Wednesday, 31 August 2016 12:54
ዶክተር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም
በኦሮሚያ እና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሰሞኑን የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ም/ቤት በሰጡት መግለጫ ላይ የዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያ የሆኑትን ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያምን አነጋግረናቸው እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ሰንደቅ፡- ከወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ገዢው ፓርቲ በሥራ አስፈፃሚ እና በምክር ቤት ደረጃ ሁለት መግለጫዎች አውጥቷል። ከወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ጋር የተሰጠው ምላሽ ምን ያህል የተቀራረበ ነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡-አሁን ለተፈጠረው አጠቃላይ የፖለቲካ ተቃውሞ ምላሽ የሰጠ መግለጫ ነው የሚል እምነት የለኝም። ጠቋሚ ሃሳብም አላየሁበትም። ምክንያቱም በዋናውን የችግሩን ምንጭ ላይ ያሉት ነገር ባለመኖሩ ነው። ይኽውም በሰላማዊ ሰልፎቹ የሰማነው የሰላም፣ ፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ብቻ አይደለም። በተደረጉት ሰልፎቹ ሕዝቡ ግልፅ የሆነ የስልጣን ጥያቄ አንስቷል። ሀገራችን በኢሕአዴግ ብቸኛ የስልጣን ቁጥጥር ስር ብቻ አትውልም፤ ለሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችም በሀገራቸው ፖለቲካ ውስጥ የመወሰን መብታቸው ሊጠበቅ ይገባል እና ሌሎችም ከስልጣን ጋር የተያያዙ መልክቶች ሕዝቡ በአደባባይ አሰምቷል።
ስለዚህም ኢሕአዴግ ይህን የሕዝቡን ፍላጎት በድፍረት ሊጋፈጠው ይገባል። ሕዝቡ አማራጮችን መመልከት ፈልጓል። ሕዝቡ ከእንግዲህ ኢሕአዴግ ብቻውን የማስተዳደሩ ነገር ሊቆም ይገባል ብሏል። ለዚህ የሕዝብ ጥያቄ ከፓርቲው የወጡት መግለጫዎች ግልፅ ምላሽ አልሰጡም። ይህም በመሆኑ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ እስካሁን ድረስ አልበረደም። በሌሎቹም ተመሳሳይ ነው።
ሰንደቅ፡- የሥልጣን ጥያቄ ተነስቷል ባሉት ነጥብ ላይ፣ የሥልጣን ጥያቄ ሲባል በምን መልኩ የሚስተናገድ ነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- የሥልጣን ጥያቄ ሲባል ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብ በሚሰጣቸው ድምፅ መጠን ሥልጣን ተከፋፍለው ይህችን ሀገር ማስተዳደር ማለት ነው። የአንድ ፓርቲ አገዛዝ በምንም አይነት ተቀባይነት የለውም። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገሮችም የአንድ ፓርቲ አገዛዝ ተቀባይነት አይኖረውም። በዓለም ላይ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ስር የሚገኙ ሀገሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ይህንን አስተዳደር እንዴት መፍጠር ይቻላል ወይም ይደረስበታል ለሚለው መነጋገር ይቻላል።
ይኽውም፣ አንድ በጣም ትልቅ ሀገራዊ ጉባኤ አድርጎ ከውስጥም ከውጭም የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጋብዞ መወያየት። በዚህ ጉባኤ የሐይማኖት መሪዎች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች የሀገር ባለውለታዎች ተሰብስበው ሀገራችን እንዴት ትተዳደር? እንዴት ወደፊት ትሂድ? የፖለቲካ አደረጃጀታችን ምን ይምሰል? እና ሌሎች ጥያቄዎችን አንስቶ መወያየት ያስፈልጋል። በመቀጠል ደግሞ የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት ማድረግ ነው። ሁለት ዓመት የሽግግር መንግሥቱ ቆይቶ ነፃ ምርጫ ተደርጎ ያሸነፈ ያሸንፍ። ኢሕአዴግ በነፃ ምርጫ ካሸነፈ ሕዝቡ በደስታ ይቀበለዋል። ስለዚህ መነጋገሩ ጥሩ ነው።
ሰንደቅ፡- መሬት ላይ ካለው ጥሬ ፖለቲካ አንፃር፣ ስልጣን ለማጋራት ጥሪ የሚያቀርብ የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላው ሀገር አለ ብሎ መውሰድ ይቻላል? የዓለም ተሞክሮንስ በዚህ አግባብ መጥቀስ ይቻል ይሆን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ብዙ ሀገሮች ውስጥ የሚሰራ አሰራር ነው። ለምሳሌ በሀገራችን ብንወስድ የሽግግር መንግስት ከተቋቋመ በኋላ ነው ወደ ቋሚ መንግስት አስተዳደር የተሸጋገር ነው። ይህን አሁንም መጠቀም እንችላለን።
ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የሽግግር መንግስት በሕገ መንግስታዊ የአስተዳደር መዋቅር ከተተካ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኖታል። የመንግስት ስልጣን እንዴት እንደሚያዝ በግልፅ ሰፍሯል። ስለዚህም ምንአልባት ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ምርጫ እንዳይገቡ የሚከለክል ወይም እንቅፋት የሚፈጥር የሕግ ማዕቀፍ ካለ ይህንን ችግር ተነጋግሮ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ቀርፆ እርስዎ ወዳነሱት ሃሳብ መድረስ አይቻልም?
