ኢ.ኤም.ኤፍ –
ዳዊት ከበደ ወየሳ
በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች እየተነሳ ያለው የህዝብ ተቃውሞ፤ ከእለት ‘ለት እየተባባሰ እንጂ እየበረደ አልመጣም። በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአማራ የተነሳው የህዝብ አመጽ የህወሃት ወይም የትግራይ ነጻ አውጭ ወታደሮችን ከክልሉ እየጠራረጋቸው ነው። ከዚያም አልፎ ህዝቡ በየደረሰበት፤ የሰይጣን አርማ (አንዳንዶች አምባሻ ይሉታል) ኮከብ
ያለበትን ባንዲራ በማውረድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰንደቅ አላማ የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ በመስቀል ላይ ናቸው።
ህዝቡ በልዩ ልዩ መንግስታዊ ተቋማት እየገባ፤ የሰይጣን አርማ ያለበትን ባንዲራ በማውረድ የህዝቡን ሰንደቅ አላማ ሲሰቅል፤ የመስሪያ ቤቱ ዘቦች ነገሩን በዝምታ ከማየት ውጭ ምንም አይነት ተቃውሞ አላሰሙም። ከዚህ ውጭ ህዝቡ በሚገርም ሁኔታ፤ የመንግስት ተቋም የሆኑ ንብረቶች… ነገ መንግስት ቢለወጥ መልሶ የራሱ መሆኑን በማመን፤ በተቋማቱ ላይ ምንም አይነት የጥፋት እርምጃ አልወሰዱም። ይህ ደግሞ የህዝቡን ሰላማዊነት ብቻ ሳይሆን፤ አርቆ አሳቢነት የሚያሳይ ነው።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በኢትዮጵያ ህዝብ ሰንደቅ አላማ ላይ በውጭ አገር፤ በተለይ የሰይጣን እምነት ተከታዮች አርማ የሆነውን በክብ መደብ ላይ የተቀመጠ ኮከብ ማድረጉ ይታወቃል። ይህን በክብ መደብ ላይ የሚቀመጥ የኮከብ ምልክት የሰይጣን አርማ መሆኑን፤ በወቅቱ በተለይ በነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ተከታታይ የሆኑ የተቃውሞ ጽሁፎች ይቀርቡ ነበር። እንዲያውም አትቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ ተከታዮቻቸው ሃይማኖት የማይገዛቸው ኮሚኒስቶች ስለነበሩ፤ ያቺን የሶሻሊስት ቀይ ኮከብ ለማስታወስ ያደረጉት ነው የሚል አስተያየት የሰጡ ሰዎችም ነበሩ። ሆኖም ኮከቡ በክብ ከተቀመጠ ግን ትርጉሙ ግልጽ ሆኖ ሳለ፤ የገዥው መደብ ነገሩን በማክረር፤ ይህ የሰይጣን ምልክት በኢትዮጵያ ህዝብ ሰንደቅ አላማ ላይ እንዲለጠፍ በአዋጅ ጭምር አጽድቆታል።
ይህ ምልክት የሌለበትን ባንዲራ የያዘ ሰውም በወንጀል የሚጠየቅበትን አዋጅ አውጥቶ አጸድቋል። በአዋጁ መሰረት ኮከብ ያለበትን ባንዲራ ያልተጠቀመ ሰው እስከአንድ አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል። በአንድ ወቅት በዚህ ምክንያት ብዙ ቲሸርቶች እና ኮከብ የሌለበት ባንዲራ እየተወረሰ ተወስዷል። አዋጁ እንደሚለው ‘ኮከብ የሌለበት ባንዲራ ያቃጠላል’ እና በሙሉ ወስደው አቃጥለውታል። ብዙ ወጣቶችም ታስረዋል። አሁን ይሄ ሁሉ ወደጎን በመተው ወጣቱ የአባቶቹን ሰንደቅ አላማ ማውለብለብ መጀመሩ ብዙዎችን አስደስቷል።
ይህን ክስ እና ውንጀላ ሳይፈራ ነው፤ ህዝቡ ይህን ባለኮከብ አርማ እያወረደ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰንደቅ አላማ እየሰቀለ ያለው።
አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ፡እየተከናወነ ያለው የአንድ ዘር የበላይነት አሰራር ግን እኩልነትን አይገልጽም፤ አንድነት እንዳይመጣም ኢህአዴግ ህዝቡን በዘር ከፋፍሎታል። በተለይ በከተሞች አካባቢ ህዝቡ ተስፋ እንዲያጣ እየሆነ ነው። ይህም ሆኖ ግን የኮከቡ አርማ ትርጉም… በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ 654/2001 መሰረት – አንቀፅ 8 ላይ “በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ሰላምን፣ እኩልነትን አንድነትን እና ተስፋን ገላጭ ነው” ይላል። ሃቁ ግን ኮከቡ እኩልነትን ሳይሆን፤ እኩይነትን የሚወክል የኢህአዴግ ሰይጣናዊ አርማ መሆኑን ህዝቡ በሂደት የተረዳው ይመስላል።
የሰንደቅ አላማውን አዋጅ ጉዳይ ካነሳን አይቀር አንድ ነገር እንጨምር። የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/ 2001 አንቀፅ 4 “ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በየዓመቱ መስከረም ሁለኛ ሳምንት ሰኞ ይከበራል” ይላል፡፡ እንደአዋጁ ከሆነ፤ ይህ ቀን ሊከበር ጥቂት ሳምንታት ቀርተዋል። አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ… በዚህ ቀን ባለኮከቡን ሰንደቅ አላማ ማውረድ እንጂ፤ ማውለብለብ የሚታሰብ አይመስልም። ይልቁንም የህዝብ የሆነው ሰንደቅ አላማ፤ በአንድ ወቅት ፓን አፍሪካውያን “የኛም ባንዲራ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ይሁንልን” ያሉት ሰንደቅ ከፍ ብሎ ይውለበለባል።