Wednesday, 17 August 2016 12:27
· የከተማው የታክሲና የባጃጅ ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል
በጎንደር ከተማ ለሶስት ቀናት በቆየው የቤት ውስጥ አድማ በርካታ የመንግስት ተቋማት ከስራውጪ መሆናቸውና የከተማዋ የታክሲና የባጃጅ ትራንስፖርትም ሙሉ በሙሉ መቋረጡን የከተማዋ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ አዳነ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ምንም አይነት ግጭት ያልታየበትን ሰላማዊ ሰልፍ ያስተናገደችው ከተማዋ ከባለፈው እሁድ እስከ ማክሰኞ (ከነሐሴ 8 እስከ 10 ቀን 2008 ዓ.ም) ድረስ በቤት ውስጥ አድማ ቆይታለች። በከተማዋ የትራንስፖርት መቋረጥ ምክንያት አብዛኛው ሰራተኛ በስራ ገበታው አልተገኘም ያሉት ኃላፊው፤ ቢያንስ ከ70 በመቶ ያላነሱ የመንግስት ሰራተኞች ግን ወደስራ ገበታቸው እንዲደርሱ ተጨማሪ ሰርቪስ መጠቀማቸውን አስረድተዋል።
በከተማዋ የመብራት ኃይል እጥረትና የኔትወርክ መጥፋት አጋጥሟል፤ በዚህም የተነሳ የከተማዋ ነዋሪዎች ምንም አይነት የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙበት አጋጣሚ ሳይኖር ይህ የቤት ውስጥ አድማ እንዴት እውን ሊሆን ቻለ? ስንል ጥያቄ ያቀረብንላቸው ኃላፊ ሲመልሱ፣ “ከፌስቡክ ውጪ በቀጥታ የስልክ ጥሪና በቃል ልውውጥ” ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው አስረድተዋል።
በሶስቱ ቀናት የቤት ውስጥ አድማ በከተማው እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ መኖሩን የተናገሩት ኃላፊው፤ በተለይም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያሉ ሰዎች ከእጅ ወደአፍ በሆነ ኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል” ብለዋል።
በተደረገው የቤት ውስጥ አድማ ምክንያት በስራ ገበታቸው ላይ ባልተገኙ የመንግስት ሰራተኞች ከደሞዛቸው እንደሚቆረጥ ክፍያ ይኖል የሚል ማስፈራሪያ እየተሰማ ነው መባሉን ተከትሎ፤ የከተማው የኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ፤ ይህ ነገሩ አሉባታ ነው፤ ሰራተኞቹ ከስራ ገበታቸው የቀሩት አንድም በፍርሃት አለበለዚያም ደግሞ በትራንስፖት እጥረት ነው ሲሉ የደሞዝ መቆረጥ ነገር አልተነሳም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በከተማዋ ምንም አይነት የመብራት መቆራረጥ የለም ያሉት ኃላፊው፤ የኢንተርኔት መቆራረጥን በተመለከተ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገጥመው ወጣ ገባ ነው ሲሉ በአካባቢው ያሉ የፋይናንስ ተቋማትን እንቅስቃሴ ለገደብ እንደሚችል ግን አልሸሸጉም። የከተማዋ የትራንስፖርት መቋረጥ እንዳለ ሆኖ አገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻዎች ግን ወደከተማው መናኸሪያ በሰላም ገብተው እየወጡ ነው ብለዋል።
የጎንደር ከተማን ህዝብ ጥያቄ ለመስማት አስተዳደሩ ዝግጁ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ምንጊዜም ሰላማዊ ውይይት ለማድረግ ተዘጋጅተናል። በየክፍለ ከተማው ለሚገኙ የስራ አመራሮች ጥያቄያቸውን እንዲቀርቡና መልሱንም በትእግስት እንዲጠባበቁ ሲሉ ተናግረዋል። የአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል መንግስት ለህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የሚጠብቅ ነው ያሉት ኃላፊው በውይይት ወደመግባባት እየመጣን ነው ሲሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ስንደቅ