Wednesday, 31 August 2016 12:51
“ጠንካራ የሀይማኖት መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ
እንዲህ አይነቱ ሥጋት ላይ አንወድቅም ነበር”
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
በይርጋ አበበ
ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተለያዩ ወቅታዊ የማህበራዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሳል አስተያየቶችን በተለያዩ መንገዶች በመጻፍ መፍትሔ ከሚፈልጉ ወጣት ምሁራን አንዱ ነው። ወደ 30 የሚጠጉ ሀይማኖታዊ ማህበራዊና ፖለቲካ ነክ የሆኑ መጽሃፎችን ለአንባቢያን አቅርቧል። ወጣቱ ብዕረኛ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትምህርቱን ተከታትሎ የተመረቀ ሲሆን በቤተ ክህነት አገልግሎቱ ደግሞ “ዲያቆን” ነው።
በወቅቱ የአገራችን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት የተነሳ በርካታ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን አስመልክቶ በርካቶች በአገራችን የሚገኙ የሀይማኖት መሪዎች ሚና ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ይታያሉ። በእንደዚህ አይነት የአገር አለመረጋጋት ሲያጋጥም የሀይማኖት መሪዎች ሊጫወቱት ስለሚገባቸው ሚና፣ አሁን አገሪቱ ለምትገኝበት ሁኔታ የበቃችው በምን ምክንያት እንደሆነ እና በቤተ ክህነት ዙሪያ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው የመፍትሔ ሀሳቦች ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ሰንደቅ፦ አገራችን ያለችበትን ሁኔታ እና የሀይማኖት መሪዎችን እንቅስቃሴ እንዴት ትገልጸዋለህ?
ዲያቆን ዳንኤል፦ከየአቅጣጫው የምንሰማቸው ነገሮች ጥሩ ዜና አይደሉም። ይህ የሚያሳየው ስጋት ላይ መሆናችንን ነው። ሀይማኖት አጥፊውን ገስጾ ወይም አስተካክሎ ለተጠቂው የሚቆም ተቋም ነበር በታሪክ ውስጥ። ለምሳሌ ክርስቶስን ያየህ እንደሆነ የተከሰሰበት ከተጠቂው ወይም ከድሃው ወገን ስለነበረ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክም የቀድሞ የሀይማኖት መሪዎች ንጉሱን ገስጸው ከተጠቂው ወገን ሲቆሙ ተመልክተናል። በሂደት ይህ አሰራር እየተሸረሸረ መጥቷል። ጠንካራ የሀይማናት መሪዎችና የሀይማኖት ተቋማት ቢኖሩ እንዲህ አይነቱ ስጋት ላይ አንወድቅም ነበር። ምክንያቱም ነገሩ ሲከፋ “ተዉ” ይሉ ነበር። ተዉ የሚል የሀይማኖት መሪ ባለመኖሩ ነው ለዚህ አይነት ስጋት የተዳረግነው።
የሀይማናት መሪዎቹ ተዉ ማለት ብቻ ሳይሆን ተዉ ለማለትም አቅም ይኖራቸዋል። ሲናገሩ ደግሞ ይሰማሉ። ይህን አቅም የምታገኘው ደግሞ ከንጽህና ነው። ከዚህ በፊት ከነበረህ የህይወት ጉዞ ከአንዱ ወገን ከወገንህ ወይም ወይም የአንተን ድክመት እያወቀ ሲመጣ ግን ህዝቡ የምትናገረውን አይሰማህም። የአንተን ንጽህና እና አቋም ጠንካራ መሆን ሲያውቅ ግን ህዝቡ ይሰማሃል። ስለዚህ መንግስትንም ሆነ ህዝቡን ተው ማለት ይችላል ማለት ነው። በመሃል ገብቶ ከዚያም ከዚህም መስተካከል ያለበትን ማስተካከል ይቻላል። ይህን ማድረግ የሚችል ሰው አለመኖሩ ግን እኛን ጎድቶናል።
ሰንደቅ፦ የሀይማኖት መሪዎች ሚና ምን መሆን አለበት?
ዲያቆን ዳንኤል፦የሃይማኖት መሪዎች መካከለኛ ሚና መጫወት አለባቸው ብዬ ነው የማምነው። መንግስትንም ሆነ ህዝቡን መደገፍ ሳይጠበቅባቸው እውነትን ደግፈው ሊቆሙ ይገባል። የእምነት ተቋማት መሪዎች ምንጊዜም እውነትን ይዘው ነው መቆም የሚገባቸው። ምናልባት እውነቱ ባይገለጽላቸው እንኳ ጥያቄ ያነሱት እና የሚጠየቀው አካል ማለትም ህዝብ እና መንግስት የሚነጋገሩበትን መንገድ በባህላችን መሰረት ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ መፍጠር አለባቸው። አኮረፍኩ የሚለው ኩርፊያውን ትቶ፣ አንተ አታስፈልገኝም የሚለውም ይህን አቋሙን ትቶ ተቀራርበው ወደ ሰላም የሚመጡበትን መንገድ ነው ማመቻቸት ያለባቸው። ልዩነት ሊኖር ይችላል፤ ልዩነት ሁሉ ጥላቻ ስላልሆነ ልዩነትን ወደ ጎን ትቶ ወደ ውይይት እንዲያመሩ ለማድረግ መንገዶችን ማመቻቸት ያለባቸው የሃይማኖት መሪዎቹ ናቸው።
ሰንደቅ፦ አንዳንዶች የወቅቱን የአገራችንን የፖለቲካ አለመረጋጋት ሲገልጹ “አገሪቱ ወደለየለት ቀውስ ውስጥ ልትገባ ነው። አልቆላታል” ሲሉ ይገልጹታል። በተቃራኒው መንግስት ደግሞ በአገሪቱ እዚህ ግባ የሚባል የጸጥታ ችግር አለመፈጠሩን፣ ለግጭቶች መፍትሔ የሚሆን ሀይል ደግሞ ከመንግስት አቅም በላይ አለመሆኑን ይገልጻል። አንተ የወቅቱን ሁኔታ እንዴት ነው የምትገልጸው?
ዲያቆን ዳንኤል፦ እኔ ሁለቱም ትክክል ናቸው አልልም። ኢትዮጵያ አልቆላታል የሚባለውን ስናይ ኢትዮጵያ አላለቀላትም ግን ተንገጫግጫለች። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በነበረው ረጅም ታሪኳ እኮ እንደዚህ አይነት ችግር ሳይገጥማት አይደለም የኖረችው። ስለዚህ ኢትዮጵያ አላለቀላትምም፣ አያልቅላትምም። ነገር ግን ያለችው በጦርነት እና በሰላም መካከል ነው። ህዝቡ ጥያቄ አለው። ይህን የህዝብ ጥያቄ ደግሞ መንግስት መፍታት አለበት።
እንደ ተማሪ እና አስተማሪ ካየኸው ተማሪው ጥያቄ አለኝ ሲል አስተማሪው ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ መስጠት እንጂ “ይህን ጥያቄ መጠየቅ የለብህም ወይም ጥያቄውን የጠየከው አጎትህ ነግሮህ ነው” ማለት የለበትም። ተማሪው ጥያቄውን አጎቱም ይንገረው አክስቱ ጥያቄ እስከጠየቀ ድረስ ግን አስተማሪው ጥያቄውን መመለስ አለበት። አስተማሪው የተማሪውን ጥያቄ ሰምተው የማይመለከታቸው ቢሆን እንኳ ይህን የሚመልስልህ የዚህኛው ትምህርት አስተማሪህ ስለሆኑ ጥያቄውን ለእኒያ አስተማሪህ አቀርብልሃለሁ ማለት አለበት እንጂ ፈጽሞ ጥያቄውን አልሰማም ማለት የለበትም።
ህዝብ ደግሞ ሲጠይቅ መንግስት የህዝብ ስለሆነ የህዝቡን ጥያቄ መስማት አለበት። በነገራችን ላይ ህዝብ ስላለ እኮ ነው መንግስት የኖረው። ከመንግስት ህዝብ ይቀድማል። መንግስት ሳይኖር ህዝብ መኖር ይችላል። ህዝብ ሳይኖር ግን መንግስት ሊኖር አይችልም። የመንግስት ህልውና የተመሰረተው በህዝብ መኖር ላይ ነው። ስለዚህ ህዝብ ላይ ህልውናውን የመሰረተ መንግስት ምንድን ነው ጥያቄያችሁ ብሎ መስማት አለበት። አሁን ያለው የአገራችን መንግስት ማድረግ ያለበት የህዝቡን ጥያቄዎች ሊያቀርቡለት የሚችሉ ገለልተኛ ህዝቡ ይወክሉኛል ያላቸውን መርጦ የሚልክለትን ጥያቄ ቁጭ ብሎ መስማት ነው። ጥያቄዎቹ አንዳንዶቹ ወዲያውኑ የሚመለሱ ይሆናሉ አንዳንዶቹ ደግሞ በወር ጊዜ ውስጥ የሚፈቱ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በሂደት የሚፈቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያ ላይ ተግባብቶ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሞ መስራት ተገቢ ነው።
ሰንደቅ፦ መንግስት እኮ ከህዝቡ የሚነሱለትን ጥያቄዎች ከመስማት ይልቅ የመግፋት እና በሌላ ሶስተኛ ወገን ላይ በማሳበብ ጊዜውን ያጠፋል እየተባለ ነው የሚታመው። በዚህ አይነት መልኩ የህዝቡን ጥያቄ እንዴት መፍታት ይቻላል?
ዲያቆን ዳንኤል፦ መንግስት ሆኖ የማይሳሳት የለም። መንግስት አልሳሳትም ብሎ መነሳት የለበትም። መሳሳት ብቻ አይደለም ሊያጠፋም ሁሉ ይችላል። በዓለም ላይ የማያጠፋ መንግስት የለም። ልዩነቱ ጥፋቱን የሚያምን እና ጥፋቱን የማያምን መንግስት መኖራቸው ነው እንጂ የማያጠፋ መንግስትማ በዓለም ላይ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ጥፋትን አምኖ መፍታት ይገባል እንጂ ባልተፈታ ቁጥር ግን ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ ይሄዳሉ። ህዝብ ለመንግስት ሶስት እድሎችን ይሰጣል ይባላል። “አስተካክል፣ ተስተካከል እና ተወገድ” ብሎ። የመጀመሪያው አንተ ትክክል ነህ ግን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግር እየገጠመህ ስለሆነ አሰራርህን አስተካክል ብሎ ይጠይቃል። ይህን ጥያቄ ዝም ብሎ ካለፈው ሁለተኛው ጥያቄ ይከተላል። ሁለተኛው ጥያቄ “አንተ ላይ፣ አሰራርህ ላይ፣ ጠባይህ ላይ፣ አካሄድህ ላይ ችግር አለ። ችግሩ የአንተ አሰራር ችግርህ ነጸብራቅ ነው እንጂ አንተ ጥሩ ሆነህ ችግሩ መጥፎ ሆኖ አይደለም። ስለዚህ ተስተካከል ይላል። ይህኛውም ጥያቄ ካልተመለሰ ሶስተኛው ይከተላል። ይህ ጥያቄ ደግሞ “አንተ ልትስተካከልህ ስላልቻልህ ተወገድ እና ሌላ የተስተካከለ አመጣለሁ” ይላል።
ስለዚህ መንግሥት የትኛው ደረጃ ላይ እንዳለ አውቆ መልስ መስጠት ኃላፊነት አለበት። ሶስቱንም ደረጃዎች ህዝቡ ያልፋል። ችግርህን ቅረፍ አንተ ችግር ነህ ተስተካከል ወይም አንተ ራስህ ተወገድ ይላል። እዛ ደረጃ ከመደረሱ በፊት ወይም ከዛ ደረጃ ተደርሶም ከሆነ ህዝብን አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት እንጂ ለምን ተጠየኩ ማለት የለበትም። ጥያቄ ከየትም ይምጣ የጥያቄ ክፉ ስለለሌለው መንግስት ለተጠየቀው ጥያቄ ቁጭ ብሎ ጊዜ ወስዶ ለምን ይህ ተከሰተ? ብሎ በትዕግስትና በትልቅ ጥበብ መልስ መስጠት ካልቻለ ሁላችንም ወደማንፈልገው ደረጃ ልናመራ ነው። ለዚህ ነበር የሀይማኖት ተቋማት መሪዎች የሚያስፈልጉት። መንግስት ይህን ጥያቄ እንዲመልስ የድልድይነት ሚና መጫወት ይችሉ ነበር።
ሰንደቅ፦ የሃይማኖት እና የመንግስት ስራ ለየቅል ነው። መንግስት በሃይማኖት ሃይማኖትም በመንግስት ስራ ጣልቃ አይገባም (Secularism) የሚባል ነገር አለ። የሃይማኖት መሪዎች ሰሞኑን ለተከሰቱት አይነት ችግሮች ዝምታን መርጠው የተቀመጡት በዚህ ምክንያት ይሆን?
ዲያቆን ዳንኤል፦ በነገራችን ላይ ሴኪውላሪዝም ማለት ሃይማኖት የለሽነት ማለት አይደለም። ሴኪውላሪዝም ማለት ለአንደኛው እምነት አድልተህ የአንዱን እምነት ቀኖና ሳትወስድ መኖር ማለት ነው። ለምሳሌ አሜሪካ የሃይማኖት መመሪያ ሴኪውላሪዝም ነው። ግን ፕሬዚዳንቱ በፀሎት ቢጀምሩ የአሜሪካ መንግስት ሴኪውላሪዝም አይደለም ልትለው አትችልም። ይህ መመሪያ (ሴኪውላሪዝም) የሃይማኖት መሪዎች መንግስት ሲያጠፋ እንዳይተቹ ወይም ተዉ እንዳይሉ እንቅፋት ሊሆንባቸው አይችልም። የሃይማኖት መሪዎች መንግስት ሲያጠፋ ተው ማለት ግዴታቸው ነው። መንግስትን ከጥፋቱ እንዲመለስ ለመገሰጽ የመንግስትን ፈቃድ መጠበቅ አይገባቸውም። ለምሳሌ አቡነ ጴጥሮስ ጣሊያንን ሲያወግዙ ጣሊያን ፈቅዶላቸው አልነበረም። የዚህ ዘመን የሃይማኖት መሪዎችም የመንግስትን ፈቃድ ሳይጠብቁ ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው።
ሰንደቅ፦ የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆንህ ቀደም ባለው ታሪካችን የነበረው የህዝብ እና የመንግስታት ግንኙነት ሲሻክር የሃይማኖት መሪዎች ጣልቃ ገብተው የመካከለኛ ሚናቸውን የተጫወቱበት ዘመን ካለ አስታውሰን?
ዲያቆን ዳንኤል፦ ንጉስ አምደ ጺዮን ድሆችን እየበደሉ ስርዓት እያጠፉና አምባገነን እየሆኑ ሲመጡ አቡነ ፍሊጶስ ጣልቃ ገብተው ንጉሱን ተዉ ብለው ገስጸዋቸው ነበር። አጼ ዘርአያ ያዕቆብ ሀያል ንጉስ ነበሩ። ሆኖም በአስተዳደራቸው ህዝቡን ሲበድሉ እና ሲያስሩ፣ ወታደሮቻቸው ህዝቡን ሲያንገላቱ አቡነ ተክለሐዋሪያት ንጉሱን ሳያስፈቅዱ እስር ቤት ገብተው ነበር ታሳሪዎቹን የጎበኙት። እንዲያውም የአጼ ዘርአያ ያዕቆብ ወታደሮች ከጥጋባቸው የተነሳ (መረን ከመልቀቃቸው) የአንድን ድሃ አንገት ቆርጠው ገና ይጫወቱ ነበር ይባላል። ይህንን ድርጊት ያወገዙት አቡነ ሰላማ ነበሩ። በዚህ ድርጊታቸው ምክንያት መከራ ተቀብለዋል። አቡነ ጴጥሮስ ያደረጉትም ተመሳሳዩን ነው። እኒህ አባትም መከራ ተቀብለዋል። ህይወታቸውን መስዋዕት አድርገዋል። ግን ይህ ነው ለተበደለ መቆም ማለት። ለተበደለ መቆም ሲባል ሁልጊዜ መንግስትን መቃወም ብቻ አይደለም። መንግስት ተበዳይ ሆኖ ሲገኝም ከጎኑ ሊቆሙለት ይገባል። ለተጠቂው መቆም የሃይማኖት መሪዎች ግዴታ ነው። የሃይማኖት መሪዎች ከተጠቂው ወገን እንዲሆኑ የሚመረጡት “አገራችን በሰማይ ነው” ብለው ስለሚያምኑ ምድራዊው ክብር አያጓጓንም ብለው ስለሚያምኑ ነው። በዚያ ላይ ደግሞ በዚህ መንገድ ቢሞቱ እንኳ ክብር ስለሚሆንላቸው ነው።
ሰንደቅ፦ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ በመሪዎቹ ላይ እምነት እያጣ መጥቷል ይባላል። ይህ ለምን የሆነ ይመስልሃል?
ዲያቆን ዳንኤል፦ ሃሳቡ ትክክል ነው። ምዕመኑ በመሪዎቹ ላይ እምነት አጥቷል። ተቋማዊ ኪሳራ እኮ ነው የገጠመን። መቆሚያ የሚፈልግ ሰው ቢቆም የማይታመን ነው። መቆም የማይችል ሰው መደገፊያ ፈልጎ እንደሚቆመው ሁሉ የሃይማኖት መሪዎቹ ሃይማኖቶቹን መቆሚያ መድረክ አድርገው ነው እየተጠቀሙባቸው ያለው። ሰዎቹ በራሳቸው ሊቆሙ የሚችሉ አይደሉም። መጀመሪያ በህዝቡ ዘንድ ያልገነቡትን ስብዕና ዛሬ በችግር ጊዜ ከየት ሊያመጡት ይችላሉ? ሃይማኖቶቹ ሳይሆኑ ተቋማቱ እንደ ተቋም እየከሰሩ ነው ያሉት።
ሰንደቅ፦ በየእምነት ተቋሞቻችን ላይ ተቋማዊ ክስረቶች ከገጠሙን እንደ አገር ኪሳራችን እየከበደብን አይሄድም? መስተካከል የሚቻለውስ እንዴት ነው?
ዲያቆን ዳንኤል፦ አሁን እየታየ ያለው እኮ የእሱ ነጸብራቅ ነው። ይህችን አገር ይዘዋት የኖሩት ሶስቱ አካላት ማለትም ወታደር ካህን እና ንጉስ ናቸው ይባላል። ወታደሩ ዳር ድንበሯን እየጠበቀ ንጉሱ እያስተዳደረ እና የእምነት ሰዎቹ ደግሞ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን እያስተማሩ። አሁን ግን ሶስቱም ላይ ተቋማዊ ኪሳራ ታያለህ። እንዲያውም የቤተ መንግስቱ ችግር ቤተ ክህነቱ ነው ባይ ነኝ። ብዙ ሰው ቤተ ክህነቱን ያደከመው ቤተ መንግስቱ ነው ይላል። እኔ ግን በዚህ አልስማማም። ምክንያቱም ቅድም እንደነገርኩህ በእነ አጼ አምደ ጺዮን እና አጼ ዘርአያ ያዕቆብ ጊዜ ቤተ መንግስቱ ባስቸገረ ጊዜ ጠንካራ ቤተ ክህነት ነበረን። በዚህ ዘመንም ጠንካራ ቤተ አምልኮዎች ቢኖሩ ጠንካራ ቤተ መንግስት ይኖረን ነበር። ነገር ግን ቤተ መንግስቱ የቤተ አምልኮዎቹ (ቤተ ክህነቶቹ) ነጸብራቅ ነው።
ይህ ለማስተካከል እንግዲህ ሁለት ነገር ያስፈልጋል። የመጀመሪያው የህዝቡ ቆራጥነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የፈጣሪ ፈቃድ። ህዝቡ ቆራጥ ሲሆን ማለት የሃይማኖት ተቋማቱን ለማስተካከል ቆርጦ መነሳት አለበት እንጂ ዝም ብሎ ዘማሪ አምላኪ ሰጋጅ ሆኖ መመለስ ሳይሆን ተቋማቱን ለማስተካከል መጣር አለበት። ከዚህ በተረፈ ደግሞ ፈጣሪ መፍቀድ አለበት።
ሰንደቅ፦ በአንዳንድ ቦታዎች የተነሱ ግጭቶችን ከብሔር ጋር የማገናኘት ነገር ይታያል። መንግስትም በመግለጫው “የአንድ ብሔር አባላት የማጥቃት ዘመቻ” ሲል ይከሳል። ችግሩን ከመቅረፍ አኳያ የመንግስት ኃላፊነት እንደዚህ መሆን ነበረበት?
ዲያቆን ዳንኤል፦ እኔ ችግሩ አሁን የመነጨ ነው ብዬ አላምንም። የቆዩ ችግሮች ድምር ውጤት ነው። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት በመጀመሪያ የችግሩን ምንጮች በጥልቀት መመርመር ይኖርብናል። የችግሩን ምክንያት ከለየን በኋላ ወደ መፍትሔው እናመራለን። እንዲህ አይነት ጉዳዮች ችግሩን ያባብሱታል እንጂ አይፈቱትም። ለዚህ ነበር የሃይማኖት መሪዎች የሚያስፈልጉት። ጠንካራ የሃይማኖት መሪዎች ቢኖሩን ኖሮ የመጀመሪያው ጥቃት ሲደርስ ሂደው “ይህ ነገር አይበጅም ተው” ይሉ ነበር። እሱን ማድረግ እንደነበረብን አምናለሁ።
ሰንደቅ፦ ለአገራችን ወቅታዊ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ብሔራዊ እርቅ እንደሆነ የሚገልፁ ወገኖች አሉ። በአንተ እይታ ብሔራዊ እርቅ መፍትሔ ይሆናል ብለህ ታምናለህ?
ዲያቆን ዳንኤል፦ መንግስት ብዙ ጊዜ ባይቀበለውም ብሔራዊ እርቅ የፖለቲካ ቋንቋ ሆኗል። ግን ብሔራዊ ተግባቦት መፍጠር የሚችል ጉባኤ ያስፈልጋል። ይህን ለማመቻቸት ደግሞ ህዝብንም መንግስትንም ያማከለ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በማዋቀር በኩል የአገር ሽማግሌዎች ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ ወቅት የአገር ሽማግሌዎች ጥያቄ ያላቸውንም ሆነ መንግስትን ለማናገርና ችግሩን ለመፍታት ፍጠኑ ማለት እፈልጋለሁ። መንግስት ከሚሄድበትም ሆነ ህዝብ ከሚሄድበት አቅጣጫ ወጥታችሁ ሶስተኛ የተሻለ የመፍትሔ አቅጣጫ ይዛችሁ ቅረቡ። የአገራችንን ችግርም ሳይባባስ ለማስተካከል ጣሩ እላለሁ።