሀድሶው በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚታወቁ አመራሮችን ያስወግዳል ተብሎ ይጠበቃል

 

በዋንኛነት በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ባለፉት ወራት የታየውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሃሴ 10 እስከ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ያለፉትን የአስራ አምስት ዓመታት ጉዞ በመገምገም የገጠሙትን ችግሮች ለመቅረፍ ተሀድሶ ለማድረግ ውሳኔ አሳለፈ።

ግንባሩ ስብሰባውን ከትላንት በስቲያ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ «በአሁኑ ጊዜ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ከሚፈታተኑት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል። አገራዊ ለውጡ በስኬት ሲጓዝ የቆየው መንግስታዊ ስልጣንን ለህዝብ ጥቅም ማስከበሪያ ማድረግ በመቻሉ የሆነውን ያህል ይህ ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር የተጀመረው ልማት ይደነቃቀፋል። መልካም አስተዳደርም ይጠፋል።

በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው። ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ካለ ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኗል። ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅታችን ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ወስኗል። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትነ እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችም አዘጋጅቷል» ብሏል።

ኢህአዴግ በ15 ዓመታት ጉዞ ግምገማው መሰረት በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን ውስንነቶች በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ በመፍታት በምርጫ ካርድ የተሰጠውን ኃላፊነትና አደራ ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ እራሱን ገምግሞና አጥርቶ ለመንቀሳቀስ የጀመረውን የአስራ አምስት አመታት የተሃድሶ ጉዞ ግምገማ በየደረጃውና በሁሉም ተቋማት በጥልቀት አካሂዳለሁ ሲል ቃል ገብቷል።

የግንባሩ በቀጣይ በሚያደርገው ተሀድሶ ከላይ እስከታች ባሉት መዋቅሮች ውስጥ በሙስናና ብልሹ አሠራር የሚታወቁ፣ ከገቢያቸው በላይ ሐብት ያፈሩ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍጠርና በማባባስ ሕዝብን ያማረሩ ሹማምንቶቹን ከማባረርም በተጨማሪ የሚከሰሱም ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ህወሓት/ኢህአዴግ የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ተከትሎ በ1993 ዓ.ም በአመራሩ ውስጥ ባጋጠመው የመሰንጠቅ አደጋ ለመውጣት የመጀመሪያውን ተሀድሶ ማካሄዱ አይዘነጋም።

ግንባሩ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር በመቀሌ ከተማ ባካሄደው 10ኛ ጉባዔ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ከላይ እስከታች ባለው መዋቅር ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ያሳለፈውን ውሳኔ “መተግበር አቅቶታል፣ በግንባሩ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ፍርሃት ነግሷል” በሚል በአባላቱ ጭምር ትችት ሲሰነዘርበት መቆየቱ የሚታወስ ነው።

Leave a Reply