እንደሚታወቀው ላለፉት 25 አመታት መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ አፍኖ እየገዛ የሚገኘውና በወንበዴው ህወሀት የበላይነት የሚመራው የወያኔ ቡድን የአገራችንን አንጡራ ሀብት እየዘረፈና ውድ የኢትዮጵያ ፈርጥ የሆኑ ልጆቿን በማሰር በመግደልና በአጠቃላይ የግፍ ቀንበር በመጫን እያደረገ ያለውን ጭፍጨፋ በቁጭት እየተከታተልነው እንገኛለን፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በቋንቋ በመከፋፈል ህዝብን እርስ በርስ ለማጫረስ ወያኔ እያደረገ ያለውን እኩይ ተግባር የኦሮሞና የአማራ ልጆች እጅ ለእጅ ተያይዘው አስከፊውን ስርአት ከስሩ ገርስሶ ለመጣል በከፍተኛ ደረጃ እየተዋደቁ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ከ 8 ወራት በላይ እየዘለቀ ያለው የኦሮሞ ወገኖቻችን እያደረጉ ያለውን መብት የማስከበር ትግል፣ በመቀጠልም በአማራው ወገናችን የተቀጣጠለውን ህዝባዊ እምቢተኝነትና በቀሪዎች የአገራችን ግዛቶች እየተዛመተ ያለውን የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴ ለማፈን በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የወያኔ ወንበዴ አጋዚ ወታደሮች እያደረሱ ያለውን ኢ-ሰብአዊ ጭፍጨፋ እናወግዛለን፡፡
በአገራችን አራቱም ማእዘናት የኢትዮጵያ ህዝብ ለመሰረታዊ የመብት መከበር ጥያቄ ባነሳው የህዝብዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ በወንበዴው ስርአት እየደረሰበት ያለውን ማንኛውም የኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሊያስቆመው አይችልም፡፡ እየተደበደበ፣ እየታሰረ፣ እየተሰደደ፣ እየሞተና ቢዘረዘሩ ቦታ የማይበቃቸው ግፎች እየተፈጸመበት እንኳን ግንባሩን ሳያጥፍ እያደረገ ያለው ተጋድሎ እኛን ያኮራን ሲሆን ይህንኑ ቀጣይ ለማድረግ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንንቀሣቀሣለን፡፡
በአገራችን ያልተሸራረፈ የዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት ማጠናከርና የሀገራችን ዳር ድንበር ተከብሮ ህዝባችን በአለም አደባባይ ኮርቶ የሚንቀሳቀስበት፣ ከስደትና ረሃብ የሚላቀቅበት እንዲሆን ለማስቻል በወያኔ ህወሀት የሚመራው አምባገነናዊ ስርአትን ለማስወገድ በሚደረገው ህዝባዊ እንቅስቃሴ አጋር በመሆን የተከበረች ኢትዮጵያ እስክትገነባ ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፡፡ የወያኔ ቡድን ስርአት እንዳይወድቅ የአጋዚ ቅልብ ወታደሮችና የስርአቱ ደጋፊ በመሆን ትርፍራፊ ለማግኘት የተለጠፉ ሆዳም የስርአቱ አገልጋዮች ከሚያደርጉት እኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡና በመደረግ ላይ ያለውን የህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ በመደገፍ ከህዝቡ ጎን እንዲቆሙ አበክረን እናሳስባለን፡፡
የመከላከያም ሆነ የፖሊስ ሰራዊት ዋና ተግባራችሁ የሆነውን አገር ዳር ድንበር የማስከበርና የህዝብን ሰላም ማረጋገጥ መሆኑን ተገንዝባችሁ ከህዝብ ጎን በመቆም አጋርነታችሁን የምታሳዩበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢያችን ለወያኔ ስርአት የስለላ ተግባር እየፈጸሙ የሚገኙ ወገኖች ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ እያስጠነቀቅን ከዚህ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ እንደምናጋልጥና ጉዳዩንም ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እንደምናሳወቅ በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡
በተለይ በህዝባችን መካከል ለዘመናት የቆየውን የአንድነት ትስስር በመናድ በከፋፍለህ አገዛዝ በስልጣን ላይ መቆየት እንደማይቻል እስከዛሬ የዘለቀው የህዝባችን የጋራ ትግል እንቅስቃሴ አይነተኛ ማሳያ መሆኑን የወያኔ መንግስትና ለሰርአቱ በማደግደግ ላይ ያሉ ወገኖች ሊረዱት ይገባል እንላለን፡፡ ስለሆነም በአሁን ወቅት እየተቀጣጠለ ያለውን የነጻነት ጥያቄ መልስ የሚያገኘውና በህዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረው አንድነት በአስተማማኝነት ተጠብቆ በሰላም መኖር የሚቻለው ለነዚህ አቢይ የህዝብ መለያ የሆኑትን ሰላምና አንድነት ጠላት የሆነው የወያኔ አምባገነናዊው ስርአት ሲወገድ ብቻ ነው፡፡
በመጨረሻም የሁላችን ጠላት የሆነውን የወያኔ ስርአት ለማስወገድ እና ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንባትና ነጻነት የሰፈነባትን አገራችን ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በአንድነት ተነስተን እየተቀጣጠለ ያለውን የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል በማንኛውም መልኩ በመደገፍ መሆኑን ሙሉ በሙሉ በማመን ወያኔን በማስወገድ የድል ችቦ እስክናበራ ድረስ ድጋፋችንን በቆራጥነት የምንቀጥል መሆናችንን እንገልጻለን፡፡ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!
በኦክላንድ ኒውዚላንድ የምንኖር የኢትዮጵያ ማህበረሰብ።