ዶክተር ያዕቆብ፡- አሁን የተነሳው ነጥብ አንዱ መንገድ ነው። ለሌሎች ፓርቲዎች ወደ መንግስት ስልጣን እንዳይመጡ የሚከለክሉ ሕጎች ማሻሻል መቀየር አንዱ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለምሳሌ የፀረ ሽብር አዋጅ አንዱ መቀየር የሚገባው ሕግ ነው። ሌሎችም አዋጆችን አሻሽሎ ፓርቲዎች በነፃ ምርጫ እንዲወዳደሩ ማድረግ ይቻላል። ችግሩ ያለው ይህንን ሊያደርግ የሚችል ማን ነው? ካለም ኢሕአዴግ ነው። በኢሕአዴግ ግን እምነት ያለው አንዳችም የፖለቲካ ኃይል የለም። ሕዝብም የለም። በሰላማዊ ሰልፎቹም የተንጸባረቀ ነው።
በነገራችን ላይ የሽግግር መንግስት ከመመስረት የሕግ ማዕቀፎችን አስተካክሎ ወደ ምርጫ መግባት የተሻለው አማራጭ ነው። ሆኖም መተማመን ላይ ግን መድረስ አይቻልም። ለአድልዎ ይፈጻማል የሚል እምነት የለኝም።
ሰንደቅ፡- ከሕዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችን ተንትኖ የፖለቲካ መሰረት አድርጎ አደራጅቶ የወጣ ኃይል እስካሁን ብቅ አላለም። ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳይጠብቅ በራሱ ጊዜ ሰልፎችም ተቃውሞዎችንም አሰምቷል። ይህ በሆነበት ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣን መጋራትም ሆነ አዲስ የመንግስት ስልጣን ለመረከብ የሚያስችል ሁኔታ እንዴት ይፈጠራል?
ዶክተር ያዕቆብ፡- እርግጥ ነው ሕዝቡ ቀድሞ ተገኝቷል። ኢሕአዴግ በበኩሉ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ፣ ሙስናን አጠፋለሁ ነው እያለ ያለው። የሕዝቡ ጥያቄ ግን ኢሕአዴግ እንደሚለው አይደለም። ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚጠይቀው የኢሕአዴግ ብቸኛ አምባገነን የሆነ አስተዳደር መቆም አለበት ነው የሚለው። የህዝቡ ጥያቄ ካልተመለሰ ወዴት እንኳን እየሔድን እንደሆነ መገመት አይቻልም። ሕዝቡ በተከፋፈለበት ሁኔታ ወደ አላስፈላጊ፣ በጣም አስፈሪ ወደሆነ ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ከዚህ በፊት በርካታ አርቲክሎች ካየሁት መጥፎ የፖለቲካ ሁኔታዎች በመነሳት ጽፌያለሁ። በጣም የከፋ ነገር ሊገጥመን ይችላል። በጊዜ ይቀጭ። ሀገር ሊፈርስ ይችላል።
ሰንደቅ፡- በፕሬዝደነት ሙባረክ ላይ የግብፅ ሕዝብ ባቀረበው ቅሬታ መነሻ የተቀሰቀሰው ሕዝበዊ ተቃውሞ ከአንድም ሁለት ጊዜ መጠለፉ የሚታወቅ ነው። ምክንያቱም በሕዝቡ ቅሬታ ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመኖራቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑ ይነገራል። በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሳሳይ ክፍተት እንደማይፈጠር ምን ማረጋገጫ ማቅረብ ይቻላል?
