ነሐሴ 26 ቀን 2008 ዓም.
በጎንደርና በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች ከአግአዚ ጦር ጋር ስፋለሙ የሞቱና የቆሰሉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ተብሏል። ቁጥጥሩን ለመግለጽ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ባይቻልም በርካታ ክፍሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ ይገምታሉ።
በየመንገዱ በአግአዚ ተጥለው የተገኙና በየሆስፒታሉ በህክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር የሚያመለክተው ይህንኑ ነው። የወያኔው ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በቅርቡ ወታደራዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ ባለው መሰረት የጎንደርና የጎጃምን አካባቢዎች በአምስት ወታደራዊ ቀጠና ከፍሎ ከፍተኛ ወታደራዊ ስምሪት ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል። በትናንትው ቀን ብቻ በመተማ 10 ሰዎች በደብርቅ አራት ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል። በጎንደር በአብርሃጅራና በአምባጊዮርጊስም በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ መሞታችውና መቁሰላቸው ታውቋል።
የወያኔ ጦር ከወሎ ወደ ጎንደር በርካታ ወታደሮች ለማጓጓዝ ያደረገው ሙከራ ጋይንት ላይ ሕዝብ በመመከቱና ድልድይም በመሰበሩ ሙከራው መክሸፉ የሚታወቅ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሙከራ እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል። ጎጃምንና ሸዋን የሚያገናኘው የአባይ ድልድይ በሕዝቡ የተዘጋ መሆኑንና እንዲሁም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው መንገድም መተማ ላይ መዘጋቱ ከሚድረሱ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል።
በደብረታቦር የሚገኘው እስር ቤት የተቃጠለ ሲሆን ይህንን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ተኩስ እየተሰማ መሆኑ ተገልጿል።
ከባህር ዳር አጠገብ የሚገኙና የውጭ አገር ኩባንያዎች ንበረት የሆኑ የአባባ አምራች ኩባንያዎች በሕዝባዊ አመጽ የወደሙ መሆናቸው የተገኘው ዜና ይገልጻል። ከ12 ኩባንያዎች መካከል 9ኙ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ ታውቋል። ጉዳት የደረሰባችው ኩባንያዎች የእስራኤል፤ የሆላንድ፤ የቤልጅየም፤ የህንድ የጣሊያን ኩባንያዎች ሲሆኑ ከ7.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበት የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ የተናገሩትን ዋቢ በማድረግ ብሉመበርግ የተባለው የዜና ወኪል ገልጿል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄዱ ማስጠንቀቂያ አስተላለፏል። በጎንደርና በጎጃም ሕዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄዱ መሆናችውና በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ሚኒስቴሩ ገልጾ ዜጎቹ ወደ አካባቢዎቹ እንዳይሄዱ የሚመክር መሆኑን ገልጿል።
በአካባቢው የአስቸኳይ ሁኔታ አዋጅ የታወጀባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ እንደመጣና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት እንድሚችል ተናግሯል። የውጭ ጉዳዩ ሚኒስቴሩ መግለጫ ዜጎችን በርከት ያሉ ሰዎች ወደ ተሰበስቡት ቦታዎች እንዳይሄዱ የመከረ ሲሆን በአራቱም ማዕዘን በሚገኙ የወሰን አካባቢዎች ዜጎች መንቀሳቀስ የሌለባቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ አስጠንቅቋል።
Source: Finote Democracy Voice of Ethiopian Unity Satellite Radio News