ዶክተር ያዕቆብ፡- እርግጥ ነው መሬት ባለው ሁኔታ ኢሕአዴግ ነው ፖለቲካው ላይ ያለው። የለውጡ እንቅስቃሴ እንዲሳካ የኢሕአዴግ በጎ ፍቃድ ያስፈልጋል። ኢሕአዴግ ሕዝቡን ከስልጣኑ በላይ አስበልጦ መመልከት ይጠበቅበታል። ሁላችንም ኃላፊዎች ነን። ሀገር እና ሕዝብ ግን አያልፍም። መስዋዕትነት መክፈል ያስፈልጋል። አሁን የተያዘው ግን ሙስና መዋጋት፣ መልካም አስተዳደር እየተባለ ነው። ችግሮችን ሁሉ በመልካም አስተዳደር ለማጠር እየተሞከረ ነው። ዴሞክራሲ በሌለበት ሀገር መልካም አስተዳደር ሊመጣ አይችልም። ተጠያቂነት የለም። እነዚህን መዋጋት የሚቻለው ሥርዓቱን በመቀየር ነው። ሥርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ነው።
ሰንደቅ፡- መልካም አስተዳደር የሚለው የፍቺ አውድ በጣም ጠቦ ስለሚቀመጥ ካልሆነ በስተቀር መልካም አስተዳደር ከፖለቲካ ከዴሞክራሲ እና ከሰብዓዊ መብት ጋር አያይዞ መውሰድ አያቻልም?
ዶክተር ያዕቆብ፡- መልካም አስተዳደር የሚመሰረተው አስተዳዳሪው ተጠያቂ ሲሆን ነው። በሕዝብ የተመረጠ ሲሆን ነው። መልካም አስተዳደር የማያመጣ ከሆነ ሕዝብ ሊሽረው የሚችል አስተዳዳሪ ሲሆን ነው። ይህ የሚሆነው ዴሞክራሲ ካለ ነው። በአዋጅ እና በመግለጫ ብቻ ለውጥ አይመጣም። መልካም አስተዳደር የሥርዓት ጥያቄ ነው። በነፃ ምርጫ ስልጣን በሚያዝበት ሀገር ውስጥ ሙስና አንድ ችግር እንጂ የሥርዓቱ መገለጫ ተደርጎ ሲነገር አይሰማም። በእኛ ሀገር ግን ለየት ይላል። ለዚህም ነው የሥርዓት ችግር የሚሆነው።
ሰንደቅ፡- ጠቅለል አድርገው በሥርዓቱ ላይ ያሉ መልካም ጎኖች እና መታረም አለበት የሚሉትን ነጥቦች ቢገልጹልን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- መቼም ሁሉም ነገር መጥፎ ነው አይባልም። መሰረተ ልማቶች በጥሩ ሁኔታ ለማሟላት ከፍተኛ ሥራዎች ተሰርተዋል። ለምሳሌ መንገድ፣ ባቡር፣ የመገናኛ አውታሮችን መጥቀስ ይቻላል። በኢኮኖሚ ደረጃም ለውጦች አሉ። ፈቅ ያሉ ነገሮች ይታያሉ። ሆኖም ከፍትሃዊነት አንፃር ግን ብዙ የሚቀሩ ስራዎች አሉ። ዋናው ጉድለት ግን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመሆኑ ነው። በዚህ መልኩ ወደፊት የሄደው ነገር የለም።
ተጨማሪ ጽህፎች ከ news admin
“ጠንካራ የሀይማኖት መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ እንዲህ አይነቱ ሥጋት ላይ አንወድቅም ነበር”
የጥራት መንገድ
የአጭር ልቦለድ ዐበይት ባሕርያት
በዚህ አምድ: